Saturday, 23 October 2021 12:44

የካንሰር ሕክምና ትኩረት ማግኘቱ ዘግይቶአል፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

ለHPV (ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ) በትክክለኛው ጊዜና ሁኔታ ክትባት ከተሰጠ የማህጸን በር ካንሰርን ማስቀረት ይቻላል፡፡ የአለም የጤና ድርጅት የማህጸን በር ካንሰርን መቆጣጠር ወይንም መገደብ በሚለው ፕሮግራሙ ውስጥ ካስቀመጠው አንዱ ነው፡፡
ከላይ ያነበባችሁትን የነገሩን ባለፈው እትም እንግዳችን የነበሩት ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊ ስትና የመራቢያ አካላት ካንሰር ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ዶ/ር ታደሰ ለዚህ እትምም በሕመሙ ዙሪያ ቀሪ የሆኑትን ጠቃሚ ነጥቦችን አእንደሚከተለው አጋርተውናል፡፡
ዶ/ር ታደሰ እንዳብራሩት የካንሰር ሕክምና ደረጃው ምንድነው? የሚለው ጥያቄ ሲነሳ መልሱ ብዙ አይነ ቶች (multi-modality) ናቸው የሚል ይሆናል ፡፡ እነዚህ የህክምና አይነቶች የየራ ሳቸው አቅም ያላቸው ሲሆን አንዱ የአንዱን ጉድለት እያሟሉ ወደመፍትሔው የሚወስዱ ናቸው፡፡ በአብዛኛው የሚደረጉት ሕክምናዎች ግን ቀዶ ሕክምና፤ Chemotherapy እና በRadiation ሕክምና ነው። በካንሰር ሕክምና ዙሪያ በሌሎች ባደጉ ሀገራት የሚሰጡ ሌሎች የህክምና አይነ ቶች ቢኖሩም በእኛ ሀገር ግን እነዚህ ሶስቱ በዋናነት ስራ ላይ ያሉ ናቸው። እነዚህን ሕክምናዎች ለመምረጥና ለታካሚው አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችለው ታካሚው ያለበት የህመም ደረጃ እና ሕዋሱ ከየትኛው ሰውነት የተነሳ ነው የሚለው ሲታወቅ ነው፡፡
የካንሰር ሕመም ደረጃ በአራት የሚከፈል ሲሆን ደረጃ አንድ ላይ የሚገኝ ከሆነ በኦፕራሲዮን ሙሉ በሙሉ መውጣት ይችላል፡፡ የካንሰር ሕመሙ ይመለሳል የሚል ጠቋሚ ነገሮች ከሌሉ በዚሁ በኦፕራሲዮኑ ማብቃት ሲችል ነገር ግን በሚደረጉት ምርመራዎች ካንሰሩ እንደሚመለስ የሚያሳዩ ነገሮች ካሉ በተጨማሪነት ኬሞቴራፒ እና የጨረር ሕክምና እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡ አንዳንዴ ጨረርና ኬሞ Radiation & Chemotherapy በአንድነት እንዲሰጥ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ያጋጥማሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ታካሚዎች ወደ ሕክምና የሚመጡት ሕመሙ ከተባባሰ ወይንም የካንሰር ሴሉ ከተስፋፋ በሁዋላ እና ሌላ የሰው ነት ክፍል ከነካ በሁዋላ በመሆኑ በኦፕራሲዮን ማስወገድ ስለማይቻል በቀጥታ ወደ ኬሞቴራፒ አለዚያም ወደጨረር ሕክምናው እንዲያመሩ የሚደረግበት ሁኔታ አለ ብለዋል ዶ/ር ታደሰ፡፡
