Sunday, 17 October 2021 18:20

“ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)


             "ከዚሀ በላይ ምን እጨምርለታሁ፡፡ የዓለም ሀያል ሀገር መሪ ሆኖ ልቡና ከሌለው፣ እኔ ምን ብዬ ነው የምጨምርለት! ግን ጥያቄማ እጠይቀዋለሁ.."
        
             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሀሳብ አለን...“በጥቅምት አንድ አጥንት፣” የሚለው አባባል ይቀየርልን። አሀ...‘ፕራክቲካል’ አይደለማ! ይኸው ጥቅምት ከገባ ስድስት ቀን አልፎትም ወላ አጥንት የለ! ወላ ብርድ መከላከያ ጮማ የለ! እናማ... የምናየው ብቸኛ አጥንት ቢኖር ሸሚዛችንን ቀድዶ ለመውጣት እየተፈታተነን ያለው የጎድን አጥንት ነው!  (አንተ ራስህ የጎድን አጥንትህ እንዲህ እስኪያፈጥ ድረስ የማንን ጎፈሬ ታበጥር ነበር?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ! አንድዬ!
አንድዬ፡— ማነህ አንተ በጠዋት የምትረብሸኝ? ግራ የሚገባ ነገር እኮ ነው...እናንተ ሰዎች በቃ ላትተዉኝ ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ይህን ያህል አማረርኩህ፣ ይህን ያህል አሰለቸሁህ እንዴ?
አንድዬ፡— ከአቤቱታው እከሌ ነኝ ማለቱ አይቀልም!
ምስኪን ሀበሻ፡— ምስኪኑ ሀበሻ ነኛ አንድዬ! እንዲህ በአጭር ጊዜ ረሳኸኝ አንዴ!
አንድዬ፡— ስለፈልፍ ዝም ብከለህ ከማዳመጥ እንደሱ አትለኝም! አንተማ ነጋዴዎች እንደሚሉት ቋሚ ደንበኛዬ ነህ፡፡ ዛሬ ግን ተለወጥክብኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ኸረ ምንም አልተለወጥኩም፣ እዛው ያስቀመጥከኝ ቦታ ነኝ፡፡
አንድዬ፡— በል ደግሞ አንተው ራስህ ተመችቶህ ቁጭ ባልክበት ለምንድነው ከዚህ የማታነሳኝ እያልክ ውቀሰኝ አሉ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ በጭራሽ እንደሱ አላደርግም፡፡
አንድዬ፡— ምነው ግን ዛሬ ድምጽህ ያለወትሮህ ሰለለብኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን ላድርግ አንድዬ፣ ምን ላድርግ? አይደለም ደምጻችን፣ ሁሉም ነገራችን እየሰለለ ነው እኮ!
አንድዬ፡— ምነው! ምነው! ለስንቱ ነገር ስጠብቃችሁ፣ ችግርና መከራው ቢከፋም የማትሻገሩት ውቅያኖስ አይኖርም ብዬ ተማምኜባችሁ...እስከዚህ ድረስ ተስፋ ቆርጣችኋል እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን፣ በቃ፣ ግራ ገባን፡፡ በራሱ ጓዳ የቆሻሻ መአት ተከምሮ፣ የራሱ አልፍኝ በሚሊዮን ቶን አቧራ ተሸፍኖ፣ መጀመሪያ ያንን እንደ ማጽዳት በእኛ ጉዳይ ገብቶ የሚፈተፍተው በዛና ግራ ገባን አንድዬ! አንድዬ፣ ግን ይህንን ሰውዬ አትገላግለንም!
አንድዬ፡— የቱን ሰውዬ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ይሄ ባይደን ሚሉትን ሰውዬ...
አንድዬ፡— ማነው ደግሞ እሱ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ብቻ አላውቀውም እንዳትለኝ፡፡ ይሄ ትኩስ ሹመኛ የሆነብን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ነዋ!
