Print this page
Monday, 16 August 2021 00:00

አልበሽር ለአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተላልፈው ሊሰጡ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የሱዳን መንግስት በእስር ላይ የሚገኙትን የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽርንና ሌሎች የቀድሞ ባለስልጣናትን ለአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አሳልፎ እንደሚሰጥ ማስታወቁን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መንግስት የቀድሞውን መሪ ኦማር አልበሽርን ጨምሮ በዳርፉር ግጭት ወቅት የጦር ወንጀሎችንና የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን ፈጽመዋል ተብለው በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የሚፈለጉትን የቀድሞ ከፍተኛ የአገሪቱ ባለስልጣናትን አሳልፎ እንደሚሰጥ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያም አል መሃዲ ባለፈው ረቡዕ ማስታወቃቸውን ገልጧል፡፡
አልበሽርና ባለስልጣናቱ ለአለማቀፉ ፍርድ ቤት ተላልፈው እንዲሰጡ ውሳኔ የተላለፈው የሱዳን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ እንዲሁም የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ከሰሞኑ ሱዳንን በጎበኙት ተቀማጭነቱ በሄግ የሆነው አለማቀፉ ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ህግ መካከል በተደረገ ውይይት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መናገራቸውንም ዘገባው አብራርቷል፡፡
ከአልበሽር ጋር ለአለማቀፉ ፍርድ ቤት ተላልፈው ይሰጣሉ ከተባሉት የቀድሞ የሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከልም፣ የአገር ውስጥና የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አብደል ራሂም ሙሃመድ ሁሴን እንደሚገኙበት የጠቆመው ዘገባው፣ የሱዳን አቃቤ ህግ በዳርፉር ግጭት አልበሽርና ሌሎች ባለስልጣናት ፈጽመውታል የተባለውን ወንጀል በተመለከተ ባለፈው አመት የራሱን ምርመራ ጀምሮ እንደነበርም አስታውሷል፡፡
እ.ኤ.አ በ2003 በተቀሰቀሰው የዳርፉር ግጭት ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውንና ከ2.7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 4052 times
Administrator

Latest from Administrator