Monday, 10 September 2012 13:45

ኢህአዴግ በአዲሱ ዓመት ያሞላቅቀን!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(1 Vote)

“የፓርቲዬ ባህል አይፈቅድልኝም” የሚል ሰበብ አንቀበልም!

በሀዘን ክፉኛ የጨፈገገንን ደባሪ ዓመት ዛሬ እንሸኘዋለን - እንዲህ ያለ ዓመት ተመልሶ እንዳይመጣ እየተመኘን (ኧረ ፀሎትና ምህላም ያስፈልገዋል!) ግን በ2004 ምን መዓት ነው የወረደው? ብቻ በዚሁ በቃችሁ ይበለን! አሁን ወደ ዕለቱ ወጋችን ልመልሳችሁ፡፡በዛሬዋ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ሆኜ ምን እንዳማረኝ ታውቃላችሁ? በቃ … መሞላቀቅ፡፡ ግን ደግሞ በወላጅ ወይም በአያት አሊያም በፍቅረኛ አይደለም፡፡ እኔ መሞላቀቅ ያማረኝ በገዢው ፓርቲ ነው፡፡ (አሞላቆን ስለማያውቅ ይሆን?) በርግጥ ይሄ ጥያቄ የእኔ ብቻ አይደለም - የህዝብ ነው፡፡ ማስረጃ ካስፈለገም ፒቲሽን አሰባስቤአለሁ፡፡ እናም ኢህአዴግ እስኪበቃን ድረስ እንዲያሞላቅቀን እፈልጋለሁ፡፡ እየቀለድኩ እንዳይመስላችሁ… ከምሬ ነው፡፡ በቃ በአዲሱ ዓመት ሙልቅቅ ማለት አምሮኛል፡፡

እንደ ቦሌ ልጆች! እኔ የምለው… ኢህአዴግ እኛን ማሞላቀቅ ያቅተዋል እንዴ? ኧረ አያቅተውም፡፡ ዋናው ነገር የልብ መሻት ነው (When there is a will, there is a way እንዲል ፈረንጅ) መቼም አውራ ፓርቲያችን ሰበብ አያጣምና “የፓርቲያችን ባህል፤ ማሞላቀቅ አይፈቅድም” ሊለኝ ይችላል (አልሰማሁም እለዋለኋ!) እርግጥ በኢህአዴግ መዝገበ ቃላት ውስጥ “መሞላቀቅ” የሚል ቃል ላይኖር ይችላል፡፡ ግን ደግሞ የህዝብ ጥያቄ ነው እያልኩት ነው (የህዝብ አጋር ነኝ ይል የለ!) ለህዝብ ጥቅም ሲል ይቸገራ! (ለህዝብ ጥቅም እያለ ስንት ነገር ያደርጋል እኮ) ደሞ እኮ 21 ዓመት ሙሉ ለገዛው ህዝብ ከዚህም በላይ ቢያደርግ አይቆጭም (ገና 30 እና 40 ዓመት ሊገዛን ያስብ የለ!) ስለዚህ ሰበብ መደርደሩን ትቶ ጭክን ብሎ ያሞላቀን - በአዲሱ ዓመት! እንዴት ነው የሚያሞላቅቀን… በሚለው ጉዳይ ላይ ግን ወደ ኋላ ላይ እመለስበታለሁ፡፡

ግን ለልብ ሰቀላ እንዳይመስላችሁ፡፡

ይሄንን ኢህአዴግ ያሞላቅቀን የሚል ፕሮፖዛል ሳዘጋጅ ኪንድል (ኤሌክትሮኒክ መፅሃፍ) የሚመስል ሞባይል የያዘና ከኢንተርኔት መረጃዎችን ሲበረብር የነበረ ወዳጄ፤ ስለቀድሞው የሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንት ኪም ኢል ሱንግ ያገኛቸውን አስደማሚ እውነታዎች ያጋራኝ ጀመር - አንድ ቢሮ ውስጥ ተቀምጠን ስለነበር፡፡ (ከኢንተርኔት ላይ እያነበበ እኮ ነው!) እኔም ብዕሬን ጥዬ ማድመጥ ያዝኩኝ (እንደወሬ ሱሰኛ!) ወዳጄ እንደነገረኝ ታዲያ ፕሬዚዳንቱ በሥልጣን ላይ የቆዩት ለ59 ዓመት ነው፡፡ (የቆዩት ሳይሆን የከረሙት ቢባል ይሻላል)

