Print this page
Sunday, 22 August 2021 11:31

ጡት በማጥባት ወቅት ምን ይመገባሉ?

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

  የእናት ጡት ወተት ለልጅ አቻ የሌለው ጠቃሚ ምግብ መሆኑን ማንኛዋም እናት የምትገነዘበው መሆኑ አያጠያይቅም። በሌላ በኩል ጡትን ለልጅ ማጥባት ለእናትየው ጤንነት ጠቃሚ እንደሚሆን ሰምተው ያውቃሉ?
የእናት ጡት ወተት ለሚጠባው ልጅም ሆነ ለምታጠባው እናት ጠቃሚ መሆኑ በእጅጉ የተመሰከረለት ነው፡፡ ጡትን ለልጅ ማጥባት እናትየው ወደፊት በህይወትዋ ሊያጋጥማት  የሚችለውን የልብና የስኩዋር ሕመም የመሳሰሉ የጤና ችግሮችን ለመቀነስ ወይንም እንዳይ ከሰቱ ለማድረግ ይረዳል። ከዚህም በተጨማሪ ጭንቀትን ለመከላከልና ከተወለደው ልጅ ጋር ሰላማዊ የሆነ እና ደስታ የተሞላበት የቅርብ ግንኙነትን ለመፍጠር ይረዳል፡፡
የእናት ጡት ወተት ሁሉን ያሙዋላ ወይንም የተመጣጠነ ምግብ በመሆኑ ለተወለደው ልጅ ጤናማነት እና እድገት በእጅጉ ይረዳል፡፡ ለዚህም ነው በተለይም ልጅ ሲወለድ በመጀመሪያ የሚጠባው ወተት እንደፈሳሽ ወርቅ የሚቆጠረው።
ሴቶች በተፈጥሮአቸው ወርቃማውን ፈሳሽ ስለሚያመርቱ እና ልጃቸው በተወለደ በአንድ ሰአት ጊዜ ውስጥ ስለሚያጠቡ ከሚሰሩዋቸው ብርቅ እና የተለዩ ነገሮች ወይንም በህይወታቸው ካላቸው ብቸኛና በጎ ድርሻ መካከል አንዱ ነው። በእርግጥ ይህንን ለመስራት መውጣት መውረድ ወይንም ጉልበት ማባከን የመሳሰሉ የጉልበት ስራዎች የሉባቸውም፡፡ ነገር ግን ሴቶች በተፈጥሮአቸው ከታደሉዋቸው ልዩ ነገሮች መካከል ነው፡፡
የሚያጠቡ እናቶች የተሟላ ምግብ ማግኘት አለባቸው፡፡
እናቶች ልጆቻቸውን በጤና ለማሳደግ የሚረዳቸውን የጡት ወተት በተገቢው ለማምረት እንዲችሉ እራሳቸው በቂና የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ይገባቸዋል፡፡ ጤናማ ምግብ መመገብ እናቶች በጡት ማጥባት ወቅት ስነልቡናዊም ሆነ አካላዊ ደህንነት እንዲሰማቸው ይረዳል፡፡
የእናት ጡት ወተት በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከቫይታሚን ዲ በስተቀር የቀሩትን ንጥረ ነገሮች ሁሉ ለህጻናቱ ያሟላል፡፡ ነገር ግን እናትየው በአመጋገብዋ አስፈላጊ የሆኑ አልሚ ምግቦችን የማትምገብ ከሆነ የጡት ወተቱ ጥራት ከመቀነሱም ባሻገር የእናትየውም ጤንነት ሊጎዳ ይችላል፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የእናት ጡት ወተት የተሰራው 87% ከውሀ፤ 3.8% ስብ፤ 1.0% ፐሮቲን፤ እና 7% ካርቦ ሀይድሬት ነው።
