Sunday, 22 August 2021 11:56

‘ጥቁር’ እና ‘ነጭ’ ብቻ ቢሆን...እንዴት በቀለለ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይኸው... ሁለት ሺህ አሥራ ሦስት የሚሉት ራሱ ጎድሎ፣ ህዝብና ሀገርን ሲያጎድል የከረመ ዓመት፣ ውልቅ ሊልን ጫፍ ላይ ነው፡፡ ከእነ ግሳንግሱ ውልቅ ይበልልንማ! ቢያንስ፣ ቢያንስ መደማመጥ የምንጀምርበት ዓመት ይተካልን! ከልባችን “አዲሱን ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ አብሮ የመኖርና የመቻቻል ያድርግልን!” የምንባባልበት ያድርግልንማ!
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል...አላላውስ ካሉን ችግሮች አንዱ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ... ሁሉም ነገር ወይ ጥቁር፣ ወይ ነጭ ነው፡፡ ምናልባት ዘጠና ወይም ዘጠና አምስት በመቶውን የሚሸፍነው ግራጫ ብሎ ነገር የለም፡፡ እናላችሁ...እንዲህ ሆኖ ያለመደማመጣችን ምንስ ይገርማል! 
“እንደምን ነሽ?”
“ደህና፣ ደህና ነኝ፡፡ አንቺስ?”
“ደህና፡፡ እንዴት ነው ነገሩ... ቀን በቀን እኮ በጣም እያማረብሽ ነው! የማናውቀው የተገኘ ነገር አለ እንዴ?”
“ካየሽኝ ትንሽ ስለቆየሽ ነው እንጂ ምንም የተለየ ነገር የለም፡፡”
“ከዚህ በላይ ምን ትሆኚ! አንጀሊና ጆሊን ልትመስይ ምንም አልቀረሽም እኮ!” (የፈረደባት አንጀሊና ጆሊ!)
እና ከተለያዩ በኋላ...
“አንቺ ያች እንትና ዛሬ በአሽሙር አትናገረኝ መሰለሽ...”
“ረጋ በያ! የምን መርገፍገፍ ነው! ምን ብትልሽ ነው እንዲህ ያበሳጨሽ?”
“ቀን በቀን እያማረብሽ ነው አትለኝ መሰለሽ!”
“ታዲያ ምን ችግር አለው?”
“ቀን በቀን የምትለኝ፣ እሷ ትቀልበኛለች እንዴ!”
“ምናልባት አነጋገሩን አላወቀችበት ይሆናል እንጂ ለክፉ አስባ ላይሆን ይችላል።”
“እባክሽ የዘንድሮ ጓደኛ ሁሉም ምቀኛ ነው!”
በቃ በአንዲት ሰው ንግግር ምድረ ጓደኛ ሁሉ በአንድ ሙቀጫ! ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ... እሷስ በቀን አስራ ስምንት ጊዜ መስታወት ፊት የምትቆመው፣ እንዴት እያማረባት እንደሆነ ለማየት አይደለም?!
ስሙኝማ... ዘንድሮ አነጋገር ባለማወቅ ጎል የሚገባው ስንቱ መሰላችሁ! በተለይ በቦተሊካማ ምን መሰላችሁ፣ ከምንፈራረጅባቸው ‘መለኪያዎች’ አንዱ እኮ የቃላት አጠቃቀማችን ነው፡፡ (እነ እነትና... “እንዳካሄድ፣” “ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፣” ምናምን የሚሉ ቃላት ላለመጠቀም የምናመነታበት ‘ሴክሬት’ ገባችሁ አይደል! ቂ...ቂ...ቂ...)
