Print this page
Sunday, 22 August 2021 12:57

ቅዱስ ጊዮርጊስና ቡሔ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

የመጀመርያው የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ገብረስላሴ ኦዳ ተመስግነዋል ‹‹ጋሽ ይድነቃቸው ለክለባቸው የማይረሱ አርማችን ናቸው፡፡›› - የጊዮርጊስ        አስጨፋሪዎች ‹‹ከ5 ዓመታት በኋላ የአፍሪካ ሻምፒዮን ይሆናል›› - ረ/ፕሮፌሰር ጎሳ ገብረስላሴ ‹‹የጊዮርጊስ ብርቱነት አንድነታችን ነው›› - አቶ አብነት ገብረመስቀል


             ምንግዜም ጊዮርጊስ የራድዮ ፕሮግራም ባስተናበረው ልዩ የቡሔ በዓል  አከባበር ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብነት ገብረመስቀል፤ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን በቀለና ሌሎች አመራሮች ታዋቂ የክለቡ አስጨፋሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የሚዲያ ተቋማት ከትናንት በስቲያ ኦዳ መደመር አፍሪካ የስነጥበባት ስፍራን ጎብኝተዋል፡፡ የጉብኝቱ ዋና ዓለማ  የገብረስላሴ ኦዳ ቤተሰብ በስፖርቱ መስክ ያደረገውን አስተዋፅኦ በመዘከር ምስጋና ለማቅረብ እና ለስነጥበብ የሚሰጠውን ድጋፍ በአካል ተገኝቶ ለመታዘብ ነበር፡፡  በዚሁ ልዩ የቡሔ በዓል አከባበር ስነስርዓት ላይ  የጎማ ቁጠባ ሰራተኞች፤ የስነጥበብ ስፍራው መስራች ረዳት ፕሮፌሰር ጎሳ ገብረስላሴ እና ታዋቂ ሰዓሊዎች ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ደማቅ አቀባበል አድርገዋል፡፡
የምንግዜም ጊዮርጊስ ራድዮ ፕሮግራም  አዘጋጅ ካሳሁን ደርበው ‹‹ካስትሮ ሳንጃው››  ልዩ አከባበሩን ያስጀመረው የጅብራልተሩ አለት ብሎ የጠራቸውን  ክቡር ይድነቃቸው ተሰማን በ1 ደቂቃ ጭብጨባ እንዲመሰገኑ በማድረግ ነው፡፡ ታላቁ የስፖርት ሰው የትውልድ ቀናቸው መስከረም 1 ላይ በእንቁጣጣሽ ቀን እንደነበር ያስታወሰው ካሳሁን ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ደግሞ ነሐሴ 13 በቡሄ ቀን መሆኑን በማውሳት ክቡር ይድነቃቸው ቅዱስ ጊዮርጊስን ጠንንሰው ትልቅ ክለብ ማድረጋቸውን ተናግሯል፡፡ የሱን ንግግር ተከትለውም  እነ አቸኖ እና ሳክስፎኒስቱ ኢዮብ ከዋናዎቹ የጊዮርጊስ አስጨፈሪዎች ጋር ‹‹ጋሽ ይድነቃቸው ለክለባቸው የማይረሱ አርማችን ናቸው፡፡›› በሚል ዘምረዋል፡፡
በኦዳ መደመር አፍሪካ ስነጥበባት ስፍራ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የቡሄ በዓሉን ሲያከብር ከችቦ ማብራት ስነስርዓቱ በፊት የተለያዩ ፕሮግራሞች ተካሂደዋል፡፡ የጊዮርጊስ አስጨፋሪዎች በሆያ ሆዬ ጭፈራቸው  እንዲሁም የክለባቸውን ዝማሬ በማሰማት የስነጥበብ ስፍራውን ሲያደመቁት ቆይተው  ካሳሁን  ንግግሩን ከመድረክ ቀጠለ
