Saturday, 18 September 2021 16:56

“ህግ ኬሬዳሽ!” ስልጣኔ አይደለም

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አዲሱ ዓመት ከገባ ስምንተኛው ቀን፡፡ ምን መሰላችሁ...ዓመቱ ከገባ ስምንተኛው ወር ነው የምንልበት ጊዜ የቁጥሩን ያህል ላይረዝም ይችላል፡፡ ልክ ነዋ...2013 የሚሉት ጦሰኛ፣ መዘዘኛ፣ ምናምነኛ ዓመት ራሱ እኮ ዓርብ ብለን ሳናበቃ ሌላኛው ዓርብ እየመጣ አይደል እንዴ የነጎደው! እንደውም ከዛ በፈጠነ ‘ሩጫ’ በሄደ ነበር የሚያስብል ዓመት፡፡ (‘አንዳንድ’ ወዳጆቼ...ያቺ 13 የሚሏት ቁጥር መቀጠሏ ይሆን እንዴ ነገሩን ሁሉ ብልሽትሽት ያደረገው! አይ...የሴራ ትርክቶቻችን ምድርን አልፈው ‘ወደ ላይ’ ሲወጡ እያየን ስለሆነ ነው! አሀ...የጠላት እጥረት ያለብን ይመስል የማይተነኮስ እየተነኮስን 14ን 13 እንዳናስመስላት ነዋ!)
እኔ የምለው…ጥያቄ አለን...ህግ ያለማክበር መሰልጠን የሚመስለን ሰዎች እየበዛንና እየተባዛን አይመስላችሁም! ‘እየተባዛን’ የሚለው የቁጥር መጨመርን ለመጠቆም ያህል እንጂ ተቀጥላ ትርጉም እንደሌለው በአክብሮት እንገልጻለን፡፡ ልጄ፣ ዘንድሮ ቃሪያ ከመሰንጠቅ ቃላትን መሰንጠቁ በጣም ቀላል ስለሆነ ከአሁኑ ነገሩን ‘ግልጥ’ ለማድረግ ነው! ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚያተኩሩት የምትናገሯቸው ነገሮች ጽንሰ ሃሳቦች ላይ ሳይሆን የተናገራችሁባቸው ቃላት ላይ ማተኮር ሆድ የሚያባብስበት ዘመን ነው፡፡ ደግሞ ምን መሰላችሁ... ነገሮቹ 99.9 በመቶ የሚያያዙት ከፖለቲካ ጋር ነው፡፡  
“ስማ ማታ ሬድዮ ሰማህ?”
“አልሰማሁም፡፡ ያመለጠኝ ነገር አለ እንዴ!”
“የእንትን ሚኒስቴር የፋይናንስ የመምሪያ ሀላፊ የተናገረውን ብትሰማ ይቺ ሀገር ገና ሰዎች እንዳላለቁባት ታውቃለህ፡፡ እንዴት ኢምፕሬስ እንዳደረገኝ አልነግርህም፡፡”
ከጥቂት ጊዜ በኋላ በእናንተ ነገር የተበሳጨ የቅርብ ሰው ግስላ ሆኖ ያላችሁበት ድረስ ይመጣላችኋል፡፡ (እኔ የምለው፡፡ ‘ግስላ’ ሲጋራ አሁንም አለች እንዴ! አቤት ሽታ! አቤት ሽታ! ቦሌ ተጭሳ እኮ ጉለሌ ነበር የምትሸተው! ይቅርታ... አስተካክላለሁ። ‘ጉለሌ ተጭሳ ቦሌ ነው የምትሸተው!’ ማለት ፈልጌ ነው!) እናም... ይጮህባችኋል፡፡
“አንተ ሰውዬ ግን ከመቼ ወዲህ ነው እንዲህ የሆንከው!”
“እንዴት የሆንኩት?”
“ምን ጎደለህና ነው እነሱ ዘንድ የምትወሸቀው!”
“ምንድነው የምታወራው?”
“በቀደም የሆነ የመንግሥት ባለስልጣንን እንዲህ አለ፣ እንደዛ አለ እያልክ ስታሞካሽ ነበር አሉ፡፡”
“እና... ምን ችግር አለው!”
“አንተ ሰውዬ አላማርከኝም፡፡ ይቺ ወደ መንግሥት ጠጋ ጠጋ ...በጠሱልሽ እንዴ!”
