Saturday, 08 September 2012 12:30

የኑሮ ውድነት፣ የሀገራችን ፖለቲካ የመጨረሻው ፈተና!

Written by  ገዛኸኝ ፀ.
Rate this item
(0 votes)

ፈር መያዣ፡- ባለፈው ሣምንት “አቶ መለስ ለዓላማቸው ኖረዋል፤ ኢትዮጵያ ለራሷ ታልቅሥ!” በሚል ርዕስ፣ በሀገራችን የመሪ እና የተመሪ ህዝብ ግንኙነት ጥልቅ ጥናት የሚሻ እየመሰለኝ ስለመምጣቱ፣ ከፖለቲካ ንቃተ ህሊናችን ይልቅ ህብረተሠባዊው የአስተሳሰብና የአሰራር ልማዳችን የበለጠ ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ ስለ መሆኑ፣ ከተዥጐረጐረ ባህልና ቋንቋችን የሚቀዳው ዥጉርጉር ማንነታችን ያልሰከነና ያልጠራ ህዝባዊ ባህርይ ያጋባብን ስለመምሰሉ፣ የሚሉ ርዕሠ ጉዳዮች ተነስተው ነበር፡፡ በተለይ፣ ፖለቲከኞቻችን የበሰለ የፖለቲካ ርዕዮተዓለም እና አተገባበር ይዘው የሀገር መሪ ለመሆን ቢጥሩ እንኳ፣ በቅኔ የኑሮ ዘልማድ እየተገራ ባልጠራና ባልሰከነ ግንፍል ስሜት የሚናጠው ዜጋ በመጠንም በአይነትም ስለሚበልጥ፣ ሀገራዊ ልማቱ እንደሚታሠበው ቀላል እንደማይሆን በዚህ ሳቢያም፣ ህዝቡ ነው መሪ ያጣው ወይስ መሪው ነው ህዝብ ያጣው የሚል ጉዳይ ሊነሳ እንደሚገባ መጣጥፉ አውስቷል፤ በመጨረሻም የኑሮ ውድነት ሀዘናችንን እንዳያከፋው በሚል አንድ ኩንታል ጤፍ 2ሺ ብር የሚሉ ስግብግብ ነጋዴዎች እንዳጋጠሙኝ ጠቆም አድርጌ ነበር የዕለቱን ፅሁፍ የቋጨሁት፡፡ ዛሬ ታዲያ የኑሮ ውድነት የሀገራችንን ፖለቲካ የሚዘውር ትልቅ ፈተና ስለመሆኑ፣ የአቶ መለስን ቃል ዋቢ እያደረግን እንወያይ - መርዶ ለመንገር ሳይሆን መላ ለመፍጠር!

የኑሮ ውድነትና የመልካም አስተዳደር እጦት መዘዞች፡-

በሀገራችን የኑሮ ውድነት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የመልካም አስተዳደር እጦት አካል የሚሆንበት ብዙ አጋጣሚዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም በተለያዩ መድረኮች ቅጥ ላጣው የንግድ ሥርአታችን በዋናነት ተጠያቂ ካደረጓቸው ውስጥ፣ “የመንግስት ሌቦችና ጥገኛ ባለሀብቶች” መሪነቱን የሚይዙ ይመስለኛል፡፡ እርግጥ ነው የኑሮ ውድነት፣ በመልካም አስተዳደር እጦት ሣቢያ ሊከሠት እና/ወይም ሊባባስ ይችላል፡፡ በተመሳሳይ መልኩም፣ የቡድን ዝርፊያዎች (ጐጠኝነት)፣ በየደረጃው የሚታዩ፣ የየሥራ ሂደቶቹ ኋላቀርና ዘመነኛ የሙስና አይነቶች፣ የፍትህ እጦቶች መነሻቸውም ሆነ መስፋፊያቸው፣ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በሀገሪቱ እየተንሰራፋ የመጣው የኑሮ ውድነት አንዱ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ ስለዚህ፣ የኑሮ ውድነትና የመልካም አስተዳደር እጦት፣ አሁን ባለው በእኛ ሃገር ተጨባጭ ሁኔታ ተወራራሽ ናቸው ማለት ይቻላል፤ አንዱ ለአንደኛው መለኮሻ፣ አንደኛው ለአንዱ ማራገቢያ እንዲያም ሲል ቤንዚን የሚሆኑበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡

