Saturday, 04 September 2021 17:45

“ሿሿችሁን ተዉኝ!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እኔ ነኝ ምስኪኑ ሀበሻ!
አንድዬ፡— እናንተ ሰዎች ምን ይሻላችኋል...እንዲያው ዝም ብለህ እኔ ነኝ ትለኛለህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ድንገት ከረሳኸኝ ብዬ ነው፡፡
አንድዬ፡— እኔ እሱን አይደለም ያልኩህ። ደግሞስ ልርሳችሁስ ብል መች በእጄ ብላችሁ ታስረሳላችሁ! ልልህ የፈለግሁት እዛ ምድር ላይ ከሰው ጋር ስትገናኙ መጀመሪያ ምንድነው የምትባባሉት?
ምስኪን ሀበሻ፡— እንደምነህ? እንደምነሽ? ነዋ አንድዬ!
አንድዬ፡— እና... እኔስ እንደምነህ ብባል ይጠላብኛል?
ምስኪን ሀበሻ፡— እንዴ አንድዬ!
አንድዬ፡— ምን ያስደነግጥሃል! ከርመህ ነው የመጣኸው፣ እንዴት እንደከረምኩ አታውቅም፡፡ ወይስ ይሄ ጂ.ፒ.ኤስ. ነው ምናምን በምትሉት ነገር ውሎ አዳሬን ስትከታተል ከርመሀል?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ዛሬ ገና አንዲት ቃል ሳልተነፍስ እያስ..እያስደነገጥከኝ ነው። እንዴት ብዬ ነው አንተን ደህና ነህ ወይ የምለው!
አንድዬ፡— አየህ አይደል...አንደኛውን ምን ትሆናለህና ነው፣ ደህና ነህ ወይ የምልህ አትለኝም?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እኔ እንደእሱ አይነት ቃል አይወጣኝም፡፡ በስመአብ...
አንድዬ፡— ጭራሽ እኔው ፊት አማትብ እንጂ፡፡ ቆይ... ቆይ ድንጋጤውን ለዛው ለምድራችሁ አስቀምጠው፡፡ እኔ ለአንተ ልበልልህና ምን እሆናለሁ ብለህ ነው ደህና ነህ ወይ የምትለኝ! እውነቱን ልንገርህና...የሰው ልጅ ጭካኔና ክፋት እንዲሁ ደርሶ ለእኔስ ቢሆን ይመለስልኛል! በተለይ እናንተ ዘንድ የእኔን ሥራ ለመንጠቅ እየው እየተፎካከራችሁ አይደል! ...ምስኪኑ ሀበሻ እየሰማኸኝ ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ! ታዲያ አንተን ያልሰማሁ ማንን ልሰማ ነው!
አንድዬ፡— እንደው ፊትህ ኮምጨጭ ብሎ ሳየው፣ ይሄ ሰው ከርሞ ሲመጣ ጊዜ ፎርጅድ አምላክ መስዬው ይሆን...
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ! አንድዬ!...
አንድዬ፡— እሺ...እንደው በጠዋቱ የኮሶ መድሀኒት የጠጣ ስትመስልብኝ ብዬ ዘና ላደርግህ ብዬ ነው፡፡ ስማ የኮሶ መድሀኒት ስል ትዝ አለኝ፡፡ እናንተ እኮ የምትገርሙኝ ኮሶው ሳይታያችሁ የኮሶ መድሀኒት የምትጠጡ ሰዎች ናችሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አስቀድሞ ለመከላከል ነዋ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡— ምኑን ነው የምትከላከሉት?
