Saturday, 28 August 2021 12:56

ጡት ለሚያጠቡ የማይመከሩ አመጋገቦች፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(5 votes)

   የጡት ማጥባትን ሳምንት ምክንያት በማድረግ የጀመርነው እትም በዛሬው የማይመከሩ አመጋ ገቦች ይጠ ናቀቃል፡፡ ባለፈው ሳምንት ለንባብ ያልነው የሚያጠቡ እናቶች የምግብ ፍላጎት በምን መንገድ መሟላት እንደሚገባው የጠቆምንበት ነበር፡፡ በቀጥታ ወደማይመከሩት ምግቦች ከመሻገራችን በፊት ስለጠቃሚ ምግቦች ለትውስታ እናስነብባችሁ፡፡ የእናት ጡት ማጥባትን በሚመለከት ላወጣናቸው መረጃዎች ምንጫችን https://www.healthline.com ነው፡፡   
ጡት የምታጠባ እናት በየቀኑ ከ2-3 ጊዜ ፕሮቲን ያላቸውን ምግቦች መመገብ አለባት። እነዚህ ምግቦች እንደ ስጋ፤ አሳ፤ እንቁላል፤ የወተት ውጤቶች፤ ባቄላ፤ ለውዝ ..ወዘተ የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ጡት የምታጠባ እናት በየቀኑ ቢያንስ ለሶስት ጊዜ ያህል ጥቁር አረንጉዋዴ ቅጠላ ቅጠሎችን (ጎመን፤ ቆስጣ፤) እና ብጫነት ያላቸውን ቅጠላ ቅጠሎች መመገብ አለባት፡፡
ጡት የምታጠባ እናት በየቀኑ ፍራፍሬዎችን ቢያንስ ለሁለት ጊዜ መመገብ አለባት፡፡
ጡት የምታጠባ እናት ከጥራጥሬዎችም እንደ ስንዴ ዳቦ፤ ፓስታ፤ አጃ፤ የመሳሰሉትን በየቀኑ መመገብ አለባት፡፡  
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ውሀን ገፋ አድርጎ መጠጣት ጠቃሚ ነው፡፡ ጡት የምታጠባ እናት ከመራብ ባሻገር ውሀ የመጠማት ስሜት ሊኖራት ይችላል፡፡ ህጻን ጡት በሚጠባበት ወቅት የእናትየው የጡት ማማንጨት ሂደት ይጨምራል፡፡ በዚህም ጊዜ እንደልብ ወተቱ ለህጻኑ ይፈስለታል። ተፈጥሮ በራሱ በሚያደርገው ሂደት ምክንያት እናትየው ጡት በሰጠች ቁጥር የፈሳሽ መጠንዋ ይጎዳል ባይባልም ነገር ግን እንደምትመገበው ምግብ እና መጠጥ ሁኔታው ሊወሰን ይችላል። ስለሆነም ጡት በሚያጠቡ ጊዜ ይህንን ያህል ፈሳሽ መውሰድ ይገባል በሚል መወሰን ባይቻልም ባለሙያዎች በሚሰጡት ምክር መሰረት ግን ፈሳሽን መው ሰድ ይመከራል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን የጡት ወተት ምርት ከቀነሰ፤ እናትየው የድካም ስሜት የሚሰማት ከሆነ ውሀን ጨመር እያደረጉ መጠጣት ጠቃሚ መሆኑን ምንጩ ያስረዳል፡፡ እና ትየው ውሀን በደንብ ስለመጠጣትዋ ምልክቱ በሽንት የሚወገደው ፈሳሽ መልክና ጠረን ነው፡፡ የሽንት ከለር ጠቆር ያለ ብጫ ከሆነ እና ሽታው ጠንከር ያለ ከሆነ በሰውነት ውስጥ በቂ ፈሳሽ ላለመኖሩ ምልክት ስለሆነ ውሀን መውሰድ ይመከራል፡፡
በጡት ማጥባት ወቅት የማይመከሩ ምግብና መጠጦች፡፡
