Saturday, 04 September 2021 17:30

“ዓላማዬ በእርጅና ውስጥ ያለውን ውበት መግለጽ ነው”

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

ሰዓሊ ናትናኤል ምትኩ  ትውልድና እድገቱ በአዲስ አበባ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አለ የስነጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት በዲግሪ ተመርቋል፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 15ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ለማክበር ባዘጋጀው ውድድር ላይ ባቀረበው አስደናቂ ስዕል ተሸላሚ ሲሆን ብሪትሽ ካውንስል ሰዓሊዎችን አስተባብሮ ባካሄደው የሥነ ጥበብ ፕሮጀክትና የቡድን ስዕል አውደርዕይ ላይ ተሳትፏል፡፡ ሰዓሊ ናትናኤል በአሁኑ ወቅት “DEUG27”  በሚል የፓን አፍሪካን እንቅስቃሴ  ላይ በሙያው አስተዋፅኦ እያደረገ ሲሆን በተለያዩ የስነጥበብ ዘርፎች ላይ የሚሰራ “አስውራ የስነጥበብ ጋለሪ”ን ከጓደኞቹ  ጋር በምስረታ ሂደት ላይ ነው፡፡ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ግሩም ሰይፉ ጋር በሙያው ዙሪያ ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጓል፡፡ እነሆ፡-



 
             በፈንዲቃ የባህል ማዕከል ከ1 ወር በላይ ለእይታ የቀረበው አውደ ርዕይህ አጠቃላይ ይዘት ምን ይመስላል?
የኤግዚብሽኑ ርእስ #በመኪና; የሚል ነው፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ በእኔ ውስጥ እንደ ትዝታ ተቀምጦ ያለ ህልም ነው፡፡ አንዳንዴ በምናባችን ራሳችንን አስቀምጠን የምናይባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ መካኒካል ነገሮችና የተለያዩ ማሽነሪዎች በእኔ ምናብ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ የሚመላለሱ ናቸው። የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው ትላልቅ የፋብሪካ ማሽነሪዎችና አሮጌ መኪናዎች ምናቤ  ውስጥ  አገኛቸዋለሁ። ህልም ልትለው ትችላለህ፡፡ ሁላችንም ውስጥ አለ፡፡
