Friday, 23 July 2021 00:00

ቨርጂን ጋላክቲክ ታሪካዊ የጠፈር ጉዞዋን በስኬት አጠናቅቃለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)


            እንግሊዛዊው ቢሊየነር ሪቻርድ ብራንሰን ቨርጂን ጋላክቲክ በተባለችዋ የራሳቸው የጠፈር መንኮራኩር ባለፈው እሁድ ማለዳ ያደረጉትን ጉዞ በስኬት አጠናቅቀው በመመለስ በራሳቸው መንኩራኩር ጠፈር ደርሰው የተመለሱ የመጀመሪያው ሰው ሆነው በታሪክ መመዝገባቸው ተነግሯል፡፡
የ71 አመቱ ሰር ሪቻርድ ብራንሰን ከሶስት የጉዞ አጋሮቻቸውና ከሁለት የበረራ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ባለፈው እሁድ ከአሜሪካ ኒው ሜክሲኮ ወደ ጠፈር ባደረጉት ዩኒቲ 22 የሚል ስያሜ ያለው ጉዞ፤ መንኮራኩሯ ከምድር ከ85 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በመምጠቅ ጉዞዋን በስኬት አጠናቅቃ መመለሷን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ቢሊየነሩ አንድ ሰዓት ያህል የፈጀውን ጉዞ በስኬት አጠናቅቀው ምድርን እንደረገጡ በሰጡት መግለጫ፣ ጉዞው አንዳች ልዩ ደስታና ሃሴት የሚፈጥርና እንደ ተዓምር የሚቆጠር መሆኑን መናገራቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ብራንሰን በቴክኖሎጂና በጠፈር ጉዞ እየተፎካከሯቸው የሚገኙትን አሜሪካዊያን ቢሊየነሮች የስፔስ ኤክስ ኩባንያ ባለቤት ኤለን መስክና የአማዞን ባለቤት ጄፍ ቤዞስ ቀድመው ወደ ጠፈር በመጓዝ ታሪክ መስራታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ቤዞስ በቀጣዩ ሳምንት ወደ ህዋ ሊጓዙ ቀን መቁረጣቸውንም አስታውሷል፡፡
ጉዞው አጭር ቢመስልም ትርጉሙ ትልቅ መሆኑንና ኩባንያው በቅርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊያደርገው ያሰበው የጠፈር ቱሪዝም ጉዞ ስኬታማ እንደሚሆን ለማረጋገጥ ታስቦ የተደረገ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡
ከ17 አመታት በፊት የተቋቋመው ቨርጂን ጋላክቲክ በቅርቡ ሊያካሂደው ላሰበው የጠፈር ሽርሽር ተመዝግበው ተራ በመጠበቅ ላይ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ከ600 በላይ መድረሱንና አንድ መንገደኛ እስከ ሩብ ሚሊዮን ዶላር ያህል ለጉዞው እንደሚከፍልም ዘገባው አስታውሷል፡፡


Read 8168 times