Monday, 20 September 2021 16:41

ከዲያቢሎስ ጋር መደነስ

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ (singofbird@gmail.com)
Rate this item
(1 Vote)


              ሦስት ወደ ቀኝ
ሀ- ውበት እና መለኮት
‹‹የእግዜሩ ውብ በመሆንሽ ውበትሽ አዕላፋትን ከተንኮል ወደ ቅንነት ጠራ። እንቢተኞችን እንኳ አስገደደ፡፡ ከዚህ ሁሉ ያመለጠ ባንቺ ውበት ተስቦ ቅንነትን ያልተማረ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ውቅያኖስ ተጣለ፡፡›› ግፋወሰን አክሎግ ገጽ 78
*   *   *
ጥራዟ ለዓይን አትሞላም፡፡ ግን መስመር በመስመር የሚተነኩሱ ቃለ ፍላጻዎችን ተሸክማለች፡፡ ነገርየው የአንድ ዘመን እንጉርጉሮ ነው፡፡ በቀያይ መጻሕፍት መፈከር ያበደ የአንድ ሙሉ ትውልድ የአመሻሽ መድሞንሞን ያሰለቻቸው ጥቂት የስክነት በይበልጥም የውበት አሳሾች ትርጉም ላለው ቅኝት እረፍትን ይሽቱ ዘንድ የእሳት ራትን እንደሚስብ ብርሃን መግነጢስ በሆነቻቸው ሴት ዙሪያ ተኮለኮሉ፡፡
‹‹ሦራዬ አጭር ዕድሜዬ እጄ ብዙ ቦታ ገብቷል፡፡ አንዳንዱን ነግሬሻለሁ። [...] ለምሳሌ አንድ ሰሞን የተማሪዎች የዕቃ ዕቃ ጨዋታ ውስጥ ገብቼ ነበር፡፡ በመጀመሪያ አጨበጨቡልኝ፡፡ በመጨረሻ አጨበጨቡብኝ፡፡ [...] እኔም እንዲሁም ከምወደው ሰላማዊና ነጻ ሕይወቴ ተስፈንጥሬ (አገባቤ በድንገት ነው) ከዚህ የሞራል ሰዎች ምሬት እንጂ ደስታን ከማይዝቁበት የፖለቲካ ዓለም ምን ዘፈቀኝ፡፡›› ደረጄ ደስታ፣ ገጽ 56
ሁሉም ግንኙነቶች እንደ ቀልድ እንደ ጨዋታ የተጀመሩ ይመስላል፡፡ ቀልዱ እንደ ደራሽ የሚያባብል ነበር፡፡ ከያኒያኑ በዝብርቅርቅ የጊዜ አሰላለፍ፣ በተጠናገረ አንዳንዴ በሚላተም፣ በሚተላለፍ ጥብቅ መሻት ደብዳቤዎችን ሲያቀባብሉ ለውበት በመማለል በተስፋ ጀምረው በብስጭት፣ በተስፋ ማጣት (desperation) አጠናቀቁ። ምናልባት የውበትን እንደ ወይን ያለ የሚያደናብዥ ስካር መቋቋም አልቻሉም። ከየተሸጎረበት ጥጋት ተጠራርቶ ወጥቶ ለፍሙ፣ ለትንታጉ፣ ለነበልባሉ፣ የውበት፣ የውጋገን መግነጢስ የሚደንሰው፣ የእሳት ላንቃ የሚልሰው የእሳት ራቱስ ዕጣ ከዚህ የተለየ ነውን?
የእነኝህ ደብዳቤዎች ደራሲያን ከዘመን ስካር በርግገው በዚህችው የኪነት ዛር (muse) ዙሪያ ተኮልኩለው የፈጠሩት የግንኙነት ጥምርታ ውትብትብ ነው፡፡ የአንዱ ከሌላው የማይገጥም፣ የሚተላለፍ፣ የሚጣረስ... ግን ደግሞ በነፍስ ግለት የተሸመኑ... የግንኙነቶቹ ውትብታብ ይህንን መጽሐፍ የማንበቢያ ጥቂት ንሸጣዎች ለማቀበል ለሚመኝ የእኔ ቢጤ የመፍገምገሙን፣ የመላጋቱን ጥልቀት መትሮ ለመበየን፣ ለመከየን ፈታኝ ያደርገዋል፡፡ …በእርግጥስ ግን ይሄ ሁሉ መቃተት በዓይን ብቻ ለሚገባ ተሰባሪ ጉንቁል ጥላ (አካላዊ ውበት) ብቻ የሚቀርብ መስዋዕት ነበርን? ሌላ በዓይን ደንብሮ በነፍስ የሚዳሰስ ረቂቅ የውበት ዳንኪራ ጥሪ ሊኖረው ይገባል እኮ፡፡ ውበት ከማየት ብቻ አይደለምና፡፡      
ለመሆኑ ውበት ስንል ምን ማለታችን ነው?
በበኩሌ ዓለምን፣ ሕይወትን በቅጡ ለመረዳት ሁለት እንደ ተራ የምንቆጥራቸው ቃላት እጅጉን ጠቃሚ ይመስሉኛል፡፡ ውበትና ፍርሃት… መልካም ነገሮች ሁሉ ውበት በምንለው ንፍቅ ውስጥ የሚዟዟሩ ትውራን ሲሆኑ፣ በአንጻሩ ፍርሃት የጥርጣሬ፣ የንፍገት፣ የስስት፣ የበቀል፣ የክፉ ነገሮች ምንጭ ነው፡፡ ፍርሃታችን ከምን ይመነጫል? ከጉድለታችን ነዋ! እኛ እኮ የሁሉም ነገር ውስንነት ያለብን ፍጥረቶችን ነን...  ምንም ነገር በእጃችን ሳይኖረን ሁሉም ነገር እንዳለን የምናስመስል ድኩማን...  
