Wednesday, 22 September 2021 00:00

አዲስ የድርድር መንገድ መያዝ ያስፈልጋል

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 የግብፅ የሕዝብ ብዛት 104 ሚሊዮን ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ደግሞ ከ110 ሚሊዮን አልፏል። ከዘጠና ስምንት  ከመቶ የማያንሰው የግብፅ ሕዝብ የንፁህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሲሆን፣ ንጹህ የውሃ መጠጥ የሚያገኝ ኢትዮጵያዊ ሃምሳ ከመቶ መድረሱ ያጠራጥራል። ግብፃዊያን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ የመብራት ኃይል ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ ከስልሳ በመቶ በላይ ኢትዮጵያዊያን ግን የኤሌክትሪክ ብርሃን ለማግኘት ዛሬም እንደጓጉ ናቸው፡፡
ግብፃውያን ንፅህናቸውን የጠበቁ የበዙ ከተሞች ባለቤቶች ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያ ግን የዋና ከተማዋን የአዲስ አበባን  ንፅህና መጠበቅ ተቸግራለች፡፡ ግብፃዊያን በምግብ ራሳቸውን ከመቻላቸውም በላይ ከዓለም ከፍተኛ የፍራፍሬ አምራች አገሮች አንዱ ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያውያን ግን ሙሉ በሙሉ የምግብ ፍላጎታቸውን ማርካት አልቻሉም። ይባስ ብሎም በየዓመቱ ከ6 ሚሊዮን ያላነሰ ህዝባቸው የእለት ከእለት ደራሽ እርዳታ እየጠበቀ ነው። ስለዚህም መልማት ለኢትዮጵያ ግዴታ እንጂ ምርጫ አይደለም።
በቅርቡ በጣና አካባቢ ኢትዮጵያ የመስኖ እርሻ ለመጀመር መነሳቷ በግብጾች ዘንድ ጩኸት አስነስቷል፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያውን ሃይል የማመንጨት ተግባር በመጪው ጥቅምትና ህዳር ወር 2014 ዓ.ም እንደሚጀምር መገለጹ የግብጾችንና የሱዳኖችን ጩኸት በብዙ እጥፍ እንዲጨምር አድርጎታል። ከአረብ ሊግ አባል ሀገሮች አንዷ የሆነችው ቱኒዝያ፣ ኢትዮጵያ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ውሃ አሞላልና አስተዳደር ላይ “አሳሪና አስገዳጅ” ውል እንድትፈርም የሚገፋፋ የውሳኔ ሃሳብ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ም/ቤት ለማቅረብ ያነሳሳት ይህ ነው። በአንፃሩ ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ የሚገኙ የጸጥታው ም/ቤት አባል የሆኑ አገሮች አምባሳደሮችን ሰብስባ፣ ቱኒዝያ ያቀረበችውን አድሎአዊ የሆነ የውሳኔ ሃሳብ እንዳይቀበሉ አጥብቃ ጠይቃለች።
የግብፅ የመገናኛ ብዙኃን ያለፈውን አንድ ወር ያሳለፉት በኢትዮጵያ ላይ መአት በመመኘት ነበር። የኢትዮጵያን ካርታ ዘርግተው ይህ አካባቢ ሰኞ፣ ያኛው ማክሰኞ ይገነጠላል፤ ያኛው ደግሞ ከአርብ አያልፍም አትጠራጠሩ፤ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች እያሉም በድፍረት ተናግረዋል።
በአገር ቤት ጌታቸው ረዳ “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ እንወርዳለን” በማለትም አደፋፍሯቸዋል። ይሁን እንጂ የጌታቸው ፉከራ፣ ኢትዮጵያዊያንን ከዳር እስከ ዳር ወደ አንድ ዓላማ የሚጠራ ሆኖ በማረፉ፣ ትበተናለች የተባለችው ኢትዮጵያ የበለጠ ወደ አንድነት ተሰባስባ ተጠናክራለች። ተበትነው የራሳቸውን ግዛት ይመሰርታሉ ተብለው በግብፅ መገናኛ ብዙኃን ታሪካቸው የተተነተነላቸው ክልሎች “እኛ እያለን ኢትዮጵያ አትፈርስም” በማለት የሚሊሽያና የልዩ ኃይል ሰራዊታቸውን በአፋርና አማራ ክልል ወደ ተከፈቱ የጦር ግንባሮች በማዝመት የጠላትን እንጥል ቆርጠውታል።
የአማራ ሚሊሽያ ልዩ ኃይል ብቻ ሳይሆን የኦሮሚያ ክልል ሚሊሽያና ልዩ ኃይል፣ የሶማሌ ሚሊሽያና ልዩ ኃይል ወዘተ ከመከላከያ ጎን በግንባር ገብተው ጠላትን መፋለም ጀመሩ፡፡ የታለመው  መከፋፈል ቀርቶ መቁሰልና መሞት የጋራ ተግባር እየሆነ መጣ። ይህ ጊዜ የኢትዮጵያን በአገርነት ፀንታ መኖርን በማይፈልጉት ዘንድ ያልታሰበ መደናገጥን ፈጠረ። ግብፅና ሱዳን ብቻ ሳይሆኑ ከእነሱም ጀርባ ያሉ ተቸገሩ።
አሸባሪው ህወኃት  በወልቃይት  ጠገዴ በኩል ወደ ሱዳን ለመውጣት፣ በአፋር ግንባር የአዲስ አበባ ጂቡቲን የንግድ መስመር በመቆጣጠር በኢትዮጵያን መንግሥት ላይ ጫናን ለመፍጠር፣  በወልዲያ ግንባር ደሴን በመያዝ ወደ አዲስ አበባ ለመዝለቅ አስቦ የከፈታቸው ጦርነቶች፣ በየአካባቢው ነዋሪዎች  ላይ የከፋ ጉዳት ቢያስከትሉም፣ ከፈለጉት ግብ ሳይደርስ መቅረቱ የደጋፊዎቹንም ተስፋ ውሃ ቸልሶበታል።
ይህ በዚህ እንዳለ ኢትዮጵያ በመጪው ሃያ ዓመታት 15 በውሃ፣ 24 በነፋስ፣ 17 በጂኦተርማል እና 14 በፀሐይ ብርሃን የሃይል ማመንጫ ሥራ የሚሰሩ ጣቢያዎች በአርባ ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለመሥራት ማሰቧን መናገሯና ቱኒዚያ ለጸጥታው ም/ቤት የውሳኔ ሃሳብ ማቅረቧ ተደምሮ ሲታይ ሁለቱ ሃገሮች ወደ ድርድር ለመመለስ ምክንያት እየፈለጉ ስለመሆኑ አመላካች ነው ማለት ይቻላል።
ኢትዮጵያ ወደ ድርድሩ ስትመለስ ግን በነበረውና በቆየው መንገድ መሆን የለበትም። የግብፅና የሱዳን የውሃ ችግር መፍትሔ በሁለቱም አገሮች እጅ መሆኑን  በማስረጃ አስደግፋ ለእነሱና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳየት መቻል አለባት። እኛ ለመልማት እንፈልጋለን በማለት ልትለማመጣቸው አያስፈልግም። ኢትዮጵያ ማለት ያለባት “ውሃው የኔ ነው፤ እናንተ በተጠቃሚ ወንበር ላይ ቆማችሁ  ጠይቁኝ” ነው።

Read 9533 times