Wednesday, 13 October 2021 06:30

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 "ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፦

              ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ በሙዚቃ ውስጥ የህብረተሰቡን ድርሻ ሲገልጽ ምን ብሏል መሰለዎ ?
“ሕብረተሰቡማ ምን ያድርግ ? ሙሾውንም ሰጠ፤ የሰርግ ዘፈኑንም ሰጠ፤ ዓለማዊ ዘፈኑንም ሰጠ፤ ሲድር ደግሞ ‘ ጉሮ ወሸባ ‘ የሚባልበትንም ሰጠ። ሁሉንም ሰጠ። ከዚህ በላይ ምን አለውና ምኑን ይስጥ?
(“ፈርጥ” መጽሔት ሐምሌ /1992 በተፈራ መኮንን )
ይኸውልዎት እንግዲህ ሕብረተሰቡ ለእርስዎ ያለውን ሁሉ ሰጥቷል። አንድ ሕዝብ ለመሪው መስጠት የሚችለውን ሁሉ ሰጥቷል። ድጋፉን ሰጥቷል፤ ሕይወቱን ሰጥቷል፤ ድምጹን ሰጥቶ መርጧል፤ “ጦር ሜዳ ገብቶ ፈረስ አይለወጥም “ ብሎ መመረጥ ያለባቸውን የተፎካካሪዎችዎን እጩዎች ትቶ መመረጥ ያልነበረባቸውን የእርስዎን እጩዎች መርጧል። ሙሾውንም፣ የሰርግ ዘፈኑንም ሰጥቶዎታል። ሕዝቡ ያልሰጠዎት የለም። ከሕዝቡ የቀረ የለም። አሁን ያለው ከእርስዎ የሚጠበቀው ነው።
መስከረም 24 ቀን 2014 ከተመሰረተው አዲሱ መንግሥት ሕዝቡ ብዙ ይጠብቃል። ሕዝብ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ረሀቡንም ጥሙንም ችሎ ዝም ያለው፣ ሀገሪቷ እሷት ላይ መሆኗንና እርስዎም እሳት ማጥፋት ላይ መሆንዎን በማሰብ ነው። ሕዝብ በራሱ መሪዎች ሲበደልም ሲገደልም ዝም ያለው ይህን በመረዳት ነው። ስለዚህ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መስከረም 24 ቀን 2014 ለእርስዎ የደስታ ሳይሆን የፈተና መጀመሪያ ቀን ነው። ከዚያ በኋላ በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ የተመረጠ የመጀመሪያው መንግሥት ምስረታ ቀን ይሆናል። ይህ መንግሥት ከሌሎቹ የበለጠ እዳ የተሸከመ መንግሥት ነው። ይህን ጦርነት በድል ይወጡታል። ኢትዮጵያ ስለምታሸንፍ። ማሸነፍ ስላለባት። ከዚያ ግን ፈተናዎ ይብሳል። የረጋ ሀገርን መምራት ይከብዳል። ሙሾውንም የሰርግ ዘፈኑንም የሰጠዎት ሕዝብ ከእርስዎ የሚጠብቀው እስካሁን የሰጡትን ያህል ብቻ አይደለም። እጅግ ብዙ ነው። ሕዝቡን እንዲያክሉ ፈጣሪ ይርዳዎ። አሜን።

***************************************************************************
                  (አማን መዝሙር)
የእርስ በርስ ግጭት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ መፈናቀሎች፣ የክልል መሪዎች ግድያና መፈንቅለ መንግስት፣ ጦርነት፣ ከፍተኛ የሃያላን ሐገሮች ተፅእኖና ማእቀብ፣ ይህ ሁሉ መአት በሶስት አመት ውስጥ ወርዶበት
የግብፅን ፉከራና ጫና አራግፎ አባይን ገደበ፣ ከየትኛውም ጊዜ የተሻለ ፍትሃዊ ምርጫ አድርጎ አሳየ፣ ዛሬ ተቃዋሚዎች ሳይቀሩ በተገኙበት በመቶ አስር ሚሊየን ህዝብ ፊት ተሾመ! አንዳች ሃይልማ አብሮት አለ። ሰውዬው ብቻውን አይደለም!
እንኳን ደስ አልዎት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን!