ምስኪን ሀበሻ፡— የኮሰ ትሉን ነዋ፣ አንድዬ! አስቀድሞ የኮሶ መድሀኒት ከወሰድንበት ድርሽ ስለማይል ነው፡፡
አንድዬ፡— መቼም ያው ኮሶው ጤናማ ያልሆነ ጥሬ ሥጋ ከመመገብ ነው የሚመጣው፣ አይደል እንዴ፣ ምስኪኑ ሀበሻ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አዎ፣ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡— እስቲ ልጠይቅህ... እንደው በቅርብ ጊዜ ሥጋ የተመገብከው መቼ ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ በቀደም የፍልሰታ እለት ግማሽ ኪሎ ገዛንና ከቤተሰቤ ጋር እሷኑ ተቃመስናት፡፡
አንድዬ፡— ጾሙ ከመግባቱ በፊትስ፣ ብቻ ሆዴን አታባባኝ እንዳትለኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እንደዛ ባልልህም ሆዳችን እኮ ዘንድሮ ሀያ አራት ሰዓት እንደባባ ነው፡፡ ከጾሙ በፊት ሥጋ የተመገብኩበትን እንዳልነግርህ ቀኑን አላስታውሰውም፡፡
አንድዬ፡— ግን የኮሶ መድሀኒት ትወስዳለህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አዎ፣ አንድዬ፣ ትዝ ሲለኝ አልፎ፣ አልፎ እወስዳለሁ፡፡
አንድዬ፡— ኮሶን አስቀድሞ መከላከል የምትለዋን ነገር ተዋትና እኔን ግራ የሚገባኝ መጀመሪያ ሥጋ ለመመገባችሁ እርግጠኛ ሳትሆኑ በእንቆቆና በኪኒን አንጀታችሁን መከራውን የምታበሉት ለምን እንደሆነ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ያው እንግዲህ በተስፋ...
አንድዬ፡— እና በተስፋ ገና ለገና ሥጋ ልንመገብ እንችላለን በሚል አስቀድማችሁ የኮሶ መድሀኒት ትወስዳላችሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ ይባል የለ፡፡
አንድዬ፡— እንደዛ ያልከው ልታስቀኝ ፈልገህ ነው አይደል! እስቲ ንገረኝ የኮሶ መድሀኒቱ ገብቶ ሆዳችሁ ውስጥ ምሽግ ይቆፍራል እንዴ? ክትባት እየመሰለኝ ግራ ስለገባኝ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱማ...
አንድዬ፡— አየህ... አንዱ ችግራችሁ በእጃችሁ ያለውን በሚገባ ሳትጠቀሙበት በእጃችሁ ስለሌለው ማሰባችሁ ነው፡፡ የቆጡን ከማውረዳችሁ በፊት የብብታችሁን መጀመሪያ ማጥበቁ አይሻልም!  አንዳንድ ጊዜ ዜና ምናምን የምትሉት ሾልኮ ወደ እኔ እየመጣ ስሰማው የሚገርመኝን ልንገርህ...
ምስኪን ሀበሻ፡— ደስ ይለኛል፣ አንድዬ...
አንድዬ፡— በሆኑ ነገሮች ላይ በምሥራቅ አፍሪካ አንደኛ ለመሆን፤ ከአፍሪካ ቀዳሚ ለመሆን የሚሉ ነገሮች ስትሉ እሰማችኋለሁ...
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ አትቆጣኝና፣ እንደዛ ማለቱ ምን ክፋት አለው?
አንድዬ፡— ምንም፣ ምንም ክፋት የለውም፡፡ መጀመሪያ ግን የራሳችሁን፣ የህዝባችሁን፣ የሀገራችሁን ፍላጎት ሳታሟሉ አፍሪካ ላይ ምን ያንጠለጥላችኋል፡፡ እንዲሁ ነገር ለማሳመርና ለማስጨብጨብ የምታወሩት የትም አያደርሳችሁም!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ...ይህን ያህል አስቆጥተንሀል እንዴ!
አንድዬ፡— እኔ ምን ያስቆጣኛል። ዘላለም ዜማ ብቻ እየለወጣችሁ ያንን ግጥም ስትደጋግሙብኝ እንደው መቼ ነው ከትናንት የሚማሩት እያልኩ ነው እንጂ። ብቻ እሱን ተወውና አንተ የመጣህበትን ጉዳይ እኔ ለፈለፍኩ መሰለኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እንደእሱ አትበል!
