Print this page
Saturday, 25 September 2021 00:00

ጉዞ ወደ ኳታር

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 • ለዓለም ዋንጫ የሚያልፉ አገራት በFIFA 12 ሚሊዮን ዶላር ይከፈላቸዋል፡፡
      • ጋናና ዚምባቡዌ ዋና አሰልጣኞቻቸውን አባርረዋል፡፡
      • ለዓለም ዋንጫ በማለፍ ተብሎ ለዋልያዎቹ ልዩ ቦነስ አልተሰጠም
      • ባፋናዎቹ ለዓለም ዋንጫ ካለፋ እያንዳንዳቸው ከ16 , 753 ዶላር በላይ ያገኛሉ፡፡
      • ጥቁሮቹ ክዋክብቶች አፍሪካ ዋንጫን ለማሸነፍና በዓለም ዋንጫ እስከ ግማሽ ፍፃሜ ለመድረስ 10 ሚሊዮን ዶላር በጀት አላቸው፡፡
      • ዚምባቡዌ ለዓለም ዋንጫ ካለፈች ለአሰልጣኙ 600ሺ ዶላር ቃል ተገብቷል፡፡

    ከደቡብ አፍሪካ ጋር ለሚደረጉት ወሳኝ የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ግጥሚያዎች ጥሪ የተደረገላቸው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች
    ግብ  ጠባቂዎች
ፋሲል ገ/ሚካኤል (ባህር ዳር ከተማ)፣ ተክለማርያም ሻንቆ (ሲዳማ ቡና) እና ጀማል ጣሰው (አዳማ ከተማ)
    ተከላካዮች
መናፍ ዐወል (ባህር ዳር ከተማ)፣ ያሬድ ባዬ ( ፋሲል ከነማ)፣ አስቻለው ታመነ (ፋሲል ከነማ)፣ ደስታ ዮሐንስ (አዳማ ከተማ)፣ ሱሌይማን ሀሚድ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ረመዳን የሱፍ (ወልቂጤ ከተማ)፣ አሥራት ቱንጆ (ኢትዮጵያ ቡና) እና ምኞት ደበበ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
    አማካዮች
መስዑድ መሐመድ (ጅማ አባጅፋር)፣ አማኑኤል ዮሐንስ (ኢትዮጵያ ቡና)፣ ታፈሰ ሰለሞን (ኢትዮጵያ ቡና)፣ ጋቶች ፓኖም (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ይሁን እንደሻው (ፋሲል ከነማ)፣ ሱራፌል ዳኛቸው (ፋሲል ከነማ)፣ ሽመልስ በቀለ (ኤልጎውና)
   አጥቂዎች
ሽመክት ጉግሳ (ፋሲል ከነማ)፣ አቡበከር ናስር (ኢትዮጵያ ቡና)፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ጌታነህ ከበደ (-)፣ አቤል ያለው (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ቸርነት ጉግሳ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ መስፍን ታፈሰ (ሀዋሳ ከተማ)

            ኳታር በ2022 እኤአ ላይ የምታስተናግደው 22ኛው የዓለም  ዋንጫ 422 ቀናት ቀርተዋል። በአፍሪካ ዞን በሚደረገው ማጣርያ ላይ ከቅድመ ማጣርያው እንስቶ 54 አገራት የተሳተፉ ሲሆን 67 ጨዋታዎች ተካሂደው 140 ጎሎች ከመረብ አርፈዋል፡፡ የምድብ ማጣርያው ላይ ከሚሳተፉት 40 አገራት 38 ቡድኖች የመጀመርያ እና ሁለተኛ ዙር  ግጥሚያዎችን አድርገዋል። ሞሮኮ እና ጊኒ በወቅታዊው የፖለቲካ ቀውስ ሳቢያ በመደበኛው መርሃ ግብር ሳይጋጠሙ ቀርተዋል፡፡ በሁለት ዙር ጨዋታዎች ላይ ከየምድባቸው ሙሉ 6 ነጥብ በመያዝ  ወደ ኳታር የሚያደርጉትን ጉዞ የቀጠሉት በምድብ 2 ቱኒዚያ፤ በምድብ 3 ናይጄርያ፤ በምድብ 6 ሊቢያና በምድብ 8 ሴኔጋል ናቸው፡፡