ምግብና መጠጥን በመውሰድ ረገድ ለጤና አስቸጋሪ ሁኔታን የሚፈጥሩ ወይንም አለርጂ የሚባሉ ካልሆኑ በስተቀር ማንኛውንም አይነት ምግብና መጠጥ መውሰድ አይከለከልም፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ምግቦች ቃናቸው እና ጣእማቸው እንዲሁም ከምግብ ጋር ለማጣፈጫነት የሚጨ መሩ ቅመማ ቅመሞች እንዲሁም መጠጦች የእናት ጡት ወተትን የሚጠቡ ህጻናት አመጋገብ ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ አስቀድሞ መገመት ያስፈልጋል፡፡  
በሌላ በኩል ደግሞ እናትየው ከተመገበች በሁዋላ በሰውነትዋ ውስጥ አየር ወይንም ጋዝ የሚፈጥር ምግብ ለምሳሌም እንደ ጥቅል ጎመን የመሳሰሉትን እናትየው ከተመገበች ለህጻኑም ሊተላለፍ ይችላል የሚለው አስተሳሰብ የተሳሳተ ነው፡፡ እናትየው ሰውነት ውስጥ የተፈጠረው ጋዝ ወደ ጡት ወተቱ ሊተላለፍ አይችልም ይላል መረጃው፡፡
ባጠቃላይም አብዛኞቹ ምግቦች እና መጠጦች ጡት በማጥባት ወቅት ችግር የማይፈጥሩ ሲሆን አንዳንዶች ግን ሊወገዱ ይገባቸዋል፡፡ ጡት የሚያጠቡ እናቶች ለህጻኑ ትክክል አይሆንም ብለው የሚያስቡትን መመገብን ከማቆም ይልቅ የህክምና ባለሙያ ማማከር ብልህነት ነው፡፡
ቡና መጠጣት፡-
ጡት የሚያጠቡ እናቶች ለአንድ ጊዜ ከሚጠጡት ቡና ወደ አንድ ከመቶ የሚሆነው ወደ ጡት ወተት ይተላለፋል፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም ጡት የሚጠቡ ህጻናት ሰውነት ቡናን አዋህዶ ለመጠቀም ረዘም ያለ ጊዜ ሊፈጅባቸው ይችላል፡፡ በእርግጥ ቡና የጠጣችን እናት ጡት የጠባ ህጻን ይጎዳል የሚል መደምደሚያ የለም፡፡ ነገር ግን ህጻኑ በተረጋጋ መንገድ ለመተኛት ይቸገራል፡፡ ስለዚህም ጡት የምታጠባ እናት የቡና አወሳሰድዋን መመጠን አለባት፡፡ በቀን ከ2-3 ስኒ በላይ መውሰድ አትመከርም፡፡
አልኮሆል መውሰድ፡-
ጡት የምታጠባ እናት አልኮሆል የምትወስድ ከሆነ ወደ ጡት ወተቱ ሊተላለፍ ይችላል፡፡ መጠኑም የሚወሰነው በእናትየው ደም ውስጥ በገባው አልኮሆል መጠን ነው፡፡ ህጻናቱ አልኮሆልን በሰውነታቸው ውስጥ እንዲዋሀድ የሚያደርጉት ከአዋቂዎች በግማሽ ባነሰ ነው፡፡
ጡት የምታጠባ እናት ለልጅዋ ጡት የምትሰጠው አንድ ወይንም ሁለት ጊዜ አልኮሆል ከወሰደች በሁዋላ ከሆነ የጡት ወተቱ እስከ 23% ድረስ ሊቀንስና ህጻኑን ሊያስጨንቀው ፤ እንቅልፍ ሊከለክለው ይችላል፡፡ የዚህም ምክንያቱ አልኮሆል ጡት የሚጠባውን ህጻን ጤንነት ስለሚጎዳ ነው። ስለዚህም ጡት የምታጠባ እናት የምትወስደው የአልኮሆል መጠን በእጅጉ መወሰን አለበት፡፡
አንዲት ጡት የምታጠባ እናት እንደሰውነትዋ ክብደት መጠን በአንድ ኪሎ ግራም ከ0.5 ግራም የበለጠ አልኮሆል መውሰድ የለባትም።
አንዲት እናት መጠኑ ያልተዛባ አልኮሆል ለመውሰድ ብትፈልግ እንኩዋን አልኮሆሉን ከወሰደች በሁዋላ ጡት ለማጥባት ቢያንስ እስከ ሁለት ሰአት ድረስ መቆየት አለባት፡፡