አንድዬ፡— ጥሩ፣ እሺ ዛሬ ምን እግር ጣለህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ይኸው ዓመቱ ሊወጣ አንድ ሳምንት ነው የቀረን፡፡
አንድዬ፡— እና... እንዳይወጣብን አስደግመልን ልትለኝ ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— ኸረ በጭራሽ አንድዬ! በጭራሽ፣ ጦሳችንን ይዞ ከፈለገ ካይሮ ድረስ ይሂድ!
አንድዬ፡— እየው... ይቺን፣ ይቺንማ ትችሉባታላችሁ! በነገር አነካክተህ ደግሞ ከዛ ሲሲ ከሚሉት ሰውዬ ጋር ልታጋጨኝ ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እንደው ተዳፈርክ አትበለኝና፣ መጀመሪያስ እንደው እሱ ሰውዬ አንተ ዘንድ ብቅ ብሎ ያውቃል! ካይሮ ቁጭ ብሎ ቱሪናፋውን ይልቀቅ እንጂ..
አንድዬ፡— ምስኪን ሀበሻ እንዴት ዜማ ያላት ነገር ነች የተናገርካት!
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን አልኩ አንድዬ፣
አንድዬ፡— ቱሪናፋ ያልካት ምን ማለት ነች?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ለምን ይዋሻል እኔም በሚገባ አላውቃትም፡፡ ሲሉ እየሰማሁ ነው፡፡ ግን ጉራ ማለት ትመስለኛለች፡፡
አንድዬ፡— ብቅ ብሎ ያውቃል ላልከኝ፣ እንደው ስታስበው በር የምታንኳኩት እናንተ ብቻ የሆናችሁ ይመስልሀል?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እንደዛ ለማለት ፈልጌ ሳይሆን...ማለት በአንተ የሚያምን ሰው እንዴት ክፉ ይሆናል ብዬ ነው፡፡
አንድዬ፡— ጨዋታ አመጣህልኝ፤ እናንተስ በአንተ እናምናለን እያላችሁ ስንት ጉድ ትሠሩ የለም እንዴ! በአንድ ፊት እያማተባችሁ በሌላ ፊት ቤተ ክርስቲያን በመድፍ የምትመቱ አይደላችሁም እንዴ! በአደባባይ ስለ ሰላም፣ ስለ ወንድማማችነት፣ ስለ አብሮ መኖር ቃላት የተሞላ ጸሎት እያነበነባችሁ ቤተ እምነትን በዘራችሁ የምትሰይሙ አይደላችሁም እንዴ! በቀጥታ እኔኑ እከሌን ባዶውን አስቀርልኝ፣ እከሊትን ራቁቷን አስኪድልኝ ትሉኝ የለም እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ...
አንድዬ፡— ቆይ አስጨርሰኛ፣ በስሜ ጋኔን እናወጣለን፣ ምን እናደርጋለን እያላችሁ እኔኑ... እኔኑ...ምን ነበረች የሆነች ቃል...አዎ፣ እኔኑ ሿሿ ልትሠሩኝ ትሞክሩ የለም እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ሿሿ አንተም ዘንድ ደረሰች እንዴ!
አንድዬ፡— ደረሰች ወይ! እንደውም ልንገርህና እናንተን ጨምሮ ሁሉም ሿሿ የሚለማመደው በእኔ አይደለም እንዴ! ሀምሳ ሚሊዮን ብር ዘርፋችሁ የመቶ ሺህ ብር የስለት ምንጣፍ ከማስገባት የባሰ ምን ሿሿ አለና ነው!  እናንተው ራሳችሁ ሌላውን እያስለቀሳችሁ እኔን እንባችንን አብስልን ከማለት የባሰ ምን ሿሿ አለና ነው! የእናንተ ነገር እኮ... ብቻ ተወው! ስማኝ ሌላ ጊዜ ትመጣና እናወራለን፡፡ እስከዛው መጪው አዲስ ዓመት የሰላምና የደስታ ይሁንላችሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አሜን፣ አንድዬ! አሜን!
አንድዬ፡— ደግሞ ይህን ሿሿችሁን ተዉኝ ብሏችኋል በልልኝ፡፡ ስቀልድ ነው፡፡ በደህና ግባ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አሜን አንድዬ፣ አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1920 times