ከዚህ በኋላ ማውራቱ ዋጋ ስለሌለው ቢራው ላይ ደግሞ ሌላ ዙር ጭማሪ ከማምጣታቸው በፊት ሂዱና አንድ ሁለት በሉማ! “ልጄ ከማያወራው ጋር ብተክዝ ይሻላል፣” ሲሉ እኮ ምክንያት አላቸው...ወደ ሰባትና ስምንተኛው ዙር ላይ ‘ማስለፍለፍ’ ቢጀምርም ማለት ነው፡፡ ቂ...ቂ...ቂ...
እናላችሁ...ህግ ያለማክበር የስልጣኔ ምልክት ሆኖ ስታዩ ያሳዝናል፡፡ የምር እኮ… “ለምን ማስክህን አታደርግም?” ስትሉት ለጠብ የሚጋበዝ አባወራ እንደ ጉድ የፈላበት ዘመን እኮ ነው፡፡ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ከረዳቱና ከሾፌር ጋር “ማስክ ባደርግ ባላደርግ ምን አገባህ!” ብሎ ታክሲዋን ከእኛ ጋር ቀላቅሎ ‘ሊቀውጠው’ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲል የነበረ ከጎልማሳነቱ መንደር ለመውጣት በሩን ከፍቶ እየወጣ የሚመስል ሰውም አይተናል፡፡ ረዳቱ ነበር መጀመሪያ ላይ የተናገረው…
“ጋሼ፣ ማስከ አድርግ፡፡” ስሙኝማ… “ስማ ማስክ አድርግ” ከሚል ያለርህራሄ አንስቶ ዘጭ የሚያደርግ ረዳት ተገላግሎ “ጋሼ...” የሚል ማግኘት እኮ መታደል ነው፡፡ የምር ግን…አንዳንዴ አብሮ የማያኖር ባህሪያቸውን “ሥራው ራሱ የሚፈጥረው መሆን አለበት”…ልትሉ ይዳዳችሁና  ደግሞ ለተሳፋሪዎች ተገቢውን አክብሮት የማይነፍጉ ስታገኙ ሀሳባችሁን ትለውጣላችሁ፡፡ በዛ ሰሞን ለሰባት ብር መንገድ ዝናብ በመሆኑ በሚል አስር ብር የተጠየቁ አዛውንት “ከሌለህ ለምን በባስ አትሄድም!” ነበር የተባሉት። በዛ ሰዓት የስንት ልጆች አባት፣ የስንት የልጅ ልጆች አያት ሊሆኑ የሚችሉ ሰው እንደዛ ሲዋረዱ እንደማየት የሚሰቀጥጥ ነገር አልነበረም፡፡
እናላችሁ… ማስክ እንዲያደርግ የተጠየቀው ሰውያችን ከግልምጫ በስተቀር መልስ አይሰጥም፡፡ በቃ…ጭጭ! “ጋሼ፣ ማስክ አድርግ አንጂ!” ይላል ረዳቱ እንደገና። የዚህ ጊዜ ሾፌሩ ዘወር ብሎ “ምን አለ ማስክህን ብታደርግና ብንሄድበት!” ይላል። (እኔ የምለው…ያችን የምታክል ክንድ ላይ ይሄ ሁሉ ‘ታቱ!’…ከተነቃሾቹ ይልቅ ነቃሾቹ...አለ አይደል... ከአሁን አሁን የሆነች ደም ስር ምናምን ነካን ብለው እንዴት ሊሳቀቁ እንደሚችሉ አይታያችሁም! እነኚህ የፕሬሚየር ሊግ ተጫዋቾች ምናቸውንም፣ ምናምናቸውንም እያዥጎረጎሩ እኛንም መከራ ውስጥ ከተቱን!)
እናላችሁ…የታክሲ ውስጥ ማይክ ታይሰን ምን ቢል ጥሩ ነው...
“ባደርግ፣ ባላደርግ ምን አገባህ!”
ይሄኔ ተሳፋሪዎች ሰዉየው ማስኩን እንዲያደርግ ማጉረምረም ጀመሩ፡፡ ግልምጫው እኮ…አለ አይደል… አልሲሲን ከካይሮ ቤተመንግሥት “እግሬ አውጪኝ…” ባያስብለው ነው! ታሪካዊ ክንዱ ላይ ታሪካዊ ንቅሳቶች የደረደረው ሾፌር ዘሎ ወርዶ መጣላችኋ! (ለዚህ ነው ‘ጉዳዩ ከክንዲቱ ሳይሆን ከልቢቱ ነው’ የምንለው!)