ስዕል ትምህርት ቤት በነበርኩበት ሰዓት “ከራሳችሁ ምናብ ልዩ መነሻ የሚሆናችሁን ጭብጥ ፍጠሩ” ስንባል ያልታየ ሁኔታን የመሞከር ልዩ ዝንባሌ ስለነበረኝ፣ በዚያ አጋጣሚ ሙከራዬን ጀመርኩት፡፡  በምስቅልቅል አካባቢ ውስጥ የሚገኙ አሮጌ መኪኖችን፤ የተበላሹ መካኒካል ቁሶችን በምናባዊ እይታ መሳል፣ ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ያለፉ ሰዎች የተጠቀሙባቸው በኢንዱስትሪ ውስጥ ሲሰሩ የቆዩ ማሽነሪዎች በየቦታው ተጠራቅመው ተረስተው ይገኛሉ፡፡ በየሰፈሩ የተጣሉ መኪኖችንም እናውቃለን። ያደግኩትም በዚህ አይነት አካባቢ ውስጥ ነው፡፡ መነሻ ሃሳቡ ከዚያ የመጣ ነው። አሮጌ መኪኖች፤ የተረሱ ከተሞች፤ የተጣሉ ማሽነሪዎችን ምናብ ውስጥ ከትቶ መሳል … ሁኔታ ውስጥ ነው የገባሁት። በነባራዊው ዓለም ከማየው ተነስቼ ምናባዊ እይታዬን እየጨመርኩ የምሰራው ነው። ኢንዱስትሪው ሲጠቀምባቸው የቆዩ ማሽነሪዎች የስራ ጊዜያቸውን ሲያቆሙ አሁን እኔ የምሰራቸውን የስዕል ገፅታዎች ይፈጥራሉ፡፡ በኤግዚብሽኑ ላይ “በመኪና” በሚል ርእስ የቀረቡት ስራዎች ይህን ይገልፃሉ፡፡
በአንዳንዶቹ ስዕሎች መኪኖቹን የምቆልላቸው የምከምራቸው ከምናባዊ እይታዬ በመነሳት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ አሮጌ መኪናዎች አሉ፤ እንነዳቸዋለን እንጥላቸዋለን። በአኗኗር ዘይቤያችን ከኮልኮሌ ጋር የምንኖረው ህይወት የፈጠረው ዘመነኛ ‹‹ኮንቴምፖራሪ›› ባህል አለ፡፡ ይህ በአሮጌ እቃዎች ውስጥ የመኖር አፍሪካዊ ባህል ለእኔ እንደ ቀውስ የምመለከተው ነው፡፡ በቆሻሻ በቅራቅንቦ ክምሮች የተሞላ ዝብርቅርቅና  ትርምስምስ ህይወት፤ የመላው አፍሪካ መገለጫ ነው ማለት ይቻላል፡፡ መነሻ ሃሳብ የሆነኝ በዚህ ቀውስ ውስጥ ያለው ውበት ነው፡፡ ዓላማዬ በማርጀታችን በአሮጌነታችን ውስጥ ያለውን ውበት መግለፅና ማሳየት ነው፡፡ በስዕሎቼ ይሄን ውበት ለማንፀጸባረቅ ነው የምፈልገው።
በአጠቃላይ የኤግዚብሽኑ ጭብጥ በልጅነቴ ከኖርኩት ህይወት ጋር ይያያዛል። የእኛ ቤተሰብ ህይወት፣ ከመካኒካል ስራዎችና ከመኪኖች ጋር  ግንኙነት ነበረው። አንዱ ወንድሜ መካኒክ ሲሆን ሌሎቹም ሾፌር ሆነው ሰርተዋል፡፡ በመኖርያ ግቢያችን ውስጥ አሮጌ መኪኖችን ማየት የተለመደ ነው፡፡ የጋራዥ ስራዎችን እየተመለከትኩ ነው ያደግኩት፡፡ እናም ውስጤ ከእነዚህ አሮጌ መኪኖች ጋር ግንኙነት አለው፡፡ በሰው ልጆች የስልጣኔ ጉዞዎች ውስጥ ማሽነሪዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ይሰማኛል፡፡
“በመኪና” በሚል ርዕስ ያቀረብካቸው ስዕሎች ምን ያህል የታዳሚውን ትኩረት አግኝተዋል?