‹‹ጊዮርጊስ በወርሐ ታህሳስ 1928 ላይ በይፋ ቢመሰረትም፤ ክለቡ የተጠነሰሰው በነሐሴ ወር 1927 ዓም ላይ ነበር፡፡ አየለ አትናሽ ጓደኛውን ጆርጅ ዱካስን አማከረው፡፡ ኢትዮጵያዊ ለዛ ያለው፤ ኢትዮጵያዊ ጣዕም ያለው፤ አርበኛ ታላቅ ድንቅ ክለብ እንመስርት፡፡ እንጀምረው እኛ፤ ብዙዎች ይከተሉናል በማለት፡፡ ከዚህ በኋላ ሶስት ነገሮችን ማድረግ ግድ ነው፡፡ ስም ማውጣት፤ የተጨዋቾችን ቁጥር ከፍ ማድረግ እንዲሁም ማልያ መግዛት፡፡ አየለና ጆርጅ ይህን ለጓደኞቻቸው አማክረው አሳመኑ። የተጨዋቾች ብዛት 9 ደረሰ፡፡ ቡድኑን በዚህ ጊዜ ላይ የአራዳው ጊዮርጊስ ብለው ሰየሙት። የቀረው አንድ ነገር ነው፡፡ የመጫዋቻ ማልያ መግዛት፡፡ ለዚህም ይሄ ቡሔ ሊያልፈን አይገባም ብለው ነሐሴ 13 ቀን 1927 ዓ.ም ላይ ዘጠኙ ጓደኛሞች ሰብሰብ ብለው በመላው አዲስ አበባ ሆያ ሆዬ በመጨፈር የቡሄን በዓል አክብረው ያገኙትን ሙሉሙል ዳቦዎች ሰራተኛ ሰፈር ወስደው በመሸጥ ታሪካዊውን የቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመርያ ማልያ በዚሁ እለት ለመግዛት በቁ፡፡ ተጨዋቾቹን የክለቡ የመጀመርያ ስፖንሰሮች ብሎ መጥራት ይቻላል፡፡›› በማለት አስገራሚውን ታሪክ ገለፀ፡፡
ከዚህ በኋላ የመጀመርያው የክለቡ ቤተሰብ፤ የመጀመርያው የክለቡ ፕሬዝዳንት ለመሆን የበቁት አቶ ገብረስላሴ ኦዳ መሆናቸውን በመግለፅ በደጋፊው  እንዲመሰገኑ ጠየቀ፡፡ የስፖርት ክለቡ  ታሪካዊው ኢትዮጵያዊ ኩባንያ ጎማ ቁጠባ የሚገኝበትን ጊቢ እና የስነጥበብ ስፍራውን በመጎብኘት የቡሄ በዓልን ለማክበር የወሰነው ይህን ታሪክ ለመዘከር እና ለረዳት ፕፌሰር ጎሳ ገብረስላሴ ልዩ ሽልማቶችን ለማበርከት ነበር፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር ጎሳ ገብረስላሴ ባደረጉት ንግግር ታሪካዊው ቅዱስ ጊዮርጊስ የቡሄ በዓልን ያከበረበትን መንገድ አድንቀው ክለቡ በሚቀጥሉት አምስት አመታት የአፍሪካ ሻምፒዮን እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል።
በቀጣይ አቶ አብነት ገብረመስቀል የተናገሩ ሲሆን ‹‹የክለባችን ደጋፊዎች በትእግስት ከእኛ ጋር መጓዝ ለምዳችኋል፤ አይታችኋል፡፡ እንኳን ለእኛ ለሌላውም የምታስቀኑ ናችሁ፡፡ በርቱ ነው የምንለው፡፡ አጎቴ አቶ ገብረስላሴ ኦዳ ከውጭ አገር በተመለስኩበት ወቅት፤ በጊዮን ሆቴል ትልልቅ ሰዎችን ሰብስበው ጠርተው፤ ልጄ እኛ ለፍተን እዚህ አድርሰነዋል፡፡ አሁን ደግሞ ጉልበትም አቅሙም ሊኖርህ ስለሚችል ይህን ቡድን ተረከብ ሲሉኝ  የምይዘው የምጨብጠውን ያጣሁት፡፡ እንዴት አድርጌ እንደምይዘው እንዴት አድርጌ እንደምመራው አላውቅም ነበር። በወቅቱ ግን ቀኛዝማች ከድር ኤባ፤ አቶ አባተ ልመነህ እና አቶ አሸናፊ ተሰማ ሌሎች ትልልቅ ሰዎች በሙሉ በአጠገቤ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ማድረግ ያለብኝን ሁሉ፤ ማዳመጥና መከተል የነበረብኝን ሁሉ አድርጌያለሁ፡፡ ዛሬ ደግሞ እነሱ ሲያልፉ እኔን እየመከሩ፤ እየቀረፁ እዚህ አድርሰውኛል፡፡
ጊዮርጊስ ብዙ ውጣውረድ ያየ፤ ለምንም ነገር ደግሞ የማይንበረከክ ዓላማ ያለው ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ ደጋፊውም ጥንካሬው ከብረት የጋለ ነው፡፡ ጠንካራ ነን። በፀሃይ፤ በብርድ፤ በድብደባ ተፈትነነናል። ተበድለን  ያው ተመልሰን እናሸንፋለን፡፡ የጊዮርጊስ ብርቱነት አንድነታችን ነው፡፡ አንድ ክለብ አንድ ቤተሰብ ሆነን እስከዘለቅን ድረስ የሚነካን ምንም ሃይል የለም፡፡ ስለዚህም ሁሌም አደራ የምላችሁ እኛ ባለን አቅም ከአባቶቻችን የወረስነውን ትልልቅ ነገሮች ለማስተላለፍ እንሞክራለን፡፡ እድሜ ሲመጣ ደግሞ ተተኪ ወጣቶች አሉ፡፡ ከኋላዬ እየመጡ ነው፡፡ እነሱም ከእኛ ተምረው አንድ ላይ ሆነን እንሰራለን። ወንድሜ አቶ ጎሳ ከአምስት አመታት በኋላ ትንሽ አፋጥኖታል የአፍሪካ ሻምፒዮን እንሆናለን ብሏል እንግዲህ አይቀርም፡፡ ተጋግዘን ነው የምንደርሰው እየተመካከርን እንደቤተሰብ ሆነን ክለባችን ትልቅ ቦታ እንደምናደርስ ተስፋ አለኝ ፡፡ ይህን  የቡሔ በዓል ስናከብር እግዚአብሄር አገራችንን ሰላም ያድርግልን ይባርክልን›› በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ፕሬዝዳንት አቶ አብነት በዕለቱ  ሶስት የተለያዩ ሽልማቶችን በክለባቸው፤ በደጋፊዎቻቸው እና በቢጂ አይ ኢትዮጵያ ስም ለጎማ ቁጠባ ምክትል ስራ አስኪያጅ ለረዳት ፕሮፌሰር ጎሳ ገብረስላሴ አበረክተውላቸዋል፡፡ ሽልማቶቹ በፍሬምና በመስታወት ውብ ተደርጎ የተቀመጠ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ማሊያ፤‹‹ ለዘመን ተሻጋሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ታሪካዊ ጉዞ ላበረከቱት አስተዋፅኦ እናመሰግናለህ›› የሚል ፅሁፍ ያረፈበት ልዩ ዋንጫ እና  ሙክት በግ   ናቸው። የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ከፍተኛ አመራሮች፤ የክለቡ አስጨፋሪዎች እና የሚዲያ ተቋማት በችቦ ማብራት ስነስርዓቱ ላይ ከተሳተፉ በኋላ ኦዳ መደመር አፍሪካ የስነጥበብ ስፍራን ተዘዋውረው  ከመጎብኘታቸውም በላይ ለክለባቸው ማስተወሻ በተዘጋጀ ‹‹መደመር ካንቫስ›› ላይ በተለያዩ ቀለማት ለስፖርት ክለባቸው ያለቸውን ስሜት ገልፀዋል፡፡
በቅዱስ ጊዮርጊስ የ2013 የቡሄ በዓል አከባበር ላይ በከፍተኛ ደረጃ የተመሰገኑት አቶ ገብረስላሴ ኦዳ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ መስራችና የመጀመርያው ፕሬዝዳንት፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አባል፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ደጋፊ ብቻ አልነበሩም፡፡ 65 ዓመታት ያስቆጠረው የመጀመርያውን የኢትዮጵያ የግል ኢንዱስትሪ የጎማ ቁጠባ ኩባንያ መስራች፤ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንትና በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ጊዜ አርበኛ ሆነው ማገልገላቸውም በታሪካቸው ይወሳላቸዋል፡፡
አቶ ገብረስላሴ ትዝታ ለመታሰቢያ፤ ከሁሉም በጥቂቱ በሚል ርእስ በ1990 ዓ.ም ላይ ግለ ታሪካቸውን የያዘ መፅሃፍ ለህትመት አብቅተዋል፡፡ በመፅሃፉ ውስጥ ስለ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ፤ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ፤ ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ልዩ ልዩ ፈርቀዳጅ ታሪኮች በተለያዩ አንቀፆች የቀረቡባቸው ገፆች ይገኛሉ፡፡
ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ለመታሰቢያ እንዲሆናቸው በሰጧቸው ፎቶግራፍ ላይ በጀርባው ከተፃፉት ግጥሞች ጥቂት መስመሮችንም አስፍረዋል።
ስንረታ ደስታው ስናጣው ሃዘኑ፣
ሁለቱም ሲበዙ ህመም እየሆኑ፣
ቅዱስ ጊዮርጊሶችን በመደጋገፍ፣
ትኩሳት ብቻ ነው ያገኘሀው ትርፍ፡፡
ትዝታ ለመታሰቢያ ከገፅ 208 ጀምሮ  ስለ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ  በተጨማሪ የገለፁት ከዚህ በታች ተቀንጭቦ እንደቀረበው ነው፡፡
