Monday, 11 October 2021 11:15

ቀዳሚ ምኞቱ

Written by 
Rate this item
(9 votes)

   "--ጡረታ ወጥቼ በየማኪያቶ ቤቱ ለምን ላውደልድል? አለ። ከጓሮ የጸሎት ምንጣፍ የምታክል ሥፍራ አበጃጅቶ ዘንጋዳ ዘራባት፤ ዘንጋዳዋ ጊዜዋን ጠብቃ ራሷን ቀና አደረገች። አንድ ቀን፣ ከዳር ያለችዋ ያማረባት ዘንጋዳ ተቀንጥሳ ወድቃ አገኘ።--"
    ቀዳሚ ምኞቱ አራሽ መሆን ነበር። በወቅቱ መሬት ለባላባት እንጂ ላራሽ ስላልነበረ የቀለም ትምህርቱ ላይ ተጋ። ጊዜው ሲደርስ እርሻ ኮሌጅ ገብቶ ተመረቀ። ቤተሰብ ሲል፣ ሹመትና ዝውውር ሲል፣ አለቃ ሲጠምበት፣ ከተማ ለከተማ፣ ሚኒስቴር መ/ቤት ለሚኒስቴር መ/ቤት ሲንፏቀቅ፣ ከዚያ ለኮርስ ውጭ አገር፣ ልጅ ሲያስተምር፣ ለልጁ ሥራ ሲያፋልግ፣ ሲድር፣ አብዮት መጣ። መሬት ለመንግሥት እንጂ ላራሽ ሁሉ አይደለም ሲሉት፣ ልማታዊ መንግሥት መጣ። አሁን ቀናኝ ብሎ፣ በድብቅ ሲያስታምማት የኖረችውን የሙያ ፍቅሩን ቢቀሰቅሳት፣ በክልልህ የሚሉት መጣ። ለአንዳንዶች እንደ ሆነላቸው፣ ብሔሩ ሎተሪ ቀርቶ የሚሳቀቅባት ያልለየች ሰንካላ ዕጣ ሆነበችበት። በዚህ መሃል ጡረታህ ደርሷል፣ መንገድ ልቀቅ ተባለ።
በማህበር ተመርቼ  ያሠራሁት ቤቴ ነው ክልሌ፤ ለኔ ገነት የዐፀዴ ሥፍራ ነው ብሎ በሩጫው ዓመታት ሎሚ ተክሎ ነበር። ግቢው የፈረስ ከንፈር ታክላለች፤ ግን እንደ ዐቃቢት መቀነት ብዙ ጉድ አሸክሟታል። የአበሻ ጎመን ካመት ዓመት አጥቶ አያውቅም፤ የአበሻ ጎመን ያለ ቃርያ ምን ያደርጋል ብሎ ቃርያ ጨምሯል። ቡና ያለ ጤና አዳም፣ ክረምት ያለ በቆሎ፤ የበቆሎ ወዙ ዱባ። ወፎች እንኳን ከመሳፈርያቸው ጎራ ብለው እንደ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ፓርክ የሚያደንቁለት ሆነ።
ጡረታ ወጥቼ በየማኪያቶ ቤቱ ለምን ላውደልድል? አለ። ከጓሮ የጸሎት ምንጣፍ የምታክል ሥፍራ አበጃጅቶ ዘንጋዳ ዘራባት፤ ዘንጋዳዋ ጊዜዋን ጠብቃ ራሷን ቀና አደረገች። አንድ ቀን፣ ከዳር ያለችዋ ያማረባት ዘንጋዳ ተቀንጥሳ ወድቃ አገኘ። አንስቶ፣ ማ ቀነጠሳት? ከብት አይመስልም፤ ከብት በየት በኩል ገብቶ? ወፍም ሊሆን አይችልም፤ በምን አቅም?
ሌላ ቀን ሁለት ራስ ከሥር ተመንቅረው ወዲያ ተጥለው አገኘ። ኮቴ ባገኝ ብሎ ላይ ታች አለ፤ እንኳ የወፍ የሰይጣንም ኮቴ የለም። አሽክላ አጠመደ፤ አሽክላው እስከ ዛሬ ምንም አልያዘም።
(በምትኩ አዲሱ፤ ፋቡላ ከንደገና፣  ገጽ 269-270.)

Read 2014 times