በዓለም ዋንጫ ላይ ለአፍሪካ የተመደበው የተሳትፎ ኮታ ለአምስት ብሄራዊ ቡድኖች እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለዚህም በኮንፌደሬሽኑ በስድስት ዙር ከሚደረጉ የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች በኋላ ከየምድባቸው በመሪነት ያጠናቀቁት 10 ብሄራዊ ቡድኖች  በመጨረሻው የጥሎ ማለፍ ማጣርያ ተገናኝተው በ22ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ አፍሪካን በመወከል የሚሰለፉት አምስት አገራት ይወሰናሉ፡፡  ለዓለም ዋንጫ የሚያልፉ አገራት በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር FIFA 12 ሚሊዮን ዶላር ይከፈላቸዋል፡፡
ምድብ 7 ላይ ከሁለት ዙር የምድብ ማጣርያ ግጥሚያዎች  በኋላ  ደቡብ አፍሪካ በ4 ነጥብና በ1 የግብ ክፍያ መሪነቱን ስትይዝ፤ ጋናና ኢትዮጵያ እኩል 3 ነጥብ ያለምንም የግብ ክፍያ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃዎች ላይ ተከታትለው ተቀምጠዋል፡፡  ዚምባቡዌ በ1 ነጥብ እና በ1 የግብ እዳ 4ኛ ነች። ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ 7 ላይ በሁለት ዙሮች በተካሄዱ ጨዋታዎች የተመዘገቡት ውጤቶች ተቀራራቢ መሆናቸው በቀጣይ የሚከናወኑትን 3ኛ እና 4ኛ ዙር የማጣርያ ግጥሚያዎች አጓጊ አድርጓቸዋል። የኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ዋና አሰልጣኞች በቀጣይ ጨዋታዎች ላይ መስራታቸውን ሲቀጥሉ የጋና እና የዚምባቡዌ ዋና አሰልጣኞች ግን ከሃላፊነታቸው ተባርረዋል፡፡  
ዋልያዎቹ ከባፋናዎቹ መሪነቱን ለመንጠቅ
በዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሁለቱ ዙር ጨዋታዎች  ተስፋ ሰጭ አቋሙን አሳይቷል።  ዋልያዎቹ በመጀመርያ ጨዋታቸው በኬፕ ኮስት ስታድዬም  ከጥቁሮቹ ክዋክብቶች ጋር በተገናኙበት ጨዋታ በጠባብ ውጤት 1ለ0 የተሸነፉ ቢሆንም፤ ኳስ ይዘው በመጫወትና የጋናን ምርጥ ፕሮፌሽናሎች  ተቋቁመው ጨዋታውን በመጨረስ ተደንቀዋል፡፡ የዚምባቡዌ  አቻቸውን ባህርዳር ስታድዬም ላይ ባስተናገዱበት ጨዋታ ደግሞ ድራማዊ ትእይንቶች ከተፈጠሩ በኋላ 1ለ0 በማሸነፍ በምድቡ  ተፎካካሪነት የሚቀጥሉበትን እድል አለምልመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የምድቡን ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታዎች መስከረም 26 በባህርዳር እንዲሁም መስከረም 30 በጆሃንስበርግ  ከተሞች ከደቡብ አፍሪካ አቻው ጋር የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ዋልያዎቹ ወደ ኳታር ጉዟቸውን ለማሳካት በሁለቱ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ከፍተኛውን ውጤት ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል፡፡ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከጨዋታዎቹ በፊት በቂ ዝግጅት ለማድረግ በመጀመርያ ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ ዋልያዎቹም ከመስከረም 12 ጀምሮ ጥሪውን በመቀበል መደበኛ ልምምዳቸውን ወደ ባህር ዳር በማቅናት ጀምረዋል፡፡
