Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 September 2012 11:14

ከአጫጭር ልብወለዶች ድርቀት የታደገችን “ኩርቢት”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በዚሁ ጋዜጣ ላይ አያሌ ሥነጽሑፋዊ ሂሶችን አስነብቦናል፡፡ በልሲለውም ከሥነጽሑፋዊ ሂሶች ወጣ ይልና ማህበራዊ ሂሶችንም ይከትባል፡ ታዲያ ሥነጽሑፋዊም ይሁን ማህበራዊ ሂስ ሲጽፍ ፈራ ተባ እያለ አይደለም፡፡ ጨከን ኮስተር ብሎ ነው፡፡ ልቡ ይመንበት እንጂ ጽሑፉ ከወጣ በኋላ ስለሚፈጠረው ውዝግብ ወይም ስለሚነሳው አቧራ ብዙም አይጨነቅም፡፡ (ወይስ አቧራ ማስነሳቱን ይፈልገው ይሆን;) ለዚህ መልስ ለመስጠት ራሱን ባለቤቱን መሆን ያስፈልጋል - ጋዜጠኛ፣ ደራሲና ሃያሲ ዓለማየሁ ገላጋይን፡፡ አሁን ስለማንእየደሰኮርኩላችሁ እንደሆነ አውቃችኋልና በቀጥታ ወደ ጉዳዬ መግባት እችላለሁ፡፡ እንግዲህ በዚህ ጽሑፌ ለመቃኘትም ሆነ ለማስቃኘት የምሞክረው ሃያሲውን ወይም ሁለት ረዥም ልብወለዶች ከምናቡ አምጦ ያበረከተልንን ዓለማየሁ ገላጋይን አይደለም፡፡