ስዕሎችን የምሰራቸው ሰዎች ምን ሊሰማቸው ይችላል? ምን ይፈልጋሉ? የሚለውን አስቤ አይደለም፡፡ ያለፉትን አራት ዓመታት ስለማመዳቸው የቆዩ ስራዎች ናቸው፡፡ ለእይታ ከቀረቡ በኋላ አብዛኛዎቹን ተመልካቾች እኔን የተሰማኝ ስሜት አግኝቷቸዋል፡፡ በከፊል አብስትራክ የሆነው አቀራረብ ስዕሎቹን አይተህ እንድትረዳቸው ነው፡፡ ስዕሎቼን ሰዎች ሲመለከቷችው በሆነ ስሜት እንዲወያዩ ቀለል ብሏቸው እንዲመለከቱ አድርጓቸዋል። አሮጌ መኪኖችን ስስል ብራንዳቸው ትዝ አይለኝም፤ አንድ የሚያደርጋቸው ሁሉም አሮጌ መሆናቸው ነው፡፡ የትኛውም መኪናን በስብሶ ሳየው በቀለማት ያንን መግለፅ ነው፤ የሆነ ታሪክ እንዲኖረው በስዕሉ ለመፍጠር ለማንፀባረቅ ነው፡፡ ከአሮጌ  መኪኖች ጀርባ ያለው ታሪክ  ስሜት እንዲፈጥር ትዝታውን እንዲቀሰቅስ ነው፡፡ ከታዳሚዎች መካከል አንዳንዶቹ፣ የአሮጌ መኪኖችን ሁኔታ ካላየንበት አንፃር ነው ያመጣኸው ብለውኛል፡፡ አሮጌ መኪኖች መካኒካል ነገሮች ስዕል ይሆናሉ ብለው ያሰቡም አልነበሩም፡፡ ስዕልን ከተፈጥሮ፤ ከአብስትራክት የቀለም ህብር አንጻር ለሚመለከቱ፣ የእኔ በከፊል አብስትራክት የሆነ አቀራረብ ልዩ ሆኖባቸዋል፡፡ አንድ ቁስ ተወስዶ እይታዊ በሆነ መንገድ ይገለበጣል ብሎ ለማሰብ የሚከብዳቸውም ይኖራሉ፡፡ አንዳንዶች በትዝታ ውስጥ መግባታቸውን ገልፀውልኛል፡፡ ተመልካቾች በኤግዚብሽኑ መደመማቸው ለእኔ ትልቅ ተነሳሽነት ፈጥሮልኛል፡፡ ስዕል ትጀምረዋለህ እንጅ አትጨርሰውም፡፡ ወደፊት ብዙ ለመስራት የማስባቸው ነገሮች አሉ፡፡ አፍሪካዊ ነኝ ብዬ ስለማስብ፣ በአፍሪካ ህይወት ውስጥ ያለውን ኮልኮሌና ዝብርቅርቅ እየሳልኩ ለመቀጠል እፈልጋለሁ፡፡
ፈንዲቃ የባህል ማዕከል በቋሚነት ከሚያዘጋጃቸው የጃዝ እና የባህል ሙዚቃ ምሽቶቹ ባሻገር በየጊዜው የስነጥበብ ኤግዚቢሽኖች በማቅረብ  ይታወቃል፡፡ ማዕከሉ  ለኢትዮጵያ ስነጥበብ እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ እንዴት ታየዋለህ?
ልናገረው የምፈልገውን ትልቅ ነጥብ ነው ያነሳኸው፡፡ ፈንዲቃ የባህል ማዕከል ለእንደኔ አይነት ወጣትና አዲስ ለሚወጡ አርቲስቶች በሚሰጠው እድል ከሁሉም ጋለሪዎች ልዩ ያደርገዋል፡፡ በአብዛኛዎቹ ጋለሪዎች የሚታየው የቢሮክራሲ አሰራር ፈንዲቃ ላይ አልገጠመኝም፡፡ ብዙ ሰዓሊዎች በተለያዩ ጋለሪዎች ኤግዚብሽን ለማሳየት በሚያደርጉት ጥረት ላይ ቢሮክራሲ መብዛቱ በስቱድዮ ውስጥ ለመወሰን ያስገድዳቸዋል። የስዕል ኤግዚብሽንን በፈንዲቃ ማቅረብ ከሌሎች የሚለየው በመጀመርያ ከአርቲስቱ ጋር ግንኙነት በሚያደርገው ታዋቂ ሰዓሊ ሃይሉ ክፍሌ ምስጉን አሰራር ነው። ሰዓሊ ሃይሉ እንደ ኤግዚብሽኑ አደራጅ በመጀመርያ ስቱድዮዬን ጎብኝቶ፤ ስዕሎቼን ከተመለከተ በኋላ ለእይታ የማቀርብበት ሁኔታዎችን አመቻችቶልኛል፡፡ በሌላ በኩል፤ የማዕከሉ መስራች መላኩ በላይንም ከልብ ነው የማመሰግነው፡፡ ከተወሰኑ ወራት በፊት ገና በመጀመርያው ግንኙነታችን ስዕሎቼን ተመልክቶ “ወጣት አርቲስት ነህ በርታልን” ሲለኝ በጣም ሞራል ነው ያገኘሁት፡፡ ኤግዚብሽኑን በባህል ማዕከሉ ለማቅረብ ወስኜ ስንቀሳቀስ በቅን ትብብር፣ ምንም አይነት ቢሮክራሲ ሳይገጥመኝ ነው የተሳካው፡፡ የባህል ማዕከሉ እንደ አርቲስት ስራዎችን አዘጋጅተህ የኤግዚብሽንን ፅንሰ ሃሳብ ገልፀህ ስታቀርብ፣ ወዲያውኑ ራስህን በመወከል ለእይታ የሚያበቃህ ነው። በኤግዚብሽኑ ላይ ከምታገኘው ሽያጭ ምንም አይነት ፐርሰንት አለመቆረጡም በጣም ያበረታታል፡፡
በነገራችን ላይ የባህል ማዕከሉ ላይ ኤግዚብሽንህ  እየቀረበ  በአንድ የጃዝ ምሽት ላይ “ቃየን ላብ” ከተባለው ባንድ ጋር በቀጥታ ስዕል እየሰራህ ተጫውተሃል፤ በጃዝ ሙዚቃ ውስጥ ስዕልን መስራት ምን አይነት ስሜት ይሰጣል?
ይህ ሁኔታ የመላኩ በላይን አዲስ ነገር የማየት ፍላጎት ያረጋገጠ ነው፡፡ በጃዝ ምሽቱ ላይ ከሚጫወቱት ሙዚቀኞች ጋር ተቀላቅዬ፣ ካንቫሴን በመወጠር ስዕል ስሰራ አብሬያቸው ሙዚቃ እንደምጫወት ነው የተሰማኝ፡፡ ስቱድዮ ውስጥ ስሰራም ሙዚቃ እየሰማሁ ይመቸኛል። ከሙዚቃ ስልቶች ደግሞ ጃዝ ከስዕል ስራ ጋር በጣም ይጣጣማል። ጃዝና ስዕል በጣም ይሄዳል። ስዕሉን እየሰራህ ያለማቆም ስሜት ውስጥ ነው የምትገባው፡፡ እነሱ ሙዚቃቸውን እየተጫወቱ ስዕሉን ስሰራ ስቱድዮ ውስጥ እንዳለሁ ነበር የሚሰማኝ። የሳልኩትን  ስመለከተውም ከሙዚቃው ስሜት ጋር ተዋህዶ እንደወጣ ነው የገባኝ። ብዙ ሰዓሊዎች ለትኩረትና ለጥሞና ምንም ነገር ባይረብሸን ይላሉ፡፡ እኔ ግን በጃዝ ሙዚቃ ውስጥ ለመሳል የሚመች ትኩረትና ጥሞና ነው ያገኘሁት፤  ለአራት ሰዓታት ከባንዱ ሙዚቃ ጋር ስዕሉን እየሰራሁ መቆየቴ እንኳን አልታወቀኝም። ደግሞ ለተመልካቹም ሃይል የሚሰጥና የሚማርክ ትእይንት ነበር። የጃዝ ሙዚቀኞቹ ልክ የባንዳቸው አባል እንደሆንኩ ቆጥረውኛል። መድረኩ ላይ ስሜት ውስጥ እየገባን ስንተያይ፣ ስዕሉን እየሰራሁ ልክ እንደ ሙዚቃ ተጫዋች ነው የተመለከቱኝ፡፡ ስዕልም የሙዚቃ አካል መሆን እንደሚችል፤ ካንቫስ ላይ ቀለም ስትቀባ የሙዚቃ መሳርያ ተጫዋች ትሆናለህ፡፡ ካንቫሱ መድረክ፤ የሙዚቃ መሳርያው ብሩሽ ፤ዜማው ቀለማት፤ ስዕሉ  ደግሞ ዳንስ ናቸው፡፡
ወደ ስዕል ሙያ እንዴት ገባህ?
