Saturday, 09 October 2021 00:00

ጉዞ ወደ ኳታር በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ በአፍሪካ ዞን

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ በአፍሪካ ዞን
‹የ3ኛና 4ኛ ዙር ጨዋታዎች በጣም ወሳኝ ናቸው›› ሁጎ ብሮስ (የባፋናዎቹ አሰልጣኝ)
ደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያን አሸንፋ አታውቅም
የማለፉ ግምት ከምስራቅና ደቡቡ፤ ለሰሜንና ምዕራቡ ያይላል
በ2022 የዓለም ዋንጫ በአፍሪካ ዞን በሚካሄደው የምድብ ማጣርያ 3ኛና የ4ኛ ዙር ጨዋታዎችም በሳምንት ልዩነት ይካሄዳሉ፡፡ የአህጉሪቱ ብሄራዊ ቡድኖች ወደ ካታር በሚወስደው ጉዞ  ላይ የደርሶ መልስ ጨዋታዎቹ ወሳኝ ይሆናሉ። ባለፈው ረቡዕ በአፍሪካ ዞን የምድብ ማጣርያው ሲጀምር በ2ኛ ዙር የተራዘመ ግጥሚያቸው ሱዳንና ጊኒ በራባት ተገናኝተው አንድ እኩል አቻ ሲለያዩ፤  እንዲሁም ሲያደርጉ ሞሮኮ 5ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት ጊኒ ቢሳዎን አሸንፋለች። በ3ኛ ዙር የምድብ ማጣርያው ሐሙስ ሲቀጥል  ኬፕቨርዴ አክራ ላይ ላይቤርያን 2ለ1 የረታች ሲሆን ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎ በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ ማዳጋስካርን 2ለ0 አሸንፋለች። ባዳሬሰላም ቤኒንን ያስተናገደችው ታንዛኒያ 1ለ0 ስትሸነፍ ኢኳቶርያል ጊኒ በማላቦ ከዛምቢያ ጋር የተገናኘችበትን 2ለ0 ያሸነፈች ሲሆን ናይጄርያ ሜዳዋ ላይ በመካከለኛው አፍሪካ ያልተጠበቀው 1ለ0 ሽንፈት ገጥሟታል፡፡ የምስራቅ አፍሪካዎቹ ቡድኖች ኪጋሊ ላይ ሲጫወቱ ሩዋንዳ 1ለ0 በኡጋንዳ ስትሸነፍ፤ ቱኒዚያ ሞውሪታኒያን 3ለ0 እንዲሁም ማሊ ኬንያን 5ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት ድል አድርገዋል፡፡ ትናንት የ3ኛ ዙር የምድብ ማጣርያ ጨዋታ ላይ ማላዊ ከኮትዲቯር በጆሃንስበርግ፤ ካሜሮን ከሞዛምቢክ በድዋላ፤ አንጎላ ከጋቦን በሉዋንዳ፤ አልጄርያ ከኒጀር በብሊዳ፤ ጅቡቲ ከብሩኪናፋሶ በማራኬሽ እንዲሁም  ግብፅ ከሊቢያ በአሌክሳንድሪያ ከተሞች ተጫውተዋል፡፡ ዛሬ ቅዳሜ ላይ ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ በባህርዳር፤ ጋና ከዚምባብዌ በኬፕ ኮስት፤ ቶጎ ከኮንጎ በሎሜ እና ሴኔጋል  ከናሚቢያ በቴይስ ከተሞች ይገናኛሉ፡፡
በባህርዳር ስታድዬም ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ የሚያደርጉትን ጨዋታ እንዲመሩ አራት ዳኞች ከሊቢያ የተመደበ ሲሆን ጨዋታው በዝግ እንዲካሄድ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ወስኗል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ዘገባ  ቅዳሜ 10 ሰዓት የሚደረገውን