ፍርሃታችን ከዚህ የውስንነት ልምሻ ይመነጫል፡፡ ፍርሃት በጊዜያት ክፍልፋይ ሁነት የሚከወን አጥበርባሪ ክስተት ሲሆን ውበት ግን ከዘመን በላይ ነው፡፡ ፍርሃት ከመለኮቱ ጋር እንዳንደንስ ከዘለዓለማዊዋ የሕይወት ምንጭ እንዳንቃመስ ብቸኛ ደንቃራችን ነው፡፡ ውበት ግን ከዚህ እስራት ፈጽሞ ነጻ የምታወጣን የነፍስ ማደሪያ ሥፍራ፣ ሙዳይ ነች፡፡  
ውበት በቅርጽ፣ በቀለም፣ በምት(rythm)፣ በሥርዓት(order)፣ በቅጥ(pattern)፣ በወጋወግ፣ በይትብሃል(style)፣ በዝማሬ፣ በትይዩነት(parallalism)፣ በእንቅስቃሴ… የሚገለጽ የሚታይ፣ የማይሆን፣ የማይታሰበውን ሁሉ የሚጠቀልል ጥልቅና ጽንፍየለሽ(deep and vast) ሀሳብ ነው። ውበት በገል ስባሪ ላይ በምትኖር ትል ንቅናቄ እንኳን ሊገለጥ ይችላል፡፡ ሰሎሞን ደሬሳ ለ‹ልጅነት› የግጥም መድበሉ በጻፋት አጭር መግቢያ ላይ ስለ ውበት ያለንን አረዳድ የምታጎላ የሆነች ሀሳብ ሰንዝሯል፡፡
‹‹በልጅነት ብስክሌት መጋለብ የሚጥመው ከእግር ስለሚያፈጥንና በችኮላ የሚደረስበት አድራሻ ስለአለ ሳይሆን ውበትን ማሳደድ (ቅርጽን ማሳደድ) ራሱ መድረሻ ስለሆነ ነው። ውበቱ የብስክሊቷ ወደ ጎን ሳትወድቅ ቀጥ ብላ መንጎድ ነው፡፡›› በበኩሌ በምንኖርበት ጽንፈ ዓለም ውስጥ የውበትን ያህል እጅጉን የተትረፈረፈ (superabundant) መኖሩን እጠራጠራለሁ፡፡
ውበት ይለወጣል እንጂ አይከስምም፤ አይጠፋም፡፡ በየቅጽበታቱ ከቅጠሏ መጠውለግ ጋር አብሮ ከንቱነትን የሚላተም፣ ከንቱነትን  የሚስም ውበት ቢኖርም ቅሉ ከስሞ አይቀርም፡፡ ከተፈጥሮ የማያቋርጥ እርግብግቢት ጋር ዘወትር በታደሰ፣ በተለወጠ ቅኝት እንደገና ይነሳል። ውበትን ውበት ይጠራዋል፡፡ ያሻግረዋል (transcend) ...ማሻገር ዘሩን ቡቃያ፣ ቡቃያውን ዘር ማድረግ ሊሆን ይችላል። ይህን በመሰለ ሂደት ተፈጥሮ የሰው ልጅ ጣልቃ ገብነት ሳያስፈልጋት ራሷን ችላ ስትር ብላ ሽግግሩን ትከውነዋለች፡፡
ውበትን ከድንጋጌ (principle) ይልቅ ሥልት፣ ቅጥ (pattern) ይገዛዋል። ከመታዘዝ ይልቅ ማፈንገጥ፣ መጋፈጥ፣ መጋለጥ (Expose to danger) ያበለጽገዋል። ውበት ከመምሰል፣ ከመመሳሰል አይደለም። ከመለየት፣ ከማመጽ፣ ከሕመም እንጂ... ውበት ይገለጣል (reveal) እንጂ አይፈጠርም… መፍጠር የእኛ አይደለም። ምንም ነገር የእኛ አይደለም፡፡  አልቦ ሕልውና ራሱ የእኛ አይደለም… እኛ እኮ ከነጻ ፈቃዳችን ውጪ ምንም ነን፡፡
ውበት እውነት ነው፤ ቅጥ ነው፤ ፍቅር ነው፤ ውበት ሕመምም ነው፡፡ beauty is pain እንዲል ምድረ ሞኛሞኝ ፈረንጅ... ውበት አይቆጠርም፣ አይሰፈርም… በነፍስ መሻት እስከተያዘ፣ ለርካሽ ዓላማ እስካላሰገሩት፣ የዚህኛው ከዚያኛው አይበልጥም፤ አያንስም። ማንም ውበትን መበየን አይችልም፡፡ በጽንፍ የለሽነቱ መጥበርበር እንጂ... በአጭሩ ለእኛ በሚገባን ውስን የቋንቋ አቅም ተቀንብቦ ሲቀርብ ውበት ከመለኮቱ ጋር የመግባባት ቋንቋ ነው፡፡
ውበት ተፈጥሮ ራሱ ነው፡፡ የተፈጥሮ ሂደት ሥሩ ክፋት ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲያውም ውበት፣ ህብር ነው:: ሆኖም የተፈጥሮ ሂደት በቀኝም በግራም ለተሰለፈው የድርጎውን ሲቸር ምህረት የለሽ መሆኑ እሙን ነው። መሞት ካለብህ በናዳ ተጨፍልቀህ ሆነ በደራሽ ጎርፍ ተደፍቀህ ትሞታታለህ፡፡ ለዚህ ምንም ማመንታት የለም፡፡ ክስመቱ ራሱ የውበቱ መገለጥ፣ መለወጥ አካል ነውና፡፡ ለነገሩ ሞት ራሱ ቦቅቧቃ ሆነህ ካላሰብከው ምንም የሚያስፈራ ገጽ የለውም፡፡ Arabian night ላይ ይህንን ሀሳብ የምታጠናክርልኝ የወደድኳት ኢስላማዊ ጥቅስ አንብቤያለሁ። ‹‹መልዓከ ሞት ሲመጣ የሚያብረከርክ ነው። ሲይዝህ ግን የሚያፍነከንክ...›› የምትል፡፡ ይቻትላችሁ እንግሊዝኛዋ ‹‹When the angel of death comes, it is terrible.  When he has reached you, it is bliss.››
እናም ዙሪያህን ከከበህ ከዚህ ሁሉ የውበት ንኝት ቅንነትን መማር ከተሳነህ፣ የወፍጮ ድንጋይ በአንገትህ ታስሮ ውቅያኖስ እንድትጣል ‹በወንጌል› ተጽፎብሃል፡፡
ለ - ውበትና መለኮት ምንና ምን?
