Saturday, 14 August 2021 10:55

August 1-7 የእናቶች ጡት ማጥባት ሳምንት

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

     እናቶች ልጅ በሚወልዱበት ጊዜ ጡት ለማጥባት ጉጉት ሊያድርባቸው ይገባል፡፡
እናቶች፡-
የተወለደው ልጅ መቼ ጀምሮ ጡት መጥባት አለበት?
በየስንት ሰአቱ ጡት መጥባት አለበት?
ምን ያህል መጠን ጡት መጥባት አለበት?
እስከመቼ ጡት ብቻ መጥባት አለበት?
የሚለውን ከሕክምና ባለሙያዎች በሚያገኙት ምክር መሰረት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ይመከራል። የኢትዮያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበርም ይህንኑ ምክር ለመላው እናቶች ይድረስ ይላል፡፡
ልጆች ከተወለዱ ከአንድ ሰአት ጀምሮ
በተገቢው ሰአት፤
በተገቢው መጠን፤
ለተገቢው ወቅት፤
ጡት መጥባት እንዳለባቸው አለምአቀፉ ህብረተሰብ የተስማማበት እና ለተግባራዊነቱም በየአመቱ August 1-7 የጡት ማጥባት ሳምንት ተብሎ እንዲታሰብ ስምምነቱ አለ፡፡ በዚህም መሰረት በኢትዮጵያም ይህ ሳምንት በክብር ታስቦ ከርሞአል፡፡
ጡት ለማጥባት ፈቃደኝነት እና ተነሳሽነቱ በእናቶች በኩል ሊኖር የሚገባውና ልጆች እንደ ተወለዱ በጥሩ ሁኔታ እስኪጠግቡ እንዲሁም ለተከታታይ ጊዜያት ማለትም እስከ ስድስት ወር ድረስ የጡት ወተት ብቻ እንዲመገቡ እና ቢቻል እስከ ሁለት አመት ድረስ እንዲጠቡ ቢደረግ የህጻናቱን ሞት መጠን ለመቀነስ እንደሚያስችል ብርሀኑ ተሾመ ወልደማርያም በInternational Breastfeeding Journal  volume 15 ገልጸዋል። ብርሀኑ ተሸመ በጆርናሉ ላይ ያሰፈሩት ጽሁፍ እንደሚያስረዳው ጥናት ያደረጉበት ምክንያት በኢትዮጵያ ያሉ እናቶች ልጆቻቸውን ጡት ለማጥባት ያላቸውን ተነሳሽነት እና ፈቃደኝነት እንዲሁም ፍላጎት ምንያህል እንደሆነ ለማወቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህ ጥናት ሀሳቡን መነሻ ያደረገው እ.ኤ.አ በ2016 የተደረገው DHS (Ethiopian Demogra- phic and Health Survey 2016) ሲሆን በጥናቱም ወደ 5122/አምስት ሺህ አንድ መቶ ሀያ ሁለት የሚሆኑ ህጻናት ሁኔታ ታይቶአል፡፡ ህጻናቱ በጥናቱ የተካተቱበት ምክንያትም ከጡት ማጥባት ጋር በተያያዘ ያሉትን የእናቶች ልምዶች ለመፈተሸ ነበር።
በተደረገው ጥናት የተገኘው ውጤት እንደሚያሳየውም ወደ 81.8 % የሚሆኑት በተወለ ዱበት ቀን በተወለዱ በአንድ ሰአት እድሜ ጡት የጠቡ ሲሆን ወደ 47% የሚሆኑት ደግሞ ከተወለዱ ጀምሮ ለስድስት ወራት ካለማቋረጥ ጡት ጠብተዋል፡፡ አብዛኛውን ጡት የማጥባት ጊዜ ወደ 22 ወራት ሲሆን በገጠር የሚኖሩ እናቶች፤ ከእርግዝና በሁዋላ ክትትል የሌላቸው እናቶች፤ በቀዶ ሕክምና የወለዱ እናቶች፤ እና በቤት ውስጥ የወለዱ እናቶች ልጃቸውን በተወለደ በአንድ ሰአት እድሜ ጡት የማጥባት ፍላጎት አልታየባቸውም፡፡