‹‹ምድባችን በመሪነት ለማጠናቀቅ እንችላለን›› ቤልጅማዊው ሁጎ ብሩስ
ደቡብ አፍሪካ በመጀመርያ ዙር ጨዋታ ሃራሬ ላይ ከዚምባቡዌ ጋር ያለምንም ግብ አቻ ከተለያየች በኋላ በሁለተኛ ዙር ጨዋታ በጆሃንስበርግ ጋናን 1ለ0 በማሸነፍ ምድቡን እየመራች እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሁኔታው ለደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሁጎ ብሩስ ከፍተኛ በራስ መተማመን ፈጥሮላቸዋል፡፡ ‹‹በሃላፊነት የያዝኩት በጣም ጥሩ ጨዋታን  በልበ ሙሉነት የሚጫወት ቡድን ነው። በወጣቶቹ ተጨዋቾች የምወደውን ቆራጥነትና የማሸነፍ ፍላጎት አይቻለሁ። በሁለት ጨዋታ ሊገኙ ከሚችሉት ስድስት ነጥቦች አራቱ  አግኝተናል፤ እንደጠበቅኩት ነው›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሁግ ብሮስ ከኢትዮጵያ ጋር ለሚያደርጉት የደርሶ መልስ ጨዋታ በጊዚያዊ ምርጫ 34 ተጨዋቾችን ከአገር ውስጥ እና ከውጭ ሊጎች ጠርተዋል፡፡ የተጨዋቾች ስብስቡ በወጣቶች የተሞላ ሲሆን ከደቡብ አፍሪካ ትልልቅ ክለቦች ሱፕር ስፖርት ዩናይትድ፤ ካይዘር ቺፍ፤ ሜመሎዲ ሰንዳውንስ እና ኦርላንዶ ፓይሬትስ የተመለመለየ ቁልፍ ተጨዋቾች ይገኙበታል። 23 ተጨዋቾች የሚገኙበትን የመጨረሻ ዝርዝር በዛሬው ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።  ባፋናዎቹ የጋናን ብሄራዊ ቡድን ባሸነፉ ማግስት ቤልጅማዊው ወደ ትውልድ አገራቸው ቤልጅዬም የስራ ፈቃዳቸውን ለማግኘት መጓዛቸው የአገሪቱን ሚዲያዎች አላስደሰተም።  ከኢትዮጵያ ከሚያደርጓቸውዎች ጨዋታ በፊት የተወሰኑ የሊግ ጨዋታዎችን ተመልከትው የተጨዋቾች ስብስባቸውን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል በሚል ትችት ነው። እንደ ደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን ገለፃ አሰልጣኙ በአምስት አመታት ኮንትራት ለመስራት ሃላፊነቱን የያዙ ሲሆን በጊዜያዊ ወረቀት ሲሰሩ ቆይተው ከሳምንት በፊት ፈቃዳቸውን ለማደስ ወደ አገራቸው እንደተጓዙ አስታውቋል፡፡ ዋና አሰልጣኙ ‹‹ኢትዮጵያን በደርሶ መልስ ጨዋታዎች በማሸነፍ ምድቡን በመሪነት ማጠናቀቅ እንችላለን›› ብለው የተናገሩት ጊዜያዊ የተጨዋቾች ስብስባቸውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡
የደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን በ2021 ካሜሮን ለምታዘጋጀው  33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ባፋና ባፋናዎቹ ባለማለፋቸው ከፍተኛ ቁጭት አድሮበታል፡፡ ደቡብ አፍሪካዊውን አሰልጣኝ ሞሌፊ ንቴስኪ  በማባረር ቤልጅማዊውን ሁጎ ብሩስ በሃላፊነቱ ላይ  ያስቀመጣቸው ቢያንስ ወደ ዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ይመልሱናል በሚል ተስፋ ነው፡፡