ዛሬ ሀገር እየመራ ያለው “አውራው” ፓርቲ ኢህአዴግ እና/ወይም መንግስት “የህዳሴ መሀንዲሱንና ባለራዕይ” መሪውን ባጣበት በዚህ ከባድ የሀዘን ወቅት፣ ጠንካራ ምስጢራዊነቱና በምንም የማይሸበር መሆኑ ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ የተቀዳጀው ብቃቱ እንደሆነ በአጽንኦት ይናገራል፡፡ በተጀመረውም “የለውጥ” ጐዳና በመጓዝ የመሪውን “ራዕይ” እና እቅድ ከግብ እንደሚያደርስ በልበ ሙሉነት እየተናገረ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ፣ የኑሮ ውድነት፣ ታላቅ ህዝባዊ ፈተና ሊሆንበት እንደሚችል እና ለዚህም ተገቢውን ጥንቃቄና ተጨባጭ መፍትሔ እያደረገ እንዳልሆነ፣ የመሪውን የአቶ መለስን የስጋት ቃል እያጣቀሰ ጠንካራ አቋሙን አጉልቶ አላወጣም ማለት ይቻላል፡፡

የኑሮ ውድነቱ ግን፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ህልፈት በኋላ እያሻቀበና ህዝቡን እያስደነገጠ ነው፡፡ 1ሺ 4 መቶ ብር ይሸጥ የነበረ አንድ ኩንታል ጤፍ በሀዘን ቀናቱ ወደ 2ሺህ ብር ማሻቀቡን ሰምቻለሁ፤ “ሪፖርተር” ጋዜጣ በረቡዕ እትሙ 2ሺህ 1 መቶ ብር መሸጡን መረጃ ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ የሽንኩርት፣ የቲማቲም ወይም አጠቃላይ የምግብ ፍጆታዎች ሰሞኑን ዋጋቸው አሻቅቧል፡፡ የኑሮ ውድነቱ ችጋር (ድህነት)፣ ችጋሩ ደግሞ ጐጠኛ አስተሳሰብና አሠራርን፣ ልቅ ሙስናን፣ የፍትህ እጦትን እየፈጠሩ ወይም እያባባሱ ሊሄዱ ይችላሉ፤ የፖለቲካ ሥርአቱንም አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል፤ የባለ ራዕዩን መሪ ተስፋዎች ብቻ ሳይሆን ሥጋቶችንም በወጉ መመርመር ይገባል!

የኑሮ ውድነት፣ የሀገራዊ ፖለቲካ የመጨረሻ ፈተና

የኑሮ ውድነት፣ ለድህነትና ለመልካም አስተዳደር እጦት እንደሚያጋልጥ ይታወቃል፡፡ በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ግን አንዱ የሌላው መንስኤና ውጤት በመሆን ስለሚወራረሱ፣ መዘዛቸው ፖለቲካዊና ሀገራዊ መልክ መያዛቸው አይቀርም፤ ተገቢውን የፖለቲካ ውሳኔ በፍጥነት መስጠት ካልተቻለ፣ አሁን እያሻቀበ ያለው የኑሮ ውድነት፣ ድህነትንና የመልካም አስተዳደር እጦትን እያባባሰ አንድን አውራ ፓርቲ ቀርቶ፣ ሀገርን እስከ መበታተን ሊያደርስ እንደሚችል ሁሉም ዜጋ ሊገነዘብ ግድ ይላል፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የተናገሩትን ማስታወስ ብልህነት ነው፡፡