በሌላም በኩል ትምህርት ያልተማሩ እናቶች፤ የወለዱትን ልጅ ወደህክምና ክትትል የማይወ ስዱ፤ ውፍረት ያለው ልጅ የወለዱ፤ ከጤና ተቋም ውጭ የወለዱ እናቶች ጡት ማጥባትን እስከ ስድስት ወር ድረስ ብቸኛ ምግብ አድርገው እንደማይተገብሩት ታይቶአል፡፡
በጥናቱ የተረጋገጠው ሌላው ነገር እናቶች ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች ሲታይ ለምሳሌ በአማራ፤ በኦሮሚያ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ያሉ እናቶች ለረዥም ወራት ጡት የማጥባት ልማድ ያላቸው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ስራ ያላቸው እናቶች፤ በላይ በላዩ የወለዱ ወይንም መንትያ የወለዱ እና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው እናቶች የጡት ማጥቢያቸው ወቅት አጭር ሊሆን እንደሚችል ጥናቱ ያሳያል፡፡  
በአለም አቀፍ ደረጃ 800.000 ያህል ለሚሆኑ ጨቅላ ህጻናት ሞት ምክንያት ሆኖ የተመዘገበው እናቶች ልጆቻቸውን እንደወለዱ የማጥባት ፍላጎት ወይንም ተነሳሽነት እንዳላሳዩ ወይንም ከተለያዩ ነገሮች ጋር በተያያዘ ጡት ያልጠቡ እና እስከ ስድስት ወር ድረስ ባለው እድሜአቸውም በትክክል ጡትን ብቻ ያልተመገቡ መሆናቸው ታውቆአል፡፡ ልጆች እንደተወለዱ ወዲያውኑ በአንድ ሰአት እድሜ ውስጥ ጡት ከጠቡ በአለም አቀፍ ደረጃ በተወለዱ በአንድ ሳምንት ውስጥ ለመሞት የሚያበቃቸውን ጠንቅ በ22% ለመቀነስ ያስችላል፡፡ በስድስት ወር እድሜ የእናት ጡት ወተትን ብቻ ለህጻናቱ መስጠት በህጻንነት እድሜአቸው የሚከሰተውን የሞት አደጋ ለመቀነስ ይረዳል፡፡
እ.ኤ.አ በ2030, ዘላቂነት ያለው የልማት ግብ የታቀደ ሲሆን የልማቱ እቅዶች ካካተቱዋቸው አበይት ነጥቦች መካከልም በአለም አቀፍ ደረጃ ገና የተወለዱትን ሞት ከ1000 በሕይወት ከሚወለዱ ወደ 12 ለማውረድ እና ከአምስት አመት በታች ያሉ ህጻናትን ሞት ከ1000 በሕይወት ከሚወለዱ ወደ 25 ዝቅ ለማድረግ የተለያዩ የስራ መመሪያዎች ይፋ ሆነዋል፡፡ ይህም እውን የሚሆነው የተለያዩ ሊከላከሉአቸው የሚገቡ የህጻናት ሞቶችን በማስቀረት ነው፡፡ ከሰሀራ በታች ያሉ ሀገራት ከፍተኛ የሆነ አዲስ የተወለዱ ህጻናት ሞት የሚመዘገብባቸው ሀገራት ሲሆኑ ይህም በየአመቱ ከ100 በሕይወት ከሚወለዱ 28/መሆኑ ተመዝግቦአል፡፡
ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት አንዱዋ ስትሆን አዲስ የተወለዱ እና ጨቅላ ህጻናት ሞት በከፍተኛ ሁኔታ ይታይባታል፡፡ በኢትዮጵያ የተሰራው የመጨረሻው DHS እንደ ሚያሳየው ከ5 አመት በታች ያሉ ህጻናት ወደ 92% የሚሆኑት በጥናቱ የተካተቱት እንደተወለዱ በአንድ ሰአት ውስጥ ጡት መጥባታቸው የተረጋገጠ ሲሆን ወደ 58% የሚሆኑት ደግሞ ሌላ ምግብ ሳይቀላቀልባቸው ለስድስት ወራት የእናት ጡት ወተት ጠብተ ዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከአምስት አመት በታች ያሉ ህጻናት ሞት በፊት ከነበረበት የቀነሰ ሲሆን አዲስ የተወለዱና ጨቅላ ህጻናት በአብዛኛው የሚሞቱት በኢንፌክሽንና በአልሚ ምግቦ እጥረት መሆኑ ታውቆአል፡፡      
