Tuesday, 24 August 2021 00:00

የቶማስ ሳንካራ ግድያ ከ35 አመት በኋላ በፍ/ቤት ሊታይ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 አፍሪካዊው ቼ ጉቬራ በሚል ስያሜ በሚታወቀው የቀድሞው የቡርኪናፋሶ መሪ ቶማስ ሳንካራ ግድያ ክስ የተመሰረተባቸውና በስደት ላይ የሚገኙት የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬ ጉዳይ ከ35 አመት በኋላ በፍርድ ቤት ሊታይ መወሰኑን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ በ1987 በፈተጸመ ጥቃት ቶማስ ሳንካራን በመግደል ወንጀል የተከሰሱትንና ድርጊቱን እንዳልፈጸሙት በተደጋጋሚ ሲናገሩ የሚደመጡትን የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬን ጨምሮ  ክስ የተመሰረተባቸው 13 ሰዎች ጉዳይ በመጪው ጥቅምት ወር መጀመሪያ በጦር ፍርድ ቤት መታየት እንደሚጀምር የአገሪቱ አቃቤ ህግ ባለፈው ማክሰኞ ማስታወቁን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ከሚታየው ሌሎች ተከሳሾች መካከል የኮምፓዎሬ የቀኝ እጅ እንደነበሩ የሚነገርላቸው የቀድሞው የአገሪቱ ደህንነት ሃላፊ ጄኔራል ጊልበርት ዴንድሬ እንደሚገኙበት የጠቆመው ዘገባው፣ ጉዳዩ ከሶስት አስርት አመታት በላይ ለህግ ሳይቀርብ ከመቆየቱ ጋር በተያያዘ ክስ ቢመሰረትባቸውም ከዚህ አለም በሞት የተለዩ ተጠርጣሪዎች እንዳሉም አስታውሷል፡፡
እ.ኤ.አ በ1983 በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዘው ቶማስ ሳንካራ፣ ከአራት አመታት በኋላ በኮምፓዎሬ ሴራ በ37 አመት ዕድሜው መገደሉን ያስታወሰው ዘገባው፣ ኮምፓዎሬ በበኩላቸው ለ27 አመታት በስልጣን ላይ ቆይተው በ2014 በተቀሰቀሰ ህዝባዊ አብዮት ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ወደ ኮትዲቯር ተሰድደው እስካሁን በዚያው በስደት ላይ እንደሚገኙም አክሎ ገልጧል፡፡


Read 4321 times