የመለስን ምልልሶችና ንግግሮች በቀጥታ ያሰፈረው የትኩእ ባህታ፣ “መለስ፤ ከልጅነት እስከ እውቀት” የሚለው መጽሐፍ በገጽ 73 ላይ እንዲህ ይላል፤ “ተቃዋሚዎች ኢትዮጵያ በድህነትና በመልካም አስተዳደር እጦት የተነሳ ለመበታተን አደጋ አትጋለጥም ሲሉ ይሰማሉ፡፡ ይህን እንዴት ይመለከቱታል?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው የሚከተለውን ስጋት ያዘለ የማንቂያ መልስ ሰጥተዋል፤

“መቼም እንግዲህ ማንም ሰው ሰማይ ከመሬት የራቀው፣ በቅሎ ስትንፈራገጥ ስለመታችው ነው ብሎ ማመን ይችላል፡፡ ይህ ትክክል ነው አይደለም ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ እነዚህም ሰዎች ድህነትና የመልካም አስተዳደር እጦት አገርን አይበትንም የሚል አቋም የመያዝ መብት አላቸው፤ ልክ ሰጐን ራሷን አሸዋ ውስጥ የመቅበር መብት እንዳላት ሁሉ፡፡

ስለገሃዱ እውነታ የምናወራ ከሆነ ግን በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ብቻ መወሰኑ በቂ አይመስለኝም፡፡ ወደ ግራ፤ ወደ ቀኝ፣ ወደ ታች፣ ወደ ላይ፣ ወደ ፊትና ወደ ኋላ ማየትን ይጠይቃል፡፡ ወደ ምስራቅ በምናይበት ወቅት ሶሚሊያን ማየት ነው፡፡ ድህነትና የመልካም አስተዳደር እጦት አገርን ሊበትን እንደሚችል ሶማሊያን በማየት መረዳት ይቻላል፡፡ ወደ ምዕራብ ካቀኑም ላይቤርያንና ሴራሊዮንን ማየት ይቻላል፡፡ ከክፍለ አህጉራችን እንውጣ ካልን ደግሞ እነአፍጋኒስታንን ማየት ይቻላል፡፡ እናም ይሄ የንድፈ ሃሳብ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ በተግባር በብዙ አገሮች እየተፈፀመ ያለ ነው፡፡ የአገሮች መበታተን፣ የህዝቦች መነጣጠል ንድፈ ሃሳባዊ ጉዳይ አይደለም፡፡ በተጨባጭና በተግባር እየታየ ያለ ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡

የኑሮ ውድነት፤ የተለያዩ የፖለቲካ ርዕዮተዓለም ተከታዮችን፣ የመንግሥት (የአውራው ፓርቲ) አባላትንና ደጋፊዎችን፣ ተቃዋሚዎችን እና “መሀል ሠፋሪዎችን፣” በአጠቃላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በአንድ የሚያሰልፍ ፖለቲካዊ ችግርም ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ የአቶ መለስን ርዕይ ዳር እናደርሳለን ስንል፣ “ድህነት ዋነኛው ጠላታችን ነው” ያሉትን እየረሳን አይደለም፡፡

የኑሮ ውድነት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ዋነኛው ጠላታችን ከመሆኑ የሚገታው አንዳች ሀይል እስካልፈጠርን ድረስ፣ ሀገራዊ መዘዝ ሊያመጣ እንደሚችል አለመጠርጠር ከባድ ነው፤ ለፖለቲካ ሥርአቱ የመጨረሻው ፈተና ሊሆን እንደሚችል አለመገመት ችግር ነው፤ ለፖለቲካ መሪዎች ብቻ የሚተው ሳይሆን፣ ሁሉም ዜጋ የየድርሻውን የሚያዋጣበት ነው ብሎ አለመንቃትም ሀገራዊ ሀጢያት ነው ማለት የሚቻል ይመስለኛል፡፡

 

 

Read 1656 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 12:36