ይነጋል!
.ታድለሻል ቢሉም፣
የ13 ወር ፀሀይ፣ የ13 ወር ፀጋ
ብርሀንሽ ተሰርቆ፣
ሲጨላልም እንጂ፣ መች አየን ሲነጋ?
ተፈጥሮ ቸር ሆና፣
ሰማይዋ ባይነጥፍ፣ ምድሯ ቢለመልም፣
ከልጆቿ ልብ ውስጥ፣
ፍቅር ሲጎድል ነው፣ ሀገር የምትጨልም!፣
“አረ ነግቷል” ቢሉ የታለ የነጋው?
አዕላፋት ተቧድነው፣ በየጎጥ በመንጋው፣
ሰው ከነገ ይልቅ፣ ዛሬን እያሰጋው የታለ የነጋው?
ታሪኩን እንዳይፅፍ፣ ትውልድ እጁ ታስሮ፣
በትላንቱ ሾተል ዛሬው ተሸንቁሮ፣
ባልኖረው ተካሶ፣ ባልሰራው ተዋቅሶ፣
ለፀብ መዶለቻ፣ ያ’ያቱን ስም ጠቅሶ፣
ላለፈው ሲናከስ ለመጪው ሳይተጋ፣
በምን ስሌት ይሆን፣
ትዉልዷ ጨልሞ ሀገር የምትነጋ?
.
የህሊና መስታወት በጥበብ ሲፀዳ፣
ማስተዋል እንዳ’አደይ ፈክቶ ሲፈነዳ፣
መገፋፋት ሲቀር፣ መደጋገፍ ነግሶ
አንዱ ማገር ሲሆን፣ ሌላኛው ምሰሶ፣
የአብሮነትን ሸማ ትዉልዱ ሲሸምን፣
ያኔ ነው ሀገሬ መንጋቷን የማምን።
በረከት በላይነህ

**********************************************************************
                       አንቀፅ 39 እና ዋለልኝ መኮንንን የሚያገናኛቸው ነገር የለም!
                               ጌታሁን ሔራሞ

