በውድድሩ ላይ መሃመድ አማን ዴቪድ ሩዲሻን በመቅደም ሲያሸንፍ ያስመዘገበው 1 ደቂቃ ከ42.53 ሰኮንዶች የሆነ ጊዜ በርቀቱ የኢትዮጵያ አዲስ ሪኮርድ ሆኗል፡፡ ዘንድሮ በ800ሜ የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው እና በ30ኛው የለንደን ኦሎምፒያድ 6ኛ ደረጃ ያገኘው አትሌት መሃመድ አማን የርቀቱ ንጉስ የሚባለው ዴቪድ ሩዲሻ ባለፉት ሁለት አመታት ለሁለት ጊዜያት ማሸነፉ በተለያዩ የዓለም ሚዲያዎች ከፍተኛ ውዳሴ አትርፎለታል፡፡ በስዊድን ስቶክሆልም እና በስዊዘርላንድ ዙሪክ የተካሄዱ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮችን ያሸነፈው መሃመድ አማን በ800ሜትር 1377 ነጥብ በማስመዝገብ በዓለም 2ኛ ደረጃ እንዳለው ኦልአትሌቲክስ በድረገፁ አመልክቷል፡፡በሌላ በኩል አትሌት አበባ አረጋዊ በሴቶች 1500ሜትር ዳይመንድ ሊጉን ለማሸነፍ የበቃችው በ22 ነጥብ የደረጃ ፉክክሩን በመምራት ሲሆን ዙሪክ ላይ በተደረገው ርቀቱን በ4 ደቂቃ ከ05.29 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ በመሸፈን ነበር፡፡በዳይመንድ ሊጉ በጣሊያን ሮም ፤በኖርዌይ ኦስሎና በስዊዘርላንድ ዙሪክ የተካሄዱ 3 ውድድሮችን ያሸነፈችው አበባ አረጋዊ ኦል አትሌቲክስ በድረገፁ በሰራው አሃዛዊ መረጃ በ1500ሜ ሴቶች በ1359 ነጥብ ከዓለም 1ኛ ደረጃ ይዛለች፡፡በዶሃ ከተማ ኳታር ውስጥ ተጀምሮ ትናንት በቤልጅዬም መዲና ብራስልስ የሚጠናቀቀው ዳይመንድ ሊጉ ዘንድሮ ለ3ኛ ግዜ ሲካሄድ በ14 ከተሞች 32 ውድድሮች በተለያዩ የስፖርት መደቦች ተካሂደውበታል፡፡