አንድዬ፡— እሱን ማለትህ ነው እንዴ! እኔም እራሴ ከእሱ የሚገላገልኝ አጥቼ ነው። ለእኔም ነገረ ሥራው ሁሉ ግራ ገብቶኛል፡፡ እሺ...እስቲ አንተ ይህን አደረገ፣ ይህን አጠፋ በለኛ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ምኑን ነግሬህ ምኑን ልተወው አንድዬ!
አንድዬ፡— የመሰለህን ንገረኝና ያልመሰለህን ደግሞ ተወው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እሱ ሰውዬ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ነው እንጂ፣ የእኛ ፕሬዝዳንት ነው እንዴ! ለምንድነው የማይተወን?
አንድዬ፡— እናንተንም በጣም አበሳጭቷችኋል ማለት ነው፡፡ ፉከራ አበዛባችሁ እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን ፉከራ ብቻ አንድዬ፣ ምን ፉከራ ብቻ! ጭራሽ የራሱ አልበቃ ብሎት ሌሎች ሀገራትን እየሰበሰበ ይኸው ያስዶልትብናል፡፡
አንድዬ፡— እናንተም እሱ አንድ ነገር ባሉ ቁጥር ከምትመላለሱ ጠንከር ብላችሁ፣ አያገባህም አትሉትም! በገዛ ጉዳያችሁ እንዲህ ሲያስቸግራችሁ እኔ ዘንድ ከመምጣት፣ እዛው ለምን #በማያገባህ ጥልቅ ትላለህ;  አትሉትም!
ምስኪን ሀበሻ፡— እኛማ እያልን ነው...አንድዬ፡፡ መች ዝም አልን ብለህ...
አንድዬ፡— አይበቃማ! እሱ ነገረኝ አንዳትሉት ግን... "መጀመሪያ አሽከርካሪው የአካል ጉዳተኛ መሆኑን እየነገራቸው ከመኪና ጎትተው የሚያወጡ ፖሊሶችህን አደብ ማስገዛት፣ በየትኛው የሞራል ስንቅህ ነው እኛን ይሀን አድርጉ፣ ይህን አታድርጉ የምትለው" አትሉትም! "ዓለም እያየ እነኛን ሁሉ ሺዎች ምስኪን የሀይቲ ስደተኞችን እንደ ከብት እየሰበሰቡ ሲያጉላሉ የከረሙ ሰዎችህን ቢያንስ ትንሽ የሰብአዊነት ምክር መስጠት ያልቻልክ፣ በየትኛው የሞራል ከፍታህ ነው ስለእኛ የምትናገረው; አትሉትም፡፡ ምስኪኑ ሀበሻ! ጎሽ፣ ጭራሽ ትስቅብኝ ጀመክ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ! ይቅርታ አድርግልኝ፣ አይለምደኝም፡፡
አንድዬ፡- ቆይ ቆይ፣ ወዴት፣ ወዴት! መጀመሪያ ለምን እንደሳቅህ ንገረኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን ላድርግ አንድዬ፣ አሁን የተናገርከው፣ አንተ ያልከው ሳይሆነ እኔ ያልኩት ነው የሚመስለው፡፡  
ምስኪን ሀበሻ፡— በነጋ በጠባ እያስለፈለፍክ አጋብተህብኝ ይሆናላ! "ከምን የዋለች ምን፣ ምን ተምራ መጣች" የምትሉት ተረት አላችሁ አይደል!
አንድዬ፣ ግን በቃ ሰሞኑን ፌስቡክ ላይ ያው...
አንድዬ፡— ይወርዱብሀል በለኝ....
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣  ለአንተማ እንደዛ አይነት ቋንቋ አልጠቀምም! ምን ልልህ ፈልጌ መሰለህ...ያው ለእነሱ ያዳላል ይሉሀል፡፡
አንድዬ፡—  ምስኪኑ ሀበሻ...
አንድዬ፡—  አቤት፣ አንድዬ!