Chemotherapy እና Radiation ጨረር ሕክምናን ቅደም ተከተል በተመለከተ ዶ/ር ታደሰ የገለጹት በአብዛኛው ጨረር እና ኬሞቴራፒ በአንድነት እንደሚሰጥ ነው፡፡ ሕመምተኞቹ ያሉበት ሁኔታ ለቀዶ ሕክምና አመቺ አይደለም ወይንም ተሰራጭቶአል ሲባል የሚታዘዝላቸው ጨረር እና ኬሞቴ ራፒ የተሰኘው መድሀኒት በአንድነት ነው። ሰውነት የተሰራው ከህዋሳት ወይንም ከሴሎች ስለሆነ መድሀኒቱ የካንሰር ሴሎቹን ሲገድል ጤናማ የሆኑትን የተፈጥሮ ሴሎችንም አብሮ የመግደል ሁኔታ ስላለ ይህን ለመከላከል ሲባል ሁለቱም ሕክምናዎች ተደጋጋፊ ሆነው እንዲወሰዱ ይደረ ጋል፡፡ በተቻለ መጠን ጤናማ የሆኑት ሴሎች እንዳይሞቱ ለማድረግ የሚወ ሰደውን መድሀኒት መጠን በመቆጣጠር የካንሰር ሴሎቹ ብቻ እንዲሞቱ ይደረጋል፡፡ ኦፕራሲ ዮን ከተሰራ በሁዋላ ግን የካንሰር ሴሎቹ ሊኖሩ ይችላሉ ወይንም ሊተካ ይችላል የሚል ጥርጣሬ ካለ አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ወይ Chemotherapy ወይንም ደግሞ Radiation ጨረር ብቻ ይታዘዛል፡፡ በተቻለ መጠን ሕክምናው ትኩረት የሚያደርገው የታመሙት ሴሎች ከሰውነት ውስጥ እንዲጠፉ ማድረግ ስለሆነ የሚወ ሰደውን መድሀኒት መጠን በጥንቃቄ መወሰን ትልቁ ኃላፊነት ይሆናል፡፡
በሰውነት ውስጥ የሚገኙት ጤናማ የሆኑ ህዋሳት እና በካንሰር ምክንያት የታመሙት ሕዋሳት ባህሪያቸው ይለያያል፡፡ በካንሰር የታመሙት ሕዋሳት በፍጥነት የሚራቡ እና ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ ሲሆኑ ጤናማዎቹ ግን በተፈጥሮአዊው ሕግ መሰረት በእርጋታ የሚራቡ እና የሚሞቱ ናቸው፡፡ ስለዚህ የኬሞቴራፒ ሕክምናም ሆነ የጨረር ሕክምናው እነዚህን የካንሰር ሴሎች እንዲገድል የሚሰጥ ነው፡፡ ጤናማዎቹ ህዋሳቶች የመራባት ሂደታቸው በጣም ዝቅተኛ በሆነ ደረጃ ስለሆነ እንደ ካንሰር ሴሎቹ ፈጥነው የሚጋለጡ አይደሉም፡፡ ያ ማለት ግን መድሀኒቱ ጭርሱንም ጤናማ ሴሎችን አይነካም ማለት አይደለም፡፡ ጤናማ የሆኑትን ሴሎችም የሚጎ ዳበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ አንዳንድ የሰውነት ክፍሎች ላይ ለምሳሌም አንጀት ግድግዳ ላይ ያሉ ጤናማ ሴሎች በፍጥነት እራሳቸውን መተካት ስለሚጠበቅባቸው በፍጥነት የመራባት ባህርይ አላቸው፡፡ ሰለዚህ በዚህ የህክምና ወቅት እነዚህ ሴሎች አብረው የመጎዳት እድል ይኖራቸዋል፡፡ ጉዳት ሲያደር ሱም በቋሚነት የሚደርሱ ወይንም ጊዜያዊ የሚባሉ ችግሮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡  ስለዚህ ሲነጻጸር በከፍተኛ ሁኔታ የካንሰር ሴሎችን ሲገድል ጤናማ ሴሎችን ግን በዝቅተኛ ደረጃ ሊጎዳ ይችላል። ነገር ግን ጤናማዎቹ ሴሎች እራሳቸውን የመተካት እድላቸው ሰፊ ነው፡፡ በእርግጥ ጤናማዎቹ ሴሎች በካንሰር ሕክምናው ከተጎዱ በሁዋላ አንዳንዶች ቶሎ የማገገም ሁኔታ ሲኖ ራቸው አንዳንድ ጊዜ ግን የሚቆይ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ በአብዛኛው ግን ይህ ህክምና ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ የሚበልጥ መሆኑን ሁሉም ሊያውቀው ይገባል ብለዋል ዶ/ር ታደሰ፡፡
የጨረር ሕክምናውና Chemotherapy አንድነትና ልዩነት በሚመለከት ዶ/ር ታደሰ እንደሚሉት ሁለቱም የጎንዮሽ ጉዳት አላቸው። ነገር ግን የካንሰር ሴሎቹን የሚያጠፉበት ሁኔታ ይለያያል።
የRadiation (ጨረር) ሕክምናው የካንሰር ሴሉ አለ የሚባልበት የሰውነት ክፍል ብቻ እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ ስለዚህ ለጊዜውም ቢሆን የሚጎዳው ጤናማ ሴልም በዚሁ ውስን በሆነ አካባቢ የሚኖረው ነው፡፡