ጨዋታ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር በፊፋ ቲቪ (ዩ ቱብ ቻነል) ላይ እንደሚያሰራጭ ሲሆን ከውጪ ሀገር የቀረፃ እና የስቱዲዮ ባለሙያዎች እንደሚገቡና ጳጉሜ 2 በኢትዮጵያ እና ዚምባብዌ ጨዋታ ላይ ያጋጠመው ድንገተኛ የሳተላይት ችግር በአሁኑ ጨዋታም እንዳይከሰት ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ አስታውቋል። ከፊፋ ቲቪ ውጪ ጨዋታው በሀገር ውስጥ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስለሚተላለፍበት ዕድል ግን የታወቀ ነገር የለም። በባህርዳር ከተማ የሚገኘውና እስከ 60ሺ ተመልካቾች የማስተናገድ አቅም ያለው የባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታድዬም ላለፉት 6 ዓመታት ብሄራዊ ቡድኑ የሚሳተፍባቸው  ዞናዊ፤ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች እያስተናገደ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን 39 የልዑካን አባላቱን በመያዝ በቻርተር በረራ ከትናንት በስቲያ የገባ ሲሆን አሰልጣኝ ሁጎ ብሮስ ከኢትዮጵያ ጋር ለሚገናኙባቸው የደርሶ መልስ ጨዋታዎች በዋናነት በአገሪቱ የሊግ ውድድር ከሚሳተፉ ትልልቅ ክለቦች የተመለመሉ ተጨዋቾች የያዘውን ቡድን ለ2 ሳምንታት አዘጋጅተዋል፡፡ በትራንስፈርማርከት ድረገፅ  ላይ በሰፈረው መረጃ  መሰረት ባፋና ባፋናዎቹ ከደቡብ አፍሪካ  ውጭ የሚጫወቱ 4 ምርጥ ፕሮፌሽናሎችን ጨምሮ በተጨዋቾች ስብስባቸው ከ16.48 ሚሊዮን ዩሮ በላይ የዋጋ ግምት ይኖራቸዋል፡፡ በተያያዘም  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ስብስብ  በተመሳሳይ ድረገፅ ስብስቡ በ500ሺ ዩሮ የዝውውር ገበያ ዋጋው በአምበሎቹ መተመኑንም መጥቀስ ይቻላል። ለግብፁ ክለብ አልጉዋና የሚጫወተው ምክትል አምበሉ ሽመልስ በቀለ 350ሺ ዩሮ እና  ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን ለቅቆ ወደ ወልቅጤ ከነማ  ዋናው አምበል ጌታነህ ከበደ 150ሺ ዩሮ ዋጋ ተሰጥቷቸዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካው ዋና አሰልጣኝ ሁጎ ብሮስ ከኢትዮጵያ ጨዋታ በፊት የስራ ፈቃዳቸውን ለማደስ ቤልጅየም ደርሰው ተመልሰዋል፡፡ ከብራሰልስ ሲመለሱ  የኦርላንዶ ፓይሬትስን ጨዋታ ለመመልከት ስታድዬም ደጃፍ ላይ ደርሰውም እንዳይገቡ  መከልከላቸው ቅሬታ ፈጥሮባቸው ነበር። የዓለም ዋንጫው ማጣርያ ሲጀመር የሊግ ጨዋታዎችን ብዙ አይመለከቱም በሚለው ትችት የደቡብ አፍሪካ ሚዲያዎች ሲያብጠልጥሏቸው ሰንብተዋል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በሰጠው መግለጫ ኦርላንዶ ፓይሬት በስታድዬም  ደጃፍ ዋና አሰልጣኙ ለፈጠራቸው መጉላላት ይቅርታ መጠየቁን አስታውቋል። ፕሬዝዳንቱ ዳኒ ጆርዳን ከኢትዮጵያ ጋር በጆሃንስበርግ የሚደረገውን የመልስ ጨዋታ ስታድዬም