‹‹እንዳላመልክሽ ሰው ነሽ ይባላል። እንዳልተውሽ አንቺን ያላመለኩ ማንን አመልካለሁ? ባታመልክ ቢቀርስ እንዳትይኝ ደሞ ‹‹አምልክ - አምልክ›› ይለኛል፤ ተምበርክከህ ሽቅብ ተመልከት ይለኛል፡፡ አጠገቤ ያለሽው አንቺው ከሆንሽ፡፡... አንቺን መውደድን ያህል ቀላል ነገር አንቺን ማወቅን ያህል ከባድ ነገር ... እንዲያውም አንቺን መውደድ ያለ ነው። አንቺን ማወቅ ግን የለም፡፡ አንቺን ማወቅ ክልክል ስለሆነ ወደ ማመሳሰል እንሂድ - አንቺና - ‹‹0shane›› አንቺና ኢየሱስ ነፍሴ ... እንኳን ማለቂያ መጀመሪያ የለሽም፡፡ ለእኔ ዘለዓለሜ ነሽ። እና ማን ትሆኚ?›› ስብሃት ገብረእግዚአብሔር፤ ገጽ 15
‹‹የነካችውን ብነካ ከለምጼ እፈወሳለሁ!... አፍልቄ የጻፍኩት ሁሉ የእርሷ ነው፡፡ በልቤ ያሰብኩትም!›› ባሴ ሀብቴ
‹‹ሦራዬ አስር ጊዜ ደስ ይላል የምልሽ ሌላ ቃል ስላጣሁ ወይም ስለማላውቅ ነው፡፡ ብዙ ቃላትና ሥያሜ ያጡ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ስላሳየሽኝ ውብ (ቃሉን ልብ እያልሽልኝ) ሥዕሎች ምን ማለት እችላለሁ? አላውቅም። ይህ ደግሞ አስገድሎ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ሦራዬ ይሄን ውበት ለመግለጽ እኔ ቃል የለኝም፡፡ ያላቸው ጋ ውሰጂው። ሕሊናን ለመግለጽ ሕሊና አያስፈልግም። ከሕሊና በላይ እንጂ! ያ ደግሞ ያ ነው፡፡ ያ ባናውቀውም በግምት የምንስማማበት እግዚአብሔር ነው፡፡››  ደረጀ ደስታ
***
በጠቅላላው የውበትን ነገረ ሰበዝ ሳነሳ ስለሴት ልጅ ዳሌና ከንፈር ብቻ እያወራሁ እንዳልሆነ ከላይ ባቀረብኩት ሀተታ አንባቢዬ የሚረዳው ይመስለኛል፡፡ ውበት ግን ከመለኮቱ ጋር የምንግባባበት ቋንቋ ብቻ አይደለም፡፡ ራሱ መለኮቱ ነው፡፡ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር፣ ባሴ ሀብቴ፣ ደረጀ ደስታ የመሳሰሉ ደብዳቤዎቻቸው በዚህች ጥራዝ የተካተቱላቸው ደራሲያን ለኪነት እና ለፍቅር ጣዖቷ ስንዱ በጻፉላት ደብዳቤዎች ላይ  የውበትን ጫፉን፣ ጥጉን ወይ ምልዓቱን ለመዳሰስ፣ ለመድረስ በቃላት ባደረጉት መንጠራወዝ፣ የውበት ሰለባ የመጨረሻ መድረሻ አምልኮ መሆኑን አሳይተውናል። በመጽሐፉ ውስጥ የውበት ጣዖቷ ስንዱ ምልዓቱን ለመጨበጥ ለታጨ የተሻገረ ‹ኢሰንስ› ተመልምላ ከስነ ተረቷ ሻህራድ እስከ ስነ አምልኮው ኢየሱስ ትዛመዳለች።  ስብሃት እንዲያውም በአንድ ደብዳቤው ላይ ‹‹አሁን እንግዲህ የቅዱስ ሚካኤልን ስም ትቼ በቅዱስ ስንዱ ስም መማል ልጀምር ነው፡፡›› ይላል፡፡ ቅድስና፣ አምልኮት፣ ከደዌ የመፈወስ ኃይል የመሳሰሉ ከላይ ለማሳያ በመዘዝኳቸው ጥቅሶች ውስጥ የተኳሉ መገለጦች በአንድም በሌላ የመለኮቱ ወይም በመለኮቱ ብቻ የሚቸሩ ጸጋዎች ናቸው፡፡
ፊዮዶር ደስታየቭስኪ The Idiot በተሰኘ መጽሐፉ ላይ የሰነዘራት ‹‹beauty will save the world›› የምትል በብዙ ያነጋገረች አባባል አለችው፡፡ የሀገሩ ልጅ ሶልጀንስታይን እ.ኤ.አ በ1970 የኖቤል ሽልማቱን ሲቀበል ይህችን ጥቅስ እንደ መነሻ ተጠቅሞ ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፡- ‹‹Dostoevsky’s remark, ‹beauty will save the world› was not a careless phrase but a prophecy. After all he was granted to see much,  a man of fantastic illumination. And in that case Art can, literature might really be able to help the world today››   
የመካከለኛው ዘመን የፈረንሳይ ፈላስፋ Peter Abelard 1079-1142 እ.ኤ.አ)  በበኩሉ፤ ‹‹Mankind yearning for God and God yearning for mankind met in compassionate at the cross.›› ይላል፡፡ ሰው እና እግዜር በጥብቅ፣ በናፍቆት ሲፈላለጉ በክርስቶስ መከራ መስቀል ላይ ተገናኙ እንደማለት... እናስ እርቁ ውበት አልነበረምን? ለዚያውም የስነ መለኮትን አረዳድ በብዙ የቀየረ የውበት መንገድ... በእርግጥም በክርስቶስ ለሚያምን ሁሉ የክርስቶስ ደምግባቱ፣ ወዘናው፣ የክርስቶስ ክርስቶስነቱ በሚገባ የተገለጠው ቀራኒዮ አደባባይ በመስቀሉ ሕማም ነበር ብሎ ማለት ስሜት አይሰጥምን? በእርግጥስ ጅራፉ ፊደል አልነበረምን?
