Print this page
Saturday, 08 September 2012 11:49

ህዝቡ ካድሬ እንደማያስፈልገው አረጋገጠ!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(2 votes)

የቤተመንግስቱ በር ተከፈተልን፤ የመንግስት ልብስ?

ዘንድሮ አሪፍ ዓመት አልነበረም፡፡ ታላላቆቻችንን በሞት የነጠቀንና ህዝቡንም የሀዘን ማቅ ያለበሰ ክፉ ዓመት ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ የጠ/ሚኒስትሩ ድንገተኛ ህልፈት እጅግ አስደንጋጭና ልብን የሚሰብር ነበር፡፡ ለዚህም ነው አገር ሙሉ ህዝብ በሀዘን የሰነበተውና የአገሪቱ ባንዲራ ዝቅ ብሎ የተውለበለበው፡፡ “ኖሮ ኖሮ ወደ አፈር” እንዲሉ ባለፈው እሁድ የጠ/ሚኒስትሩ የቀብር ሥነስርዓት በታላቅ ክብር በአስደማሚ የህዝብ አጀብ ተፈጽሟል፡፡ ከዚያ በኋላ ኢህአዴግ የእስካሁኑ ሀዘን በቂ ነው በሚል በማግስቱ “ሀዘን አብርድ” በሚል ስሜት ሁሉም ወደ ወትሮው ሥራ እንዲመለስ ማድረጉን ወድጄለታለሁ፡፡

የሀዘን ብዛት አቶ መለስን ከሞት እንደማይመልሳቸው እያወቅን ከዚህ በላይ ሥራ ፈትተን ሃዘን ብንቀመጥ አንዳችም ትርፍ - የለውም፤ ኪሳራ እንጂ፡፡ የእሳቸው አጥንትም ቢሆን እኮ ይወቅሰናል፡፡ እኔማ ሳስበው እሳቸው በእስካሁኑም ሀዘን ቢሆን ደስተኛ የሚሆኑ አይመስለኝም፡፡ በድህነት አበሳዋን የምትበላ አገር በሀዘን ሰበብ ሥራ ፈትታ መቀመጥ የለባትም እንደሚሉ ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም፡፡

ግን ግዴለም ይሁን፡፡ መሪ ሞቶብን በቅጡ አዝነን በክብር ስንቀብር የመጀመሪያችን ነውና የሀዘን ጊዜው በዝቷል ላይባል ይችላል፡፡ ይልቅስ በሃዘኑ ወቅት ጐጂ ባህል ነው ተብለው የተከለከሉ እንደ ደረት መደለቅ ያሉ የሃዘን ሥርዓቶች ሲከናወኑ ታይተዋል፡፡

አንዳንድ ታዛቢዎቹ እንደሚሉት፤ በአሁኑ ጊዜ በለቅሶ ወቅት እንዲህ ያሉት ጐጂ ባህሎች አይፈቀዱም፡፡ ሲደረጉ ከታየም የሰፈር ዕድሮች ድንኳናቸውን ነቅለውና እቃቸውን ሸክፈው እብስ ነው የሚሉት አሉ፡፡ ይሄኛው ግን ብሔራዊ  ሀዘን ስለነበር “ግዴለም ይሁን” ሊባል ይችላል፡፡ (ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ እንደሚባለው) የእኔ ፍራቻ ግን ምን መሰላችሁ? በዚህ ሰበብ በጐጂ ባህልነት የተፈረጀው የለቅሶ ልማድ ተመልሶ እንዳይመጣ ነው፡፡ (እድሮች ይበርቱዋ!) አያችሁ… ሞት መቼም ለማንም የማይቀር ተፈጥሮአዊ ክስተት ነው አይደል፡፡ ስለዚህ ከልክ በላይ መሪር ሀዘን አይገባም - በተለይ በቁም ያለውን የሚጐዳ!!

በነገራችሁ ላይ የጠ/ሚኒስትሩን ህልፈት ተከትሎ በተፈጠረው ብሄራዊ ሀዘን በህዝቡ ዘንድ የታየው አንድነትና አገራዊ መግባባት ለኢትዮጵያ ህዝብ ቀስቃሽ ካድሬ እንደማያስፈልገው ማረጋገጡን እውቅ የፖለቲካ ተንታኞች እየተናገሩ ነው፡፡ መቼም ኢህአዴግም ሆነ ሌላ ወገን በዚህ ጉዳይ ክርክር አይገጥመኝም ብዬ አምናለሁ (የፈጠጠ ሃቅ ነዋ!) እርግጠኛ ነኝ ያ ሁሉ ጐርፍ ህዝብ ከያለበት ነቅሎ በመውጣት ጐዳናዎቹን የሞላው በካድሬ ቅስቀሳ ወይም በ1ለ5 የአደረጃጀት ስትራቴጂ አይመስለኝም፡፡ ካድሬ ይሄን ያህል አቅም ቢኖረውማ ኢህአዴግ የትናየት በደረሰ ነበር፡፡