የChemotherapy ሕክምና በደም የሚሰጥ ነው፡፡ ስለዚህ በየትኛውም የሰውነት ክፍል ውስጥ የመዳረስ ባህርይ ያለው ስለሆነ ለጊዜውም ቢሆን የሚጎዳውም በመላው ሰውነት ውስጥ ያለውን ሴል ነው፡፡
መረሳት የሌ ለበት ነገር ጤናማ ሴሎቹ ምንም እንኩዋን በህክምናው የተነሳ አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር በአብዛኛው እራሳቸውን መልሰው የመተካት እድል ያላቸው ስለሆነ አሳሰሰቢ አይደሉም፡፡ የኬሞቴራፒ ሕክምናውን ከጨረሱ በሁዋላ አንዳንዶች ወደ ጨረር ሕክምና ይተላለፋሉ። ይህ ደግሞ አሁንም መታከም ያለባቸው የካንሰር ሴሎች መኖራቸውን ያመላክታል፡፡ በአገራችን ያለው የጨረር Radiation ሕክምና የሚሰጠው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ሲሆን መሳሪ ያውም አንድ ብቻ ነው፡፡
ዶ/ር ታደሰ እንደሚሉት የህክምናው አላማ ታካሚውን ከሕመሙ ሙሉ በሙሉ ማዳን ሲሆን በሽታውን ማጥፋት ባይቻል እንኩዋን ምልክቱን በሙሉ በማጥፋት በሕይወት እያሉ የሚደርስ ባቸውን የህመም ሁኔታ ለመቋቋም ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም የሚመሩት ወደ Radiation (ጨረር) ሕክምና ነው፡፡
ለካንሰር ሕክምና በአለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት የተሰጠው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ በማህጸን በኩል ያለው የካንሰር ሕመምም በከፋ ሁኔታ እየጨመረ የመጣው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ በጨረር እና በኬሚካል ሕክምናው ቢረዱ ይድናሉ የተባሉ ሰዎች የ Radiation (ጨረር) መሳሪያ ወረፋውን በመጠበቅ ብዙ ስለሚቆዩ ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ የካንሰር ሕመም ባህርይ ሁለት አይነት ነው፡፡ አንዳንድ ሕመምተኞች የካንሰር ሴሎች በፍጥነት የሚራቡባቸው ሲሆን አንዳ ንድ ታማሚዎች ደግሞ ካንሰር ሴሉ ቀስ ብለው የሚራቡባቸው ናቸው፡፡
ይህንን የጨረር ሕክምና መስጫ መሳሪያ በሚመለከት ዶ/ር ታደሰ ሲያነጻጽሩ እንደሚከተለው ብለዋል፡፡
በአሜሪካ ወይንም በአውሮፓ ለ120ሺህ ሰዎች አንድ የጨረር ሕክምና መሳሪያ አለ፡፡
በኢትዮጵያ ለ110 ሚሊዮን ሰዎች አንድ የጨረር ህክምና መሳሪያ አለ፡፡
ከዚህ በባሰ መልኩ አንድም የጨረር ሕክምና መሳሪያ የሌላቸው 28 የአፍሪካ አገራት መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
የጨረር ሕክምና መስጫ መሳሪያ እጥረት መኖሩ የገንዘብ መጠኑ ከፍ ማለቱ ብቻ ሳይሆን ከገንዘቡ በላይ ግን ትኩረት ማጣቱ ዋነኛው ነው፡፡ በእርግጥ የጨረር መሳሪያው በቂ የተማረ ሰው ኃይል እና ሌሎች ተያያዥ ነገሮች ስለሚያስፈልጉት በቀላሉ ይገኛል ባይባልም ነገር ግን ትኩረት ከተሰጠው እና ጥረት ከተደረገ የማይኖርበት ምክንያት የለም። በአሁን ጊዜ በኢትዮጵያ ያለው የጨረር ሕክምና መሳሪያ አንድ በመሆኑ በተለያየ የካንሰር ሕመም ለተያዙ ሰዎች በተገቢው አገልግሎት መስጠት አያስችልም። ምናልባት በቅርብ ባይባልም ወደፊት ሊስተካከል የሚችል ይሆናል በሚል ተስፋቸውን ጠቁመዋል ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ የጽንስና ማህጸን ህክምና እስፔሻሊስት እና የመራቢያ አካላት ካንሰር ሕክምና እስፔሻሊስት፡፡

Read 12884 times