ይልቁንም ከዚህ ቀደም ብዙም በማይታወቅበት የሥነጽሑፍ ዘውግ (genere) ብቅ ያለውንና የአጭር ልብወለድ ፀሐፊ የሆነውን ዓለማየሁንና በቅርቡ ለንባብ የበቃችውን “ኩርቢት” የተሰኘች አስራ አራት ታሪኮችን ያካተተች አዲስ የአጭር ልቦለዶች መድበል ነው፡፡ በእርግጥ አለማየሁ በዚህ የሥነፅሁፍ ዘውግ ያለውን ርቀትና ልቀት የማውቅበት ደረጃ ላይ አልነበርኩም - “ኩርቢት” እጄ ስትገባ፡፡ መጽሐፏ የደረሰችልን የአማርኛን የሥነጽሑፍ ንፍቀ ክበብ የአጫጭር ልብወለዶች ድርቅ ክፉኛ ባጠቃበት ወቅት በመሆኑ እንደ ክፉ ቀን እህል ተሻምቼ ማንበቤን አልደብቃችሁም፡፡ በ127 ገፆች የተቀነበበችው “ኩርቢት” ከሁለት ቀናት በላይ አልፈጀችብኝም፡፡ ያውም በሥራ መሃል በማገኛቸው ሽርፍራፊ ደቂቃዎች እያነበብኳት፡፡ አንድ ሁለት ታሪኮች ደግሞ በአንድ ንባብ ብቻ አላጠገቡኝም፡፡ በመድበሉ ውስጥ ከተካተቱት ታሪኮች በብዛቱ (26 ገፆች ገደማ) ሪከርድ የሰበረውን “ኩርቢት” እና “አንድ ለእናቴ” የተሰኘውን ሁለተኛውን ረዥም ታሪክ (15 ገፆች ገደማ) ሁለት ጊዜ ለማንበብ ተገድጄአለሁ - ሳይገባኝ ቀርቶ ሳይሆን የበለጠ ለማብላላትና ለማጣጣም ፈልጌ፡፡ ደግሞም ተሳክቶልኛል፡፡ ሁለቱም ውብ ታሪኮች ናቸው፡፡ ደግመው ደጋግመው ቢያነቧቸው አዲስ መረዳት፣ አዲስ ዕይታና ጣዕም የሚፈጥሩ እንጂ ፈፅሞ የማይሰለቹ፡፡ “ዝግመተ ለውጥ” የተሰኘው ታሪክ በመድበሉ ውስጥ ከተካተቱት ሁሉ እጅግ አጭሩ ታሪክ ሲሆን ከአንድ ገጽ በላይ ርዝመት የለውም፡፡ የሥነጽሑፍ ባለሙያዎች ወይም ሃያስያኑ የአጭር አጭር ልቦለድ የሚሉት ዓይነት ነው፡፡ መጠኑ ብቻ ግን አይደለም አጭር፡፡ ዓ.ነገሮቹም በጣም አጫጭር ናቸው - እንደግጥም የተደረደሩ የሚመስሉ (ቤት ባይመቱም) ታሪኩ በሁለት ሰዎች ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው፡፡ አሳምነውና አስማሩ ይባላሉ፡፡አሳምነው የትዳር ጥያቄ ሲያቀርብ ነው ታሪኩ የሚጀምረው፡፡ “ወንድምና እህትነቱ ይበልጣል” የሚል ተስፋ አስቆራጭ ምላሽ ያገኛል - እሱ ተስፋ ባይቆርጥም፡፡ የልቡን ፍላጐት ለመፈፀም የተጓዘበት መንገድ ጅላጅል ቢያስመስለውም ተሳክቶለታል፡፡ እስቲ ከታሪኩ ጥቂት መስመሮች መዝዘን እንይለት:- ጃኬቱን አውልቆ ሄደ፡፡ አስማሩ እሱንም አጥባ አኖረችው፡፡ ሱሪውን ደርቦ መጣ “ወበቀኝ” አወለቀው፡፡ አስማሩ አጥባ አኖረችው፤ ካፖርቱን ጥሎ ሄደ፤ አጥባ አኖረችው፡፡ አንድ ቀን በጠራራ ፀሐይ ብርድልብሱን ለብሶ መጣ፣ አስማሩ “ምነው;” አለችው፡፡ “በጠራራ ፀሐይ ብርድ ሆዴ ገባ” አላት “ምች ይሆናል” አለችው፡፡ የምች መድሃኒት ብታሽለትተሻለው፡፡ ሲሻለው ብርድ ልብሱ አላስፈለገውም ጥሎት ሄደ፡፡ አስማሩ አጥባ አኖረችው፡፡ እንግዲህ ምን ቀረው? ፍራሹ ነው አይደል፡፡ እሱንም ይዞላት ይሄዳል - ላሳድሰው መሄዴ ነው በሚል ሰበብ፡፡ አልተጠራጠረችውም፡፡ በምንስ ትጠርጥረው? በኋላ ግን ፍራሹን እረስቶት ሄደ (የረሳ መስሎ ብንል ይሻላል) ከዚህ በኋላ ምን ሊሰራ እቤቱ ይሂድ? በእኩለሌሊት ወደ አስማሩ ቤት ገሰገሰ፡፡ እሷ ሆዬ ቦታ አጥታ ኖሮ ፍራሹን ፍራሿ ላይ ደርባው ኩሽ ብላለች፡፡ “ተነሽ” ማለት ከበደውና “ጠጋ በይ” አላት፡፡ አላሳፈረችውም፡፡ ጠጋ አለችለት፡፡ መቼም በዚህ ሰዓት “ወንድምና እህትነቱ ይበልጣል” የምትልበት አፍ የላትም፡፡ መዝናናት ለሚሻ አንባቢ ይሄን የመሳሰሉ ታሪኮች “ኩርቢት” ውስጥ አያጣም፡፡ በዚህ መድበል ውስጥ እንዳስተዋልኩት ዓለማየሁ ኮሚክ ይዘት ያላቸውን ታሪኮች መፃፍ ይችልበታል፡፡ በኩምክና የታጀቡ ኮስታራ ጭብጦችን ማስተናገድም ተክኖበታል፡፡ አብዛኞቹ ታሪኮች በዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል “ቅልጣን”፣ “ዘሩባቤል”፣ “አንድ ለእናቴ” ይጠቀሳሉ፡፡ በድሆችና በድህነት ላይ የማተኮራቸውን ያህል ግን የጨለምተኝነት ድባብ ያጠላባቸው ባለመሆናቸው በአንባቢ ላይ የመጨፍገግ ስሜት የሚፈጥሩ ዓይነት አይደሉም፡፡ የዚህ ምስጢሩ ምን ይሆን?  