Print this page
Saturday, 18 September 2021 16:38

የሳምንቱ ወሬዎች (ከዚህም ከዚያም)

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 እርዳታ ጭነው ትግራይ ከገቡ ተሽከርካሪዎች 428ቱ አልተመለሱም ተባለ


             ሰብዓዊ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ከተጓዙ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች መካከል 428ቱ ከክልሉ እስካሁን አለመውጣቸው ተገለጸ። ይህ የተባለው የጠቅላይ ሚንስቴር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም  ሐሙስ መስከረም 6 ቀን 2014 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ ነው።
በተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት አማካኝነት ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን የጫኑ 590 ከባድ ተሽከርካሪዎች ከሰመራ ወደ መቀለ መጓጓዛቸውን ተናግረዋል።
የፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም፤ በአንድ የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅት አማካኝነት የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲያደርሱ ከገቡ 466 ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች መካከል 428 የሚሆኑት እስካሁን ከክልሉ አለመውጣታቸውን አስረድተዋል።
 ከክልሉ ሳይወጡ የቀሩት ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎቹ በክልሉ ውስጥ ለምን አገልግሎት እየዋሉ እንደሆነ ግልጽ ባለመሆኑ በመንግሥት ዘንድ ጥርጣሬን መፍጠሩን ቢልለኔ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ፣ የሰላም ሚኒስቴር ከሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ፣ ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ ጭነው የገቡ ተሽከርካሪዎች በተቀመጠው የአሰራር ሥርዓት መሠረት ተመልሰው መውጣት ሲገባቸው አለመመለሳቸው ጉዳዩን እጅግ አሳሳቢና ጥርጣሬ እንዲፈጠር እንዳደረገ ገልጾ ነበር።
ሚኒስቴሩ፤ “በተጨባጭ ከአላማቸው [ተሽከርካሪዎቹ] ውጪ ተሰማርተው ላለመሆኑ ማረጋገጫ የሚሰጥ አካል አልተገኘም” ብሎ ነበር፤ ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፡፡
ቢልለኔ፤ ወደ ትግራይ የሚደረጉ የአየርና የየብስ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ጉዞዎች እንደቀጠሉ መሆናቸውን አመልክተው፤ የአውሮፓ ሕብረት የሰብዓዊ እርዳታ በረራም ከአንድ ሳምንት በፊት መጀመሩን ተናግረዋል።
እስከ መስከረም 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ 32 ተቋማት ለሰብዓዊ ሥራቸው 144 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ወደ መቀለ መውሰዳቸውንም ጠቅሰዋል። ከምግብ ውጪ፤ ወደ 760 ሺህ ሊትር የሚጠጋ ነዳጅና ከ1ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የግብርና ግብዓቶች ወደ ክልሉ መጓጓዙን አመላክተዋል።
እስከ መስከረም 4 ድረስ እንቅስቃሴያቸው ተስተጓጉሎ የቆሙ ተሽከርካሪዎች የሉም ያሉት ቢልለኔ፤ መንግሥት የእርዳታ ቁሳቁሶች ወደ ክልሉ በፍጥነት እንዲገቡ ለማቀላጠፍ ሰባት የነበሩትን የፍተሻ ጣቢያዎች ወደ ሁለት ቀንሷል ብለዋል።
የሰብዓዊ እርዳታ በአማራ ክልል
ቃል አቀባይዋ ጨምረውም፤ በአማራና በአፋር ክልል በህወሓት አማጺያን ጥቃት ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ በርካታ ዜጎች አሉ ብለዋል።
በአማራ ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ500 ሺህ መሻገሩንና አብዛኛው ሕዝብ የተፈናቀለው ከዋግ ኽምራ፣ ከሠሜን ጎንደር፣ ከደቡብ ጎንደር፣ ከሠሜን ወሎና ከደቡብ ወሎ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሠሜን ወሎ ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ተጠልለው የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ወደ 270ሺህ እንደሚጠጋም አመልክተዋል።
ከቀያቸው ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ለሚገኙ ዜጎች መንግሥት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን እስከ መስከረም 4 ቀን 2014 ድረስ 27ሺህ ኩንታል እህል አቅርቧል። ከ2600 በላይ ኩንታል እህል ደግሞ በዋግ ኽምራ ዞን ለሚገኙ ተፈናቃዮች ተልኳል።
ይሁን እንጂ በህወሓት አማጺያን ቁጥጥር ሥር በሚገኙ የሠሜን ወሎ ወረዳዎች የሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁሶችን ማቅረብ አልተቻለም ብለዋል ቢልለኔ።
ወትሮም ቢሆን የምግብ እጥረት ባለበት ሠሜን ወሎ፤ ህወሓት የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች እርዳታ እንዳያደርሱ እክል መሆኑ ሁኔታዎችን ያባብሳል ብለዋል።
መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለትግራይ ክልል የሰጡትን ትኩረት ለአማራና ለአፋር ክልል ተጎጂዎችም እንዲሰጡ መንግሥት ማሳሰቡንም ተናግረዋል።  
(ቢቢሲ)

