Saturday, 09 October 2021 00:00

“6ኛው የአርአያ ሰው" ሽልማት በዮድ አቢሲኒያ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

መቀመጫውን በአሜሪካ ዳላ ቴክሳስ ያደረገው አድዋ የባህልና የታሪክ ህብረት፤  የአርአያ ሰው ሽልማት መስራች ነው፡፡
ከኢትዮጵያ የባህል አልባሳት ውጭ መልበስ፣ እራስን ካለማክበር ይቆጠራል  ይላል። ለሀገር ለወገን ብዙ የሰሩን ባመሰገንን ቁጥር፣ ብዙ የሚሰሩ ዜጎችን እንፈጥራለን ብሎ ያምናል ዲያቆን ፍሬው ሰይፉ፡፡  የአርአያ ሰው ሽልማት መርሃ ግብር ላለፉት አምስት ዓመታት በአሜሪካ ነበር የተካሄደው ስድስተኛው የአርአያ ሰው ሽልማት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ይካሄዳል።  አዲስ አድማስ ጋዜጣ ከመስራቹ ዲያቆን ፍሬው ሰይፉ ጋር ተከታዩን ቃለመጠይቅ አድርጓል።



                  ከምን ያህል ጊዜ በኋላ ነው ወደ አገርህ ከመጣህ?
በመሃል አንድ ሁለቴ ብመጣ  ስድስት ዓመት ያህል  ሳልመጣ ቆይቻለሁ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለስኩ ሁለት ሳምንትንት ሆኖኛል። እስካሁን ነገሮች ጥሩ እየሄዱ ነው።
ባህላዊ አልባሳትን ታዘወትራለህ፡፡ ሁሌም ነው?
ይሄ ልምድ አስራ አራት አመታትን አስቆጥሯል፡፡ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከ2000 ጀምሮ እነደዚህ ነው የምለብሰው፤ 365 ቀናት በአራት ዓመት አንዴም 366 ቀን ማለት ነው፡፡
ለስራና ለዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ?
አይከብድም! ምክንያቱም ለኔ በጣም ተመችቶኝ ነው የምለብሰው፡፡ መመቸት ወይንም ያለመመቸት ጭንቅላት ውስጥ ነው የሚያልቀው፡፡ በትክክል አሁን ትውልዱ የሚያደርገው ነገር የሚመች ነው ወይ ካልን ብዙ ምቾት የሚነሱ ነገሮች እናያለን፤ ግን ትውልዱ ደግሞ ተመችቶኛል ብሎ እየለበሰ ነው፤ ስለዚህ መመቸት ወይንም ያለመመቸት መጀመሪያ ጭንቅላት ላይ ነው የሚሰራው። ዓለም የሚያከብርሽ መጀመሪያ ራሽን ስታከብሪ ነው የራስነ ጥሎ ስልጣኔ የለም፡፡ ስልጣኔ ማለት የራስን እያከበሩ መኖር ማለት ነው፡፡ ምን አልባት እኛ ያለን የህይወት ዘይቤ እንዳይመች አደርጎት ሊሆን ይችላል፡፡ የሆነው ሆኖ ግን ስራዬ ብለሽ ከያዝሽው ግን  ለዛ ነገር የሚያስፈልገውን እያበጀሽ ትሄጃለሽ፡፡ እርግጥ ቀላል አይደለም አብዛኞቹ ልብሶች ነጭ እንደመሆናቸው ጥንቃቄ በጣም ይፈልጋሉ ሲታጠቡ እነኳን ከሌላ ልብስ ጋር ተደባልቀው መታጠብ ላይኖርባቸው ይችላል። ደረቅ እጥበት ብቻ ሊፈልጉም ይችላሉ፡፡ እሱ ደግሞ ራሱን የቻለ ሌላ ወጪ ነው፡፡ ስለዚህ በጣም በጉዳዩ ላይ ማመን ያስፈልጋል፡፡
ወደ አርአያ ሰው ሽልማት እንምጣ። መቼ ተመሰረተ አላማውስ?