እናንተ … የኛው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሥልጣን ላይ ተሟዘዙ የተባለው እኮ የ80ኛ ዓመት ልደታቸውን ዙፋን ላይ ሳሉ በማክበራቸው ብቻ ነው፡፡ የኮሪያው ግን ድፍን 82 ዓመት ሥልጣን ላይ ነበሩ (አይሰለቻቸውም እንዴ?) ለነገሩ “የዝንተ ዓለም መሪ” (Eternal leader ነበር የሚባሉት) መቼም እንደሳቸው ሞትን የሚጠላ የነበረ አይመስለኝም፡፡ እንዴ… ሞት እኮ ነው ከስልጣን ያወረዳቸው! (እሳቸውማ በድዴም ቢሆን እገዛለሁ ብለው ነበር) እናላችሁ … ከኢንተርኔት ላይ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ ሱንግ ሥልጣን ላይ ለረዥም ዓመት በመቆየት የትኛውም የዓለም መሪ አይደርስባቸውም፡፡

በዓለም ታሪክ ስልጣንን ሙጭጭ እንዳሉ ከሚነገርላቸው አምባገነን መሪዎች እንኳን 20 እና 40 ዓመታት የበለጠ በዙፋን ላይ ተቀምጠዋል - የሰሜን ኮሪያው ኪም ኢል ሱንግ፡፡ የሶቭየት ህብረቱን ስታሊንን በ40 ዓመት ይበልጡታል - በስልጣን ላይ በመክረም፡፡ የቻይናውን ማኦ ቴሱንግን በ20 ዓመት የሥልጣን እድሜ ያጥፉታል፡፡ ይኸውላችሁ … ሱንግ ከስልጣን ሳይወርዱ እኮ በአሜሪካ 10 ፕሬዚዳንቶች ተፈራርቀዋል፡፡ በጃፓን ደግሞ 21 ጠ/ሚኒስትሮች ተቀያይረዋል፡፡ በታላቋ ብሪታንያ 17 ጠ/ሚኒስትሮች ተለዋውጠዋል፡፡ በደቡብ ኮሪያ ስድስት፤ በሶቭየት ህብረት ደግሞ ሰባት መሪዎች ተተካክተዋል፡፡ የሰሜን ኮሪያው መሪ ግን ራሳቸውን እየተኩ ለስምንት አስርት ዓመታት ገዝተዋል፡፡

ዘይገርም ነው! ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ! የኢህአዴግ የሥልጣን መተካካት!! ሱንግ ግን  “ራስን በራስ መተካት” የሚል ነበር ስትራቴጂያቸው፡፡ ለአዲሱ ትውልድ (New generation) ሥልጣን መስጠት… ምናምን ብሎ ነገር ፈፅሞ አይገባቸውም፡፡ ለሳቸው አዲሱም አሮጌውም ትውልድ ሥልጣናቸው ነበር፡፡ ለነገሩ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ቢደላቸው እኮ 100 ዓመትም ከስልጣን አይወርዱም ነበር፡፡ የቱኒዚያው፤ የሊቢያው፣ የግብፁና የየመኑ መሪዎች የህዝብ አመፅ ባይፈነግላቸው ኖሮ መቼ ከስልጣን ይወርዱ ነበር (እባብ የልቡን አይቶ እግር ነሳው አሉ!)

