Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 September 2012 12:13

“የቤጂንግ የወርቅ ሜዳልያዎቼ ለጠ/ሚ መለስ ማስታወሻ ይሁኑልኝ”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ህልፈተ-ዜና እኔ፣ ባለቤቴና መላው ቤተሰቤ በሰማን ቀን ውስጣችን በሃዘን ደምቷል፡፡ የወንድማቸው ቤት እኛ በምንኖርበት አካባቢ ስለነበር ከትዳር አጋሬ ዳናዊት ጋር በመሆን እዚያ ሄደን በለቅሶ እና በከፍተኛ ቁጭት ሃዘናችንን ገልፀናል፡፡ ሃዘናችን ዛሬም ወደፊትም የሚበርድ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለስፖርቱ ነፃነት የፈጠሩ፤ በአመራር ደረጃ ስፖርተኛውን አገርን ለሚያስጠራ ውጤት እንዴት ማነሳሳት እንደሚገባ ያስተማሩ፤ በምናስመዘግበው ውጤት ሁሉ አስፈላጊውን ክብርና ድጋፍ በመስጠት ከጎናችን ያልራቁ መሪያችን ስለነበሩ ስኮራባቸው እኖራለሁ፡፡

በአንድ ወቅት በሚሊኒዬም አዳራሽ ባደረጉልን አቀባበል የተናገሩትን አልረሳውም፤ “አትሌቶች ከወደቁበት እየተነሱ” ብለው ለሰራነው ሁሉ ክብር እየሰጡና እያመሰገኑ ማበረታታቸው ከምንም በላይ ሊመሰገን የሚገባ ተግባር ነው፡፡ የእርሳቸው አድናቆት፣ የከበረ ምስጋና እና ደስታ ለእኛ ብቻ ሳይሆን በስፖርቱ ላሉ ተተኪዎቻችንም ሆነ በሁሉም መስክ ለተሰማሩ ወጣቶች ትልቅ ዋጋና ትርጉም ይኖረዋል፡፡ አንድ አገሩን ከሚወድና ህዝቡን ከሚያፈቅር ታላቅ መሪ የሚገኝ ፀጋ መሆኑን አስባለሁ፡፡

ክቡር መለስ ዜናዊ ክርስቶስ ለሚወደው ህዝቡ እንደተሰዋ ሁሉ እርሳቸውም ለአገራቸውና ለህዝባቸው መስእዋትነት የከፈሉ ናቸው፡፡ መለስ ዜናዊ ሚሊዮኖች በስራቸው የሚያከብሯቸውና የሚወዷቸው፤ ወደር የማይገኝለት እውቀት የታደሉ፤ ጥንካሬ እና ብስለትን ጠንቅቀው ያሟሉ የሁላችን አባት፣ የለውጥ መሪ ናቸው፡፡ ትልቅ መሪ፤ ትልቅ ሰው በማጣታችን ለሁላችንም መፅናናቱን ይስጠን፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፤ ኢትዮጵያን በታላቅ ፅናትና ጀግንነት አስተዳድረዋል፡፡ አገራችንን ከፍተኛ እድገት እንድታሳይ፤ በዓለም ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት እንዲኖራት የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ ስለዚህም ሁላችንም በእሳቸው የተጣለብንን አገራዊ ሃላፊነት እና የለውጥና የስኬት መሰረት ከግብ ለማድረስ ከፍተኛ አደራ አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ በእሳቸው ፈርቀዳጅነት የተያያዝናቸውን ጅማሮዎች ወደ ኋላ በሚመልስ ተግባር አንዘናጋም፡፡ በእልህ እና በቁጭት የበለጠ መስራት ይገባናል፡፡ የኢትዮጵያን እድገት ለማደናቀፍ በውስጥም ሆነ በውጭ የሚሯሯጡትን አሸንፈን፣ በያዝነው ራዕይና የእድገት አቅጣጫ ወደፊት መግፋት አለብን፡፡

እኔ በስፖርቱ በፅናት በስኬት መቀጠል እፈልጋለሁ፡፡ በኢንቨስትመንቱ በየቦታው የጀመርኩትን ሁሉ ከዳር የማድረስ  ዓላማዬን ከበፊቱ በላቀ ሁኔታ ለማከናወን አስባለሁ፡፡ በተሰማራሁባቸው ኢንቨስትመንቶች አገራችን እንድትለወጥ፤ ወገኖቼ ተጠቃሚ እንዲሆኑና የኢትዮጵያ ገፅታን በመገንባት ለመስራት በፅኑነት ቃል እገባለሁ፡፡ ሁላችንም ለአገራችን የበኩላችንን በማድረግ እንደጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ህዝባችንን ከድህነት ነፃ ለማውጣት አስፈላጊውን መስዕዋትነት እንክፈል፤ ወደፊት ለመራመድ ቁርጠኞች ሆነን እንነሳ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዓለም ሻምፒዮናና ከኦሎምፒክ ውድድሮች ስንመለስ ሁሌም የደስታችን ተካፋይ ነበሩ፡፡ ብዙ ማበረታቻዎች እና ሽልማቶች ከእርሳቸው ዘንድ አግኝቻለሁ፡፡ በተለይ ግን ከቤጂንግ ኦሎምፒክ መልስ “ለኢትዮጵያ ታላቅ ባለውለታ ነህ” ብለው ሙሉ ለሙሉ ወርቅ የሆነ፣ ማንገቻው በኢትዮጵያ ባንዲራ የተሰራ የክብር ኒሻን አበርክተውልኛል፡፡ ይህን ሽልማት ከእኔ ሌላ ክቡር ዶ/ር ሼህ አላሙዲ እንደተቀበሉም ስለማውቅ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ነው፡፡ አዎ እኔ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች አገሬን በማስጠራት ደጋግሜ ባንዲራዋን ከፍ አድርጌያለሁ፡፡ በሁሉም ስኬቶቼ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የመሪነት ሚና  አስተዋፅኦ አለው፡፡  ስለዚህም አንድ ነገር እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኔን “የአገር ባለውለታ ነህ” ብለው ሸልመውኛል፤ አክብረውኛል፡፡ እኔ ደግሞ የእርሳቸው መሪነትና ደጋፊነት የማልረሳው በመሆኑ ባለውለታዬ ናቸው፡፡ በቤጂንግ ኦሎምፒክ ያገኘኋቸው ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች ለእርሳቸው ማስታወሻዎቼ ይሁኑልኝ፡፡

(አትሌት ቀነኒሳ በቀለ)

 

 

Read 2439 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 12:16