ትዝ ይላችኋል… አዲሱ የመሬት ሊዝ አዋጅ የወጣ ጊዜ የተፈጠረውን ንትርክና ተቃውሞ! መሬት ይቅለላቸውና ራሳቸው ጠ/ሚኒስትሩ ብዥታውን ለማጥራት በሚል በፓርላማ ማብራሪያ መስጠታቸውን የምንዘነጋው አይመስለኝም፡፡ ያኔ ታዲያ ብዥታው የተፈጠረው በዋናነት በካድሬዎች የአቅም ማነስ መሆኑን ጠ/ሚኒስትሩ ተናግረው ነበር እኮ!

እናላችሁ… በዚህች አጋጣሚ ህዝብ ካድሬዎቹን እንደሚበልጥ አረጋገጠ ተብሏል፡፡ እውነቴን እኮ ነው …ህዝብ የሚፈልገውና ያመነበት ጉዳይ ከሆነ አንዳችም የካድሬ ቅስቀሳ አያስፈልገውም (እንደ ሀዘኑ ግልብጥ ብሎ ይወጣል) በ97 ምርጫ ወቅት ያ ሁሉ ማዕበል ህዝብ የወጣው እኮ በካድሬ ቅስቀሳ አልነበረም፡፡ በዓለም አቀፍ መድረክ በድል ያንበሸበሹን ወርቅ አትሌቶች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ከቦሌ አየር ማረፍያ ጀምሮ ህዝቡ በአጀብ የሚቀበላቸው በካድሬ ተቀስቅሶ ነው እንዴ? (ካድሬና አትሌቲክስ የት ይተዋወቁና!) እናላችሁ… ኢህአዴግ ከሰሞኑ ሁኔታ የኢትዮጵያ ህዝብ ካድሬ እንደማያስፈልገው አውቆ ለካድሬዎች ቦታ ቦታ ቢሰጣቸው ሳይበጀው አይቀርም፡፡ እንዴ…ከህዝቡ ጋር በቱርጁማን ከመገናኘት በቀጥታ መነጋገር፤ ስሜት ለስሜት መናበብ አይሻለውም; (ቱርጁማን ያልኩት ካድሬውን እንደሆነ ይታወቅልኝ) በእርግጥ የተነሳውን ጉዳይ ወይም አጀንዳ ህዝቡ አይቀበለውም ብሎ ካሰበና በውዴታ ሳይሆን በግዴታ መጐስጐስ ካማረው ሌላ ምርጫ የለም - ከካድሬ ውጭ!

ችግሩ ግን ካድሬ ሲያጐርስ በፍቅር አይደለም፡፡ እንደ ባህላችን በሞቴ ብሎ አያጐርስም፡፡ አንድም “ብትጐርስ ጉረስ ያለዚያ ገደል ግባ” ይላል አሊያም ደግሞ በግድ ይጐሰጉስሃል፡፡ ያኔ ደግሞ የጐረስነው ገና ስንውጠው ይተናነቀናል፤ ፈጽሞ አይስማማንም (ያልወደድነው ምግብ እንደሚጣላን ማለት ነው) እናም ኢህአዴግ በአዲስ ዓመት ውለታ ይዋልልን - ከነዝናዛ ካድሬዎች እኛን በማላቀቅ፡፡ ፓርቲውንም እኮ አልጠቀሙትም፤ ከህዝብ አራራቁት እንጂ!

አንድ ወዳጄ በጠ/ሚኒስትሩ የሀዘን ወቅት ስለ ኢህአዴግ ካድሬዎች የታዘበውን ሲነግረኝ ምን አለኝ መሰላችሁ; “አንቀሳቃሽ ሳይሆን ተንቀሳቃሽ ነው የሆኑት” (ካድሬዎቹን የመራው ህዝቡ ነው ሊለኝ ፈልጐ ነው) አይገርማችሁም…የወዳጄን ሃሳብ ዝም ብዬ ከመቀበል ውጭ ልከራከረው አልቻልኩም (ሃቅ ነዋ!)