ሁጎ ብሮስ በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ የካሜሮን ብሄራዊ ቡድንንን እያሰለጠኑ  የአፍሪካ ዋንጫ ያሸነፉ ሲሆኑ፤ በተጨዋችነት ዘመናቸው በ1986  የዓለም ዋንጫ ለቤልጅዬም ብሄራዊ ቡድን ተሰልፈዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካ የእግር ኳስ ፌደሬሽን  ባፋና ባፋናዎቹ ለ22ኛው የዓለም  ዋንጫ ካለፉ ለእያንዳንዱ የብሄራዊ ቡድኑ አባል በነፍስ ወከፍ ከ16 , 753 ዶላር በላይ (250 ሺ የደቡብ አፍሪካ ራንድ) እንደሚበረከትላቸው ያሳወቀ ሲሆን በማጣርያው ላይ በሚደረጉ ጨዋታዎች ለድል 4022 ዶላር ለአቻ ውጤት ደግሞ 2011 ዶላር እያሰበ ይገኛል፡፡
ጥቁሮቹ ክዋክብቶች ዋና አሰልጣኝ
እያፈላለጉ ናቸው
የጋና ዋና አሠልጣኝ  የነበሩት ቻርልስ አኮኖነር  ከሜዳቸው ውጭ በደቡብ አፍሪካ ተሸንፈው ምድቡን የሚመሩበትን እድል ከተነጠቁ በኋላ ለ20 ወራት የቆዮበትን ሃላፊነት በማጣት ተባረዋል፡፡  ቡድናቸው በሁለት የዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች የተጨዋቾች ስብስቡን ሙለሙሉ ለማጠናከር አልቻሉም ነበር፡፡በተለይ  በኮሮና ገደብ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የሚጫወቱና  በጉዳት ሳቢያ ምርጥ ተጨዋቾቻቸውን ማሰልፍ አለማቻላቸው ውጤት አሳጥቷቸዋል።  የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ሃላፊዎች በአገር ውስጥ ያሉትን ተጨዋቾች በቡድን ስብስቡ መጠቀም አለመቻሉን ከመውቀሱም በላይ ጥቁሮቹ ክዋክብቶች በደቡብ አፍሪካ በመሸነፋቸውና ከኢትዮጵያ ጋር በተደረገው ጨዋታ ደካማ አቋም ማሳየታቸው አሰልጣኙን ከየአቅጣጫው ሲያስተቻቸው ሰንብቷል፡፡ አኮኖር በጋና ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ለ21 ወራት በነበራቸው ቆይታ 10 ጨዋታ አድርገው 4 ድል ሲያደርጉ በሁለት አቻ ወጥተው በ4 ሽንፈት ገጥሟቸዋል፡፡  
የጋና እግር ኳስ ፌደሬሽን አዲስ ዋና አሰልጣኝ ለመቅጠር ኮሚቴ አቋቁሞ እየሰራ ሲሆን ሰርቢያው ሚሎቫን ራጃቬክ ዳግም ሊጠሩ እንደሚችሉ እየተገለፀ ነው፡፡ ሰርቢያዊው የጋናን ብሄራዊ ቡድን በ2010 እኤአ ላይ ደቡብ አፍሪካ ላስተናገደችው 19ኛው የዓለም ዋንጫ በማብቃት እስከ ሩብ ፍፃሜ ደርሶ የላቀ ውጤት እንዲያስመዘገቡ ያስቻሉ ነበሩ፡፡ በ1998 የዓለም ዋንጫ ከፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ጋር ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ማርሴይ ዴሳይ ም ጥቁሮቹን ክዋክብቶች በሃላፊነት ሊረከብ እንደሚችልም ተወርቷል፡፡