በአዲስ ዓመት ዋዜማ የለየላቸውን አምባገነን መሪ ታሪክ ሳወጋችሁ ዝም ትሉኛላችሁ (ለነገሩ በመረጃ ላስታጥቃችሁ ብዬ እኮ ነው) አሁን ወለም ዘለም ሳልል በቀጥታ ወደ አዲሱ ዓመት ጥያቄዬ ልውሰዳችሁ - “ኢህአዴግ በአዲስ ዓመት ያሞላቅቀን!” ወደሚለው ማለቴ ነው፡፡

መቼም መሞላቀቅ የሚጠላበት የለም አይደል … (ካለ እጁን ያውጣ!) ለምን መሰላችሁ? ሳይፈልግ ተሞላቅቆ አመም ቢያደርገውስ (እብድ እህል ገዝቼ ሚስቴን አሳበድኳት ማለት ይመጣል) የዚህችን ተረት ታሪክ ታውቃላችሁ? ባል ለሚስቱ የሚፈነዳ በቆሎ (ፈንዲሻ) ገዝቶ ይወስድላታል፡፡ እሷ ሆዬ ሙያ የላት ኖሮ… በቆሎውን ክዳን በሌለው ድስት ልታፈነዳ ስትሞክር ተፈነጣጥሮ ጉድ ይሰራታል፡፡ በየቦታው የተፈናጠረውን በቆሎ ለመለቃቀም ስትንደፋደፍ ያየ ባል ነው የተረተው “እብድ እህል ገዝቼ ሚስቴን አሳበድኳት” እያለ፡፡

ወደ መሞላቀቁ እንመለስ፡፡ እንግዲህ ማናችንም ብንሆን መሞላቀቅን በደንብ እስክንላመደው ድረስ መቸገራችን አይቀርም (እንደ ቁርጠት ቢጤ ሊለን ይችላል!) ለወር ለሁለት ወር ፆመን ፆመን ጮማና ቅባት በበዛው ምግብ ስንፈስክ እንታመም የለ፡፡ ይሄም እንደዚያው ነው፤ ተሞላቀን ስለማናውቅ ሊያመን ይችላል፡፡ (ይሄ የቦሌና የዲታ ልጆችን አይመለከትም!)

በነገራችሁ ላይ እስካሁን የነገርኳችሁን ምስጢር ለማንም እንዳትነግሩብኝ (በተለይ ለአውራው ፓርቲ) ለምን መሰላችሁ … አጅሬ ኢህአዴግ እቺን ከሰማ “ህዝብን  ከቁርጠትና ከመጐርበጥ ለመታደግ” በሚል የማሞላቀቅ ጥያቄውን አልቀበለውም ሊለን ይችላል፡፡ አዲሱ ዓመት ጨፈገገብን ማለት አይደል (የህዝብ ነገር አይሆንለትማ!)

እንግዲህ ገዢው ፓርቲ ቁርጡን ይወቅ - ጥያቄያችን እንደማይቀር፡፡ ግን ደግሞ ይሄን  ያህልም “ሊቦካ” አይገባም፡፡ እኛ እኮ እንደ አንዳንድ የቱጃር ልጆች የባለድግሪ ደሞዝ የሚያህል የኪስ ገንዘብ አንጠይቅም (ኢህአዴግ ጠላታችን ነው እንዴ?) እንደ ቀበጥ የሃብታም ልጆች መኪና ይገዛልን፣ ውድ ት/ቤት ካልተማርን፣ ቫኬሽን አሜሪካ ካልሄድን፣ ወዘተ… ፈጽሞ ከአፋችን አይወጣም፡፡ የእኛ ጥያቄ መሰረታዊ ፍላጐቶች ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ የናረው የኑሮ ውድነት መላ ይፈለግለት፤ በቀን ሦስቴ በልተን እንደር፤ ሁላችንም እኩል የትምህርትና የሥራ ዕድል ይሰጠን (በፓርቲ ሎሌነት ሳይሆን በችሎታ) ይሄውላችሁ … ኢህአዴግ ይሄን ሲያሟላልን ተሞላቀቅን ማለት ነው፡፡

እኔ የምለው … በEBS ቶክ ሾው የሚያቀርቡ አንዳንድ ዳያስፖራዎች ሲናገሩ ሰምታችሁልኛል? (የሚናገሩ ሳይሆን የሚሞላቀቁ እኮ ነው የሚመስሉት!) አንዳንዴማ አማርኛውን የሚያሞላቅቁት ይመስለኛል!