ታዲያላችሁ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል...ሁሉም ነገር ጥቁርና ነጭ ሆኖ ጠቃሚ ሀሳቦች፣ ጠቃሚ ምክሮች፣ ጠቃሚ ተሞክሮዎች፣ ጠቃሚ የመፍትሄ ሀሳቦች እያመለጡን ነው፡፡ ቦተሊካው ውስጥ እንደየ ግላዊ አስተሳሰቦቻችንና እንደየ እምነቶቻችን ምነም ነገራቸው ደስ የማይሉን ፖለቲከኞች አሉ፡፡ ምን አለፋችሁ... ሁሉም ነገራቸውን እኛ እንደግፈዋለን የምንለውን ወገን ለማጥፋት የሚደረግ ጥረት አድርገን እናየዋለን፡፡ ምን ይሆናል መሰላችሁ... የእነሱን የሬድዮና የቴሌቪዥን ቃለ መጠይቆች ማዳመጥና ማየት፣ እነሱን በተመለከተ ጋዜጦችና መጽሄቶች ላይ የሚወጡትን ነገሮች ማንበብ፣ እንደ ሀጢአት ነው የሚሆንብን፡፡ (“እሱን ሰውዬ እንደው ከዚህ ሀገር ፖለቲካ ውስጥ በወረንጦም ይሁን በምናምን ነቅሎ የሚያወጣልን እንጣ!” በሚል ርእስ፣ በያንዳንዱ የ‘ፕሬሚየር ሊግ’ ፖለቲከኛ ላይ የህዝብ አስተያየት ይሰብሰብልንማ!
“ስማ ትናንትና እነ እንትን ቴሌቪዥን ላይ የቀረበውን የእንትናን ክርክር አላየሁትም እንዳትለኝ!” (ይህችን አይነት አቀራረብ ‘ማካበጃ’ አትመስላችሁም! ልክ ነዋ...“አየኸው ወይ?” አይነት ቀጥተኛ አባባል እያለች...አለ አይደለም... “አላየሁትም እንዳትለኝ!” አይነት አነጋገር፣ ስዌዝ ካናልን የሆነ መርከብ ስለዘጋው አንድ ጠርሙስ ጠጅ ላይ የአስራ ሰባት ብር ጭማሪ እንደ ማድረግ በሉት! እኛ እኮ ድሮም “ጠጅ ውስጥ ማር ድሮ ቀረ” ሲሉን የነበሩትን የ‘ጉዳዩን ኤክስፐርቶች፣ “ይቺ እኳን ከስምንተኛው ብርሌ በኋላ የምትመጣ ሀሳብ ነች፣” ብለን መተረቡን ትተን ብናዳምጣቸው፣ ለስኳር እንዲህ መጥፋትና መወደድ አንዱ ምክንያት ምን እንደነበር መጠርጠራችን አልቀረም ነበር፡፡  እኔ የምለው...እንደው ምንስ ቢቸግር ጨው ላይ ይጨምሩብናል!)
“እንትና ያቀረበው ሀሳብ እንዴት እንደተመቸኝ ልነግርህ አልችልም፡፡ ፖለቲካውን እኮ እንደ ዶሮ ብልት ገነጣጥሎ ነው ሲተነትነው የነበረው!” (ዶሮን በማታውቀው አታነካኳትማ!)
“አንተ...እንዲህ ስትል ሰው እንዳይሰማህ። ማንም ካሜራ ፊት ቀርቦ የቀባጠረ ሁሉ ሀሳብ አቅራቢ ነው ማለት ነው!”
“እየው እንግዲህ... ድሮም የሀበሻ ነገር እኮ እውቀት ያለው ሰው አትወዱም፡፡”
(ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል... እንደዚች አይነት አባባል በጥቅል ስትነገር ደጋግመን እንሰማለን፡፡ ሰዉ መሰል አስተያየቶችን  ሊሰጥባቸው የሚችሉ ምክንያቶች አንዳንዴ “ያስብላሉ...” የሚባሉ አይነት ቢሆኑም፣ እንዲህ እውቀትና እውቀቱ ያላቸው ላይ ጅምላ አሉታዊ አመለካከት ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡ እዚህ ሀገር ብዙ ነገር፣ በጣም ብዙ ነገር እየተበላሸ ያለው፣ በእውቀት ባለመመራቱና ባለመሠራቱ ይመስለናል፡፡)
“እውቀት! እውቀት ነው ያልከው!...”