ምናልባት ኢህአዴግ ካድሬዎቹን ምን እንደሚያደርጋቸው ይጨነቅ ይሆናል፡፡ ግን ከሰማኝ መፍትሔ ልጠቁመው፡፡ አቅም ያለውን በህብረት አደራጅቶ ኮብልስቶን ያስነጥፍ፡፡ ስለ ኮብልስቶን ገና ሳይጠየቅ ይንጣጣ የነበረው ካድሬ ሁሉ ሰርቶ ያሳየን (ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር …ይባል የለ!) አቅም የሌለውን ደግሞ በሴፍቲኔት እንዲታቀፍ ያድርገው (ችግሩ ተቃለለ አይደል)

ያን ጊዜ በተለይ አንጀታችንን እርር ድብን ከሚያደርጉን የጋዜጠኛ ካድሬዎችም እንገላገልና ከጨጓራ ህመምም እንፈወሳለን ብዬ አስባለሁ (ምህላ እንግባ ይሆን እንዴ;)

እኔ የምለው… በሰሞኑ ሃዘን ሰበብ ለስንት ዘመን ተደፍሮ የማያውቀው ቤተመንግስት በህዝብ መደፈሩን አያችሁልኝ አይደል (ፍቅር የማይበጣጥሰው አጥር የለም!) አንዳንዶች ምን እንዳሉ ታውቃላችሁ; “አባይን የደፈረ መሪ ቤተመንግስትን የደፈረ ህዝብ ፈጥሯል” (በጠብመንጃ ሳይሆን በፍቅር!) ይገርማል እኮ…እንኳንስ ህዝብ በሰልፍ ቤተመንግስት ሊገባ ቀርቶ በአካባቢው እንኳን ዝር ማለት አይፈቀድለትም ነበር፡፡ (ኧረ ፎቶ ማንሳት ሁሉ ክልክል ነበር!) ዘንድሮ ግን ህዝቡ እንደልቡ ገባበት - በጠ/ሚኒስትሩ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን ለመግለጽ (የቤተመንግስቱ በር እንደተከፈተልን ሁሉ የመንግስትም ልብ ይከፈትልን!)

በጽሑፌ መግቢያ ላይ እንዳልኩት መንግስት “ሀዘን አብርድ!” ብሎ ህዝቡ ወደ ሥራ እንዲገባ የመሪነቱን ሚና መውሰዱን ወድጄለታለሁ፡፡ (አንዳንዴ እንኳ ይመስገን እንጂ!) ህዝቡ በአገሩ መሪ ህልፈት ላሳየው የጋራ ሀዘንም ምስጋናውን መግለፁን ሳላደንቅ አላልፍም (ኢህአዴግ ልብ ገዛ ልበል?) ሌላው ያደነቅሁት የጠ/ሚኒስትሩ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ በቀብሩ ሥነስርዓት ላይ የተናገሩትን ንግግር ነው፡፡ በተለይ ደግሞ መለስ በህይወት ቢኖሩ ኖሮ በሀዘኑ ሰበብ በየአደባባዩ የተለጠፉት ፖስተሮች እንዲለጠፉ እንደማይፈልጉ የተናገሩት አስደምሞኛል፡፡ (በእርግጥ የኢህአዴግ ባህል አለመሆኑንም እናውቃለን) በነገራችሁ ላይ ራሳቸው ጠ/ሚኒስትሩ ከውጭ ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ “አምልኮተ -ሰብ” (ፈረንጆቹ Cult የሚሉትን) እንደማይፈልጉ መግለፃቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ካሸለቡበት ዘላለማዊ እንቅልፍ በተዓምር ለአፍታ ቀና ብለው የህዝቡን እንባ ቢያዩ ህዝቡ ላሳያቸው ክብርና ልባዊ ሀዘን ልባቸው እንደሚሰበር ቅንጣት ታህል አልጠራጠርም፡፡ ነገር ግን ተመልሰው ከማሸለባቸው በፊት “እንባችሁን ሳይሆን ራዕያችሁን አሳዩኝ” የሚሉን ይመስለኛል፡፡ ባለቤታቸው እንደተናገሩት የእሳቸውን ምስል የያዘ ፖስተር መለጠፍና ሃዘን መቀመጥ ለእሳቸው ቁምነገር አይደለም፡፡ ለእሳቸው ትልቁ ጉዳይ ድህነትን ታግሎ ለማሸነፍ ቀን ተሌት መትጋት መታተር ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግ ሳይረፍድ “ሀዘን አብርድ” ብሎ ወደ ሥራ እንመለስ ማለቱን የወደድኩለትም ለሌላ ሳይሆን ለዚህ ነው፡፡

ይኸውላችሁ…በፍጥነት ወደ ሥራ እንመለስ (back to business እንዲሉ) ባይባል ኖሮ አብዛኛው ካድሬ ፖስተር እየለጠፈና “የጠ/ሚኒስትሩን ራዕይ እናሳካለን” የሚለውን መፈክር እንደበቀቀን እየደገመልን ዓመቱን ማገባደዱ አይቀርም ነበር (ካድሬ ሌላ ምን ስራ አለው?) በፖስተርና በመፈክር ደግሞ የእሳቸው ራዕይ ፈጽሞ እውን ሊሆን እንደማይችል ይታወቃል፡፡