ገብቶ ለመመልከት የኮቪድ 19 ክትባት መውሰድ እንደሚያስፈልግም በተመሳሳይ መድረክ ላይ ገልፀዋል፤ ክትባት ለወሰዱ ስፖርት አፍቃሪዎችም ነፃ መግቢያ እንደሚፈቀድላቸውም አስታውቀዋል፡፡ በኤፍ ኤን ቢ ስታድዬም በሚስተናገደው የመልስ ጨዋታ ተመልካች ይግባ ወይም አይግባ በሚለው ጉዳይ ግን የመጨረሻው ውሳኔ አልተሰጠም፡፡ ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ በባህርዳር ስታድዬም ከሚያደርጉት ጨዋታ በኋላ እንደሚገለፅም ተነግሯል፡፡
በአፍሪካ እና በዓለም ዋንጫ በ3ኛና 4ኛ ዙር የሚካሄዱ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች በጣም ወሳኝ መሆናቸውን ለስፖርት 24 የገለፁት አሰልጣኙ፤ በማጣርያው ለመቀጠል ወይም ለመደናቀፍ ሙሉ ስድስት ነጥቦችን ከኢትዮጵያ ላይ በመውሰድና ከፉክክሩ ውጭ በማድረግ የሚቻለውን እንጥራለን ብለዋል፡፡ ‹‹ከጋና ጋር ያደረግነውን ጨዋታ በተመሳሳይ እምነት እና ጥንካሬ በኢትዮጵያ ላይ ከደገምነው ከሜዳ ውጭ እናሸንፋለን፡፡›› በማለትም ሁጎ ብሮስ ተናግረዋል፡፡ ታዋቂው የደቡብ አፍሪካ አጥቂ ካቴላጎ ምፕፌላ ለኪክኦፍ መፅሄት  በሰጠው አስተያየት ለሁጎ ብሮስ ድጋፉን የገለፀ ሲሆን በሜመሎዲ ሰንዳውንስና በካይዘርቺፍ ክለቦች ሲጫወት በነበረው ልምድ የኢትዮጵያን ተጨዋቾች እንደሚያውቃቸውና በተለይ በሜዳቸው ለማሸነፍ እንደሚያስቸግሩ ጠቁሟል፡፡ ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ ዛሬ በባህርዳር ስታድዬም ከመፋለማቸቸው በፊት በ3 ጨዋታዎች ታሪክ አገናኝቷቸዋል፡፡ በ20ኛው የዓለም ዋንጫ  ቅድመ ማጣርያ በደርሶ መልስ በተገናኙበት ወቅት ጆሃንስበርግ ላይ 1 እኩል አቻ ተለያይተው፤ በአዲስ አበባ ስታድዬም ደግሞ ኢትዮጵያ 2ለ1 አሸንፋለች፡፡ ይህ የደርሶ መልስ ውጤት የባፋናዎቹ አሰልጣኞች ለነበሩት ፒትሶ ምስማኔ እና ጎርደን ሌግሱንድ መባረር ምክንያት ነበር፡፡ በ2012 እኤአ ላይ በሴካፋ ዋንጫ ሲገናኙም 1ለ0  ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ናት፡፡
 በዚሁ ምድብ ኬፕኮስት ላይ  ጋና እና ዚምባቡዌ የሚገናኙበት የ3ኛ ዙር የምድብ ማጣርያ ጨዋታ አዳዲስ ዋና አሰልጣኞችን የሚሳተፉበት ነው፡፡ የዚምባቡዌ ቡድንን ከክሮሽያዊው ሎድራዝፊክ የተከቡት የቀድሞ ተጨዋች ኖርማን ምፔንዛ ሲሆኑ ቡድናቸው ከሜዳው ውጭ ጋናን በማሸነፍ ተፎካካሪነቱን ለማሳየት ይፈልጋል ብለዋል፡፡ በጋና ብሄራዊ ቡድን በኩል ሰርቢያዊው ሚሎቫን ራጄቫክ ወደ ዋና አሰልጣኝነቱ እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡ ሚሎቫን ራጄቫክ  ከ2008 እስከ 2010 እኤአ ድረስ የጥቁሮቹ ክዋክብቶች አሰልጣኝ የነበሩ ሲሆን ፤በ19ኛው የደቡብ አፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍና እስከሩብ ፍፃሜ በመድረስ የላቀ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ ዘንድሮ  ወደ ስራቸው በድጋሚ ሲመለሱ  ጋናን ወደ  ኳታሩ 22ኛው የዓለም ዋንጫ እንደሚያሳልፉ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡ ዋና አሰልጣኙም የምድብ ማጣርያው እስኪጠናቀቅ ሁሉም ጋናውያንና ሚዲያዎችን ሙሉ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል፡፡ በጋና እና በዚምባቡዌ ጨዋታ ላይ 15 ተመልካች በሚይዘው የኬፕ ኮስት ስታድዬም በከፍተኛ የኮቪድ 19 ፕሮቶኮል 4000 ተመልካች እንዲገቡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ፈቅዷል፡፡ የዚምባቡዌ እግር ኳስ ፌደሬሽንም ከሳምንት በኋላ ከጋና በሃራሬው ስታድዬም በሚገናኝበት የመልስ ጨዋታ 5000 ተመልካች ለማስገባት  አመልክቶ ከካፍ ምላሽ እየተጠባበቀ እንደሆነም ታውቋል፡፡
ለ2022 የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በአፍሪካ ዞን በሚካሄዱት የማጣርያ ምዕራፎች የሰሜንና የምዕራብ አፍሪካ ቡድኖች ከምስራቅ እና ደቡብ ቡድኖች የላቀ ውጤት እያስመዘገቡ ናቸው፡፡ 2021 ከመጠናቀቁ በፊት የምድብ ማጣርያዎቹ ጨዋታዎች በ5ኛ እና 6ኛ ዙር ጨዋታዎች ከተካሄዱ በኋላ  ከ10 ምድቦች በአንደኛነት የጨረሱ አገራት ይለያሉ፡፡  በመጨረሻው የደርሶ መልስ ማጣርያ በመጋቢት ወር 2022 ላይ አስሩ ብሄራዊ ቡድኖች ተገናኝተው በኳታሩ የዓለም ዋንጫ አፍሪካን የሚወክሉ 5 ብሄራዊ ቡድኖች የሚታወቁ ይሆናል፡፡ በተለያዩ ትንታኔዎች  በ22ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ አፍሪካ በሚኖራት የአምስት ብሄራዊ ቡድኖች ኮታ ላይ ለሰሜንና ለምዕራብ አፍሪካ ቡድኖች  ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷል። አልጄርያ፤ ግብፅ፤ ናይጄርያ፤ ሴኔጋል፤ ሞሮኮና ቱኒዚያ በምድብ ማጣርያው ላይ ከፍተኛው ውጤት ከሚያስመዘግቡ ቡድኖች የሚጠቀሱ ሲሆኑ ወደ 22ኛው የዓለም ዋንጫ ለመጓዝም ሰፊ እድል መያዛቸውም ይገለፃል። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር  በ2026 እኤአ ላይ 3 የሰሜን አሜሪካ አገራት በጣምራ በሚያስተናግዱት 23ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ 48 ብሄራዊ ቡድኖች እንዲሳተፉ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ በዚሁ የኮታ ድልድል መሰረት አፍሪካን 9 ብሄራዊ ቡድኖች እንዲወክሏት የተወሰነ በመሆኑ ምናልባትም የምስራቅ አፍሪካ ቡድን የዓለም ዋንጫ ህልም የሚሳካው በዚያን ጊዜ ይሆናል፡፡ በ2026 እኤአ ላይ ዓለም ዋንጫውን ለማስተናገድ አሜሪካ፤ ካናዳ እና ሜክሲኮ ሃላፊነቱን ተጋርተዋል፡፡ አሜሪካ ከምድብ ማጣርያው አንስቶ የሩብ ፍፃሜ፣ የግማሽ ፍፃሜ እና የፍፃሜ ጨዋታዎችን ጨምሮ 60 ግጥሚያዎችን ስታስተናግድ፤ ካናዳ እና ሜክሲኮ ደግሞ እያንዳንዳቸው 10 ጨዋታዎችን በየከተሞቻቸው ያስተናብራሉ።

Read 16007 times