Sunday, 24 October 2021 00:00

ማስጠንቀቂያም፣ ማበረታቻም፣ አስደናቂም፣ አስደንጋጭም ናቸው - የውጤት ሕጎች።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

     “ሊሰበር የሚችል ነገር ይሰበራል”… የሚሉት ህግ አለ። የተጋነነ ወይም የተሳሳተ አባባል ቢመስልም፣ እውነት ነው። እንዴት?
    • “ጊዜው ሲደርስ፣ ውሎ አድሮ፣ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል”… ይላሉ የጥንት አዋቂዎች። ሊሳካ የሚችል ከሆነ ይሳካል - ለስኬት ካደረሱት።
     “የሺ እርምጃ ጉዞ፣ በአንድ እርምጃ ይጀመራል” የሚል አባባልም አለ። አንድ ስንራመድ፣ ወደ ግባችን አንድ እርምጃ እንቃረባለን።
     “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት” የሚለውን ትዕዛዝ መጥቀስ ይቻላል - የሚሆን አይመስልም፤ ግን ይሆናል። ለክፉም ለደጉም፣ ለብልፅግናም ለኑሮውድነትም።
            “ሊሰበር የሚችል ነገር ይሰበራል”…
ቀላል አባባል አይደለም። ለአውሮፕላን ምህንድስናና ለበረራ ደህንነት፣ እጅግ የጠቀመ ባለ ትልቅ ውለታ አባባል ነው። Murphy’s law በሚል ይታወቃል። “latent cause” ብለውም ይጠቀሙበታል። ዛሬ እዚህ ቦታ የምንሰራው ስህተት፣ ስንዝር ሳይርቅ እዚያው በዚያው መዘዙ ላይታይ፣ ዛሬውኑ ወይም በማግስቱ የኪሳራ እዳ ላያሸክመን ይችላል። ግን እናመልጣለን?
የአቶ መርፊ ህግ፣ ወዲህ ወዲያ አያወላዳም።  አታመልጡም፤ አይቀርላችሁም ይለናል። ጭካኔ ወይም ሟርት ይመስላል። ግዑዙ ዓለም፣ “ሆን ብሎ ጠማማ ይሆንብናል” የሚል ትርጉም ከሰጠነው፣ ተስፋ የለሽ አባባል እናደርገዋለን። ሪቻርድ ዳውኪንስ በዚህ ምክንያት፣ ይህን አባባል አይወዱትም። እውነት አላቸው። ነገር ግን፣ የአባባሉ አመጣጥ እንደዚያ አይደለም።
ትክክለኛ ሃሳብ እንድናገኝበት፣ አባባሉን፣ እንደ ክፋት ወይም እንደ ደግነት ሳይሆን፣ እንደ ተፈጥሮ ሕግ ብንቆጥረው ይሻላል። በቃ! መርፌ በተፈጥሮው ይዋጋል። እሳት ይነዳል፤ ነበልባሉ ያቃጥላል። እንደዚያ ነው ፍጥረቱና ምንነቱ። “የጋለ ይሞቃል” እንደማለት ነው። ለጋስነት ወይም ንፉግነት፣ ምህረት ወይም ፍዳ አይደለም።
በረዶ ይበርዳል፤ ያቀዘቅዛል። ይሄም፣ የደግነት ወይም የክፋት ጉዳይ አይደለም። እውኑ ተፈጥሮ እንደዚህ ነው። እውኑን ደግሞ፣ በአዎንታ መቀበል እንጂ፣ ሌላ ምን አማራጭ የለም።
በተፈጥሮ ላይ አመፅ ማስነሳት፣  በእውነታ ላይ ጦርነት ማወጅ፣ ከዚያም ማሳደድ አይቻል ነገር! ቢቻልስ ምን  ሊበጀን? ቢሳካልንስ ምን ሊውጠን? ምን ላይ ቆመን ምን ላይ እንደምናምፅ፣ ምንን ተማምነት ምንን እንደምናሳደድ፣ ለአፍታ ያህል ማገናዘብ፣ ቅንጣት ታክል ማሰብ አቅቶናል ማለት ነው። እየኖሩ አለመኖር፣ በቁም ማለቅ ካልሆነ በቀር፣ እውነታ ላይ ማመፅ፣ ተፈጥሮን ማሳደድ፣ ከስካርና ከቅዠት ያለፈ ትርጉም አይኖረውም። ሊኖረው ይችላል?