ኬ.ኤም. ጆርጅ The silent roots - orthodox perspectives on Christian spirituality በተሰኘች ሚጢጢ ግን ጣፋጭ መጽሐፉ ላይ  ሀሳባችንን የሚያጠናክር ሌላ አስደናቂ አስተውሎት ሰንዝሯል፡፡
‹‹The final judgment is a discernment of beauty. The Christian tradition has seen beauty and holiness as identical and the ‹‹image›› of God as key to both. This image in us by its very nature calls us to undertake a pilgrimage to the source of beauty and holiness in God.››  
እናስ የደስታየቭስኪ ዓለምን መታደግ የሚቻለው ውበት መለኮቱ ራሱ ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? እግዜርን እንደ አንባገነን ንጉሥ ካሰብነው በእርግጥ ያኔ የውበትን ዘፍጥረት ለመረዳት ፍንጭ እንኳን የለንም ማለት ነው፡፡  እግዜርና ውበት በምልዓተ ዓለሙ ጽንፍ የለሽ ሰሌዳ ላይ የሚደንስ የምልዓት እርግብግቢት ሹረት ተለዋዋጭ ስሞች (ምናልባትም መልኮች) ናቸው፡፡ ይህ የምልዓት ክንውን የአንድነት መተሳሰሩ ይደንቃል፡፡ በመተሳሰሩ ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌለው ዓይነተ ዓይነትነት (variety) ራሱን ያቀርባል፡፡ ገር፣ ገበርባራ፣ ስጉጥጉጥ፣ ዘርዛራ፣ ጭርንቁስ፣ ጭርንቡስ፣ ጭፍግግ፣ ግፍጭጭ... እንዲህም ሁሉ ሆኖ ግን ውብ፡፡
ማንም የምልዓተ ዓለሙን የምልዓት የእርግብግቢት ክንውን በመቅኖ ቢስ ቃላት ጥርቅም ሊያመሰጥረው አይችልም፡፡ ጥቂቷን ነገር ብቻ መግለጽ ይችል ይሆናል... ‹‹ያለ እና የሚኖር እኔ ነኝ›› ብሎ ማለት ከጥቂቶቹ ጥቂቱ ቢሆን ነው፡፡ ቅዱሳቱ መጻሕፍት ከጥቂቶቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ይህ የምልዓት ክንውን ግን የማይታወቅ፣ የማይነገር ነው፤ ውበት ነው፤ እግዜሩ ራሱ ነው፡፡ እኔም የዚህ የምልዓት ክንውን አካል ነኝ፡፡ ለምልዓት ክንውኑ አካል ፍንጣቂ ውበት ነኝ፡፡ መለኮቱን የመሆን ሳይሆን፣ መለኮቱን የማከል ስንኩል አቅም (potentiality) የተቸረኝ የእግዜሩ መልክ ነኝ፡፡
መለኮቱ በእያንዳንዱ የውበት ፈርጅ ውስጥ ራሱ ይገልጣል፡፡ ይህች ተረትነት የሚታከካት ታሪክ ነገረ ሀቲታችን ማጣፈጫ ልትሆን ትችላለች፡፡ ሰውየው የታወቀ የዜን መምህር ነው፡፡ የሆነ ቀን መገለጥን የሚሹ በርካታ ደቀ መዛሙርቱ ከአትሮኖሱ ስር በእርጋታ ተቀምጠው ቃለ ስብከቱን (ምናልባት ትምህርቱን) ለመስማት እየተጠባበቁ ነበር። መምህሩ በተረጋጋ መንፈስ ወደ ማስተማሪያ መድረኩ ሲወጣ ግን በዛፉ አናት ላይ ያረፈች መንገደኛ ወፍ ደጋግማ ደጋግማ ዘመረችና በረረች፡፡ መምህሩም አለ... ‹‹እነሆ ስብከቱ፣ ትምህርቱ በሰማችሁት መልኩ ተጠናቋል፡፡›› ከመድረኩ ወረደ፡፡ ደካማ ሰዎች ብቻ ናቸው በወዮላችሁ ክርስቶሳዊነትንና ሞሐመዳዊነትን ሊሰብኩን የሚሞክሩት፡፡ መለኮቱ ግን በእያንዳንዱ የውበት ፈርጅ ውስጥ ራሱን ይገልጣል፡፡ ውበት ራሱን የሚያቀርብበት መንገድ ደግሞ ህልቆመሳፍርት ነው፡፡  የውበቱ መገለጫ መልኩ የሆነች አበባ፣ ወይ ፏፏቴ፣ የብስክሌት ግልቢያ አሊያም የሆነች ሴት መሆኑ ልዩነት አያመጣም፡፡ ማንኛውም ውበት ለብቻው የሚወደስ ግንጥል ጌጥ፣ ለብቻው የሚነበብ ንጡል ገጽ አይደለም፡፡ የምልዓተ ዓለሙ እርግብግቢት በሙላት ሲነበብ የሚገኘው ድምር ውጤት እሱ መለኮቱ ራሱ ይሆናል፡፡ እኛ ግን ለዚህ ዓይነት ጊዜንና ቦታን የተሻገረ ልህቀት የታደልን አይደለንም፡፡ የጊዜ እና የቦታ ምርኮኞችና ምንደኞች ነንና፡፡
ሆኖም በተሰጠችን ውስን መስተሃልይ በእያንዳንዱ የውበት ገጽ መስታውትነት እግዜሩን እናውቀዋለን፡፡ ስብሃት ገብረእግዚአብሄርና መሰሎቹ ያደረጉት ይህንኑ ነው፡፡ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር በሌላ አንድ ደብዳቤው ላይ ስንዱን ከማግኘቱ በፊት የመለኮቱን ህልውና በካደ ባዶ የኑረት ድግግሞሽ ውስጥ ሲቃብዝ እንደኖረ ይናዘዛል፡፡ ‹ሁለመናዋ› በተዋበው ስንዱ እጹብ የነፍስ መስኮቱ በኩል ከእግዜሩ ጋር ሲጋፈጥ ግን የውበት መጥበርበሩ አስደንብሮት በድንጋጤ ማን ነሽ? አለ፡፡ ይኸው አንብቡት... ‹‹ማን ነሽ አንቺ፣ ሴት የለችም ካልኩ በኋላ ሴት ሆነሽ የመጣሽ?...  እግዜር የለም እያልኩ በባዶ ሰላም መኖር ስጀምር ስጋ ለባሽ እንደኔው ለሁሉ አደጋ የተጋለጥሽ ሆነሽ የመጣሽ- ማነሽ?...››
እኔም እላለሁ... እውነትስ እነዚህን ሁሉ ከያኒያን በረቂቅ የነፍስ ጣቶች ነካክተሸ ማስደንበር የቻልሽ፣ አንዳችስ እንኳን ሳይቀር ሁሉንም የሕይወት ቅንጣቶች ለመዋጥ ባለ መቋመጥ መኖርን፣ መጠበብን እንዲያልሙ ማትጋት የቻልሽ፣ አንቺ ሴት ማን ነሽ? እነዚህን ሁሉ ኪነታዊያን በከሰሙ ለጋና ለግላጋ ወዳጅነቶች፣ የሚያስደነግጥ ጥርጣሬ በታከለበት አረመኔ መውደድ መጠፍነግ፣ እናም ለሆነ ዓይነት ኪናዊ ተራክቦ ማስገር የቻልሽ አንቺ ሴት ማነሽ? አንቺ ሴት ማነሽ?
ይሄን ነገር እንዲህ ብለን እንዝጋው...  ለውበት መማለል፣ በውበት መደነቅ ጥጉ አምልኮ ነው፡፡ አምልኮ ለማን እንደሚገባ በመተንተን ፍለጋዬን የሰነፍ ስራ አላደርገውም፡፡ ይታወቃልና! ውበት ግን ከሕመም፣ ከቃል፣ ከአፈርና ከትንፋሽ ተገኘ። ዘመንም አልተቆጠረለት፡፡
ሐ- የኪነት ጣዖት(muse)፣ ወሲብና ጥበብ
‹‹sex and art are the same thing›› Pablo Picasso
*   *   *
ከስድስት ወይም ሰባት ዓመታት በፊት የሆነ አመሻሽ ከአንዲት የድሮ ወዳጄ ጋር በእግር ጉዞ እየተንሸራሸርን ስለ አንድ ሴቶች አጠገቡ አይጠፉም የተባለለት የሀገራችን ገጣሚ እያወራን ነበር፡፡ ይህች የድሮ ወዳጄ በዚያች አመሻሽ ስለዚህ ‹ዝነኛ› ገጣሚ የነገረችኝ ነገር ዛሬም ድረስ ትዝ ሲለኝ ያስገርመኛል፡፡ ይሄው ስሟት...