ልጆች በተወለዱ በአንድ ሰአት ጊዜ ጡትን ማጥባት አዲስ የተወለዱ እና የጨቅላዎችን ሞት በ45% ሊቀንስ ይችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ህጻናቱ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ካለምንም ተጨማሪ ምግብ የእናት ጡት ወተት ብቻ በመጥባታቸው ካልጠቡት ህጻናት ወደ 14 እጥፍ ያህል ደህንነታቸው ሊረጋገጥ ይችላል፡፡ የምግብ አለመሟላት ለህጻናት ሞት ዋናው ምክንያት ነው። ዩኒሴፍ እ.ኤ.አ በ2010 እንደገመተው በአለም ላይ ከ40-60% የሚሆኑ ከአምስት አመት በታች ያሉ ህጻናት የጤና ቀውስ ምክንያት የጡት ማጥባት ተነሳሽነት ያለመኖር ወይንም ለስድስት ወር የእናት ጡት ወተትን ብቻ አለማግኘት ነበር፡፡
የአለም የጤና ድርጅት የሚመክረው የሚከተለውን ነው፡፡
እናቶች ልጆቻቸውን እንደወለዱ በአንድ ሰአት ጊዜ ውስጥ ጡት እንዲያጠቡ፤
እናቶች ለስድስት ወራት የእናት ጡት ብቻ ለልጆቻቸው እንዲያጠቡ፤
እናቶች ልጆቻቸውን ከስድስት ወር በሁዋላ ተጨማሪ ምግብ እየሰጡ ቢቻል እስከ 2 አመት ድረስ ጡት እንዲያጠቡ ይመክራል፡፡
የጡት ወተት ህጻናትን ጤነኛ በማድረግ እና ህመም እንኩዋን ቢገጥመው ለመቋቋም እንዲችል ያደርጋል፡፡
ህጻናቱ እንደተወለዱ ጡት ማጥባት ክብደታቸው ዝቅ እንዳይል እና በኢንፌክሽን ምክንያት  ለሞት እንዳይዳረጉ ይረዳል፡፡
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በአለም አቀፍ ደረጃ 10% የሚሆነው ከአምስት አመት በታች ያሉ ህጻናት የሚያጋጥማቸው ህመም የእናት ጡት ወተት ብቻ በመጥቢያ ጊዜያቸው ባለመጥባታቸው ነው፡፡ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ህጻናት ለመጀመሪያው ስድስት ወር በትክክል ባለመመገባቸው ምክንያት የሚከሰተው የጨቅላዎች ሞት 96% የሚሆነው የጡት ወተት በትክክል ካለማግኘታቸው ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡
በኢትዮጵያ ጡት ማጥባት በከፍተኛ ሁኔታ የሚተገበር ሲሆን ህጻኑ ከተወለደ እስከ ስድስት ወር ድረስ የእናት ጡት ወተት ብቻ መመገብ ግን ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ እ.ኤ.አ 2016 የወጣው DHS እንደሚያሳየው ወደ 97% የሚሆኑት ህጻናት የጡት ወተት ያገኙ ሲሆን ወደ 58% የሚሆኑት ግን ከስድስት ወር በታች ጡት የጠቡ ናቸው፡፡
ህጻናትን የእናት ጡት ወተት ማጥባት የህጻናቱን ደህንነት ወይንም ጤንነት ማረጋገጥ፤ ህይወታቸው እንዲቀጥል ማድረግ፤ ጠንካራና ጤናማ፤ ብቃት ያለው ዜጋን ለቤተሰብ፤ለ ሀገር፤ ለወገን ማበርከት መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ 

Read 13399 times