             እስከ አሁን ድረስ በሕገመንግስቱ የተቀመጠውን አንቀፅ 39ን ዋለልኝ የዛሬ 52 ዓመት ከፃፈው የብሔር ጥያቄ መጣጥፍ ጋር የሚያገናኙ ቡድኖች ይገርሙኛል። ህዳር 7 ቀን 1962 ዓ.ም. ዋለልኝ መኮንን የመገንጠል መብትን በቅድመ ሁኔታ ቀንብቦ ነበር ያስቀመጠው። ይህም ቅድመ ሁኔታ ኢንተርናሽናሊዝምና የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ነው። ማለትም የመገንጠል መብት ተቀባይነትን የሚያገኘው ወደ ሶሻሊዝም በሚደረገው ጉዞ በላብአደሮችና በአርሶ አደሮች በሚደረግ ትግል በስትራቴጂነት ማዕቀፍ ብቻ ነው። ለምሣሌ በዋለልኝ ዕሳቤ፣ የኬንያ ላብአዳሮች የመገንጠል ጥያቄን ይዘው ሲነሱ ድጋፍ ሊሰጣቸው ዘንድ ይገባል፤ ምክንያቱም ትግሉ በድል ተጠናቅቆ ሶሻሊዝም እውን ሲሆን በሀገራት መካከል ያለው ድንበር ተሽሮ ኢንተርናሽናሊዝም ይተገበራል። ነገሩ ዞሮ ዞሮ መገናኘታችን አይቀርም ነው።
ዋለልኝ የብሔር ጥያቄን ከእነ ርዕሱ እንደወረደ የኮረጀው ከስታሊንና ከሌኒን መሆኑ ይታወቃል(ስለ “self determination” በአውሮፓም ሲነሳ እንደነበረ ቢታወቅም)። መገንጠልን በተመለከተ የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታም የተኮረጀው ከዚያው ከሶቪየት ምድር ነው። እንዲያውም የሌኒን የመገንጠል ቅድመ ሁኔታ በጣም ተጣጣፊ(flexible) እና ዲያሌክቲካዊ እንደሆነ ይነገራል። ለዚህም በዋቢነት Juan Ignacio, Castien Maestro የተባሉ ስፔናዊያን የማድሪድ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን “LENIN AND THE NATIONAL QUESTION. BEYOND ESSENTIALISM AND CONSTRUCTIONISM” በሚለው ጥናታዊ ፅሁፋቸው ያስቀመጡትን መጥቀስ ግድ ይሆናል። የሌኒን የመገንጠል ድጋፍ የቱን ያህል ተጣጣፊ እንደሆነ ያሰመሩት በዚህ መልኩ ነው፦
“While he insisted on the recognition of the right to secede, he also believed that in the case of having to decide about holding a referendum, there would be many situations in which the most appropriate thing to do would be to vote against that secession. If according to him, russian workers must defend the Ukrainian’s right to secede, at the same time they should try to convince them of the advisability of remaining within the State. This State should be a guarantee for their autonomous national existence and would also reject any compulsory homogenisation.”