‹‹በጣም ነው ማደንቀው፡፡ አንድ ቀን በድምጹ የተቀዳ ግጥሙን በጆሮ ማዳመጫ እየሰማሁ ስራመድ ፊት ለፊት አገኘሁት፡፡ እሱን ራሱን እስኪገርመው ድረስ ዓይኖቼን ከእርሱ ላይ መንቀል አቃተኝ፡፡ በዚያው ቅጽበት እንሂድ ቢለኝ አብሬው ለመተኛት ዝግጁ ነበርኩ፡፡ አሁንም አንድ ቀን ብቸገርለት አይከፋኝም፡፡››
እነሆ ከዚያች ዕለት ጀምሮ በኪነት ሥራው መነሸጥና እና ከሚያደንቁት የኪነት ጣዖት ጋር በወሲብ የመጣመር መጣደፍ ምንጩ ምንድን ነው? የሚለው ዘወትር በአዕምሮዬ የሚመላለስ ጥያቄ ሆነ፡፡ ነገርየው በግልባጩም ይነበባል። ዘመኔን የሞላው ከምታደንቀው እያንዳንዷ ሴት ቀሚስ ጋር ለመተናነቅ፣ ትንፋሽ ለመናጠቅ ያሰፈሰፈ ባለ ሦስት መስመር ስንኝ ገጣሚ፣ ባለነጠላ ዜማ ዘፋኝ ብቻ ነው፡፡ ይሄኛው መልክ ለራስ መታመን የሚጎድለው መቅበዝበዝ መሆኑን አላጣውም፡፡ ያም ሆኖ የጥበብና እና የፍትወት መተቃቀፍ፣ መግነጢሳዊ መሳሳብ እንዴትነት የሆነ መላምታዊ ምላሽ እንደሚያሻው አስባለሁ፡፡
በኋላ ነው ‹የእኔ ማስታወሻን› አንብቤ ስጨርስና ንባቤን ረጋ ብዬ ስፈትሽ የሲግመን ፍሮይድን ‹libido›፣ የአናሊቲካል ሳይኮሎጂስቱ ካርል ዩንግን ‹anima and animus› እንዲሁም ከግሪክ አፈታሪክ የተወሰደውን muse(ሚውዝ) የሚል የስነ ተረት ሀሳብ ደርቦ በማናበብ ለመልስ የሚበቃ የሆነ የመረዳት ቅርጽ መፍጠር እንደሚቻል የገባኝ የመሰለኝ፡፡
በሲግመን ፍሮይድ አረዳድ ‹libido› ቅንዝር ብቻ ተብሎ የሚታለፍ ቁንጽል ሀሳብ አይደለም፡፡ ተለጥጦ ሲተነተን በማህበራዊ፣ ጾታዊ፣ ፈጠራ ነክ ፍላጎቶቻችን መከናወን የሚያንደረድር ፍላጎት፣ ደመነፍስ ነው፡፡ አሁንም እንደ ሲግመን ፍሮይድ አረዳድ፤ የሰው ልጅ በሕይወቱ ውስጥ የሚያከናውነውን ማንኛውንም ነገር የሚፈጽመው ለ‹ሊብዶ› ፍላጎቱ መሟላት መዳረሻ ይሆነው ዘንድ ነው። የሚያስደንቀኝ የፖላንድ ተወላጅ አሜሪካዊው ሰዓሊና ቀራጺ Szukalski - struggle and the lost art of szukalski በተሰኘ ለዓመታት እንደዕለት ማስታወሻ በተቀረጸ ዶክመንተሪው ላይ ‹‹ኪነትን በዋናነት የምጠቀምባት ሴቶችን ወደ እኔ ለመሳብ ነው›› ብሏል፡፡ እንደ ዙካልስኪ ድፍረት ኖሯቸው አይናገሩት እንጂ ይህ የሁሉም የኪነት ሰዎች ህልም ነው ለማለት ደፋር መሆን አያስፈልግም፡፡  
በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ጠቢቡ ሰው ዘወትር የተጨቆነው የስነ ወሲብ ነክ ነጻነት ማሳያ(sex model) ነው፡፡ በእኛ ሀገር ልምድ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ለዚህ ጥሩ ምሳሌያችን የሚሆን ይመስለኛል፡፡ ከሰማንያዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ሕልፈቱ እስከተሰማበት ዕለት ድረስ ከኪናዊ ልህቀቱ እኩል ምናልባትም በላቀ ሁኔታ ፍትወትን የተመለከተ ነጻነቱ ብዙ ወጣቶች ወደ እርሱ እንዲሳቡ ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡ ከላይ ለአብነት የጠራነው ፒካሶም በዘመኑ ይህንን የሚያስደነግጥ ጥበብና ወሲብን ደርቦ የመከወን ድፍረት የተካነ ጠቢብነቱን ተውኖት ተሸኝቷል፡፡
ፒካሶ በሕይወት ዘመኑ ከሰባት ሴቶች ጋር ከፈጠረው የትዳር ግንኙነት ውጪ ስፍር ቁጥር ከሌላቸው ሴቶች ጋር ፍትወትን ይፈጽም ነበር ይባላል፡፡ ‹‹መሳል ሌላኛው የዕለት ማስታወሻ የመያዣ መንገድ ነው- to draw is another way of keeping a diary›› በሚለው መርሁ በመመራት ቅንዝራሟን ዓለም በስልቷ ሰልጥኖ እስከ ውስልትናዋ እርቃኗን አገማሽሯታል፡፡ እስከ ሰማንያ ሺህ ከሚገመቱ የስዕል፣ ንድፍና ቅርጻቅርጽ ሥራዎቹ አብዛኞቹ ይህንን ጽልመትን የሚታከክ፣ ከዳቢሎስ ጋር የመደነስን ያህል የሚያስበረግግ ሴቷን ከኮርማ ጋር የሚያዳራ የፍትወት ጭፍን መቋመጥ ያተመባቸው ናቸው፡፡