የስዕል ዝንባሌውን ያዳብርኩት ገና በልጅነቴ ነው፡፡ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ቤት ቆይታዬ፣ በስዕል ችሎታዬ ነበር የምታወቀው፡፡ ስዕል ሲያስፈልግ ሁሉም ወደ እኔ ነበር የሚመጣው፡፡ የስዕል ክለብ አቋቁመን እንቀሳቀስም ነበር፡፡ ይህ ሁኔታዬን ቤተሰቦቼም ታዝበውታል። በቀለም ትምህርት ጎበዝ ነበርኩ፤ ጎን ለጎን ደግሞ ለስዕል ያለኝን ፍቅርና ችሎታም ከእኔ የበለጠ ተረድተውታል። በኢትዮጵያ ባህላዊና ሃይማኖታዊ የስዕል ስራ ባለሙያነታቸው የሚታወቁና ሰዓሊ ካሳ ወንድማገኘሁ የሚባሉ ትልቅ ሰው በሰፈራችን ነበሩ፡፡ የእናቴ ጓደኛ ነበሩ፡፡ “ከልጆችዎ መሃል ጥበብ የማስተምረው” ብለው እናቴን ሲጠይቁ፣  ስለ እኔ ዝንባሌ ነገረቻቸውና አንዳንድ ስራዎቼን ወስጄ አሳየኋቸው፡፡ “በጣም ጥሩ ነው” ብለው እርሳቸው ዘንድ ባህላዊ አሳሳልን የምማርበት እድል ሰጡኝ፡፡ ስምንተኛ ክፍል በነበርኩበት ጊዜ  ከትምህርት በኋላ በሳምንት ሶስት ቀን እሳቸው ቤት እየሄድኩ መማር ጀመርኩ፡፡ ያስተምሩኝ የነበረው ባህላዊውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ስዕል አሰራር ነው፡፡ በግድግዳ ላይ መንፈሳዊና ሃይማኖታዊ ስዕሎችን መስራት ነው፡፡ የሚያስተምሩበት ዘዴ ስዕልን እንዳፈቅረው አደረገኝ፡፡ በየሳምንቱ ሶስት ቀን የነበረው ፕሮግራም፣ ከትምህርት በኋላ ሮጬ እሳቸው ቤት በመሄድ ሳምንቱን ሙሉ የምማረው ሆነ። ከእሳቸው ጋር ለአራት ዓመታት በመቆየት የኢትዮጵያን ባህላዊ የአሳሳል ትምህርት በሚገባ ለመቅሰም ቻልኩ፡፡ እንደ ዘመናዊው የስዕል ትምህርት በየደረጃው ከምትወስዳቸው ትምህርቶች በኋላ በባህላዊ አሳሳል ዘይቤም ተገቢውን መሰረታዊ እውቀት ቀስሜ ከሳቸው ዘንድ ተመረቅኩ፡፡ ትዝ ይለኛል የመጨረሻው የትምህርት ደረጃ ስላሴዎችን  መሳል ነበር። በጣም ምስጢራዊ ጥበብ የሚጠይቅ ነው፡፡ ስላሴዎች በእጃቸው አቋቋም፤ በአይኖቻቸው አተያይ ሁሉም ሁኔታቸው ተመሳሳይ መሆን አለበት፡፡ ሶስትነታቸውንም አንድነታቸውንን ስዕሉ እንዲገልፅ ይጠበቃል፡፡ 12ኛ ክፍል ስደርስ ይህን የብቃት ደረጃ ሙለ በሙሉ አሟልቼ ለመጨረስ በቃሁ፡፡
መንፈሳዊ ስዕል ለመስራት  ህጎች አሉ። ስለወደድኩት ደስ ስላለኝ ብሎ ስዕል መስራት የለም፡፡ በአሳሳል ዘይቤው በአምልኮቱ ዘንድ ያለውን ሳይንስ ነው የምትከተለው። እንደ ዘመናዊ ስዕል ፕረስፔክቲቭ፣ አንዱን አቅርበህ አንዱን አርቀህ፣ አንዱን አሳንሰህ አንዱን አግዝፈህ የምትስለው ነገር የለም። ምንም አይነት መበላለጥን በባህላዊ አሳሳል አትሰራም፤ ሁሉንም እኩል ነው የምትሰራው። ይህም ራሱን የቻለ ፍልስፍናዊ እይታ ነው። ባህላዊና ሃይማኖታዊ የአሳሳል ቀመሮች፤ ህጎችና ቀለሞች አሉት፡፡ የቅዱሳንን ስዕል ስታለብስ አለባበሱን የምትሰራው በምክንያት ነው፡፡ የመንፈስ ዝግጅት የሚጠይቅ ጥንካሬን የሚሻ ስነጥበብ ነው፡፡ ይህን እውቀት ልቀስም ችያለሁ።  