ሐሳቡ ሲጨመቅ ይህን ይመስላል፦ ለምሣሌ የራሺያ ላብአደሮች በዩክሬን የሚደረገውን የመገንጠል ትግልን ደግፈው፣ የዩክሬኖቹ ላብአደሮች ልክ እንዳሸነፉ፣ በትግሉ ወቅት ለዩክሬን ላብአደሮች መገንጠል ድጋፋቸውን የሰጡ የራሺያ ላብአደሮች በድል ማግስት በተቃራኒው መገንጠልን መቃወም አለባቸው ይላል። በሌኒን ዕሳቤ ተገንጣዮቹ የራስ ገዝ አስተዳደር በነባሩ መንግስት ሥር መስርተው መቆየት አለባቸው እንጂ በራሳቸው ሀገር መሆን የለባቸውም (በሌላ አነጋገር የኢቲኖ-ናሽናሊዝም ጥንስስ/እርሾ መሆኑ ነው)። ሌኒን የመገንጠል ትግሉን መነሻ ላይ የደገፈው ሶሻሊዝም የመገንጠል ጥያቄ በተነሳበት ሀገር እግሩን እንዲሰድ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንጂ ተገንጣዮቹ ሀገር እንዲመሠርቱ አቅዶ አይደለም። ሌኒን ሀገር ለመሆን ትልቅ ኢኮኖሚ ያስፈልጋል ብሎ ነበር የሚያምነው።
ሕወሓት አዲስ አበባ የገባችው የዋለልኝ ፅሁፍ ከቀረበ ከ21 ዓመታት በኋላ ነው (1983)። ያኔ የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ከርዕዮቱ አመንጪ ሀገሮችም ጭምር በካልቾ እየተጠለዘ የወጣበት ወቅት ነበር። ዋለልኝ መኮንን የብሔር ጥያቄን ያነሳበት ሀገራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ አውድ ፈፅሞ አልነበረም። እናም ቀደም ሲል ዋለልኝ ከአለቆቹ በስትራቴጂነት ብቻ ፈርጆ የኮረጀውን የመገንጠል መብት፣ ምንም ዓይነት ሶሻሊስታዊ ቅድመ ሁኔታ በሌለበት፣ እነ መለስ ዜናዊ፣ ከስትራቴጂነትም አሳልፈው የማይለወጥ የማይሻሻል የሕገመንግስቱ ምሰሶ አድርገው ተከሉት። ይህ አካሄድ ከዋለልኝ ዕሳቤ ጋር አለፍ ሲልም ከሌኒንና ስታሊንም የመገንጠል መብት ንድፍ ጋር ፊት ለፊት እንደ መላተም ይቆጠራል። ከላይ ያስቀመጥኩትን የሌኒን ዲያሌክቲካዊ ዕሳቤን እንኳን ዕውን እናድርግ ቢባል፣ ሕወሓት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ሳትገነጠል የራስ ገዝ ክልል ብቻ መስርታ እንድትቆይ በመከረቻት ነበር፤ የሆነው ግን ተቃራኒው ነው፤ ሕወሓቶች ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትገነጠል ለተባበሩት መንግስታት ድጋፋቸውን ገልፀው ነበር የሸኟት።
እናም አንቀፅ 39 እና ዋለልኝ መኮንን ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም። የአንቀፅ 39 አርክቴክቱ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነው፤ ይህ አንቀፅ ለመገንጠል ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ(ያለ ገደብ በማናቸውም ሁኔታ) ባለማስቀመጡም በዓለም አቀፍ ደረጃ በፀጉረ ልውጡነቱ (የካሪቢያን ደሴቶቹን ጨምሮ) ሁሌም የሚጠቀስ ነው።
**************************************************************