ሁሉም ሴቶቹ ግን የአዲስ ዘመን ጀማሬ ምልክቶችና ተዋኒያን ነበሩ፡፡ ከ‹ብሉ ፔሬድ› ወደ ‹ሮዝ ፔሬድ› እንደገና ወደ ‹ኩቢይዝም› ሲሸጋገር መረማመጃዎቹ ሴቶች ነበሩ፡፡ ሽርሽሩ ሁሌም ድንገት ያበቃል፡፡ ሴቷም በድንገት እንዳልባሌ እቃ ትጣልና፣ ሌላኛዋ ሰለባ ለሌላ መነሸጥ መነሻ ትሆን ዘንድ ወጥመድ ይጣልባታል፡፡ በዚህ መልኩ በትዳር የተጣመራቸው ሁሉም ሴቶች በፒካሶ ፍጹም አመጸኛ ብሩሽ ከደነበረው ቅንዝራም የተምታታ ዓለም ጋር ግራ ተጋብተው ዕጣቸው አሳዛኝ ሆኗል፡፡ ሁለቱ ራሳቸውን ሲያጠፉ፣ ከአንዷ በስተቀር የተቀሩት ለከፋ የአዕምሮ መረበሽ ተዳርገዋል፡፡
የልጅ ልጁ ማሪያና ፒካሶ በ2001 እ.ኤ.አ ባሳተመችው ‹Picasso: my grandfather› በተሰኘ መጽሐፏ የሰጠችውን ይህን ሀሳብ የሚያጠናክርልንን ምስክርነት ጠቅሰን እንሻገር ... ‹‹He submitted them to his animal sexuality, tamed them, and crush them on to his canvas... After he had spent many nights extracting their essence, ones they were bled dry, he would dispose of them.››
አሁንም ግን መጠየቃችንን እንቀጥላለን። ጥበብና የፍትውት መዳዳት ምንና ምን ናቸው? ኦስትሪያዊው ገጣሚ ሬይነር ማሪያ ሪልከ (Rainer Maria Rilke 1875-1926 እ.ኤ.አ) ለአንድ ወዳጁ በላከው ደብዳቤ ላይ የጥበብን እና የወሲብን ድርብ ዳንኪራ፣ ጨካኝ መተዛዘል፣ ከሰመመን፣ ከመቃተት፣ ከእቶን ትንፋሽ ሰሌዳ የሚጸነሱ መንታ ገጽነት አስመልክቶ ሲጽፍ ቀጥሎ የማስነብባችሁን ሀሳብ አንስቷል፡፡ ‹‹Artistic experience lies so incredibly close to that of sex, to its pain and its ecstasy, that the two manifestations are indeed but different forms of one and the same yearning and delight.››
በእኔ አረዳድ የሳይኮሎጂስቱ ካርል ዩንግ ‹anima and animus› ነገሩን በሌላ መንገድ ከመተርጎም ውጭ ከላይ ካነሳነው ሀሳብ ብዙ የሚለይ አይደለም፡፡ በአካላዊ ሕልውናው ወንድ ሆኖ የሚተውነው እሱ በውስጡ ግን እንስታዊ ማንነት(anima) አለው፡፡ ወንዱ ይህንን ወንድነቱን የተተገነ እንስታዊነቱን(contra sexuality) ታነቃ ታሰለጥንለት ዘንድ ሴቷን ይፈልጋታል፡፡ አውስትራሊያውቷ አክራሪ የስነ ጾታ ተሟጋች Germaine Greer ይህንን ሀሳብ የሚያጠናክር ግሩም ሀሳብ አላት፡፡ እንቀንጭብ...
 ‹‹The muse in her purest aspect is the feminine part of the male artist, with which he must have intercourse if he is to bring into being a new work. She is the anima to his animus, the yin to his yang, except that, in a reversal of gender roles, she penetrates or inspires him and he gestates and brings forth, from the womb of the mind›› ወንዱ ጠቢብም ይሁን ሌላ ለተሰናሰለ እሱነቱ ስምረት (for the uniqueness of oneself) አንስታይ ማንነቱ  በተገቢው ልክ መደመጥ አለበት፡፡ ይሄው ሂደት በግልባጩ ለሴቲቷም ወንዴያዊ ማንነት(animus) ይሰራል፡፡ ጉዳዩ በታኦይስት አስተሳሰብ በክብ ውስጥ የሚያድረው yin (ጥቁሩ) እና yang(ነጩ) ተምሳሌትነት አለው። አንዱ ያለ አንዱ ምልዑ ሊሆን አይችልም። ወንዱ ‹ይን› ለሚዛናዊ ሕልውና ሴቷ ‹ያንግ› ታስፈልገዋለች እንደማለት፡፡  
ሴቴያዊ ማንነቱን በምልዓት ማድመጥ ያልቻለ ሰው እሱ ንጡል፣ ቁጡ፣ ረባሽ፣ ኃይለኛ፣ ያልተረጋጋ ይሆናል፡፡ እንደገና ሴቴያዊ ማንነቱን አለቅጥ ያስታመመ እሱ በሀገራችን አባባል ሴታሴት፣ ቦቅቧቃ፣ ይሆናል። አሁንም እንደ ካርል ዩንግ አባባል ሁለቱን በቅጡ ማሰናኘት የቻለ እሱ ስክነትን የተላበሰ፣ በራሱ የሚተማመን፣ የተረጋጋ... ይሆናል። በዚህ አረዳድ ሴቷን ወይም ወንዱን ወደ ስበት መግነጢሱ/ሷ የሚያንደረድራቸው ቅንዝር ብቻ አይደለም። የመሟላት፣ ምልዑ የመሆን (fulfillment) ምኞትም ጭምር አንጂ...