‹‹…አገራችን ወዲያው በ1945 ዓ.ም የኢንተርናሽናል ፉትቦል ፌደሬሽን አባል ለመሆን በቃች፡፡ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአፍሪካ የኢንተርናሽናል ፉትቦል ፌደሬሽን አባል ስትሆን ሶስተኛ አገር ነበረች፡፡ ይሀውም ማለት መጀመርያ ግብፅ ከዚያ ሱዳን ቀጥሎ ኢትዮጵያ እንግዲህ እንደምናስታውሰው እንደግብፅ ያሉ አገሮች ፉትቦል በአገራቸው የተጀመረው ትክክለኛውን ዘመን እንኳን ባላውቅ በትንሹ ከኢትዮጵያ በፊት ከሃያና ሰላሳ ዓመት ሳትቀድም አልቀረችም፡፡ የኢትዮጵያ ፉትቦል ወደኋላ እንደመዘግየቱ ጨዋታውን ከጀመረ በኋላ በትልቅ ግስጋሴ መጥቶ የኢንተርናሽናል ጨዋታ ተሳታፊ ለመሆን የበቃው ትልቅ ርምጃ እና እድገት ነው ብየ እገምታለሁ፡፡ በዚህ ስራ የተሰማሩት አባላት እጅግ አድርገው ለዚህ ጨዋታ  በጣም ፍላጎትና ፍቅር ስላላቸው ከልባቸው ይሰሩ ስለነበር ይሄ ጨዋታ በጣም እንዲስፋፋ ትልቅ ጥረት አደረጉ፡፡ በተለይ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ለዚህ ፉትቦል ጨዋታ ፈጣሪ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በሱ ጥረት ነው። ምንም እንኳን እኛ አባላቶቹ በስራው ላይ ብንገኘም ርግጥ እንረዳለን፡፡  ከፍተኛ ጥረት ያደርግ የነበረው አቶ ይድነቃቸው ተሰማ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ብገልፅ ደስ ይለኛል፡፡
አቶ ይድነቃቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ለፉትቦል መስፋፋት ያደረገው አስተዋፅኦ ችሎታው እጅግ ከፍ ያለ መሆኑን ገልጿል። ይህም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይወሰን  አቶ ይድነቃቸው በጠቅላላው ፉትቦልን በተመለከተ ሁሉ ችሎታው በከፍተኛ ደረጃ የሚቆረጥለት መሆኑ በኢንተርናሲዮናል ደረጃ የታወቀ ስለሆነና ስለተረጋገጠ በመጨረሻው የአፍሪካ ፉትቦል ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ለመሆን በቃ። እስከዕለተ ሞቱ ድረስ የፊፋ አባልና የአፍሪካ ፉትቦል ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሆኖ መመረጥ ኢትዮጵያ በዚህ ፉትቦል አለም በቅርብ ጊዜ የተነሳችምቢሆን አቶ ይድነቃቸው ባለው ከፍተኛ ችሎታ ተመርጦ ከዚህ ትልቅ ቦታ መድረሱ እሱን ብቻ አይደለም የሚያኮራው ኢትዮጵያንም ጭምር ስለሆነ የሁላችንም ደስታ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡…….››
በኢትዮጵያ ክለቦች የፕሪሚዬር ሊግ ታሪክ ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተመሰረተ 85 ዓመታትን  አስቆጥሯል። በኢትዮጵያ ሻምፒዮና፣ በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ፣ በኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግና በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ በርካታ ዋንጫዎችን እንደሰበሰበም ይታወቃል፡፡  በአፍሪካ ደረጃ ግን  የሚፈለገውን ያህል ስኬታማ በመሆን ለኢትዮጵያ ክለቦች ፈርቀዳጅ ውጤትን ማስመዝገብ አልቻለም፡፡ ባለፉት 3 የውድድር ዘመናት በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ላይ የቀድሞ የበላይነቱን ያጣው ክለቡ በቀጣይ የውድድር ዘመን ወደ ዋንጫው ፉክክር ለመግባት