Tuesday, 28 September 2021 00:00

የእመጫት እናቶች ተስፋ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

     የገንዘብ አቅም የሌላቸውና ተሯሩጠው ሰርተው ማደር የሚፈልጉ እመጫት እናቶች፣ ልጆቻቸውን ተቀብሎ በመንከባከብና መሰረታዊ ትምህርቶችን እንዲያገኙ በማድረግ የሚያቆይና ከክፍያ ነጻ የህጻናት ማቆያ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት መኖሩን ሰማንና ወደ ስፍራው አቀናን። ድርጅቱ ካሌብ ፋውንዴሽን ይባላል። ኮተቤ መሳለሚያ አካባቢ የሚገኘው ይኸው ድርጅት፤ ገና በጨቅላ ዕድሜያቸው ከእናቶቻቸው ጋር በየገበያ ስፍራውና በየመንደሩ ለህጻናት ምቹ ባልሆነ ሁኔታ የሚቆዩ ህጻናትን እየተቀበለ የምግብ የመጠጥና የንጽህና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ በሞግዚቶች እየተንከባከበ ያቆያቸዋል። ህጻናቱ በማዕከሉ ውስጥ ከምግብና መጠጥ በተጨማሪ፣ ነጻ ህክምናና መሰረታዊ ትምህርቶችን እንዲያገኙ ያደርጋል። ለዚሁ በተመደቡ መምህራን ለየዕድሜያቸው የሚመጥን ትምህርት እንዲያገኙ ያደርጋል። የሕጻናቶቹ እናቶች ስራቸውን ሰርተው  ውለው እስከሚመለሱ ድረስ በማቆየት፣ ልጆቹን ለወላጆቻቸው ያስረክባል። በዚህ ሁኔታ ድርጅቱ በቀን ከ30 በላይ ህጻናትን እየተቀበለ አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛል።
በስፍራው ያገኘናቸው ወላጆች እንደነገሩኝን፤ ልጆቻቸውን ይዘው ስራ ለመስራት እጅግ ይቸገሩ  ነበር። አብዛኛዎቹ ሴቶች የሚሰሩት እንደ ልብስ አጠባና እንጀራ ጋገራ አይነት ስራዎች በመሆኑና እነዚህ ስራዎችም ልጅ ይዞ መስራት እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ሲቸገሩ መቆየታቸውን ይናገራሉ። ማእከሉ ከተከፈተ በኋላ ግን ልጆቻቸውን በማእከሉ ውስጥ እንዲቆዩላቸው ሰጥተው ያለ ሃሳብ ስራቸውን ሲሰሩ እንደሚውሉ ነግረዋል። ማዕከሉ ለዚህ አገልግሎቱ ምንም አይት ክፍያ የማይጠይቅ መሆኑንም እነዚሁ እናቶች ተናግረዋል።
በማቆያው ውስጥ የሚገኙ ህጻናት ሲታመሙ የሚያክሟቸው በጎ ፈቃደኛ ሃኪሞች አሏቸው። የህጻና በሽታ ጠንከር ያለ ከሆነ ወደተለያዩ የግልና የመንግስት የህክምና ተቋማት ሄደው  የሚታከሙበት ሁኔታ ይመቻቻል።
ዓለማችን ለህጻናት ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚቆዩና ለተለያዩ የጤና ችግሮች የሚዳረጉ ሕጻናትን መታደግ ነው የሚሉት የካሌብ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ተወካዩ አቶ ዮሐንስ ግርማ፤ መስራት እየቻሉና እየፈለጉ በህጻናት ልጆቻቸው ሳቢያ ከስራ የታቀቡ እናቶችም ሰርተው ራሳቸውን ለመለወጥ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው ብለዋል።
ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት 450 ችግረኛ እናቶች ልጆችን ተቀብሎ በመንከባከብ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በማድረግ ላይ ይገኛል። አቅማቸው እጅግ ደካማ የሆኑና የመስራት ፍላጎት ያላቸውን እናቶች ደግሞ ለተለያዩ የስራ ዘርፎች መነሻ የሚሆን የብድር ገንዘብ  በመስጠት ሥራ እንዲጀምሩ ያግዛቸዋል።
ማዕከሉ በየዕለቱ ከእናቶቻቸው የሚረከባቸውን ከ30 በላይ ህጻናት በእንክብካቤ በማቆየት እናቶቻቸው ያለ አንዳች ሃሳብና ጭንቀት ስራቸውን ተረጋግተው ሰርተው እንዲውሉ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ፍላጎታችን አገልግሎቱን ለማስፈትና ለበርካታ እናቶች እንዲደርስ ለማድረግ የገንዘብ አቅም የሌላቸው ነገር ግን ሰርተው መለወጥ የሚፈልጉ እናቶችን ማገዝ ቢሆንም የቦታ ጥበት ማነቆ ሆኖብናል የሚሉት አቶ ዮሐንስ፤ ከግለሰብ ተከራይተው በያዙት አነስተኛ ግቢ ውስጥ አገልግሎቱ እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ይህንን የአቅመ ደካማ እናቶችን ያሳረፈ ነፃ አገልግሎት በስፋት ተደራሽ በሚሆንበት ስፍራ ለመስጠት የሚያስችለንን ሁኔታ ቢያመቻችልን የበለጠ ለመስራት እንፈልጋለን ብለዋል።
የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽ/ቤት የህጻናት ባለሙያ የሆኑት ወ/ሪት ቃልኪዳን ተስፋዬ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የገንዘብ አቅም የሌላቸው እናቶች ስራ ለመስራት ቢፈልጉም ልጆቻቸውን ማቆየት የሚችሉበት ቦታ ስለማይኖራችሁ ከፍተኛ ችግር ያጋጥማቸዋል። ይህ ሁኔታ በዚህ ማዕከል ተቀርፎ እናቶች ልጆቻቸውን በማዕከሉ አስቀምጠው ያለ ሃሳብ ስራቸውን ሲሰሩ ውለው ይመለሳሉ። ህፃናቶቹም ለጤናቸው አደገኛ በሆኑ  ቦታዎች ከመዋል ይልቅ እንክብካቤ ማግኘት በሚችሉበት ስፍራ ትምህርታቸውን እየተማሩ እንዲቆዩ መደረጉ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ህጸናቱ በቀላሉ በበሽታ እንዳይያዙና ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ ያደርጋቸዋል ሲሉ ተናግረዋል። ካሌብ ፋውንዴሽን ባለፉት 6 ዓመታት በህጻናትና ሴቶች ላይ እየሰራ የሚገኝ ድርጅት ነው።


Read 1395 times