ሚውዟ ለኪነቱ ሰው የልኬታው መስፈርቱ ነች፡፡ የመነሳሳቱ ምንጭ (source of inspiration)... በዛለ ጊዜ ከመለኮቱ የተቀበለችውን ሕያው ትንፋሽ እፍፍፍ የምትልበት የኪነት ጣዖቱ ነች፡፡ ጉልበት ትለግሰዋለች፡፡ ወደ ነፍሱ መስኮት ለመድረስ ቀላሉን መንገድ የትኩስ ትንፋሽ ሽሚያውን መንገድ ትጠቀማለች፡፡ ለሌላ ለሌላው ሁሉ ጋንጩር የሆነውን ሰው ለእርሷ ጭራውን የሚቆላ ለማዳ ውሻ ታደርገዋለች፡፡ ነፍሱን መነሸጥ፣ ማስገር ማቁነጥነጥ ይቻላታል፡፡ እሱም ከሌላ ከማንም ይልቅ የኪነት ጣዖቷን  መወድስ ይመርጣል፡፡ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ማስታወሻ ላይ ‹‹ከሀና ይልማ ጋደም ብለን የጻፍኩትን ሳነብላት ‹‹you are my author›› ካለችኝ ለእኔ ከዚህ የሚበልጥ አድናቆት የለም›› ይላል፡፡
ይህችን ሴት የማጣት ሕመሙ በጥልቀት የሚገባን ለስንዱ አበበ ‹የመጨረሻ ደብዳቤዬ ይሁን በሚል› ኑዛዜ መልክ የጻፋትን የምትከተለውን ዐረፍተነገር ስናነብ ነው፡፡ ‹‹ስንዱ ነፍሴ - ምናልባት (ካስቻለኝ) የመጨረሻ ደብዳቤዬ... አንቺና ‹‹ወይዘሮ›› በብዙ ዓይነት ትመሳሰሉብኛላችሁ - ከልማድ ውጪ እነብሴ ውስጥ እሆናለሁ እናንተን ሳገኛችሁ፡፡››
በ‹የኔ ማስታወሻ› ውስጥ የምናነባቸው የእነዚህ ሁሉ የደብዳቤዎች መራወጦች በዚህ የአረዳድ ማዕቀፍ ውስጥ የሚተነተኑ ናቸው። ራሷ የኪነት ዛሯ ስንዱ አበበ ከቴዎድሮስ ተክለአረጋይ ጋር በፍልስምና 4 ላይ ባደረገችው ቃለምልልስ፣ ሚውዝነቷን የሚያረጋግጥ ምስክርነት ሰጥታለች፡፡  ‹‹... ሁሉም ይወዱኛል። ግን ከሁሉም ጋር የስጋ ግንኙነት አይደለም  ያለን፡፡ ግንኙነታችን የመንፈስ ነው፡፡ ደስ ይሉኛል፡፡ ‹‹የሆነ ነገር ላደርግ ነው›› ስትል አንተ እያለህ መደሰት እጀምራለሁ፡፡ ‹‹በቃ እኮ ግማሽ ሄደህበታል፡፡ ዋናው ሀሳቡ ነው፡፡ ቶሎ ቶሎ በል እያልኩ አጣድፍሃለሁ፡፡ አንተ ችላ ብትለውም እኔ እሺ አልልህም፡፡ ‹‹እንዲህ አደርጋለሁ ብለህ አልነበረ እንዴ? ምን ደረሰ?›› እልሃለሁ፡፡ ይሄም ደስ ይላቸዋል፡፡ የጽሑፍ ስራ መነቃቃት ይፈልጋል... ደስ ይለኛል እኔ ራሴ፡፡ ‹‹እንደው አሁን ከዚህ ቀጥሎ ምን ሊል ነው?›› ብዬ አስባለሁ፡፡ ፈጠራው ራሱ ሌላ ዓለም ውስጥ ይከተኛል እኔን ራሱ፡፡››   
ስንዱ ከሁሉም ጋር ስጋዊ ግንኙነት አልነበረኝም ትበል እንጂ ጥቂትነትን ከሚሻገሩት ጋር ንክኪ እንደነበራት ደብዳቤዎቹና ጭምጭምታዎቹ ምስክር ናቸው፡፡ ለዚያውም ደብዳቤዎቹ ተነካክተው ምናልባት አንዳንዶቹም ሆነ ተብለው ከህትመት ተዘለው ሊሆን እንደሚችል እጠረጥራለሁ፡፡ አካላዊ ግንኙነቱ ባይፈጸም እንኳን በሁሉም ልቦና ውስጥ የሚፋጅ የፍላጎት እሳት ይመላለስ እንደነበር መጠርጠር ይቻላል፡፡ ስንዱ እስከመጨረሻው አንቱ እያለች ትጠራው የነበረው አቦይ ስብሃት ሳይቀር በአንድ ደብዳቤው ላይ ከእርሷ ጋር ለአንድ ቀን ብቻ እንኳን ተራክቦ የመፈጸም ጥልቅ መሻቱን መረር ባለ አገላለጽ አስፍሮት እናነባለን፡፡ ‹‹ከመልክሽ ከድምጽሽ ከውጪ ሆኜ ከማይሽ ስንዱ አልፌ አንቺን ስንዱን አንዴ ባየሁሽ! አንዴ ብቻ! አንዴ ብቻ! እንደማይቻል የታወቀ ነው፡፡ እየታወቀም ናፍቆቴ ነው፡፡›› ገጽ 23
ወንዶቹ ከላይ ከተወያየንባቸው ሦስት የግንኙነት መርሆዎች የትኛውንም ተከትለው በሚውዟ ዙሪያ ቢሽከረከሩ ልዩነት አያመጣም። የመሳባቸው የመጨረሻ ግብ ፍትወት ቢሆንም ባይሆንም አሁንም ልዩነት አያመጣም። ፍትወትም ቢሆን ርካሽነት ባልታከከው መዳዳት(with the noblest motive) ለሚከውነው ከመለኮቱ ጋር የሚያጨባብጥ የምልዓት ክንውን(Meditation) መሆኑ እሙን ነው፡፡
ዋናው ነገር ሴቴያዊ ማንነታቸውን ታነቃ፣ ነፍሳቸውን፣ ሕይወታቸውን ታበለጽግ፣ የኪነት ደመነፍሳቸውን ታሰለጥን ዘንድ የኪነት ጣዖቷ በራሷ የበቃች ልትሆን ይገባል፡፡ ወፎቹ ይሰፍሩበት ዘንድ ሌላ ማረፊያ ዛፍ የሌለ እስኪመስል ብዙ የአንድ ዘመን ኪነታዊያን፣ በዚህችው ሴት ዙሪያ የመረባረባቸው ምክንያቱ ስንዱ ለዚህ የተሰናዳ ነፍስ ስለነበራት ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬም ቢሆን የፈጠራ ሂደቱ የሚጠይቀውን መሳከር መሸከም የሚችሉ ሴቶቻችን (ወንዶቹስ ቢሆኑም) በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ የባህል እና የሀይማኖት ጭምት እስረኞች የመሆናቸው ነገር ዛሬም ድረስ በቅጡ የተቀረፈ አይመስልም፡፡
በዚህችው የስበት ማዕከል ስንዱ ዙሪያ ይሽከረከሩ የነበሩቱ ትንንሽ ከዋክብት ግን ምህዋራቸው ይጣረሳል፡፡ ሁሉም መገፋት ብስጭት፣ ቁጣ ያትከነክናቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ራስን የመግለጥ እልህ ያንደረድራቸዋል። ሁሉም (ከአንዳንድ ገጣሚያን በስተቀር) የለየላቸው እብዶች ነበሩ፡፡ ስንዱ ከቴዎድሮስ ተክለአረጋይ ጋር ባደረገችው ቃለ መጠይቅ ‹‹ባሴ ሀብቴ አለልህ አጋንንት በለው፡፡›› ስትል አውጃለች፡፡ በእኔ አተያይ ሙሉጌታ ተስፋዬ እብድ እብድኛውን በመጫወት ባሴ ሀብቴን ቢያስከነዳው እንጂ የሚያንሰው አይደለም። የትኩሳት፣ የሌቱም አይነጋልኝ፣ ከሁሉ በላይ የሰባተኛው መልዓክ ጌታ ስብሃት ገብረእግዚያብሔርስ አጋንንት ለመሰኘት ምን ይጎድልበታል?  
