Print this page
Sunday, 03 October 2021 18:25

“ባልደራስ” አዲስ ከሚመሰርተው መንግስት ምን ይጠብቃል?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አዲስ አበባን ራስ ገዝ የማድረግ አላማ አንግቦ የሚንቀሳቀሰው ባልደራስ ለእውነተኛና ለዲሞክራሲ ፓርቲ በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ውጤት አልቀናውም። የአዲስ አበባን ም/ቤት ሙሉ በሙሉ ያሸነፈው ብልጽግና ፓርቲ እንደሆነ ይታወቃል። ከሰሞኑ ወ/ሮ አዳነች አበቤን ከንቲባ አድርጎ በሰየመው አዲሱ የአዲስ አበባ አስተዳደር ምስረታ ላይ ፓርቲው ምን ይላል? ተቀዋሚዎች በመንግስት አስተዳደር ውስጥ መካተታቸው ፋይዳው ምንድን ነው? ከአስተዳደሩ ጋር ምን አይነት  የሥራ ግንኙነት ይኖረዋል? ባልደራስ ከአዲሱ የፌደራል መንግስት ምን ይጠብቃል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ከባልደራስ ስራ አስፈፃሚ ኢ/ር ጌታነህ ባልቻ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል። እነሆ፡-


  አዲስ የተመሰረተውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተመለከተ ምን አስተያየት አለዎት…?
እንደሚታወሰው፤ እኛ ከምርጫው ጋር ተያይዞ ስናነሳቸው የቆዩ ነበሩ። ከዚህ አንፃር፤ ይሄ አስተዳደር ወደ ስልጣን የመጣበት ምርጫ፣ ምን ያህል ፍትሃዊ ነው የሚለውን ስንመለከት፣ ብዙ ጥያቄዎች ያሉበት ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ኢትዮጵያ ከተጋፈጠችው የህልውና አደጋ አንፃር፣ መጀመሪያ በሃገሪቱ ላይ የተጋረጠው አደጋ በርብርብ ይስተካከልና ቀሪውን ጉዳይ ወደፊት እንነጋገርበታለን በሚል ትተነው ነው። በአዲስ አበባ  ያነሳናቸው ጥያቄዎች በርካታ ናቸው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጥያቄዎቻችን አሁንም እንዳሉ ናቸው፡፡ አሁን በተመሰረተው የከተማ አስተዳደር ውስጥም አዲስ አበቤ በአግባቡ ተወክሏል ብለን አናምንም፡፡ የከተማዋን ነዋሪዎች የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጥያቄዎች የሚፈታ አይመስለንም። እንደሚታወቀው የአዲስ አበባ ነዋሪ በርካታ የኢኮኖሚ ማነቆዎች አሉበት፣ የትራንስፖርት የስራ አጥነት የመሳሰሉት ሰፊ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው። ለእነዚህ ጥያቄዎች ይሄ አስተዳደር ምን ያህል መልስ ይሰጣል የሚለውን በሂደት የምናየው ይሆናል። በፖለቲካው ረገድ አሁንም የዘረኝነት ችግር አለ ብለን እናምናለን። አሁንም ቁልፍ የከተማ አስተዳደሩ የስልጣን ቦታዎች በውግንና የተያዙ ናቸው፡፡ በባለሙያዎች የተዋቀረ አስተዳደር ለመፍጠር ጥረት አልተደረገም፡፡ ወደፊት እነዚህን ሁሉ ጥያቄዎች ማንሳታችን፣ የመታገያ አጀንዳችን ማድረጋችን አይቀርም፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ እንዳልኩት፣ አሁንም ይሄን ለማድረግ ጊዜው ምቹ አይደለም፡፡ አሁን በአንድነት ቆመን ልንታገለው የሚገባን በሃገሪቱ ላይ የህልውና አደጋ የጋረጠ ሃይል አለ፡፡ ሌላውን በኋላ እንደርስበታለን።
አዲስ በተዋቀረው የከተማዋ አስተዳደር ውስጥ ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ በተመለከተ ምን ይላሉ? የባልደራስ አመራሮች ተመሳሳይ እድል አልገጠማቸውም?
በዚህ ላይ ብዙ መናገር የምችለው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን አንድ አካል ተመርጫለሁ ብሎ ስልጣን ከያዘ በኋላ ስልጣን ማደላደልና ማደል፣ የሱ ሥልጣን ነው የሚሆነው። ሊታዘዝልን ከእኛ ጋር አብሮ ሊሰራ ይችላል የሚሉትን የመምረጥ ስልጣኑ የእነሱ ስለሆነ አድርገውታል፡፡ ከዚህ ባለፈ ተቃዋሚዎች ስልጣን ማግኘታቸው ምን ውጤት ያመጣል ከተባለ፣ ብዙም ውጤት አያመጣም ነው መልሱ፡፡ የሚያስፈፅሙት የብልፅግናን ፖሊሲና ፕሮግራም ነው የሚሆነው፡፡ ይሄ ማለት ተግባራቸው እንደ ብልፅግና ሰው ይሆናል ማለት ነው፡፡ እንደ ባልደራስ እኛ ህዝባችንን ምረጡን ብለን አደባባይ የወጣነው፣ የራሳችንን ፖሊሲ ይዘን መጥተን ለማስፈፀም ነው እንጂ በብልጽግና ውስጥ ለመሾም አይደለም፡፡ እንዲህ አይነቱ ፍላጎትም የለንም፡፡ ብልጽግናዎች እኛን ባለማካተታቸውም የሚቀርብን ነገር የለም። እኛ አሁንም እንደ በፊቱ የህዝባችን ድምጽ ሆነን እንቀጥላለን፡፡ ከዚህ ዓላማችን ወደ ኋላ አንልም፡፡ እኛ መሰረታዊ ጉዳያችን ማንም በስልጣን ላይ ይቀመጥ፤ የህዝቡ ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ እንዲያገኝ እንጥራለን። ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው ሁሉ ባልደራስ የህዝባችንን ድምጽ እያሠማና፣ ስልጣን ላይ ያለውን አካል እየሞገተ ይቀጥላል፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በመንግስት አስተዳደር ውስጥ መካተት፣ ለሃገሪቱ የፖለቲካ ባህል አዲስ ነገር ይዞ የመጣ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። ከዚህ አንፃርስ እርስዎ ምን ይላሉ?
ምናልባት ወደ ኋላ መለስ ብለን ብንመለከት፣ በ1997 ዓ.ም ከ100 በላይ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ፓርላማ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች በገቡበት ወቅት የሀገሪቱ ዲሞክራሲ ተሻሽሏል? የሃገሪቱ የፖለቲካ ባህል ተለውጧል? እንዲያውም ወደ ዜሮ ነው የወረደው፡፡ ስልጣን ቆነጣጥሮ ማደላደል ዲሞክራሲያዊ አያስብልም ህዝብ በነፃነት ሲመርጥ ብቻ ነው ፖለቲካው ዘምኗል፤ ዲሞክራሲያዊ ሆኗል የሚባለው እንጂ ስልጣን ተቆነጣጥሮ ስለተከፋፈለ አይደለም፡፡ እነዚህ ሹመት ያገኙ ሰዎች እኮ በፓርቲያቸው በኩል ሲታገሉ የራሳቸውን አላማ ይዘው ነው። አሁን ታዲያ ሲሾሙ የማንን አላማ ሊያስፈጽሙ ነው? ሹመት ተለዋዋጭ መሆኑ እንዳለ ሆኖ የተቃዋሚዎች ሹመት ማግኘት ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ አንዳች ነገር ያመጣል ማለት ስህተት ነው። ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም ምንም የሚያመጣው የዲሞክራሲ ለውጥ አይኖርም፡፡
ከአዲሱ የከተማዋ አስተዳደር ምን አዳዲስ ለውጦችን ይጠብቃሉ?
ምንም አልጠብቅም፡፡ ምክንያቱም በህወኃት ዘመን ከነበረው አስተዳደር ምኑ ተለወጠ? መዋቅሩ ላይ ምን ተለወጠ? ምርጫ የህዝብ ውክልና ነው፤ ታዲያ እነዚህ ሰዎች በትክክለኛ ምርጫ የተወከሉ ናቸው? እኛ ትክክለኛ የህዝብ ወኪሎች ናቸው ብለን አናምንም። አስቀድሜ እንዳልኩህ፤ አሁን ያለንበት ጊዜ ለሃገር ህልውና ቅድሚያ የሚሰጥበት በመሆኑ ነው ነገሮቹን እያለፍን ያለነው እንጂ ብዙ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡
ባልደራስ ከሚያነሳቸው ጥያቄዎች አንጻር፣ ከአዲሱ የአዲስ አበባ አስተዳደር ጋር ምን አይነት ግንኙነት ይኖረዋል?
ሁለት ተግባራትን እናከናውናለን። አንደኛው፣ አስተዳደሩ የሚሰራቸውን ተግባራት በሙሉ በአንክሮ እንከታተላለን። ትኩረት የሚደረግባቸውን አንስተን ከህዝባችን ጋር እንወያያለን፡፡ በየትኛውም መስክ ላይ አስተዳደሩ የሚያደርጋቸውን አሉታዊ እንቅስቃሴዎች ለህዝቡ እናጋልጣለን፡፡ እንተቻለን ህዝባችን በውሳኔዎችና በተግባሮቹ እንዳይጎዳ ጥረት እናደርጋለን፡፡
ሁለተኛው፤ ህዝባችንን ከምንጊዜውም በተሻለ ተንቀሳቅሰን እናደራጃለን፡፡ በተለይ አዲስ አበባ በራሷ ልጆች መመራት እስክትችል ድረስ ትግላችን ይቀጥላል፡፡ በራሷ ተወላጆች እንዲሁም አዲስ አበቤዎች በመረጡት ሰው እስክትመራ ከተማዋ የምናደርገውን ትግል በሰላማዊ መንገድ አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ማንኛውንም ኢ-ፍትሃዊ ተግባራት እያጋለጥን እንቀጥላለን ማለት ነው፡፡
የፌደራል መንግስቱ ሰኞ ይመሰረታል… ይሄ አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ምን ጉዳዮችን ቅድምያ ሰጥቶ እንዲከውን ትሻላችሁ?
እንግዲህ አሁን ሃገሪቱ ለገባችበት ጦርነትና ቀውስ በእጅጉ የዳረገን የህገ መንግስት ማሻሻያ አለማድረግና የብሔራዊ መግባባት ሂደት ውስጥ አለመገባቱ ነው የሚል ግምገማ አለን፡፡ ከዚህ ሃገራዊ ቀውስ እንድንወጣ እንግዲህ በወሳኝነት መፍትሔው ላይ መስራት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ትናንት ዳተኛ የተሆነበት የብሔራዊ መግባባትና እርቅ ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ለዚህ ፖለቲካዊ ቁርጠኝት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ወር በኋላ ይጀመራል ይባላል፤ ግን በትክክል ይሄ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

Read 12112 times
Administrator

Latest from Administrator