“ቆዩ እስቲ፣ ቆዩማ! እስቲ እኛ ደግሞ ሁለታችሁንም ልጠይቃችሁ፡፡ አንተም ጥሩ ናቸው የምትላቸውን ነጥቦች አንድ በአንድ ነቅሰህ ተናገር፤ አንተም ሃሳብ ሳይሆኑ መቀባጠር ናቸው ያልካቸውን ነገሮች ለይተህ ተናገር፡፡ ምን ለማለት ነው... በየራሳችሁ መንገድ ስንዴና እንክርዳዱን ብትለዩልን እኮ፣ ለእኛም ለፍርድም ያመቻል፡፡”
‘በዚህ ዘመን እንዲህ የሚያግባቡ ሀሳቦች የሚሰጡ ሰዎች ሲገኙ፣ “እውነት ብላችኋል። ተደማመጡ የሚሉ ሰዎች መኖራቸው በራሱ እሰየው የሚያሰኝ ነው” ምናምን መባል ይገባው ነበር... አብዛኛውን ጊዜ አይሆንም አንጂ!
“እሱ የሚናገረው ምን እንክርዳድ አለውና ነው፣ እንክርዳዱን ለይ የምትሉኝ! መቼም ቢሆን እሱ የሚሰጣቸው ሀሳቦች ውስጥ እንዲች የምታክል ስንጥር የሚገኝበት ሰው አይደለም!” (ይቺ ሀገር አንተ እንደምትለው አይነት አይደለም ሚሊዮንና መቶ ሺዎች፣ መቶ ሰዎች እንኳ ቢኖሩ፣ ሀገር ምን ያህል በተባረከች ነበር!)
“አንዲት ፍሬ እህል የማይገኝበት ውስጥ፣ የሌለውን ስንዴ ከየት ነው ለይቼ የማወጣው! እሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎቹም እኮ ያው ናቸው!” (አንተ እንደምትለው፣ ከምትደግፈው ቡድን ውጪ ሌላው ሰው ሁሉ እንደዛ ከሆነ አንዲት ነገር ልትተባባረን ይገባል... ገሀነም እኛን ሁሉ ሊያዝ የሚችል ቦታ እንዳለው አስቀድመህ መረጃ ሰብስብልንማ! እንግዲህ ቁርጣችንን ከነገራችሁንና ከ‘ፈረደባችሁን’ ምን እናድርግ!) 
ወይ እዚህ ነህ፣ ወይ እዚያ ነህ!
ወይ ደግ ነህ፣ ወይ ክፉ ነህ!
ወይ አዋቂ ነህ፣ ወይ ደደብ ነህ!
ዓለም እንዲህ ለይቶላት ጥቁርና ነጭ ብትሆን እንዴት አሪፍ ይሆን ነበር፡፡ አይደለም እንጂ! አይሆንምም እንጂ!
እከሊት ወይ ‘ቆንጆ’ ናት፣ ወይ ‘አስቀያሚ’ ናት...አለቀ፡፡ የምር... ልክ አይደለም! ልክ ነዋ...እንዲህ አይነት ነገር እኮ... አለ አይደል ዘጠና ስምንት ከመቶ የሚሆኑትን ከጨዋታ ውጭ የሚያደርግ ነዋ!
እከሊት ወይ ባለሙያ ነች ወይ ሙያ የላትም፡፡ (‘ገልቱ’ የሚለው ቃል ‘ፖለቲካሊ ኮሬክት’ ስላልሆነ ነው፡፡ ቂ...ቂ...ቂ...)
ጥርግ አድርገን ከበላን በኋላ...
“አሁን ዶሮ ሠራሁ ብላ ልቧ ውልቅ ብሏል እኮ!”
“ከዚህ በላይ ምን እንዲሆንልህ ፈለግህ? እኔ እንደውም እንዲሀ አይነት ክሽን ያለች ዶሮ ወጥ ከበላሁ ስንት ጊዜ!”
“አይታይህም እንዴ! ዶሮዋ ራሷ ተገነጣጥላ የገባች ሳይሆን በዱቄት መልክ የተነሰነሰች ነው እኮ የምትመስለው፡፡”
ብቻ....ሁሉን ነገር በጥቁርና ነጭ መልክ ከመተርጎም እስካልወጣን ድረስ፣ ሁሉም ነገር አስቸጋሪ ሆኖ ሳይቀጥል አይቀርም ለማለት ያህል ነው፡፡
ጾመ ፍልሰታ ላይ ለከረማችሁ...መልካም ፍስክ ያድርግላችሁ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1642 times