ስለዚህ የኢህአዴግ ውሳኔ ካድሬውን ቢያስከፋም እኛን እንዳስደሰተን ልገልጽ እወዳለሁ፡፡ እሳቸውን “ጀግና” እያልን ማወደስና ዕውቅና መስጠት ተገቢ መሆኑን ባልክድም ይሄን ማለት ግን እኛን “ጀግና” እንደማያደርገን መዘንጋት የለብንም፡፡ ልብ በሉ…ከዚህ በኋላ “መለስ ላይ መንጠላጠል አይቻልም”

አሁን ጊዜው የፈተና ጊዜ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ደግሞ አገር ለሚመራው አውራው ፓርቲ ለኢህአዴግ፡፡ አንዳንድ የኢህአዴግ ባለስልጣናት የአገር አመራር የአንድ ሰው (ግለሰብ) የአዕምሮ ውጤት ሳይሆን የቡድን ውጤት መሆኑን በተደጋጋሚ ሲነግሩን ነበር አይደል፡፡ ከጠ/ሚኒስትሩ ህልፈት በኋላ ግን ብዙዎቹ ራዕዮች የፓርቲው ሳይሆን የእሳቸው ተደርገው ሲቀርቡ ነው የሰነበተው፡፡ ነገሩ እውነት እንደዚያ ከሆነ ግን “የኢህአዴግ ራዕይስ ምንድነው;” (መጠየቅ የዜግነት መብቴ ነው አይደል?!)

የጠ/ሚኒስትሩ ትልቅ ራዕይ ድህነትን ማሸነፍ እንደሆነ የሚያከራክረን ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ሌሎች ሃሳቦችና ህልሞችም እንደነበሯቸው ግን እሳቸው ካለፉ በኋላ ከአንዳንድ ወገኖች እየሰማን ነው፡፡ ሰሞኑን ከኢቴቪ የMeet Etv ፕሮግራም አዘጋጅ ተፈራ ገዳሙ ጋር ቃለምልልስ ያደረጉት ፕ/ር ኤፍሬም ይስሃቅ፤ ጠ/ሚኒስትሩ በየዓመቱ በዘመን መለወጫ የተወሰኑ እስረኞችን በምህረት ለመፍታት ቃል እንደገቡላቸው ጠቅሰው፤ ዘንድሮም በመስከረም ወር ተመልሰው እንዲመጡ እንደነገሩዋቸው አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሽማግሌዎች ቡድንን የመሰረቱት ፕሮፌሰሩ፤ መንግስትን ከተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በማደራደር ብሔራዊ እርቅና ስምምነት ለመፍጠር ዕቅድ እንደነበራቸውና ጠ/ሚኒስትሩም “ሁልጊዜ አንኳኩ፤ ምንጊዜም ከማንኳኳት አትቦዝኑ” የሚል ተስፋ ሰጪ ምላሽ እንደሰጧቸው ለጋዜጠኛ ተፈራ ገዳሙ ነግረውታል - በ Meet Etv፡፡

አሁን የእኔ ጥያቄ (የፕ/ር ኤፍሬምም ይመስለኛል) ኢህአዴግ ለእኒህ የሽማግሌ ቡድኑ ጥያቄዎች መልሱ ምን ይሆን የሚል ነው፡፡

እንግዲህ ጠ/ሚኒስትሩ ህያው እንዲሆኑ የሚሻ ከሆነ፣ የእሳቸውን ሃሳብና ህልም እውን ያደርጋል ብዬ አስባለሁ - የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታትና ከተቃዋሚዎች ጋር እርቅና ድርድር በመፈፀም፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ግን አቶ መለስ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ እንዲፈጠርና ኢትዮጵያ ፓርቲዎች እየተፈራረቁ ሥልጣን የሚይዙባት አገር እንድትሆን የማድረግ ህልም ነበራቸው፡፡

ይሄን ህልም አውራው ፓርቲ “ሳይበርዝ ሳይከልስ” እውን ያደርገዋል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ ይሄ ደግሞ ለእዚህ ጨዋና ታላቅ ህዝብ ሲያንሰው እንጂ ፈጽሞ አይበዛበትም፡፡

እናም የእሳቸውን ራዕይ ሙሉ በሙሉ በመተግበር ለዚህ መሪውን ለሚያከብር ክቡር ህዝብ ውለታውን ይመልስ ዘንድ ለኢህአዴግ የማስታውሰው በታላቅ ትህትና ነው (ህገመንግስታዊ መብቴ እንደሆነም አልዘነጋሁትም!) መልካም አዲስ ዓመት ለሁላችንም እመኛለሁ!!

 

 

Read 3276 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 12:03