የላም ወተት፡-
ባልተለመደ ሁኔታ አንዳንድ ህጻናት ለላም ወተት አለርጂክ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ህጻናቱ ለላም ወተት አለርጂክ መሆናቸው ከታወቅ ጡት የሚያጠቡት እናቶች የላም ወተት እንዳይጠጡ ይመከራል። ምናልባትም ማስወገድ የሚያስፈልገው የላም ወተትን ብቻ ሳይሆን የወተት ተዋጽኦን በጠቅላላው ሊሆን ይችላል፡፡ የጤና አገልግሎትን የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች የላም ወተትን ወይንም የእንስሳት ተዋጽኦዎችን ለምን ያህል ጊዜ ከእናትየው አመጋገብ ማስወገድ እንደሚገባ እና ከመቼ ጀምሮ መመገብ እንደሚቻል ሊያማክሩ ይችላሉ፡፡
ጡት ማጥባትና የክብደት መቀነስ፡-
አንዲት እናት ከወለደች በሁዋላ በፍጥነት ክብደትዋን የመቀነስ ፍላጎት ሊኖራት ይችላል፡፡ ነገር ግን ክብደትን መቀነስ ጊዜ ሊፈጅ ስለሚችል ያሉበትን ሁኔታ አምኖ መቀበል ለጊዜው ያስፈ ልጋል፡፡ ጡትን በማጥባት ወቅት በሚኖረው የሆርሞን ለውጥና የጡትን ወተት በማጥባት ሂደት በሚያስፈልገው ካሎሪ ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የምግብ ፍላጎት ሊኖር ስለሚችል የክብ ደቱ መጨመር ወይንም እንደፈለጉት ክብደትን ለመቀነስ አለመቻል ሊኖር ይችላል፡፡  
እናቶች በወለዱ የመጀመሪያዎቹ ወራት ውስጥ ክብደትን ለመቀነስ በሚል የካሎሪን መጠን የሚገድቡ ከሆነ የጡት ወተቱን መጠን ሊቀነስ እና ከፍተኛ የሆነ አቅምን የማሳነስ ሁኔታ ይኖረዋል። በሌላ በኩል ግን በአንዳንድ እናቶች ላይ ጡት ማጥባት በራሱ ክብደትን ለመቀነስ የሚረዳበት አጋጣሚም ይኖራል፡፡ በተለይም እስከ ስድስት ወር ድረስ እና ከዚያም በላይ ጡትን በተከታታይ የሚያጠቡ እናቶች ክብደታቸው ሊስተካከል እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በእርግጥ ይህ ለሁሉም እናቶች የሚያጋጥም አይደለም፡፡
አንዲት ጡት የምታጠባ እናት አስፈላጊውን የተመጣጠነ ምግብ እየወሰደች እንዲሁም የአካል ብቃት እንቅስቃሴን እያደረገች በአንድ ሳምንት ውስጥ በአማካይ እስከ 1.1 ፓውንድ ድረስ ክብ ደትዋን ብትቀንስ የጡት ወተትዋን መጠን እና ይዘት አይቀንሰውም፡፡ በዚህ መንገድ እናቶች ክብደታቸውን ለመቀነስ እርምጃ ቢወስዱ ይበረታታሉ፡፡  
ሁሉም የሚያጠቡ እናቶች ምንም ያህል ክብደት ቢኖራቸውም የሚያስፈልጋቸውን እና በቂ የሆነ ካሎሪ ማግኘት እንዳለባቸው መዘንጋት የለበትም። ስለሆነም ክብደታቸው የቀነሰ እናቶች የወተት መጠናቸው እንዳይቀንስ የምግብ አይነታቸውንና አወሳሰዳቸውን ማስተካከል እንዲሁም በባለሙያ በሚመከረው መሰረት ጠቃሚ የሆኑ ፈሳሾችን ወይንም ውሀ መጠጣት ይጠቅማል፡፡   


Read 15542 times