ምስኪን ሀበሻ፡— እንደሱ ሲሉ ከሰማችኋቸው ምን በሏቸው መሰለህ...ለእኛ ቢያዳላ ኖሮማ፣ አሁን ስእሉ ሁሉ ሌላ ይሆን ነበር በላቸው፡፡ እሺ፣ ይሄ ባይደን ያልከውን ሰውዬ፣ አሁን ምን አድርገው እያላችሁኝ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ትንሽ ነገሮችን ገላልጦ ማየትና ማመዛዘን ያሚያስችል ልቦና ጨምርለት፡፡
አንድዬ፡-- ከዚሀ በላይ ምን እጨምርለታሁ፡፡ የዓለም ሀያል ሀገር መሪ ሆኖ ልቡና ከሌለው፣ እኔ ምን ብዬ ነው የምጨምርለት! ግን ጥያቄማ እጠይቀዋለሁ..
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን ጥያቄ፣ አንድዬ?
አንድዬ፡— "ሰማንያ ዓመት እዚህ ዓለም ላይ የቆየኸው አሁን በያዝከው ልቦና ነው ወይስ የበፊቱን መንገድ ላይ አሽቀንጥረህ ጥለህ ነው?" ብዬ እጠይቀዋለሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ደግሞ ራሱን ቢችል አንድ ነገር ነው፡፡ ዙሪያውን የተኮለኮሉ እኛንም ሀገራችንንም ጥምድ አድርገው የያዙ አሉልህ፡፡ በተለይ ደግሞ ሱዛን ራይስ የሚሏት ጉድ አለች፡፡ አንድዬ፣ እሷ ሴትዮ ግን ይሀን ያህል ምን አድርገናት ነው ለውድቀታችን ቀን ከሌት የምትጸልየው?
አንድዬ፡— መጀመሪያ ማንነቷን መች ነገርከኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡— የባይደን የጸጥታ ጉዳይ አማካሪ ነች ይላሉ፡፡
አንድዬ፡— እሷን ነው እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ በእኔ እየሳቅህብኝ ነው?
አንድዬ፡— በአንተማ ስቄ ካበቃሁ ስንት ጊዜዬ፡፡ እኔ የገረመኝ ነገር ስለ የትኛው ጸጥታ ነው የምታማክረው? ሰላም እንዳይኖር ውስጥ ለውስጥ ‘ግፋ በለው’ እያለች፣ ምን የሚሉት ጸጥታ ነው የምታማክረው! እኔ እኮ ነገር ማባባስ ስላልፈለግሁ እንጂ ዝም የምለው፣ የማላውቅ ሆኜ አይደለም፡፡ ሁሉንም ነገር አበጥሬ አውቀዋለሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አስደሰትከኝ!
አንድዬ፡— እሺ ሌሎቹስ..
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ስንቱን ልዘርዝርልህ! ብቻ...እኛን ለማጥፋት ሚሲሲፒ ወንዝ ዳርቻ ተሰብስበው የተማማሉ ነው የሚመስለው፡፡ በየቦታው ደግሞ አጨብጫቢዎች አሏቸው፡፡  
አንድዬ፡— ምስኪኑ ሀበሻ፣ ዝም ብለህ የጠላት ብዛት ከመቁጠር እኔን ስማኝ... ሁሉ ነገር እኮ የሚሆነው መጀመሪያ እናንተ ውስጣችሁን ስታጸዱ ነው፡፡ የውጪውም ሰብሬ ካልገባሁ የሚለው በውስጥ የተበላሸ ነገር መኖሩን ስለሚያውቅ ነው፡፡ የምልህ እየገባህ ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— በሚገባ አንድዬ! በሚገባ!
አንድዬ፡— ጎሽ! እንግዲህ ከእነ ተረታችሁ “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ፣” አይደል የምትሉት...! ለራሳችሁ ስትሉ ጣፍጡ፡፡ ደህን ሁን፣ ሰላም ግባ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አሜን አንድዬ፣ አሜን!  አሜን!

Read 1871 times