የተመሰረተው እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ2006 ዓ.ም ነው አስካሁን ዘጠነኛው መሆን ነበረበት ግን በመሃል እኔ ወደ አሜሪካ ስሄድ እዛ ያለውን ማህበረሰብ እስካውቅና ማን አንዴት ነው የሚሸለመው የሚለው መልስ እስኪያገኝ ለሶሰት ዓመታት ተቋርጦ ቆይቷል፡፡ ዋና ዓላማም ምንድን ነው? እኛ እንዳለመታደል ሆኖ ከመመሰጋገን ከመከባበር ይልቅ መጠላለፍ ነው የሚቀናን። ብዙ ጊዜ ሰዎች ብዙ መልካም ነገሮችን ከማመስገን ይልቅ የተሳሳቷትን ጥቂት ነገር አጉልተን እያሳየን፣ ሰዎች ለተሻለ ነገር እራሳቸውን እንዳያዘጋጁ እናደርጋለን፡፡ ስለዚህ ይህን ለመቅረፍ ምን እናድር አርአያ ሰዎች፤ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎች ያስፈልጉናል፤ ቢኖሩንም ግን ሳናመሰግናቸው ሃሳባቸው ተቀብሮ እንዳለነ ሲገባን የአርአያ ሰው ሽልማት በ2006 ዓ.ም አርአያዎቻችን ለማመስገን ተወለደ፡፡ ያኔ እኔ ካለሁበት ነው የተነሳው። ለረጅም ዓመታት የኢትዮጵያን ባህላዊ አልባሳት ዲዛይን በማድረግ፣ የቆዩት እማማ ፅዮን አምዶም (ኮሎኔል አማረ ኣምዶም እህት)  በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሞዴልና ዲዛይነር የነበሩት፣ የክብር ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ወላጅ እናት እማማ ቅድስት የታወቁ ዲዛይነር ነበሩ። እሳቸው በህይወት ባይኖሩም፣ ይህንን መንገድ የክብርት ፕሬዚዳንቷ  እህት ወ/ሮ ራሔል አስቀጥለውት፣ አሁንም “ቅድስት ጥበብ” አለ፣ እማማ ደስታ (ዲዛይነር ደስታ) “የህዝብ ለህዝብን” ሙሉ ልብስ ያዘጋጁ እና ለ365 ቀናት የጥበብ ልብስ በመልበስ ከወንድ ፕ/ር ኤፍሬም ይስሀቅን ከሴት  ደግሞ የህሊና ገንቢ ምግቦች ፋብሪካ ባለቤት ወ/ሮ ገነት በለጠን በዛን ጊዜ ለ13 ዓመታት ጥበብ በመልበስ፣ ለ53 ዓመታት ብራና ዳምጠው ቀለም በጥብጠው፣ ብዕር ቀርፅው ታሪክን የዘገቡ መምህር ጌታ መክብብ የሚባሉ  ታዋቂ የብራና ፀሃፊ …. እነዚህ እነዚህን የመሳሰሉ የሙካሽ ሠራተኞች ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጀምሮ ለነገስታቱ ይሠሩ የነበሩ ትልልቅ የሀገር ባለሙያዎችን ፈልጎ፣ እነሱን በማግኘት ያመሰገንበት ሁኔታ ነው የመጀመሪያው ሽልማት፡፡
በቀጣይ ዓመት ሁለተኛው ሽልማት ደግሞ መታሰቢያነቱን ለቱሪዝም አባት አቶ ሀብተስላሴ ታፈሰ እንዲሁም፣ ለኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች፣ ለኢትዮጵያዊቷ ሆሜር ተብለው ለሚታወቁት ልበ ብርሃኗ እማሆይ ገላነሽ እና ለፊደል ገበታ አባት ተስፋ ወልደስላሴ እንዲሁም አወዘ ውስጥ እነ ጋሽ አበራ ሞላ፣ ጌታ መሳይ አበበ፣ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ እነ አለሙ አጋ እና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ የሆኑ ባለውለታዎች የተሸለሙበት ነበር፡፡
ከዛ ሶስተኛው ሽልማት ደግሞ በአሜሪካ ሀገር ተደረገ ኮሚኒቲውን በፍፁም ተህትና ሲያገለግሉ የነበሩ ከዛ እልፍ ሲል ደግሞ እንደ ማህበረሰብ እንደ ዜጋ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ለነበሩ እንደነ ታማኝ በየነ፣ የአምባሰሏ ንግስት ማሪቱ ለገሰ የመሳሰሉት ተሸልመዋል፡፡
ይኸው ዘንድሮ ስድስተኛው የአርአያ ሰው ላይ ደርሰናል፡፡ ዘንድሮስ ሽልማቱ በምን መስፈርት ነው የሚሰጠው?
እንደ ተቋም አድዋ የባህልና የታሪክ የሚባል አለ፤ መቀመጫውን አሜሪካን ሀገር ያደረገ ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ መሰረቱ ቴክሳስ የሆነ፣ በሃገሩ እውቅና ያለው፤ አርአያ ሰው የዛ ተቋም አንድ አካል ነው፡፡ በዋናነት ታሪክ ባህልና ቅርስን ነው የሚያስተዋውቀው ተቋሙ፡፡ ይልቁንም አሜሪካን አገር ተወልደው ለሚያድጉ ህፃናት እራሳቸውን ወደ ማወቅ እንዲመጡ፣ በራሳቸው እውቀት ላይ ተመስርተው ታሪካቸውን እንዲያውቁ በትምህርት ቤት ከሚማሯቸው ልጆች ጋር ስለ ማንነታቸው በደንብ እንዲናገሩ፣ ክህሎታቸውን ማሳደግ ነው፡፡ በዘርፉ ደግሞ በባህል በቱሪዝም በቅርስ አይተኬ የሚባል ትልልቅ ስራዎች ሰርተው ያለፉ እንዲሁም በህይወት ያሉ ኢትዮጵያውያን በዚህ ዝግጅት ላይ የሚዘከሩበት የሚታሰቡበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ወደ መስፈርት  ስንመጣ  የኛ ሽልማት ውስጥ ምንም አይነት የተለየ ማወዳደሪያ የለም የሚወዳደርም የለም ሲጀምር፡፡ ዋናው ነገር አይተኬነት ነው። ለዘርፉ ዋጋ እየከፈሉ የሚያገለግሉ፣ እየተከፈላቸው ሳይሆን አስከ ህይወት መስዋትነት እየከፈሉ የሚያገለግሉ ናቸው። እርግጥ እንደዚህ አይነት ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት አሉ ወይ ቢባል የሉም ነው መልሱ፡፡ ለዛም ነው በብዛት የማናወዳድረው። በጣም ትንሽ ከመሆናቸው አንጻር እንሳሳላቸዋለን። ድንገት በሆነ ዘርፍ ላይ  ሁለት ሰዎችን ብቻ ልናገኝ እንችላለን፤ እነዚህ ሰዎች ደግሞ በየተሰማሩበት የቱሪዝም መስክ በጣም የሚገርም አይነት አቅም ያላቸው እየተከፈላቸው ሳይሆን እየከፈሉ እንደዜጋ ኃፊነታቸውን እየተወጡ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ታዲያ እንደዚህ አይነት ዜጎችን ማወዳደር በራሱ የነሱን ድካም ዋጋ ማሳጣት ነው፡፡ የሚሰሩት ለገንዘብ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ቱሪዝም እድገት ነው፡፡ ስለምንሳሳላቸው በአንደኛው አመት አንዱን ካመሰገንን በሚቀጥለው አመት አንደኛውን ከነሙሉ ክብራቸው እናመሰግናለን ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የዛሬ ሁለት ዓመት ተጓዡ ጋዜጠኛ ሔኖክ ስዩም ተሸላሚ ነበር በዘንድሮ ደግሞ የህይወት ዋጋ እስከመክፈል የደረሰው ታዋቂው የፎቶግራፍ ባለሙያ አዚዝ አህመድ በቱሪዝም ዘርፍ ተሸላሚ ነው፡፡ አዚዝን ከሄኖክ ጋር ማወዳደር አትችይም፡፡ ሁለቱንም በተሰማሩበት ዘርፍ  እንቁዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ እንሳሳላቸዋለን፤ ለማወዳደር፤ እራሱ አንደፍርም! ሀበሻ ልብስ ላይ ብትሄጂ በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፤ ሶስት አራት አይሞሉም፤ ሶስት መቶ ስልሳ አምስት ቀን የሚለብሱ፡፡ ለምሳሌ ወ/ሮ ገነት በለጠን ከዘንድሮ ዓመት ተሸላሚ ጋር ብናወዳድራት፣ ሁለቱም የየራሳቸው ነገር ስላላቸው ለማወዳደር ይከብዳል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሰዎቸ እየቆጠብን ነው ወደ ሽልማት የምናመጣቸው፡፡
የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ መቼና የት ነው የሚደረገው?