ሁሌም የሚገርመኝ አንድ ነገር አለ … በዓመቱ ማብቂያ ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዓመቱ እንዴት አለፈ ሲባሉ… ሁሉም መልሳቸው በእሮሮና በብሶት የተሞላ ነው፡፡ በቃ ሁሌም ኢህአዴግ በደለን ነው፡፡ ግን ለምንድነው ኢህአዴግ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የማይንከባከበው? (እንደ ሞግዚት ሳይሆን እንደ አባት ወይም እንደ አሳዳጊ!) ቆይ ለምን ያዋክባቸዋል? ለምንስ በሰበብ አስባቡ ያስራቸዋል? ለምን የመሰብሰቢያ አዳራሽ በነፃ አይፈቀድላቸውም? (ካልጠፋ የቀበሌ አዳራሽ?) ለምን የፖለቲካ ምህዳሩን ሰፋ አያደርግላቸውም? ለምንስ ይዘልፋቸዋል? ምናለ በአዲሱ ዓመት ቢያሞላቅቃቸው! ተቃዋሚዎችን ብቻ ግን አይደለም፡፡

ነፃ ፕሬሱንም… ቢንከባከብ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ አንዳንዴ የውጭ አገር ጉዞ ስፖንሰር ቢያደርጋቸውስ? የመንግስት ባለሥልጣናት ለምን የኢቴቪን ጋዜጠኞች ብቻ አስከትለው ይሄዳሉ? የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞችም እኮ የውጭ ጉዞ አይጠላባቸውም (ወጪው እንደሆነ በህዝብ ገንዘብ የሚሸፈን ነው) ከሁሉም በላይ ኢህአዴግ ጋዜጠኞችን እንደሚያሞላቅቅ የምሻው ግን ከእስር እንዲገላገሉ ብዬ ነው፡፡ ይታያችሁ … በ21 ዓመት የስልጣን ዘመኑ ኢህአዴግ አንዴም እንኳን አሞላቆን አያውቅም ስለዚህ በ2005 በደንብ ያሞላቀን!! በቃ ሙልቅቅ..ቅ እንበልበት! እስቲ አንዳንዴ እንኳን ኢህአዴግ ወግ ይድረሰውና እንደ አያት ይሁንልን! (አያት ሊሆን ምን ቀረው?)

ነፃ ፕሬስ ሲባል ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? ያ ኮሚክ ማተምያ ቤት! ሲፈልግ… “የዓይንህ ቀለም ስላላማረኝ ጋዜጣህን አላትምም” የሚለው! (የባለቤቱ ዘመድ ነው እንዴ?) የሚገርም እኮ ነው… አንዴ ደግሞ “የመንግስት ባለስልጣናት ወይም የኢህአዴግ ካድሬዎች በዘገባችሁ ስላልተደሰቱ ጋዜጣችሁን አናትምላችሁም” ብሏል አሉ፡፡

ከአሁን ቀደም የሳንሱር ክፍል ሊያቋቁም ዳድቶት ነበር እያሉ የነፃ ፕሬስ መብት ተሟጋቾች ይተቹታል (ደርግን መልሶ ሊያመጣብን!)

የሆኖ ሆኖ ኢህአዴግ ነፃ ፕሬሱን ማሞላቀቅ ሲጀምር ይሄ ሁሉ ችግር ይቀራል፡፡ ምን እናድርግ … ዘንድሮ ብቻ እኮ ሦስት የግል ጋዜጦች ተዘግተዋል!! ስለዚህ መብታችንን በዘዴ እንጠይቅ ብዬ እኮ ነው!! አዲሱ ዓመት የመሞላቀቅ እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡

 

 

 

 

 

Read 3352 times Last modified on Monday, 10 September 2012 13:50