_______________________________________


                      በአዲሱ የዴልታ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአንድ ቀን ብቻ 38 ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት ተዳረጉ


                የኮቪድ-19 ቫይረስ ዝርያ በሆነው ዴልታ በኢትዮጵያ በአንድ ቀን ብቻ ማለትም መስከረም 3 ቀን 2014 ዓ.ም. 38 ግለሰቦችን ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጋቸው ተገለጸ፡፡
ከዚህም ሌላ ከጳጉሜን 1 ቀን እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ 121፣ ከመስከረም 1 ቀን እስከ መስከረም 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ 83 በድምሩ 204 ግለሰቦች በዚሁ ቫይረስ ዝርያ መሞታቸው ተረጋግጧል፡፡
የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ዓባይነህ እንደገለጹት፣ ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ 9,164 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ከመያዛቸውም በላይ በሳምንቱ ቀናት በአማካይ 737 የሚሆኑ ሰዎች ወደ ፅኑ ሕሙማን ክፍል ገብተው ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም 158 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸውን ማጣታቸውን፣ በተጠቀሰው ሳምንት በአማካይ በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ በ17.7 በመቶ የደረሰ መሆኑን፣ ይህም ከወዲያኛው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር ከፍ ያለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ የሞት ምጣኔ በአማካይ 1.6 በመቶ መድረሱን አኃዞች ያሳያሉ ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ዴልታ›› የተሰኘው ይህ የኮቪድ-19 ቫይረስ ዝርያ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፉ ሁኔታው ቀደም ሲል ከነበሩት አልፋና ቤታ ዝርያዎች በሁለት እጥፍ እንደሚያድግ፣ በወረርሽኙ የመያዝ ምጣኔውም እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ወቅታዊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን አስመልክቶ ማክሰኞ መስከረም 4 ቀን 2014 ዓ.ም. በተካሄደው ሳምንታዊ የጋዜጣ መግለጫ ላይ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት፣ የኮቪድ-19 ቫይረስ ሁለት ዝርያዎች ማለትም ‹‹አልፋ›› እና ‹‹ቤታ›› ያጠቁ የነበሩት ዕድሜያቸው የገፋና ተጓዳኝ በሽታ ያደረባቸውን ነበር፡፡ ‹‹ዴልታ›› የተሰኘው የአሁኑ ዝርያ ግን የዕድሜ ክልል እንደሌለውና ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል እኩል የሚያጠቃ ወይም ለበሽታ የሚዳርግ ነው ብለዋል፡፡
ለዴልታ ዝርያ ተብሎ የተዘጋጀ ሌላ ክትባት በዓለም ላይ እንደሌለ፣ ቀደም ሲል የነበሩት ክትባቶች አሁንም የዴልታን ዝርያ ለመከላከል እንደሚያገለግሉ፣ ይህም ሆኖ ግን ክትባት ተወስዶ ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገ በቫይረስ የመያዝ ዕድል እንደሚኖር ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
ይህም ሆኖ ግን ሕመሙ ኃይለኛ እንደማይሆንባቸው፣ ወይም የከፋ እክል ሳያጋጥማቸው የመዳን ዕድል ሊኖራቸው እንደሚችልና የሞት ምጣኔውንም እንደሚቀንስ ከምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በመሆኑም የኮቪድ-19 ቫይረስ ዝርያ የሆነው ዴልታ እያደረሰ ያለውን ከፍተኛ ችግር ለመግታትና ለመቆጣጠር እንዲቻል በማኅበረሰቡ ዘንድ ያሉትን የተሳሳቱ ግንዛቤዎችና አመለካከቶች በማስወገድ፣ ከአሁን በፊት ሲተገበሩ የቆዩና በመካከሉም እየተዘነጉ የመጡትን የመከላከያ መንገዶችን በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ማድረግና የኮቪድ-19 ክትባት መውሰድ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡
በተለይም የተቀመጡ መመርያዎችን ያላገናዘቡ ስብሰባዎች፣ ሥልጠናዎች፣ በተጨናነቀ ሁኔታ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሚሳተፍባቸው ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ የአደባባይ በዓላት ላይ ርቀትን የመጠበቅ፣ ማስክ የማድረግና በሳኒታይዘር ወይም በሳሙናና በውኃ የእጅን ንፅህና መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ፣ ግዴታም ጭምር መሆኑን ማወቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው መመርያ 803/2013 ዓ.ም. ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው ነው የገለጹት፡፡
በአጠቃላይ በሁለት ዙር 2,794,490 ክትባት ለኅብረተሰቡ መስጠት መቻሉን፣ በሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት በኋላ ሦስት ሚሊዮን ዶዝ ክትባት ወደ አገር የሚገባ መሆኑን፣ ሰዎች በሁሉም የመንግሥት ጤና ተቋማት መከተብ እንደሚገባቸው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡
እንደ አቶ አስቻለው ማብራሪያ፣ ለኮቪድ-19 ቫይረስና ሌሎችም በሽታዎች ፍቱን ናቸው ተብለው ለኢንስቲትዩቱ የቀረቡ 20 የባህል መድኃኒቶች የክሊኒክ ሙከራ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሙከራው መቼ ይጠናቀቃል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹ትክክለኛውን ቀን ለማወቅ ያስቸግራል፤›› ብለዋል፡፡
(ሪፖርተር)