ሀሰሳዬን ስጀምር እንዳልኩት የእነኝህ ደብዳቤዎች ደራሲያን ከዘመን ስካር በርግገው በዚህችው የኪነት ዛር (muse) ዙሪያ ተኮልኩለው የፈጠሩት የግንኙነት ጥምርታ ውትብትብ ነው፡፡ የአንዱ ከሌላው የማይገጥም፣ የሚተላለፍ፣ የሚጣረስ... የባሴ ሀብቴ ደብዳቤዎች የሙሾ መልክ ለዚህ የመተላለፍ፣ የመጣረስ ጥርጣሬያችን ሁነኛ ማሳያዎች ይሆናሉ፡፡ ደረጄ ደስታ በአንድ ደብዳቤው ላይ ‹‹ውበት ንክኪነት ካለው እከክ ነው ይባላል፡፡ ውበትን በጸጥታ ለማጣጣም ጸጋን ይጠይቃል። ብዙዎቻችን አልታደልነውም፡፡ ስለዚህ እንደኔም ሆነ እንደመሰሎቼ ውበትን ራቅ አድርጎ እንደ ፏፏቴ እንደ ሸንተረር እንደ ... ማጣጣም ነው። መቼም በፏፏቴ ውበት የሚቀና ሰው የለም ባይባልም እስካሁን ግን አልቀረበም።›› ይላል። የባሴ ሀብቴን ደብዳቤዎች ያነበበ ማንኛውም የአንድና አንድን ድምር የሚያውቅ ሰው የውበት ምች አጠናግሮት እከክ ወርሶት እንደነበር መረዳት አይከብደውም፡፡ ከባሴ ሀብቴ በተጨማሪ የስብሃትም ሆነ የወሰን ደብዳቤዎች ይሄን መሰል እሚያስታምም ጥፍር የሚሻ እከክ መሳይ ሮሮ ተሸካሚ ናቸው፡፡         
በደብዳቤዎቻቸው መስኮት አጮልቀን ስናያቸው ሁሉም በዚህች ሴት ፊት ሲቆሙ እንደሚንተባተብ ህጻን ሆኑ፡፡ ግን ደግሞ በራሳቸው መንገድ ክፍልፋይ ዲያቢሎሶች... ምናልባት አጋንንታዊ እብደቱ ለጥበባዊ ልህቀታቸው ዕድገት ያስፈልጋቸው ነበር መሰለኝ፡፡ ስንዱ እነዚህን ትንንሽ አጋንንት ከማላመድ፣ ገራም ከማድረግ፣ ከማቀራረብ አልፋ አብራቸው በስልታቸው ደንሳለች፡፡ እኛም ከዚህ ‹ያልተቀደሰ› የዳንስ ንቅናቄ በብዙ ያተረፍን ይመስለኛል፡፡ የስንዱ ጥረት ባይታከልበት ይህንን መጽሐፍ ጨምሮ፣ የመስፍን አሸብር፣ የባሴ ሀብቴንና ሙሉጌታ ተስፋዬን ሥራዎች ለማየት መቻላችንም እጠራጠራለሁ... ‹የእኔ ማስታወሻን› ስናነብ እኒህንና እኒህን የመሳሰሉትን መረዳቶች ካልታጠቅን ንባባችን ስንኩል እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡                  
አንድ ወደ ግራ
*   *   *
ንፉግ እንደ ግራ ይላል ሙሉጌታ ተስፋዬ... ከርዕሱ እጀምራለሁ፡፡ ‹የእኔ ማስታወሻ› እንኳን ለዚህ ዓይነተ ብዙ መደነቆች የተሸከመ ጥልቅ ሰነድ፣ ለአንድ የጋዜጣ መጣጥፍ የሚመጥን ርዕስ አይደለም፡፡ የሆነ ለንባብ የማይጋብዝ ፍዝ በተሀ ነገር ነው፡፡ ከመታተሙ በፊት በአሳታሚው በኩል ወደ ገበያ ሊወጣ እንደሆነ ጭላንጭል መረጃ ደርሶኝ ርዕሱ እንዲቀየር ወትውቼ ነበር፡፡ እሺ አትልም ተብሎ እንዲሁ ታተመ፡፡  ሙሉጌታ ተስፋዬ እና ስብሃት ገብረእግዚአብሔር የመሳሰሉ የላቁ ጠቢባን ጋር ከአስር ዓመታት በላይ የተወዳጀች፣ ከእነሱ እጅ እየተናጠቀች ‹ያነበበች› ሴት ስለምን ይህን የመሰለ የተወነጋገረ ርዕስ እንደመረጠች ሊገባኝ አልቻለም፡፡ በበኩሌ ጥራዟ የሁሉንም ከያኒያን መቃተት የሚያቅፍ እስከ ዘለዓለም የሚያጠናግር ርዕስ ያስፈልጋት ነበር እላለሁ፡፡
ደብዳቤዎቹ የላቀ ኪናዊ ለዛ ስላላቸው እንጂ መጽሐፉ የይድረስ ይድረስ ሥራ የሚመስል ነገር አለው፡፡
ንባባችን የተሟላ ይሆን ዘንድ መጽሐፉ በግርጌ ማስታወሻዎች፣ በተጨማሪ ማብራሪያዎች መበልጸግ ነበረበት፡፡ ቢያንስ የተብራራ ሰፋ ያሉ ገጠመኞች የታከሉበት መግቢያ ያስፈልገው ነበር፡፡   
አሁንም በቀጣዩ ዕትም ይህንን ለማድረግ ዕድሉ አለ፡፡ በእርግጥ ደብዳቤዎቹ እነዚህ ብቻ ናቸውን? ጊዜና ስንዱ የሚመልሱት ይሆናል። ስንዱ ግን ከፊዝጀራልዷ ዜልዳ፣ ከካህሊሏ ሜሪ፣ ከቪትሆቨኗ ጆሴፊን የማይተናነስ በቅጡ ሊጠና የሚገባው የሚውዝነት (የንሽጠት ምንጭ) ታሪክ እንዳላት ይሰማኛል፡፡ እነዚህ ደብዳቤዎች ታትመው እናነባቸው ዘንድ ላሳየችው ድፍረትም መመስገን አለባት፡፡


Read 1119 times Last modified on Monday, 20 September 2021 17:09