የገለፃ ብቃቱና የቋንቋው ማራኪነት ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ (ከኮሚካዊ አቀራረቡ በተጨማሪ ማለቴ ነው) በነገራችሁ ላይ የዓለማየሁን አጫጭር ልቦለዶች የምናነበው ለታሪኩ ብለን ብቻ አይደለም፤ ለቋንቋውም ጭምር እንጂ፡፡ በእርግጥ ፀሐፊው ኢ- ልቦለዳዊ በሆኑ መጣጥፎቹም ቢሆን በቋንቋ ትባቱ የሚታማ አይደለም፡፡ አስደማሚ የቋንቋ ችሎታና ብቃት እንዳለው በእርግጠኝነት መመስከር ይቻላል፡፡ አብዛኛዎቹ ገለፃዎቹ አይረሴና አዕምሮ ውስጥ ታትመው የሚቀሩ ናቸው፡፡ ጠጅ ቤት ተጀምሮ ጠጅ ቤት በሚጠናቀቀው “ዘሩባቤል” በተሰኘው አጭር ልቦለድ ውስጥ ደቦጭ የተባለው ገፀባህሪ ክሩ የተባለው የጠጅ ቤት ባልደረባውን “እንደላስቲክ ወተት አንገቱን በጥሶ ደሙን እንደሚጠጣው ለሴቶቹ ምሏል” (ገጽ 8) ይላል፡፡ ሌላው የጠጅ ቤት ቤተኛ፣ ጡረታ የወጣው አስተማሪ፤ ደቦጭ ሲገባ ያሳየውን ስሜት ፀሐፊው እንዲህ ይገልፀዋል “እህሉ እንደተራገፈ ጆንያ ጭርምትምት ብሎ ጥጉን ያዘ” (ገጽ 9) ዓለማየሁ ቀልብን በሚማርኩ አካባቢያዊ ገለፃዎችም ቀልብን ይይዛል፡፡ ለማሳያነት የ”ቅልጣን” ን አጀማመር እነሆ፡- “ምን እንደሚያማስለው ሳይታወቅ ሰው ሁሉ አደባባዩን ይሽከረከራል፡፡ ዑደቱን ከአራቱም አቅጣጫ የሚቀላቀለው ሰው ወዳሻው የሚሄድ ሳይሆን በእሽክርክሪቱ ተጠልፎ የቀረ ይመስላል፡፡ የአራት ኪሎ ሃውልት ቀጥ ማለቱን ትቶ የትምህርት ማኒስቴርን ህንፃ ቢደገፍ አማስሎ አማስሎ አረፍ ያለ የወጥ እንጨት በመሰለ ነበር፡፡ የሚያቸፈችፈው ዝናብ እሽክርክሪቱ ላይ የሚነሰነስ ብትን ሽሮ መስሏል” (ገፅ 19)በነገራችሁ ላይ “ቅልጣን”ም ኮሚካዊ ይዘት ያደላበት ታሪክ ነው - የገፀባህርያቱን አገላለጽ ጨምሮ፡፡ በድህነት ታጅበው በትኩስ ፍቅር ላይ ስላሉ ሁለት ተፋቃሪዎች በሚተርክልን ታሪክ ውስጥ የሁለቱን ዋና ገፀባህርያት አስቂኝ ገለፃ እንመልከትለት፡- “ሴቷ ሁለት እግሯን ይዘው እንደዘቀዘቋት ሁሉ ደሟ የተከማቸው ፊቷ ላይ ነው፡፡ ወንዱ ጭልፊት ፊት ነው፡፡ ግንባሩ ጠቦ የአፍንጫውን አቅጣጫ ይይዛል…” (ገፅ 20) ፀሐፊው የምናብ ልጆቹ የሆኑትን ገፀባህርያቱን ሲተርብና ሲያሽሟጥጥ ለነገ የሚል አይመስልም - የጭቃ ጅራፉን እንደ ጉድ ያወርድባቸዋል፡፡ እዚያው ታሪክ ውስጥ ወረድ ብሎ ስለእነዚሁ ፍቅረኞች ሲገልጽ “ሴቷ ወፍ እግር ናት፡፡ እሱ ድፎ ከመሰለ ጫማ ውስጥ የብልቃጥ ቂጥ የሚያክል በጠፈጠፍ የተቀቀለ አውራጣቱ ብቅ ብሏል” (ገፅ 21) ይላል፡፡ የዓለማየሁ ሌላ ችሎታና ብቃት የገፀባህርያቱ አሳሳል ላይ ይመስለኛል፡፡ በደንብ አድርጐ ነው በታሪኩ ውስጥ የሚተክላቸው፡፡ አንድ ጊዜ ከተዋወቅናቸው ፈጽሞ ልንረሳቸው አንችልም፡፡ ለምሳሌ የ”አንድ ለእናቴ”ን ዋና ገፀባህሪ መመልከት ይቻላል፡፡ ፍፁም አይረሴ ነው፡፡ ይሄ ታሪክ በገፀባህርይ አሳሳል ብቻ ሳይሆን በአስገራሚ የታሪክ አጨራረስም ወደር የለሽ ነው፡፡ በተለይ የታሪኩ መጨረሻ ግድም እንደሲኒማ ትዕይንት ቁልጭ ብሎ ከመታየቱም ባሻገር ልብ ሰቃይነቱም ያስደምማል፡፡ እንግዲህ “ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም” እንዲሉ ከዚህ የተረፈውን ከ”ኩርቢት” ላይ ታገኙታላችሁ፡፡ አደራችሁን በተለይ “ኩርቢት” የሚል ርእስ የተሰጠውን አጭር ልቦለድ አንብቡልኝ፡፡ ታመሰግኑኛላችሁ፡፡ እኔ እንግዲህ ቅኝቴን የምቋጨው ከአዳም ረታ የአጭር ልቦለድ ሥራዎች ቀጥሎ አንጀቴን ያራሰኝ ሥራ ይህቺ የአለማየሁ ገላጋይ “ኩርቢት” መሆኗን በይፋ በማወጅ ነው፡፡ ፀሃፊው ሁለተኛ የአጭር ልብወለዶች መድበል

 

እንደሚደግመን ተስፋ በማድረግ ልሰናበት፡፡ መልካም አዲስ ዓመት!!

 

 

 

 

Read 2585 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 11:20