በኢትዮጵያ የባህላዊ አሳሳል ዘይቤ በኮሌጅ ደረጃ መሰጠት ይኖርበታል፡፡ ሃላፊነቱን ወስዶ በበቂ ጥናት ስልጠናውን የሚሰጥ ተቋም መፈጠር ይኖርበታል፡፡
ከሰዓሊ ካሳ ወንድማገኘሁ ጋር 4 ዓመታትን ከቆየሁና ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ በቀለም ትምህርት ጥሩ ውጤት ቢኖረኝም፣ ፍላጎቴ ዘመናዊ የስዕልን ትምህርት መማር ነበር፡፡ መላው ቤተሰቤም ወደ ስዕል ትምህርት ቤት እንድገባ ፍላጎት ነበረው፡፡ ለዚህም ልባናዊ ምስጋናዬን በዚህ አጋጣሚ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ የቤተሰቤ ማበረታታትና ሰዓሊ እንድሆን ያደረጉት አስተዋፅኦ እስካሁን ከሙያው እንዳልላቀቅ አድርጎኛል፡፡
በባህላዊ የስዕል ዘይቤ በቂ እውቀት ከቀሰምክ በኋላ ዘመናዊ ትምህርትን እንደ አዲስ ነው የገባህበት…
 በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስር ወደ ሚገኘው “አለ የስነጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት” ነው የገባሁት፡፡ በባህላዊ የአሳሳል ዘይቤ የተካንኩ ቢሆንም፣ በዘመናዊ የትምህርት ተቋም ብዙ ነገር መቅሰም እንደሚቻል አምኜበት ነው ለመማር የወሰንኩት። ለምሳሌ በጥናት ላይ የተመሰረተ የአሳሳል ዘይቤን የምትከተልበት እውቀት የምትቀስመው በዚህ አይነቱ የትምህርት ተቋም ነው፡፡ ከምን ጀምረህ ምን እውቀት ላይ እንደምትደርስ የምታውቅበትን መሰረታዊና ሳይንሳዊ ጥበብን ትማራለህ። የቴክኒክ ብቃት ይኖርሃል ወይም ታዳብራለህ፤ ለስነጥበብህ በምትጠቀማቸው ሚዲያዎች ብዙ አማራጮችን ትወስዳለህ፤ ስለ ስነጥበብ ታሪክ እውቀት ትቀስማለህ፡፡ በዓለም የስነጥበብ ጉዞ ላይም በቂ ግንዛቤ ይኖርሃል፡፡ ይህ በዘመናዊ የስዕል ትምህርት የምታገኘው እውቀት ነው። ቀለም ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነው፡፡ ስለዚህም ዓለም አቀፋዊ እይታህ ካንዱ ዓለም ወደ አንዱ ዓለም ተወራራሽ የሚሆንበትን መንገድ ይከፍትልሃል፡፡ በነገራችን ላይ አለ ስገባ ከሰዓሊ ካሳ ወንድማአገኘሁ ጋር የነበረውን የአባትና ልጅ ግንኙነት አግኝቻለሁ፡፡ ከስዕል አስተማሪዎች ጋር የነበረኝን ግንኙነት ቤተሰባዊ ሲሆን ይህም የስነጥበቡ ባህል ሆኖ የዳበረ ይመስለኛል። በአርት ስኩል ቆይታዬ አዲስ ነገር ለማወቅ የነበረኝ ጉጉት ይበልጥ ነው የጨመረው፡፡ ሶስተኛ ዓመት ላይ ስደርስ ከታዋቂው  ሰዓሊና አስተማሪ ታደሰ መስፍን ጋር ተገናኘሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ  ታዴ ያስተማረኝና የሰጠኝ እውቀት ሶስተኛውን የስነጥበብ አይኔን የከፈተልኝ በመሆኑ ከልብ የማመሰግነው  የሙያ አባቴ ነው። አፍሪካና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አሮጌነት፤ ቀውሱን፤ ኮልከሌውን በየቤታችን በየጓዳችን ስንኖር ያለውን  ዝብርቅርቅ ህይወት ለስዕሌ እንደ መነሻ ሃሳብ እንድመለከትው  ያደረገው ታደሰ መስፍን ነው፤ አለ የስነጥበብ ዲዛይን ትምህርት ቤት በአፍሪካ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ብቸኛው የስነጥበብ ትምህርት ቤት እንደሆነ ይታወቃል።
ከዚሁ ትምህርት ቤት በባችለር ዲግሪ ስመረቅ ስፔሻላይዝ ያደረግሁት በስዕል ቅብ ስራ ነበር። መመረቂያ ስራዬ የነበረውም የአፍሪካ አሮጌ አካባቢያዊ ሁኔታን የሚገልፅ ሲሆን በወቅቱ አሁንም ስለሚስተዋለው ምስቅልቅሉን የትራፊክ ሁኔታ የሚገልፅ ትልቅ የግድግዳ ስዕል  ነበር የሰራሁት። ከዚያ በተረፈ በሱማሌ ተራ ያሉትን የተበታተኑ መኪናዎችና፤ አሮጌ እቃዎችን  አሮጌነታቸውን፤ ያረጀና ያደፈ ቀለማታቸውን በሚያሳዩ ገፅታዎችም ስዕሎችን ሰርቼ ከብዙ አስተማሪዎች የማበረታቻ አድናቆትና አስተያየት አግኝቻለሁ፡፡ ስነጥበብ ማለት አዲስ አይነት እይታን ይዘህ መምጣት ነው፡፡ ሁላችንም የምናውቀውን ነገር በአዲስ መልክ ማሳየት ነው። ባለፈው ወር የታየው  ኤግዚብሽኔ መነሻው  ከዚህ የመመረቂያ ስራ ጀምሮ የመጣሁበት ጉዞ ነው፡፡ ከስነጥበብ ትምህርት ቤቱ ከወጣሁ ከአራት ዓመታት በኋላም የመጀመርያውን የብቻዬን ኤግዚብሽን “በመኪና” በሚል ርእስ ለማቅረብ ችያለሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ በስዕል ገቢ እያገኘህ መኖር እጅግ ከባድ ነው፡፡ ስዕልን የምሰራው ከራሴ ስሜት እንጂ ከሰው ፍላጎት አንፃር አይደለም፡፡ ገንዘብ ለማግኘት ደግሞ ከስው ፍላጎት አንፃር መሳል ሊኖርብህ ነው፡፡ አስተማሪዬ ታደሰ መስፍን ‹‹ስዕል ቀናተኛ ነች›› ይለኝ ነበር። ነፍሴን ነፍሴን የምትል ከሆነ ስጋዊ ስሜትህ ላይ ትጎዳሃለች፡፡ እኔ የሚሰማኝን ልሳል የምትል ከሆነ ሰው  የሚሰማውን ስለህ ገቢ ማግኘት አትችልም፡፡ እነዚህ ናቸው የሰዓሊው  ፈተናዎች፡፡

Read 1165 times