                     ጥቂት ስለ 5ኛው ፓርላማ ---
                           ሙሼ ሰሙ

               ኢትዮጵያ ስድስተኛውን ፓርላማ ልታስተናግድ ሽር ጉድ እያለች ነው፡፡ ፓርላማው ምን ይዞልን ይመጣል? ወይም ምን ይዞብን ይመጣል? ይህንን ወደ ፊት የምናየው ይሆናል፡፡ አዲሱ ፓርላማ ግን በስራ ያልተፈተሸ፣ ለወቀሳም ሆነ ድጋፍ ያልደረሰ ስለሆነ መልካም የስራ ዘመን እመኝለታለሁ፡፡
ከሶስተኛው ፓርላማ (1997) በስተቀር ያለፉት አራቱ ፓርላማዎች “በከባድ የእንቅልፍ ድባቴ የተመቱ”፣ በጭብጨባ ድምቀት በርግገው በመንቃት እውቀትና ክህሎት በሌላቸው ጉዳዮች ላይ በአጽዳቂነት ብቻ ንቁ ተሳተፎ የሚያደርጉ ፤ የፓርቲያቸውና የስራ አስፈጻሚው ማህተም (Rubber Stamp) በመሆን በትጋት እያገለገሉ የዘመናችንን ሩብ ምዕተ ዓመት ገደማ በከንቱ የፈጁብን ናቸው።
ይህም ሆኖ አምስተኛው ፓርላማ በከባድ የነውጥ ጊዜ ውስጥ ያለፈ በመሆኑ ለየት የሚያደርገው ነገር አለው፡፡ ሕዝባዊ አመጽ፣ ግድያ፣ ስደት፣ መፈናቀል፣ የመብት ጥሰት፣ ኮሮና፣ አንበጣ፣ ድርቅ፣ ጦርነትና የመሪ፣ የአመራርና የፓርቲ መተካካትን አስተናግዷል፡፡ በርካታ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆችን አውጇል፡፡ በሕዳሴ ግድብ ዙርያ መሰረታዊ ውሳኔዎችን አሳልፏል። መነቃቃት ቢሳነውም፣ በርካታ አነቃቂ ንግግሮችንም አድምጧል፡፡
ፓርላማው በተለይ የሃገራችንን ሕልውና ተፈታትኖት የነበረውን የሽግግርና የጥምር መንግስት ምስረታ ውዝግብ በማስወገድ፣ የስራ ዘመኑን ማራዘም በመቻሉ፣ ሀገራችን ላይ ተደቅኖ የነበረውን የውድቀት ደመና እንዲገፍ አድርጓል፡፡ በሕዝባዊ አመጹ ወቅት በርካታ እንደራሴዎች በመረጣቸው ሕዝብ ላይ እየደረሰ የነበረውን ግድያ፣ አፈና፣ እስርና ስደት እንዲቆምና ሕዝባዊ ጥያቄዎቹ እንዲመለሱ ታግለዋል፡፡ ባልተለመደ ሁኔታ የመረጣቸው ሕዝብን ጥቅም አያስጠብቁም ባሏቸው ፖሊሲዎችና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ተቃውሞ በማሰማት፣ በሃሳብ በመሞገትና በድምጽ ብልጫ እንዲወሰን በማድረግ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ሚናቸውን ተወጥተዋል፡፡
አምስተኛው ፓርላማ ከሌሎቹ የተሻለ ተግባር የፈጸመው በተዓምር ሳይሆን፣ የተፈጠረለትን ወቅታዊ ሁኔታ (Window Period) ወደ ትግል ምእራፍነት መለወጥ በመቻሉ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ግን የመጀመሪያን ሁለት አመት ተኩል እንቅልፉን እየለጠጠ ለመረጠው ሕዝብ ሳይሆን ለፓርቲና ለስራ አስፈጻሚው መሳርያ ሆኖ አገልግሏል። በተለይ የመጨረሻውን አንድ አመት ተኩል ግን ፓርላማው ለለውጡ ምክንያት የነበሩ ጥያቄዎች ዛሬም በፓርቲና በስራ አስፈጻሚው ሲተገበሩ እያያ እንዳላየ አልፏል፡፡ የመወሰን አይደለም የመማከር እድል እንኳን ሳያገኝ የስልጣን ጠገጉ እየተጣሰ የተለያዩ ውሳኔዎች በአናቱ ላይ ሲወሰኑ እንዴትና ለምን ብሎ አልጠየቀም፡፡ በጥቅሉ የመረጠውን ሕዝብ በፓርቲና በስራ አስፈጻሚው ተክቷል፡፡
ፓርላማው በጎ ጎኖቹ እንደተጠበቁ ሆነው በሕዝብ ትግል የተፈጠረለትን እድል በአግባቡ ተጠቅሞ ራሱን ከስህተት በማጽዳት ትግሉን በፅናት ማስቀጠል ስላልቻለ፣ ለመረጠው ሕዝብ ያልታመነና የድሮ በደሉ ሊሰረዝለት የሚገባው ፓርላማ አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ ሕዝብን በይፋ ይቅርታ ይጠይቃል ብዬ እጠብቃለሁ፡፡

