Sunday, 25 July 2021 00:00

ዕዳ ከሜዳ!

Written by 
Rate this item
(8 votes)

  ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዝማሪ ለሚስቱ በጠዋት ተነስቶ
“ዛሬ ዕዳ ከሜዳ ሲለኝ አደረ” አላት።
ሚስትየውም፡-
“ይሄ ነገር የመልካም ነገር ምልኪ አይመስለኝም። ዛሬ ከቤትህ ፈፅሞ ንቅንቅ ባትል ጥሩ ነው።” አለችው።
“በጭራሽ የታየኝን ሳላሳካ አልውልም፤ አላድርም” አላትና እምቢ ብሏት ከቤት ወጣ።
ከቤት ወጥቶ ወደ አንድ ጫካ ሄደና መሰንቆውን ይዞ ሲጫወት በድንገት አንዳች መንጋ ህዝብ መጥቶ ከበበው። አንደኛው፤
“ይኸው ይሄ ጥጋበኛ የሰረቀውን የእኛን በሬ አርዶ በልቶ ጠግቦ እየዘፈነ ነው።”
“በዚሁ ምክንያት እሥር ቤት መግባት አለበት።” አሉ፡፡
 በዚሁ ወንጀል እሥር ቤት ገባ።
*   *   *
እኛም ሆንን ሌላ ሰው ሲቀፈው ወይም የሆነ ስሜት ሲሰማው አሊያም ሲታየው መጠርጠር ወይም ነገሩን ጉዳዬ ማለት በጣም ተገቢ ነው። መፍትሄ የሚገኘው ነገርን አጥብቆ ከማስተዋል ነው። ከዚያ ቀረብ ብሎ ማጤኑ ሊከተል ይችላል። አስተውሎን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ ይበጃል።
የማያስተኛ ነገር ነግረውን ተኝተው አደሩ። የተባለው ተረት የሀገራችንን እውነታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ብዙ ቃል ተገብቷል፤ ብዙ ማስረጃ የሌለው ጥናት ቀርቧል። ብዙ መላምት በድፍረት ተሰንዝሯል። ሳናውቅ በድፍረት አውቀን በስህተት መጠነ ሰፊ ጥፋት አድርሰናል። ከዚያ የከፋው ደግሞ ምክር አለመስማትን አለማወቅን አለማወቅ ነው።
ደራሲ ከበደ ሚካኤልን ማድመጥ እጅግ መልካም ነገር ነው።
.. “አሁን የት ይገኛል ቢፈልጉ  ዞሮ
መስማት ከማይፈልግ የባሰ ደንቆሮ"
ከአቶ ከበደ አንድ እርከን አድገን ስናስብ፤
“ደግሞ ማወቅ ማለት ከውጪ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ የበራውን እንዲወጣ ማድረግ ነው” የሚለው የደግ  ስነ-ምግባር ምልክት ነው።
ሀገርን ለመለወጥ፣ አንድም ራስን መለወጥ፣ አንድም ሌላውን መለወጥ ተገቢ ነው።
“ለውጥ የእረፍት እኩያ ነው - A change is as equal to rest- ይላሉ ፀሀፍት።” ለውጥ የጊዜ ለውጥ አለው። ለውጥ የቦታ ለውጥ አለው። ለውጥ የአስተሳሰብ ለውጥ አለው። ለውጥ የወዳጅነት ለውጥ አለው፡፡ ለውጥ ለውጥን መውለዱ፣ ያለ የነበረና የሚመጣ ነው።
ከዚህ ጋር የግል ዕድገት አለ። አንዳንዴ ለውጥ የኋሊት የሚጎትተን ወቅት አለ። እንዲህ ያለውን ጎታች መንፈስ በየትኛውም ገፅታው መወልወልና ንፁህ ማድረግ ተገቢነት ያለው ሂደት ነው። ጎታች ይሁን እንጂ ቀስ በቀስ የተለየ ባህሪ እያዳበረ መልካም ህልውናው ያጸኸያል። ከእያንዳንዱ የህይወት ቅንጣት ቀንበጥ ተስፋ፣ ምኞትና ሕልም ህላዌውን ያገኛል። እነዚህ አላባውያን ሁልጊዜ አዳጊ፣ ሁልጊዜ አፍሪ ብቻ ላይሆኑ ይችላሉ። በዚሁ ውስጥ ወደ ኋላ የመቀልበስ አደጋም ንፋሱ ያንዣብብባቸዋል። ዋናው ነገር ግን አዎንታም አሉታም ውስጡ አለ። ደስታና ሐዘንም ከአብራኩ የሚወጡ ልጆቹ ናቸው። በገዛ ልጆቹ የሚያፍር ልጆቹን በወጉ ያሳደገ ወላጅ ብቻ ነው። የግል ህይወቱን ከማህበረሰባዊ ህይወቱ ነጥሎ ተገቢ ቦታ ያልሰጣት ሰው ነው!
ኑሮን በአግባቡ በመቃኘት ልዩ ዜማ፣ ሰምና ወርቅም ካላወጣላት በማንነቱ ውስጥ በሳል ጣዕም ያጣባታል። ረዥሙን አግባብ ባጭር ባጭሩ በመመርመር ቅጥ ቅጥ በማበጀት ምጣኔ መፍጠር የብልህና የአስተዋይ ሰው ተስፋ፣ የዳተኛ ራሱን በራሱ  መዋጫ ነው። ራስን በራስ መርሻ ነው።
ማስተዋል ያለብን ግን፣ ልጆቻችን ከእኛ በወጉ መማር ያለባቸውን አያሌ ጉዳዮች በስርዓት መመርመር እንዳለባቸው ነው።
ነገራችንን በሰከነ መልኩ ማጤን የአስተውሎት ሁሉ መሰረት ነው! አርባ በመቶ ለሚዛናዊ አመለካከት ሰጥተናል ካልን፣ ስልሳ በመቶውን ለጥናት ለምርምር ወደመጣንበት የመመለሻ አቅም ለማድረግ ዕድሉ አለን!
ጨለምተኝነት የተስፋ መቁረጥ ጥዋ ነው ብለን አንደምድም። ብዙም ረዥም መንገድ፣ አያሌ አቋራጮችን የያዘ መሆኑን አንርሳ! የአቋራጮችን አካሄድ ማጤን ጊዜን፣ ጉልበትን፣ እንቅስቃሴን ያበለፅጋል። ይህም የዕድገትን መሰረት ይጥላል። ይህን በሚገባ እንመዘግብ ዘንድ ልብና ልቦና ይስጠን!



Read 13101 times