የጋና እግር ኳስ ፌደሬሽን ለጥቁሮቹ ክዋክብቶች ከመንግስት ባገኘው ድጋፍ ከ25 ሚሊዮን ዶላር  በላይ በጀት  መድቧል፡፡  በአፍሪካ ዋንጫ እና በ2022 የዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች ላይ ብሄራዊ ቡድኑ ለሚያደርገው ተሳትፎ ፈሰስ ያደረገው እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህ በጀት በዋናነት ከአርባ ዓመት በኋላ አራተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ድል እንዲያስመዘግቡ እና ለዓለም ዋንጫ በማለፍ እስከ ግማሽ ፍፃሜ እንዲደርሱ በተያዘው እቅድ ነው፡፡ ፌደሬሽኑ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ለሚመዘገብ ውጤት የቦነስ ክፍያ እየሰጠ ሲሆን ኢትዮጵያን 1ለ0 ካሸነፉ  በኋላ የቡድኑ አባላት በነፍስ ወከፍ 5000 ዶላር ተሰጥቷቸዋል፡፡
ዚምባቡዌ ለዓለም ዋንጫ ካለፈች ለአዲሱ አሰልጣኝ 600ሺ ዶላር ቃል ተገብቷል
የዚምባቡዌ አሰልጣኝ የነበሩት ክሮሽያዊው  ሎጋሩሲክ በሁለተኛ ዙር ከኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ጨዋታ 1ለ0 መሸነፋቸው ከስራቸው አፈናቅሏቸዋል፡፡ የአገሪቱ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከጨዋታው በፊት ተጫዋቾቹን ድል እንዲያስመዘግቡ ለማነሳሳት 64,000  ዶላር የቦነስ ሽልማት ለመስጠት ቃል መገባቱንም ኒው ዚምባቡዌያን ዘግቦ ነበር፡፡ ኢትዮጵያና ዚምባብዌ ከ1984 ጀምሮ በሁሉም ውድድሮች ለአምስተኛ ጊዜ በተገናኙበት ጨዋታ ላይ ኢትዮጵያ አራተኛውን ድል ካስመዘገበች በኋላ ዚምባቡዌ በምድቡ ተፎካካሪ ሆና የምትቀጥልበት እድል ተሟጥጦባታል፡፡  የዚምባብዌ  ሚዲያዎችም ቡድናቸው ከደቡብ አፍሪካ አቻው ጋር በሜዳቸው 0ለ0 ከተለያየ ጀምሮ ዝድራቭኮ ሎጋሩሲክ ካሃላፊነታቸው እንዲነሱ ያደረጉትን ጉትጎታ በኢትዮጵያ ከደረሰው ሽንፈት በኋላም አጋግለስውታል። ይህንኑ ተከትሎም ክሮሽያዊው አሰልጣኝ ተባርረዋል፡፡ የአገሪቱ እግር ኳስ ፌደሬሽን በዋና አሰልጣኙ ሃላፊነት ትዕግሥት ማብዛቱን ማስተዋል ይቻላል፡፡ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ያለፈውን 1 ዓመት በሃላፊነት  የቆዩት ዝደራቫኮ ሎጋሩሲክ 14 ጨዋታዎች አድርገው 1 ብቻ አሸንፈዋል፡፡ ከሃላፊነታቸው  ሲነሱ በኋላ በካሳ ክፍያ እና ደሞዝ እስከ 200ሺ ዶላር ማግኘታቸውን ብዙዎቹን የዚምባቡዌ ሚዲያዎች አበሳጭቷቸዋል፡፡
የዚምባቡዌ የእግር ኳስ ፌደሬሽን በክሮሽያዊው ምትክ ሃላፊነቱን በሞግዚትነት ያስረከበው  ኖርማን ምፔዛ ለተባሉ የቀድሞ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋች ነው፡፡ አዲሱ ዋና አሰልጣኝ ዚምባቡዌ ከጋና ጋር ለምታደርገው የደርሶ መልስ ጨዋታ ላይ እንዲሰሩ ከባድ ሃላፊነት የተጣለባቸው ሲሆን የቅጥር ኮንትራታቸው  ለሶስት ወራት ብቻ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ኖርማን ምፔዛ ብሄራዊ ቡድናቸውን ለዓለም ዋንጫ ሊያሳልፉ ከበቁ 600ሺ ዶላር ቦነስ እንደሚታሰብላቸው በፌደሬሽኑ የተገለፀ ሲሆን ይህ ሽልማት ፊፋ ለዓለም ዋንጫ ለሚያልፉ አገራት ከሚከፍለው የገንዘብ ሽልማት 5 በመቶው እንደሚታሰብም ተጠቁሟል፡፡

Read 10433 times