ጥቅምት 11 ቀን 2014  በዮድ አቢሲንያ የባህል አዳራሽ ይከናወናል፡፡
በዕለቱ የአለባበስ ህግም እንዳለ ሰምቻለሁ?
እውነት ነው፡፡ አንዱና ዋናው አላማችን፣ የራሳችን የሆነውን ነገር ማስተዋወቅ ስለሆነ፣ በዕለቱ ከባህላዊ ልብስ ውጪ መልበስ አይፈቀድም፡፡
ውድድሩ  የዳኞችና የህዝብ ድምጽስ አለው?
የህዝብ ድምፅም ዳኝነትም የለውም፤ ምክንያቱም ቅድም እንደገለፅኩት ተሸላሚዎቹ አይወዳደሩም፡፡ በስራቸው ይመረጣሩ፡፡
የዘንድሮ ሽልማት ለሶስት ሰዎች መታሰቢያነት እንደሚውል ገልፀሃል..
አንደኛው የተሰበረ ልብን የሚጠግኑት የመጀመሪያው የልብ ማዕከል መስራች ዶ/ር በላይ አበጋዝ፤ በርግጥ እኛ ከተነሳንበት የቱሪዝም ሃሳብ ጋር ምንም አያገናኛቸውም፤ ግን አይተኬ የሚባል ክስተት ናቸው፡፡ ብዙ የተሻለ ነገር ወደሚያገኙበት ቦታ መሄድ እየቻሉ ኢትዮጵያ ሀገሬን ብለው እያገለገሉ ያሉ ናቸው፡፡ እነሱ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይሆን ኢትዮጵያ እነሱ ልብ ውስጥ ያለች እስኪመስል የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ አንድ ልቡ የተሰበረ ህፃን ልቡ እየተጠገነ ያለው እሳቸው በጣሉት መሰረት ነው፡፡ ድንገት ዶ/ር በላይ አበጋዝ ባይኖሩ ኖሩ፣ የኢትዮጵያ ልብ ህሙማን መርጃ ህልም ሆኖ ይቀር ነበር፡፡  ሁለተኛው ብ/ጄኔራል ፍሬሰንበት አምዴንም ስንመለከት ትውልድና ትውልድን እንደ ድልድይ ያገናኙ ሰው ናቸው፤ ግን ያልተዘመረላቸው፡፡ ሌላው አለም ላይ ቢሆን አሁን የምናነሳቸው ሰዎች ሳስተው ሙዚየም ውስጥ  ያስቀምጧቸው ነበር፡፡ ግን ያልሆነ ቦታ ሆነና እነዚህን ሰዎች አጉልቶ ማውጣት አልቻልንም፡፡
ሌላ ሀገር ስትመለከቺ፤ መዝናኛ ፓርክ አበባና ዛፍ ብቻ ሳይሆን ለዛ ሀገር ውለታ የዋሉ ሰዎች ሁሉ መታሰቢያ ሐውልት ቆሞላቸው በየፓርኩ ቦታ አላቸው፡፡  ወደኛ ስንመጣ ለሀገር ውለታ የዋሉ ብዙ ሰዎች አሉን፤ ግን ለዛ የሚሆን እውቅና መስጠት ነው ያልቻልነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ዐቢይም ያለፈው ዓመት ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶት የርዕሰ ብሔሯ መኖሪያ የሆነው ቤተ መንግስት ውስጥ ያለውን ቅርስ ሲያስጎበኙን ነበር፡፡ በቀጣይ ልክ እንደ ላይኛው ቤተ መንግስት የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን እየታደሰ ነው። እዛ ውስጥ ያየናቸው