______________________________________


                 በአማራ ክልል አንድ ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ይሆናሉ ተባለ

            በአማራ ክልል የሚገኙ አንድ ሚሊዮን ገደማ ተማሪዎች፤ በ2014 የትምህርት ዘመን ትምህርታቸውን መከታተል እንደማይችሉ የክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። ተማሪዎቹ ከትምህርት ገበታ ውጭ ለመሆን የተገደዱት፤ በአማራ ክልል ባለው ውጊያ “በርካታ” ትምህርት ቤቶች በመውደማቸው ምክንያት እንደሆነ ኃላፊው ተናግረዋል።
የትምህርት ቢሮ ኃላፊው፤ ለትምህርት ቤቶቹ ውድመት “ወራሪዎች” ሲሉ የሚጠሯቸውን የትግራይ አማጽያንን ተጠያቂ  አድርገዋል። አማጽያኑ “የትምህርት ተቋማትን እየዘረፉ እና እያወደሙ ነው” ሲሉ የሚወነጅሉት ዶ/ር ይልቃል፤ ለዚህም በእነርሱ ቁጥጥር ስር ቆይተው በተለቀቁ የአማራ ክልል አካባቢዎች የደረሰውን ጉዳት በማስረጃነት ጠቅሰዋል።
እስካሁን ባሰባሰቡት መረጃ መሰረት፤ በአማጽያኑ ቁጥጥር ስር በነበሩ አካባቢዎች የሚገኙ 268 ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው መረጋገጡን ዶ/ር ይልቃል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች በተጨማሪም ከአንድ ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች በከፊል መጎዳታቸውን አክለዋል። በአማጽያኑ ከፊል ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ለመጠገን እና ትምህርት ለማስጀመር የክልሉ ትምህርት ቢሮ በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ዶ/ር ይልቃል ገልጸዋል። ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ለመጠገን ግን ከወጪ ጋር በተያያዘ “ብዙ ፈተና ያጋጥመናል ብለን እናስባለን” ሲሉ ትምህርት ቤቶቹን ወደነበሩበት መመለስ ቀላል እንደማይሆን ጠቁመዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር በክልሉ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ለመጠገን በዛሬው ዕለት የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል። ድጋፉ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመደበኛነት ከሚያደርገው እገዛ በተጨማሪነት የተደረገ ነው ተብሏል።
ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች በዚህን መሰሉ ድጋፍ ጥገና ቢደረግላቸውም፤ ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ተማሪዎችን ወደ ትምህርታቸው ለመመለስ ሌሎች ተግዳሮቶች እንቅፋት እንደሚሆኑ ዶ/ር ይልቃል ያስገነዝባሉ። “ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የተማሪዎች ወላጆች ሃብት ንብረታቸውን አጥተዋል” የሚሉት የክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ፤ “ትምህርት ቤቶቹ ቢኖሩ እንኳን ወላጆች ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት የሚያስችል አቅም የላቸውም” ሲሉ ያስረዳሉ።
