Sunday, 26 September 2021 00:00

ኢሠመጉ በህውኃት ሃይሎች በተፈፀመ ጥቃት ከ500 በላይ ንፁሃን መገደላቸውን አስታወቀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የትግራይ ክልል አዋሳኝ በሆነው የሰሜን ወሎና አካባቢው በህውሃት ታጣቂ ኃይሎች ጳጉሜ 5 ቀን 2013 ዓ.ም  በተፈጸመ ጥቃት ከ500 በላይ ንጹሃን የአካባቢው ነዋሪዎች መገደላቸውንና የእርሻ ሰብልን ጨምሮ በርካታ ንብረት መውደሙን ገለፀ ።
በተፈጸመው ጥቃት ሳቢያ አካባቢያቸውን ለቀው የተሰደዱና ኮምቦልቻና ደሴ ከተማ ውስጥ የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች መኖራቸውን የገለጸው ጉባኤው፤ ስለ ድርጊቱ አፈጻጸምና በአጠቃላይ ስለደረሰው ጉዳት እንዲሁም በሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ወደፊት ሰፊ ምርመራ አደርጋለሁ ብሏል።
መንግስት የጸጥታ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የፀጥታ ኃይሎችን በማጠንከር የዜጎችን በሰላም የመኖር ዋስትና ማረጋገጥና ዜጎችን ከጥቃት የመጠበቅ ሃላፊነትን እንዲወጣ ኢሰመጉ ጠይቋል። ከዚሁ ጋር አያይዞም የሚመለከታቸው አካላት፣ የሲቪል ሰዎች ህይወትና  ንብረትን እንዲሁም የህዝብ መገልገያ የሆኑ ተቋማትን ኢላማ ያደረገ ጥቃት መፈጸሙ ከአለምአቀፍ መርሆዎች አንፃር ተገቢ አለመሆኑንና ተጠቂነትንና የሚያስከትል ድርጊት መሆኑን አውቀው ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጠይቋል።በጥቃቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች ሰብአዊ እርዳታና ፍትህ ፈጣን በሆነ ሁኔታ እንዲያገኙና የሚደረጉ ድጋፎችም ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ ክፍሎች ትኩረት በሰጠ  መልኩ እንዲሆን ሁኔታዎች እንዲመቻቹ  ኢሰመጉ በመግለጫው ጠይቋል።

Read 10077 times