የጎበኘናቸው ቅርሶች ሁሉ  ለዚህ ትውልድ የደረሰው በብ/ጄ ፍሬሰንበት አምዴ ነው፡፡ እሳቸው 34 ዓመት ሙሉ አንድ ክፍል ቤት ተኝተው ነው ያንን ቅርስ ጠብቀው ያቆዩልን፡፡ ምን አልባት እሳቸው ያንን ስራ ባይሰሩ ኖሮ፣ ዛሬ ያሉት ቅርሰች ቦታቸው ላይ ላይገኙ ይችሉ ነበር። ግን አልተዘመረላቸውም! የኢትዮጵያን ነገር ማስቀደም አልቻልንም፤ ለዛም ነው እንዲህ ያሉ ሰዎችን በባትሪ ፈልገን ማግኘት ያልቻልነው፡፡ እሳቸው በሕይወት ባይኖሩም ልጆቻቸው ከአሜሪካ መጥተው ሽልማታቸውን ይቀበላሉ፡፡ ሶስተኛዋ የዘመን ክስተት፣ የእስክስታዋ ንግስት እንዬ ታከለ ናት፡፡ አሁን ላይ የባህል ውዝዋዜያችን የቱ ጋ ነው ያለው ብንል፤ ብዙ መወያያዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ምልክቶች ናቸው፡፡ የሆነ ጊዜ ይመጣሉ፤ ከዛ እንደ ቅርስ ነው የምታያቸው፡፡ ስለዚህ የዘንድሮ የአርአያ ሰው ሽልማት የእነዚህ ሶስት ሰዎች መታሰቢያ ይሆናል፡፡
የክብርና ልዩ ተሸላሚ ተብለው የየታሰቡ አሉ?
አዎ ከዚህ ዘርፍ ውጪ የሆነ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ስራ የሰሩ  አሉ፡፡ ለምሳሌ ወደ ኪነጥበቡ ብንመጣ ፣ ህዝቡ እውቅና ሰጥቷቸው ህዝቡን የማያገለግሉ አሉ፤ በዛው ልክ ደግሞ በተሰጣቸው እውቅና ልክ ለህዝቡ የሚያገለግሉ ክብር ዝና ህዝብ እንደሆነ የሚያውቁ አሉ፡፡ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ግንባር ቀደም የሆኑ ሰዎችን በማመስገን፣ እነሱን በሚመስሉ ሰዎች ዙሪያ ንቃተ ህሊናን መፍጠር ነው። ከኪሳቸው አውጥተው የሚጠቀሙት ምንም ነገር የለም፤ እነሱ የሚጠቀሙት ስማቸውነ በቻ ነው፡፡ ህዝቡ ደግሞ ስምሽን ተጠቅሞ ሊደግፍሽ የሆነ ነገር ሊያደርግልሽ ይቆማል፡፡ ለምሳሌ “ዛሬ ልደቴ ነው፣ ልደቴን በማስመልከት አንድ ብር በማዋጣት ይህን ተቋም ይደግፉ” የሚል አናገኝም ግን ቀላሉ መንገድ ይህ ነው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር የኢንስታግራም ተከታይ ኖሯቸው፣ ህዝብን የሚጠቅም ስራ ሳይሆን የሚሰሩት የራሳቸውን ፍላጎት የሚያሟሉ የኪነጥበብ ሰዎች በሞላባት ሀገር ውስጥ ጥቂት ብቅ ያሉትን አውጥተን ስናጎላቸው ስናመሰግናቸው፣ ሌሎችን ማንቂያ፡፡ ነው እነሱን ደግሞ በርቱ ከዚህ የተሻለም አንጠብቃለን ለማለት ነው፡፡ ስለዚህ የክብር ተሸላሚያችን ሲስተር ዘቢደር ነች፡፡ በበጎ አድራጎት ስራ ይልቁንም ራሳችን ለራሳችነ መፍትሄ እንደምንሆን ያሳያችን፣ ለ27 ዓመት ምንም የውጭ ተቋም ሳታስገባ ራሷን ችላ  በአገር ውስጥ ደጋፍ ብቻ  መስራት እንደሚቻል አረጋግጣለች፡፡