ጦርነቱ ያስከትለዋል ተብሎ የሚፈራው የምግብ እጥረት፤ ሌላው በምክንያትነት የተጠቀሰ ተግዳሮት ነው። “የምግብ እጥረት ባለበት ሁኔታ ተማሪዎች ለመማር ይቸገራሉ” ይላሉ ዶ/ር ይልቃል። ጦርነቱ ራሱ በተማሪዎች ላይ የሚያስከትለው የስነ ልቦና ጫና፤ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት እንዳይመለሱ ሊያደርግ ይችላል ሲሉ ተጨማሪ ምክንያት ነው ያሉትን ጠቅሰዋል።
በአማራ ክልል ያለው ውጊያ ያስከተለው ተጽዕኖ፤ ከሶስት ቀናት በፊት ባለፈው ሰኞ መስከረም 3 በክልሉ በተጀመረው የአዲሱ የትምህርት ዘመን ምዝገባ ወቅት መስተዋሉን የትምህርት ቢሮ ኃላፊው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። በዋግ ኽምራ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች ሙሉ በሙሉ እንዲሁም በሰሜን ጎንደር በርካታ ወረዳዎች እና ደቡብ ወሎ እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች በከፊል የተማሪዎች ምዝገባ እንቅስቃሴ አለመኖሩን የሚገልጹት ዶ/ር ይልቃል፤ ይህም በአካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር የመጣ መሆኑን አብራርተዋል።
በአማራ ክልል በአጠቃላይ 9,700 ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲሆን፤ እስከባለፈው የ2013 የትምህርት ዘመን ድረስ 5.7 ሚሊዮን ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ መቆየታቸውን ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመለክታል። በአሁኑ ወቅት በትግራይ አማጽያን ቁጥጥር ስር ባሉት የክልሉ አካባቢዎች ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የሚያስተናግዱ፤ 2,900 ገደማ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ የቢሮው መረጃ ይጠቁማል።
የትምህርት ቢሮው ኃላፊ “እነዚህም ትምህርት ቤቶች ባናውቀው ነው እንጂ ከጉዳት ነጻ ላይሆኑ ይችላሉ” ሲሉ አማጽያኑ በትምህርት ቤቶቹ ላይ ጉዳት ሊያደርሱባቸው ይችላል የሚል ግምት እንዳለ ይናገራሉ። በአማጽያኑ ስር ያሉት አካባቢዎች ነጻ ሲወጡ፤ ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች ብዛት ሊያሻቅብ ይችላል የሚል ስጋት አለ ብለዋል።
 (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)



Read 1411 times
Administrator

Latest from Administrator