Saturday, 18 September 2021 16:58

አበበና ጃፓናዊው ጫማ ሰሪ ኦኒቱስካ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 በዓለም አትሌቲክስ Super shoes የሚል ስያሜ ያገኙት የመሮጫ ጫማዎች በሳይንሳዊ መንገድ የሶላቸው ውፍረት የጨመረ፤ ለአሯሯጥ የሚመቹ፤ ፤ ቅለት ያላቸውና የሚተጣጠፉ እና የሯጮችን ብቃት የሚያግዙ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ በቴክኖሎጂ የላቁ እና የረቀቁ መሮጫ ጫማዎችን ለሯጮች በማምረትን ፈሩን የቀደደው የአሜሪካው Nike  ሲሆን Adidas ፣ Puma ፣ New Balance እና Saucony …  በየራሳቸው ምርቶች  የዓለምን አትሌቲክስ እየቀየሩት መጥተዋል፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው ለታላቁ የዓለማችን የማራቶን አትሌት አበበ ቢቂላ የመሮጫ ጫማ ስለሰሩት ጃፓናዊ ኦኒቱስካ የሚያስተዋውቅ ታሪክ ነው፡፡

          በ1960 እኤአ ላይ በተካሄደው የሮም ኦሎምፒክ አበበ ቢቂላ በማራቶን ውድድር ላይ አዲስ የመሮጫ ጫማዎች ቢሰጡትም  ስላልተስማማው በባዶ እግሩ ውድድሩን አድርጎ የዓለምን የማራቶን ሪከርድን በመስበር ለኢትዮጵያና አፍሪካ በታሪክ የመጀመርያውን የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳልያ ተጎናፀፈ፡፡
ከዓመት በኋላ በጃፓኗ ከተማ ኦሰካ ላይ በተዘጋጀው  የመያንቺ ማራቶን  ላይ ተጋበዘ። ጃፓናውያን ለአበበ አቀባበል ያደረጉለት እንደታዋቂ የሮክ ሙዚቀኛ ሲሆን፤ በአካል  ለመገናኘት እና አብረውት ፎቶ ለመነሳት  ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ በተለይ  ኪቻቺሮ ኦኒቱስካ ከአበበ ቢቂላን በአካል መገናኘት ብቻ ሳይሆን  በእጆቻቸው ባዶ እግሩን የመደባበስ እቅድ ነበራቸው፡፡ በበርሊን ኦሎምፒክ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ታዋቂ በነበረው ኮሂ ማውርኩሶ የተባለ ኦሎምፒያን አማካኝነት  ኪቻቺሮ ኦኒትሱካ ከአበበ ጋር  የመገናኘት እድሉን አገኙ፡፡ ቲም ጁዳህ በፃፈው Bikila – Ethiopia’s Barefoot Olympian የተባለ  መፅሃፍ እንደተረከው ኦኒትሱካና አበበ ያደረጉት ምልልስ ይህን ይመስላል
ኦኒትሱካ -  ‹‹የመጣሁት ለድጋፍና  ጫማዎችን ለመስጠት ነው። በጫማዎቼ ውድድርህን እንደምታሸንፍ ተስፋ አደርጋለሁ።››
አበበ - ‹‹እኔ ሁልጊዜ ባዶ እግሬን ነው የምሮጠው፤ ብዙ ጊዜም አሸንፌያለሁ። ጫማ አያስፈልገኝም።››
ኦኒትሱካ - ‹‹የጃፓን መንገዶች አስቸጋሪና  ሸካራ ናቸው፡፡ ስለዚህ ጫማ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡››
አበበ - ‹‹መንገዶቹ አስቸጋሪ ሊሆኑ ይችላሉ ግን ጫማ አያስፈልገኝም።››
ኦኒትሱካ - ‹‹ባዶ እግሮችህ በጣም ጥሩ ናቸው፣  የድመት መዳፎች ይመስላሉ። ግን አሁንም በጫማ  በመሮጥ ሪኮርዶችን ማሻሻል ይቻላል፡፡››
Bikila – Ethiopia’s Barefoot Olympian በተባለው መፅሃፍ እንደተወሳው  ኦኒቱስካ ባዶ እግርን መሮጥ ለጉዳት እንደሚያጋልጥና የመሮጫ ጫማ መሬት ይዞ ለመሮጥ እንደሚያመች  ለማሳመን  ጥረት  አድርገዋል፡፡ ሻምበል ኦኒ  ኒስካነን በበኩላቸው አበበ በመየንቺ ማራቶን   ላይ ባዶ እግሩ እንዲሮጥ ባለመፈለጋቸው በጫማ መወዳደሩ ጥሩ ሀሳብ ሊሆን እንደሚችል  ምክር ሰጡት፡፡  በመጨረሻም አበበ ቢቂላ Onitsuka Tiger  መሮጫ ጫማ አድርጎ የማራቶን ውድድሩን በቀላሉ አሸነፈ፡፡
ኪቻቺሮኦኒትሱካ  ከጃፓን አንጋፋ የጫማ ኩባንያዎች አንዱ የሆነውን  አሲስ የሚባል የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያን የመሰረቱ ናቸው፡፡
ከሦስት ዓመታት በኋላ አበበ ቢቂላ በ1964 እኤአ ቶኪዮ ላይ በማራቶን ለሁለተኛ ጊዜ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ አሸነፈ፡፡ የሮጠው በኦኒትሱካ ጫማዎች አልነበረም፡፡  ‹‹ፑማ ኦሳካ›› PUMA osaka በተባለ የመሮጫ ጫማዎች ነበር። በሮም ኦሎምፒክ ባዶ እግሩን ካስመዘገበው የዓለም ሪከርድ በሦስት ደቂቃዎች በፍጥነት 42.295 ኪሎ ሜትር መጨረስ ችሏል።

Read 3284 times