በጡት ወተት ውስጥ የሚገኘው ካሎሪ መጠኑ እና ይዘቱ ሊቀያየር ይችላል፡፡ በእያንዳንዱ ጡት ማጥባት ወቅት ልጁ የሚፈልገውን ያህል ወተት መስጠት ላይቻል ይችላል፡፡ ምንጊዜም እናቶች ማወቅ ያለባቸው በመጀመሪያው ጡት ማጥባት ወቅት ልጁ የሚያገኘው ውሃማ የሆነውን ሲሆን እስከመጨረሻው ድረስ እንዲጠባ ከተደረገ ግን ወፍራም እና ንጥረ ነገሩ የተሟላ ወተት ማግኘት ይችላል፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በስተመጨረሻው የሚገኘው ወተት ከመጀመሪያው ይልቅ ከ2-3 ያህል ጊዜ እጥፍ የሆነ ስብ ወይንም ፋት እና ከ7-11 ጊዜ የሚበልጥ ካሎሪ ይገኝበታል፡፡ ስለሆነም ለትክክለኛው አመጋገብ ህጻናቱ መጥባት የጀመረውን ጡት ወተቱ እስኪያልቅ ድረስ ማጥባት ተገቢ ነው፡፡
የእናት ጡት ወተት በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ለህጻኑ የሚያስፈልገውን ሁሉ ያሟላ ሲሆን በመቀጠልም በጡት ወተት ውስጥ የሚገኘው ፋት (ስብ) እና ካሎሪው ህጻኑ እያደገ በሄደ ቁጥር ጡት በሚጠባ ወቅት እና ወደፊት በሚጠባት ወቅት ሁሉ ይዘቱ እየተለወጠ የህጻኑን ፍላጎት እያሟላ ይሄዳል፡፡
እናቶች በሚያጠቡበት ወቅት የተሟላ እና የተመጣጠነ ምግብ ያስፈልጋቸዋል፡፡
ጡት የሚያጠቡ እናቶች የረሀብ ወይንም የምግብ ፍላጎታቸው ይጨምራል፡፡ በተለይም ህጻኑ ጡት በሚጠባበት ወቅት እናትየው ሊርባት ይችላል፡፡ እናትየው ሰውነትዋ የጡት ወተትን በሚያመርትበት ጊዜ ተጨማሪ ካሎሪን እና የተወሰኑ ንጥረ ነገሮች በተጨማሪነት ሊያስፈልጋት ይችላል፡፡ በጡት ማጥባት ወቅት የእናትየው አቅም ወደ 500 ካሎሪዎች ያህል በየቀኑ በተጨማሪነት እንድታገኝ የሚጠይቃት መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በተለይም ፕሮቲንን ጨምሮ ቫይታን ዲ፤ ቫይታሚን ኤ፤ ቫይታሚን ኢ፤ ቫይታሚን ሲ፤ ቢ12፤ እና ዚንክ የመሳሰሉትን በየቀኑ በተጨማሪነት ማግኘት ይገባታል፡፡
እናቶች ጡት በሚያጠቡበት ወቅት በተቻለ መጠን የሚያገኙዋቸውን ምግቦች ሳይመርጡ ቢመገቡ የተለያዩ ጥቅሞችን ሊያገኙ እንደሚቸሉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ነገር ግን ከየትኛው ምግብ ምን ጥቅም እንደሚያገኙ አስቀድሞ መገንዘብና መምረጥ ቢቻል አነስተኛም ይሁን ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ጥቅሞች ለህጻኑም ለእናትየውም ማግኘት ያስችላል፡፡
እናቶች ጡት በሚያጠቡበት ወቅት የሚከተሉትን የተሟሉና ጣፋጭ የሆኑ ምግቦችን ቢያገኙ ሳይራቡ ልጆቻቸውን በተገቢው መመገብ ይችላሉ፡፡
አሳ እና የባህር ምግብ፤… ሳልመን...ሼል ፊሽ…ሳርዲን…ወዘተ
ስጋ እና የዶሮ ዝርያዎች፤ የዶሮ ስጋ…የጥጃ ስጋ… የአሳማ ስጋ…. የውስጥ አካል ስጋ (ጉበት…ኩላሊት…) ወዘተ
ፍራፍሬ እና አትክልቶች፤ ቲማቲም… ጥቅል ጎመን…. ነጭ ሽንኩርት… ብሮኮሊ…ወዘተ
ኦቾሎኒ እና ጥራጥሬዎች…፤
ጤናማ የሆነ ስብ ያለባቸው ምግቦች….አቮካዶ…. የወይራ ዘይት…. እንቁላል…. እርጎ…ኮኮናት፤
የእህል ዘሮች…. አጃ… ገብስ… ባቄላ…. የስኩዋር ድንች….
