Print this page
Saturday, 18 September 2021 17:08

ፕሬዚዳንቱን በመግደል የተጠረጠሩት የሃይቲ ጠ/ ሚኒስትር ከአገር እንዳይወጡ ታግደዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የቀድሞው የአንጎላ መሪ ከ30 ወራት ስደት በኋላ ወደ አገራቸው ተመለሱ

           ባለፈው ሃምሌ ወር በተፈጸመው የሃይቲ ፕሬዚዳንት ጆቬኔል ሞሴ ግድያ የተጠረጠሩት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪየል ሄንሪ ከአገር እንዳይወጡ እገዳ እንደተጣለባቸው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
በፕሬዚዳንቱ ግድያ እጃቸው እንዳለበት ተጠርጥረው ምርመራ እየተደረገባቸው የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪየል ሄንሪ፣ ከዋነኛው የወንጀሉ ተጠርጣሪ ፊሊክስ ባዲዮ ጋር ስላላቸው ግንኙነት ማብራሪያ እንዲሰጡ በአገሪቱ አቃቤ ህግ በቀረበላቸው ጥያቄ መሰረት ባለፈው ሰኞ በሰጡት ምላሽ ከባዲዮ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸውና ሰውዬውን እንደማያውቁት መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
አቃቤ ህግ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሬዚዳንቱ ግድያ ከሰዓታት በኋላ በገዳይነት ከተጠረጠረው ፊሊክስ ባዲዮ ጋር በስልክ ተደዋውለው እንዳወጉ መረጃ እንዳለው በመጥቀስ ክስ ሊመሰርትባቸው ማሰቡን የጠቆመው ዘገባው፣ እሳቸው ግን የቀረበባቸውን ክስ እንደማይቀበሉት መግለጻቸውን አብራርቷል፡፡
የሃይቲው ፕሬዚዳንት ጆቬኔል ሞሴ ከአንድ ወር በፊት መኖሪያ ቤታቸውን ሰብረው በገቡ የታጠቁ ግለሰቦች በተከፈተባቸው ተኩስ እንደተገደሉና ቀዳማዊት እመቤቷም በተፈጸመባቸው ጥቃት የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከግድያው ጋር በተያያዘ 44 ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ አንጎላን ለ40 አመታት ያህል ያስተዳደሩትና ከአራት አመታት በፊት ከስልጣን የወረዱት የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆሴ ኤድዋርዶ ዶስ ሳንቶስ ከ30 ወራት ስደት በኋላ ባለፈው ማክሰኞ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ዶስ ሳንቶስ እ.ኤ.አ ከ2019 ሚያዝያ ወር አንስቶ በስፔን ባርሴሎና በስደት ላይ እንደነበሩ ያስታወሰው ዘገባው፣ የአፍሪካ ቁጥር አንድ ሴት ቢሊየነር የሆኑት ልጃቸው ኤልሳቤጥ ዶስ ሳንቶስ በከፍተኛ ሙስና ተጠርጥረው ንብረታቸው እንደተወረሰና ወንድ ልጃቸው ጆሴ ፊሎሜኖ ዶስ ሳንቶስ ደግሞ ከመንግስት 500 ሚሊዮን ዶላር ሃብት በመመዝበር የ5 አመታት እስር እንደተፈረደባቸውም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1089 times
Administrator

Latest from Administrator