*********************************************************************


                             "ብርሃኑ ነጋ የሚለው ስም ራሱን የቻለ ታሪክ ነው"
                                    ዩሱፍ ግዛው ዓለምጉድ


                ሰውየው ዛሬ ወደ 65 ዓመት ዕድሜ እየተንደረደረ ነው።  የሀገሩን ጉዳይ ጉዳዬ ብሎ ከያዘ እነኾ ሃምሳ ዓመታትን ደፈነ።(ግማሽ ምዕተ ዓመት ማለት ነው)
ሰውየው (The versatile person) ከመምህርነት እስከ የሚዲያ ተቋም ግንባታ፣ ከኢኮኖሚ ማኅበር ምሥረታ እስከ የፖለቲካ ትግል የቀዘፈ ሁለገብ ነው።
ሰውየው (The progressive man) ከመሰናዶ ት/ቤት ተማሪዎች እስከ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ንቅናቄ፣ ከከተማ እስከ የጫካ ትግል፣ ከኢሕአፓ እስከ ጀብሃ፣ ከቀስተ ደመና እስከ ቅንጅት፣ ከግንቦት 7 እስከ ኢዜማ ማርሽ እየቀያየረ ለዜጎች ሰላም፣ እኩልነትና ነጻነት በመቆም ለሀገሩ የታመነ ተራማጅ ፍጡር ነው።
(ከጠቀስኋቸው ድርጅቶች ውስጥ ጀብሃ የትግል ድርጅቱ ሳይሆን ከኢሕአፓ ባለመስማማት ወደ ሱዳን ከሰላ ለመግባት በእስር የቆየበት ድርጅት ነው።)
ሰውየው (The saved man) በፍርሃት የማይታሰር፣ በጥቅም የማይባበል፣ በጊዜ ‘ማይንኮታኮት፣ በሥልጣን የማይደለል ኹለት ትውልድ በአብዮት ድማሚት ሲያስተሳስር የመጣ የጽናት ምልክት ነው።
ሰውየው (The man of freedom) ከባለጠጋ ቤተሰብ ወጥቶ ከድኾች የተሻሸ፣ ከዕውቀት ማማ ላይ ቆሞ ደናቁራን የሞገተ፣ ተፈጥሮ የክብር ካባ ጭናለት እሱ የመተናነስ ቡልኮ የለበሰ የነጻነት ራስጌ ነው።
ሰውየው (The peak of being human) እንደ ማንኛውም ብሔር አለኝ እንደሚል ኢትዮጵያዊ የመጣበት የዘር ምዛዥና የቋንቋ ቤተሰብ ኖሮት ... ሀገር በዘር ፖለቲካ ግልፍተኝነት የመጨረሻ እርካብ ላይ ደርሳ እሱ ግን ለብዙሃኑ ሕልም የኾነና ለሽንፈት የሚዳርግ የዜግነት ፖለቲካ ይዞ ለምርጫ የቀረበ፣ የኔ ዘመን ተራራ፤ ሰው የመሆን ደርዝ ነው።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር : –
የሀገሪቱ ቱባ ችግሮች መፈልፈያና መሽገው ያሉበት ቦታ ነው። ምግብና ዕውቀት እንድንራብ፣ ራሱን የማያከብር ትውልድ እንዲፈጠር፣ ከሐሳብ ይልቅ ዱላና ድንጋይ እንድንመርጥና ከሰውነት ዝቅ እንድንል ያደረገን ተቋም ነው።
ትምህርት ሚኒስቴር እነ አስራት ወልደየስን ጨምሮ በሀገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ አንጋፋ ምሁራን በአመለካከታቸው ሳቢያ በአቅም ማነስ ብሎ በማባረር ሀገሪቷን ያራቆተ፣ (Tibebu Belete አንድ ቀን በአስራት ጉዳይ እየተጻጻፍን ያለቀስነውን ታስታውሳለህ?) በቴክኖሎጂ ወደ ኋላ እንድንቀር ያደረገ፣ ከሥሩ ባሉ የትምህርት ተቋማት ከዕውቀት መመዘኛ ውጭ ማዕረግ እንደ ከረሜላ ያደለ፣ ከእኛ ስነ–ልቦና የራቀ የትምህርት ሥርዓት የዘረጋ፣ በራሱ የሚያፍር ትውልድ የፈጠረ፣ ተቋማትን ከጥናትና ምርምርነት ውጭ አድርጎ የካድሬ መቦረቂያ ያደረገ፣ ከኹሉ በላይ በትምህርት ሥርዓቱ ኢትዮጵያዊነትን ከትውልዱ አስወልቆ ያስጣለ ተቋም ነው።
አሁን ኹለት ነገሮች ተገናኝተዋል፣ ሰው የመኾን እጹብት ላይ የደረሰ ምሁር ብርሃኑ ነጋና ኢትዮጵያ የምትባል ትልቅ ሀገርን ከከፍታዋ የፈጠፈጣት ተቋም፤ ትምህርት ሚኒስቴር።
የሚኾነውን ኹሉ አብረን እናያለን።
የሀገራችን ጉዳይ ወዴትም ይሂድ ወዴት ይሄ ተቋም በፕሮፍ. ኃላፊነት ሥር እስካለ ድረስ የፖለቲካ መገልገያ እንደማይሆን አጥብቄ አምናለሁ!
ሰውየው፣ (ወዳጆቹ እንደሚጠሩት ካሱ) ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) መልካም የሥራ ዘመን!

Read 1377 times