ሌላኛዋ በኪነጥበብ ዓለም ተፅእኖ ፈጣሪና የኢትዮጵያ ልብ ህሙማን ማዕከል አምባሳደር የሆነቸው  አርቲስት መሰረት መብራቴም ተሸላሚ ናት። በዚህም ሌሎች የኪነጥበብ ሰዎችን የበለጠ ለማነቃቃት ይረዳናል ብለን እናምናለን። ስራዎችን እያየን እንደሆነና ያ ስራ ደግሞ እንደ ሀገር እየጠቀመን እንደሆነ ለማሳየትም ለማመስገንም ይረዳናል፡፡
በሀገራችን ሰባት ያህል የሽልማት ተቋማት አሉ ሰስለዚህ ማመስገንን ስላሳዩን ስላመሰገኑን ሰባቱን የሽልማት ተቋማት እናመሰግናቸዋለን፡፡ የሰሩ ሰዎችን ባመሰገንን ቁጥሩ ብዙ የሚሰሩ ሰዎችን እናፈራለን  እንፈጥራለን፡፡
ብዙ ጊዜ እንዲህ አይነት ስራዎች ስፖንሰር (ድጋፍ) ሲያገኙ አይታይም፡፡ ለምን ይመስልሃል?
ድጋፍ የሚሰጡ ተቋማት የንግድ ተቋም እንደመሆናቸው ምንድነው የማገኘው ትርፍ ብለው ያስባሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ የቢራ ፋብሪካ ስፖንሰር ቢያደርግ በዕለቱ ቢራውን ለታዳሚያን በነፃና በብዛት ማቅረብ ይፈልግ ይሆናል፡፡ ያ ደግሞ አርአያ ሰው ሽልማት ላይ የማይታሰብ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ሊያደርጉን አይፈልጉም፡፡ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት ሳይሆን ትርፍን ብቻ  ስለሚያስቀድሙ እንዲህ አይነት ነገሮች አይሳኩም፡፡ የሆነው ሆኖ ሌሎች  የዚህ አይነት እሳቤ የሌላቸው ተቋማት አሉ፡፡ ለምሳሌ ዮድ አቢሲንያ ያለምንም ክፍያ አዳራሹን ሲፈቅድልን፣ የኛን ስራ እየሰራህ ነው ብሎ ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ሽልማቶች ድጋፍ ካላገኙ ቀጣይነታቸው እራሱ አጠራጣሪ ነው የሚሆነው፡፡ በኛ በኩል ግን ለቀጣይ 5 ዓመታት ስፖንሰር ቢኖርም ባይኖርም ይቀጥላል፡፡ የኛ ተቋም ሲመሰረት ባለቤቴ 1000 የአሜሪካን ዶላር ሰጥታ ነው የተቋቋመው፡፡ ስለዚህ እንደዚህ የባሎቻቸውን ህልም የሚኖሩ ሚስቶችንና የሚስቶታቸውን ህልም የሚኖሩ ባሎችን ያብዛልን፡፡
ሰው ቤተሰቡ የሚሰራው ስራ ውስጥ እጁ ከሌለ በምትፈልጊው ልክ ሀሳብሽ አይሳካም። እና ሁሉን ነገር ፈቅዳና አምናበት “ያንተ ልፋት የኔ ልፋት ነው፤ ውጤትህ ውጤቴ ነው” ብላ የበኩሏን ስለምታደር ምስጋናዬ እጅግ ላቅ ያለ ነው፡፡


Read 1321 times