“እሺ፣ አሁን ውረድልን!” ሰውየው አይደለም መውረድ እንደዛ የሚመስል እንቅስቃሴ እንኳን አላሳየም፡፡ ይኸኔ ረዳቱ “ውረድ!” ብሎ ክንዱን ይዞ ይጎትተዋል። የሆነች ግርግር ቢጤም ትፈጠራለች።  ልጁ እኮ በጣም የተጋነነ የግምት እድሜ ብንጠራለት ከአስራ አምስትና አስራ ስድስት አይበልጥም፡፡  ሰውየው እጁን መነጨቀና ማስኩን አውጥቶ አደረገ፡፡ ይሄኔ ሾፌሩ ወደ ቦታው ሲመለስ ረዳቱ ግን ካልወረደ ሞቼ እገኛለሁ አለ፡፡ ቢለመን፣ ምን ቢባል እሺ ሊል ነው! መጨረሻ ሰውያችን በረዳቱ ስድቦች ታጅቦ፣ ውርደቱን ተሸክሞ የግዱን ወረዳታ!
ስሙኝማ… የእኛ ነገር እኮ አንዳንዴ ምንም ነገር ለማያመልጠው ተመራማሪም እንኳን አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ ወረርሽኙ በአሁኑ ጊዜ የደረሰበት ደረጃ በተደጋጋሚ እየተነገረ ነው፡፡ በየቀኑ ህይወታቸውን የሚያጡ ዜጎቻችን ቁጥር እንዴት እያሻቀበ እንደሆነ እያየን ነው፡፡  ግን አሁን ከተማችንን ስታዩት ምንስ የሚያሳስብ ነገር ያለ ይመስላል?
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ምን ግራ ይገባሀል አትሉኝም፣ ይህን ያህል ለህጎችና ለደንቦች ‘ኬሬዳሽ’ ያልነው ምን እያሰብን ነው! ‘ስልጣኔ’ የሚባል ነገር የሚጀምረው ህግ ከማክበር አይደለም እንዴ!
ኮሚክ እኮ ነው…ብዙዎች የትራፊክ ህግ የሚያከብሩት እኮ በአካባቢው የትራፊከ ፖሊስ እስካለ ድረስ የሆነበት ጊዜ ውስጥ ነን! ስሙኝማ…እንደው በሆነ አጋጣሚ ከተማዋ ውስጥ ለሁለት፣ ሦስት ቀን የትራፊክ ፖሊሶች መንገድ ላይ ባይገኙ ከተማዋ በአናቷ ባትቆም ነው! ምን አለፋችሁ…የሆነ ‘ዘ ፋስት ኤንድ ዘ ፊዩሪየስ’ ፊልም የሚቀረጽባት ነበር የምትመስለው!
እናላችሁ…የህግ መጣስ የሚቆጠቁጠን እላይ ሲደርስ ብቻ የሚመስለን በርከት ብለናል፡፡
“ምን ሆነህ ነው የምትወራጨው?”
“እዚህ ሀገር ህግ አይከበርም ማለት ነው!”
“ምን አደረጉህ?”
“እኔ ከጠዋት ጀምሬ ስጠብቅ ቆይቼ  በእኔ ተራ ሌላ ሰው አያስገቡ መሰለህ!”
ቆይማ…አንተስ በቀደም ያለተራህ መብራት ጥሰህ ስታልፍ አይደል እንዴ መንገዷን ጠብቃ ስትሄድ የነበረችውን ያቺን ብርጭቆ የመሰለች የእሷዬዋን መኪና ቆሼ የተገኘች ጣሳ ያስመሰልካት! እናማ...ምነው ያን እለት “እያየሽ አትሄጂም!” ብለህ እሷዬዋ ላይ ስትጮህ የነበርከው አንተ አልነበርክም እንዴ! ምነው ‘ህግ’ የሚለው ቃል ያኔ ተረስቶህ አሁን ትዝ አለህ?
ደግሞላችሁ…አለ አይደል… ህጎች ከወጡ  የሆኑ እነኛን ህጎች የማስከበር ሀላፊነት የሚጣልባቸው ከፍሎች ይኖራሉ። እናማ…ማስክ የማድረጉንና ተያያዥ ህጎች መከበራቸውን የሚቆጣጠሩ የትኞቹ ክፍሎች ናቸው! ግራ ስለገባን ነው፡፡ በሌሎች ሀገራት እንደምንሰማው እኮ አንድ ህግ ከወጣ በኋላ ወለም ዘለም የለም! ወይ ማክበር ነው፣ ወይ ጦሱን መቻል ነው፡፡
እናማ... “ባደርግ ባላደርግ፣ ምን አገባህ!” በሚል ሀገር የትም አትደርስም፣ የሥልጣኔ ምልክትም አይደለም ለማለት ያህል ነው፡፡ “ህግ ኬሬዳሽ!” ስልጣኔ አይደለም፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1300 times