Saturday, 28 August 2021 13:26

ዋልያዎቹ ፈታኙን የውድድር ዘመን ያሳልፋሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት 2014 ዋዜማ አንስቶ በ22ኛው የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን የምድብ ማጣርያዎችና በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዎች ፈታኙን የውድድር ዘመን ያሳልፋል፡፡
በአፍሪካ ዞን በሚካሄዱት የ22ኛው የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ላይ ከአንድ ሳምንት በኋላ የሚጀመሩ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በምድብ 7 ከጋና፣ ዚምባብዌ እና ደቡብ አፍሪካ ጋር መደልደሏ ይታወቃል፡፡  ዋልያዎቹ በምድባቸው የመጀመርያ ጨዋታ ነሐሴ 28 ላይ ወደ ምዕራብ አፍሪካ በማቅናት በኬፕ ኮስት ስታዲየም ከጋና ብሄራዊ ቡድን ጋር የሚጫወቱ ሲሆን፤ ጳጉሜ 2 ላይ  ደግሞ በባህር ዳር ስታድዬም  ዚምባቡዌን ያስተናግዳሉ፡፡ ለሁለቱ የዓለም ዋንጫ  የምድብ ማጣርያዎች በአዳማ ከተማ ከ2 ሳምንት በላይ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለአቋም መፈተሻ ከትናንት በስቲያ ከሴራሊዮን አቻው ጋር በባህርዳር ስታድዬም ተገናኝቶ 0ለ0 የተለያየ ሲሆን  ሁለተኛውን የወዳጅነት ጨዋታ ከኡጋንዳ ጋር የሚያደርግ ይሆናል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ5 ወራት በኋላ በካሜሩን አስተናጋጅነት በሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚሳተፉ  24 ብሄራዊ ቡድኖች የምድብ ድልድላቸውን ሰሞኑን አውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ አንድ ከአዘጋጇ ካሜሩን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ እና ኬፕ ቬርድ ጋር ተደልድሏል፡፡ ዋልያዎቹ ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የተመለሱ በውድድሩ ታሪክ ለ11ኛ ጊዜ የሚሳተፉ ይሆናል፡፡  አዘጋጇ ካሜሮን  ለ20ኛ ጊዜ፤ ቡርኪናፋሶ ለ12ኛ ጊዜ እንዲሁም ኬፕ ቨርዴ ለ3ኛ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ይሳተፋሉ፡፡ ካሜሮን ለአምስት ጊዜያት በ1984፤በ1988፤ በ2000፤ በ2002 እና በ2017 እኤአ ላይ የአፍሪካ ሻምፒዮን ስትሆን፤  በ2013 እኤአ ላይ ቡርኪናፋሶ ሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም ኬፕ ቨርዴ ለሩብ ፍፃሜ በመድረስ ከፍተኛ ውጤታቸውን ያስመዘገቡ ሲሆን የኢትዮጵያ ትልቁ ውጤት በ1962 እኤአ ላይ ዋንጫውን ማግኘቷ ነው፡፡ በትራንስፈርማርከት ላይ በቀረበው መረጃ መሰረት በተጨዋቾች ስብስባቸው ካሜሮን 90.1 ሚሊዮን ዩሮ፤ ቡርኪናፋሶ 80.56 ሚሊዮን ዩሮ፤ ኬፕ ቬርዴ 10.55 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም ኢትዮጵያ 500ሺ ዩሮ የዋጋ ተመን ወጥቶላቸዋል፡፡ የምድብ ድልድሉ ይፋ ከተደረገ በኋላ የካሜሮን የቀድሞ ተጨዋቾች በታሪክ 6ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ድል ማስመዝገብን ተስፋ አድርገዋል፡፡ ‹‹ ምድቡን በፀጋ የምቀበለው ነው፡፡ ወጣቶቹ የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች 26 ሚሊዮን ካሜሮናውያን ከጎናቸው ናቸው፡፡ አዘጋጅ አገር ለፍፃሜ ጨዋታ መድረስና ዋንጫ ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡›› በማለት ያውንዴ ከተማ ላይ ለቻይናው ዢንዋ የተናገረው ሳሙኤል ኤቶ ሲሆን፤ የማይበገሩት አንበሶች የቀድሞ አምበል ሪጎበርት ሶንግ በበኩሉ‹‹ ቡድናችን በደጋፊዎቹ ፊት መጫወቱ ትልቅ እድል ነው፡፡ ዋንጫ ለማሸነፍ በቂ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል›› ብሏል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ከምድብ ድልድሉ በኋላ ይፋ ባደረጋቸው የጨዋታ መርሃግብሮች መሰረት በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ዋልያዎቹ  ጥር 1 ላይ በያውንዴ ከተማ በሚገኘው ኦሌምቤ ስታዲየም ከኬፕቨርዴ ጋር የመጀመሪያ ጨዋታውን  ያደርጋሉ፡፡ ሁለተኛውን ጨዋታ ጥር 5 ላይ በኦሌምቤ ስታዲየም ከአዘጋጇ ካሜሩን ጋር ተጫውተው በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ጥር 9  ላይ በባፉሳም ከተማ በሚገኘው ኮውኮንግ ስታዲየም ከቡርኪናፋሶ ጋር የሚገናኙ ይሆናል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለአፍሪካ ዋንጫው ከ14.2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለሽልማት ያቀርባል፡፡ የአፍሪካ ሻምፒዮን ለሚሆነው ብሄራዊ ቡድን 7 ሚሊዮን ዶላር የሚበረከት ሲሆን፤ ለሁለተኛ 4.5 ሚሊዮን፤ ለሶስተኛ 2.5 ሚሊዮን፤ ለግማሽ ፍፃሜ 1 ሚሊዮን ዶላር ለሩብ ፍፃሜ ለደረሱ ደግሞ 800 ሺ ዶላር ይሸልማል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ እና በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች በሚያሳልፈው ፈታኝ የውድድር ዘመን ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቂ ትኩረት መስጠትና ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለብሄራዊ ቡድኑ በየጊዜው የአቋም መፈተሻ ግጥሚያዎችን ማዘጋጀቱ እና ለዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እቅድ መስራቱ ወሳኝ ነው፡፡ ከዚያን ባሻገር በሊግ የሚወዳደሩ ክለቦች ለብሄራዊ ቡድን የተመረጡ ተጨዋቾቻቸውን በአግባቡ ለመጠቀም ከዋና አሰልጣኝ ጋር ተመካክረው መስራት ይኖርባቸዋል፡፡  በተለይ በክለብ እና በብሄራዊ ቡድን ተደራራቢ ጨዋታዎች ተጨዋቾች አላስፈላጊ ጫና ውስጥ እንዳይገቡ መጠንቀቅም ያስፈልጋል፡፡

Read 3611 times