ወደ አፍሪካ ክለቦች የሚመልሰውን ውጤት ለማስመዝገብ ትኩረት አድርጓል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት የ64 ዓመቱ ስርቢያዊ ዝላትኮ ክራምፖቲችን አዲሱ የክለቡ  ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟቸዋል፡፡ በቀጣይ የውድድር ዘመን ክለቡን በፕሪሚዬር ሊግ ውጤታማ በማድረግ  ወደ አፍሪካ ክለቦች ቻምፒየንስ ሊግ ወይም ኮንፌዴሬሽን ካፕ እንዲመልሱ ለአሰልጣኙ ቅድሚያ ሃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከሁለት የውድድር ዘመናት በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን በሴካፋ የክለቦች ውድድር እንዲያሳትፉ፤ በአፍሪካ የክለብ ውድድሮችም እስከ ምድብ ፉክክር የሚገቡበትን ስራ እንዲያከናውኑም ይፈለጋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በአገር ውስጥ የክለብ ውድድሮች ከ80 በላይ ዋንጫዎች የሰበሰበ ሲሆን ከመካከላቸው 29 የፕሪሚዬር ሊግ፤ 12 የጥሎ ማለፍ፤ 16 የአሸናፊዎች አሸናፊ እንዲሁም 6 የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫዎች ይገኙበታል። በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ክለቦች  ታሪክም  በአህጉራዊ ውድድሮች በመሳተፍ ከ55 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ በአህጉራዊ ውድድሮች የተሻለ ውጤት ያስመዘገበው በ1959 ዓ.ም በአፍሪካ ክለቦች ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ የገባበት እና በ2005 ዓ.ም በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ስምንት ውስጥ የገባበት ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ከ1967 እኤአ ጀምሮ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ስር በሚካሄዱ ውድድሮች፤ለ9 ጊዜያት በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ፤ለ10 ጊዜያት በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ካፕ፤ 1 ጊዜ በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ፤ 1 ጊዜ በካፍ ካፕ እንዲሁም ለ3 ጊዜያት በካፍ የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድሮች  ተሳታፊ ነበር፡፡ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ማጣርያዎች ላይ (ውድድሩ በካፍ አዲስ መዋቅር መካሄድ ከጀመረበት ከ1997 እኤአ ወዲህ  ማለት ነው፡፡) በ2017 እኤአ ላይ ለምድብ ፉክክር መድረሱ ትልቁ ውጤት ሲሆን ለ5 ጊዜያት ተሳትፎው በቅድመ ማጣርያ ሲወሰን ለ4 ጊዜያት ደግሞ ቅድመ ማጣርያውን በማለፍ ከውድድሩ የተሰናበተው በመጀመርያ ዙር ነበር፡፡ በ2002 እኤአ በካፍ ፓፕ እስከ ሁለተኛው ዙር ሲጫወት፤ በ2012 እኤአ ላይ በካፍ ኮንፌደሬሽን ካፕ በመጀመርያ ዙር ማጣርያ መሳተፉ እና በካፍ ካፕ ዊነርስ ካፕ ላይ በ1994 እኤአ በሁለተኛ ዙር በ1975 እኤአ በቅድመ ማጣርያ እንዲሁም በ1972 እኤአ በመጀመርያ ዙር መጫወቱ ተመዝግቧል፡፡

Read 10149 times