ሌሎች ምግቦች እንደ ጥቁር ቼኮሌት የመሳሰሉትን ጡት የምታጠባ ሴት ብትመገብ ለሰውነቷ የተሟላ ንጥረ ነገር ልታገኝ ትችላለች። በእርግጥ ከላይ በተጠቀሱት የምግብ አይነቶች ብቻ ትወሰን ለማለት ሳይሆን ለማመላከት ያህል ብቻ የተጠቀሱ ናቸው፡፡ ከዚህ በተረፈ አቅም በፈጠረ መንገድ ቤት ያፈራውን እንዲመገቡ ይመከራል፡፡  
ጡት የሚያጠቡ እናቶች በተቻለ መጠን በኢንደስትሪ ተዘጋጅተው ሼልፍ ላይ የተቀመጡ ምግቦችን እና ከውጭ ተዘጋጅተው የሚመጡ ምግቦችን ባይዳፈሩ ይመረጣል፡፡ ተዘጋጅተውና ታሽገው የሚሸጡ ምግቦች ለሼልፍ ቆይታቸው ሲባል የሚኖራቸው ውሁድ ምናልባት ለእናትየውም ሆነ ጡት ለሚጠባው ህጻን ጉዳት ሊኖረው ይቸላል፡፡ በተለይም ስኩዋር የበዛባቸው ምግቦች አይመከሩም፡፡
የጡት ወተት ለሚያጠቡ እናቶች እንዲሟሉላቸው የሚያስፈልጉ ንጥረ ነገሮች የሚገኙባቸው የምግብ አይነቶችን በሁለት መክፈል ይቻላል፡፡ አከፋፈሉም ክፍል አንድ እና ክፍል ሁለት ተብለው ይለያሉ፡፡ ክፍል አንድ የሚባለውን ምግብ የሚወስዱ እናቶች የሚያገኙትን ንጥረ ነገር ከፍ በማድረግ የህጻኑን ጤንነት ይበልጥ ሊያረጋግጥ የሚችል ሲሆን ለልጁም ለእናትየውም ጥቅም የሚገኝበት ነው፡፡
በክፍል ሁለት የሚመደቡት ንጥረ ነገሮች በበኩላቸው እናትየው ምንም ያህል ብትመገባቸው በጡት ወተቱ ላይ ብዙም ለውጥ የማያመጡ ሲሆን ይበልጥ የእናትየውን ጤንነት ማሻሻል ላይ የሚያግዙ ናቸው፡፡
በክፍል 1 የተመደቡ የምግብ አይነቶች፤
ቫይታሚን ቢ1፤ አሳ…የአሳማ ስጋ…ለውዝ…ባቄላ.ወዘተ.
ቫይታሚን ቢ2፤ አይብ…. አልመንድ…ቀይ ስጋ.. እንቁላል…ወዘተ
ቫይታሚን ቢ6፤ አሳ..ድንች…ሙዝ…እንቁላል ..ወዘተ
ቫይታሚን ቢ12፤ ጉበት…እርጎ…ዘይታማ አሳ…እንቁላል..ወዘተ
ቫይታሚን ኤ… ቫይታሚን ዲ… አዮዲን..ወዘተ የመሳሰሉት ናቸው፡፡
በክፍል ሁለት የተመደቡት፤
ካልሺየም፤ ወተት.. እርጎ… አይብ… አረንጉዋዴ ቅጠላ ቅጠሎች… አቮካዶ…ወዘተ
አይረን፤ ቀይ ስጋ…. የአሳማ ስጋ…. የባህር ምግቦች… ባቄላ… አረንጉዋዴ አትክልቶች…ወዘተ
ኮፐር…ዚንክ… የሚገኝባቸውን ምግቦች መመገብ ጠቃሚ ነው፡፡
እናቶች ጡት በሚያጠቡበት ወቅት ፈሳሽ መውሰድ የሚጠቅማቸው ሲሆን በተለይም ውሀ መጠጣት ጠቃሚ ነው፡፡
ምንጭ https://www.healthline.com

Read 10915 times