በመርፌ የተሰፋ ልብስና ጫማ እያደረግን፣ በእሳት የበሰለና የተጠበሰ ምግብ እየበላን፣ “ፍሪጅ” እየገዛን፣ አንዳንዴም ቀዝቃዛ ቢራ እያማረን፣…. የመርፌ፣ የእሳትና የበረዶ ተፈጥሮ ላይ ማመፅ አያዋጣም። እውኑ ተፈጥሮ ነው መተማመኛችን። የሕልውና ዋስትናችን።
በቃ! እውነታ ነው እህል ውሃችን። ውበትና መዝናኛችንም ጭምር እንጂ። ያለ እውነታ፣ የበሰለ ምግብና የተስፋ ልብስ አይገኝም። የኮረና ቫይረስ ክትባት እንኳ፣ አይኖርም ነበር። በተወሰነ ሙቀት ካልተብላላ፣ ክትባት አይመረትም። በበረዶ ውስጥ ካልተጓጓዘ፣ አይደርስልንም። በመርፌ ወደ ሰውነታችን ካልገባ፣ ክትባት አይሆንልንም። ከበሽታ አያድነንም። ለእውነታ መታመን ነው፣ የሕልውናችን መሠረትና መተማመኛ።
እሺ ይሁን። እውነታውን፣ “አዎ፣ እውነት ነው” ብለን እንቀበል። እሺ፣ እሳት ያቃጥላል፣ መርፌ ይዋጋል፣ በረዶ ይበርዳል እንበል። ይህን መናገር፣ አንድ ነገር ነው። ጥያቄው ምንድነው? “ሊወጋ፣ ሊያቃጥል፣ ሊያቀዘቅዝ የሚችል ነገር፣ ይወጋል፤ ያቃጥላል፤ ያቀዘቅዛል” ብሎ እርግጠኛ ሆኖ መናገር፣ ትንሽ አይለይም ወይ? እዚህ ላይ፣ አቶ መርፊ ጉድ ፈላበት። ንግግር ያሳመረ መስሎት፣ ስህተት ላይ የወደቀ ይመስላል። ግን፣ ተሳስቷል ወይ?
እሳት ያቃጥላል ብሎ መናገር፣ ወይም “የሚያቃጥል ያቃጥላል” ብሎ በሰፊው መናገር፣ አልያም፣ “ሊያቃጥል የሚችል ነገር ያቃጥላል” ቢባል፣ ምንድነው ልዩነቱ? እንዲያውም፣  “ምን ማድረግ ይችላል?” የሚል ጥያቄ፣ አንድ የማወቂያ ዘዴ ነው። ከዚያ በፊት ግን፣ ሌላ ቀዳሚ ጥያቄ አለ።
የእውኑ ተፈጥሮ ሦስት ገፅታዎች - “ምን፣ እንዴት፣ ለምን?” በሚሉ ጥያቄዎች።
“ምንድነው?” የሚል ጥያቄ፣ ከሌሎቹ ሁሉ ይቀድማል። በዚህም፣ ከአንድ ነገር ህልውና በመነሳት፣ ቅርፁንና መጠኑን ጨምሮ፣ ተጨባጭ የተፈጥሮ ምንነቱን ለማወቅ እንሞክራለን።
መርፌው ብረት ነው፤ ሹል ነው።
ከሰል ጥቁር ነው፤ ሲነድ እሳቱ ፍም ነው። ጋዙ ፈሳሽ ነው፤ ሲቀጣጠል እሳቱ ነበልባል ነው።
በረዶው ጠጣር ነው…
ይሄ  ይሄ ሁሉ፣ የእውነታ ግንዛቤ ነው። እውኑን ተፈጥሮ፣ በአዎንታ መገንዘብና ለእውነታ መታመን፣ የሁሉም ነገር መነሻ መሰረት ነው- ለሰው ልጅ ሁሉ። ውሃው ውሃ ነው፤ በረዶው በረዶ ነው።  “It is what it is” ከሚለው የግሪክ ፈላስፎች አባባል ጋር አዛምዱት - (“the law of identity” እንዲሉ)። ግን  ይሄ በቂ አይደለም።
“ምንድነው?” በሚለው ቀዳሚ ጥያቄ ውስጥ፣ ሌላ የእውነታ ገፅታ፣ ሌላ የጥያቄ ጥንስስ አለ። የፈላስፋዋ አየን ራንድ አባባል ብንጠቀም ይሻላል። “It is what it is. And it acts accordingly.” ትላለች ፈላስፋዋ። “the law of Causality” ማለትም ትርጉሙ ይሄው ነው። ነገሮች፣እንዴት እንዴት ይሆናሉ? ተፈጥሯዊ ነገሮች፣ “እንደየፍጥርጥራቸው” ይሆናሉ። አኳሃናቸው እንደተፈጥሯቸው ነው - የምንነታቸው ገፅታ ነውና።
የነገሮችን ምንነት፣ ከነገሮች ቅርጽና መጠን አንፃር መገንዘብ ትልቅ ቁም ነገር ነው። ነገር ግን፣ ከዚህ ጎን ለጎን፣ የነገሮችን ምንነት ከአኳሃናቸው አንፃር ማየት ደግሞ አለ። ከመንስኤና ከውጤት፣ ከሰበብና ከመዘዝ (cause and effect) አንፃር የነገሮችን ምንነት የማገንዘብ ጉዳይ ነው።
በሌላ አነጋገር፣ ምንድነው ከሚለው ጥያቄ ባሻገር፣ “ምን ማድረግ ይችላል?” ብሎ መጠየቅ፣ ሁለተኛው የማወቂያ ዘዴ ነው (“what can it do?”)። የነገሩን ምንነት፣ ከተግባር፣ ከጊዜ፣ ከሂደት አንፃር ለማየት ይረዳናል።
ብረት ተገርቶ ሹል መርፌ መሆን፣ መርፌ ደግሞ መውጋት ይችላል።
ከሰል ጠጣር እንደሆነ፣ ቤንዚን ፈሳሽ፣ ቡቴን ደግሞ አየር ወይም ጋዝ መሆኑን አይተን ነክተን ብንገነዘብ በቂ ነው? ከሰሉ፣ ቤንዚኑ ወይም ቡቴኑ መንደድ እንደሚችል፣… ፍሙ ወይም ነበልባሉ ማቃጠልና ማሞቅ እንደሚችል ብናውቅ ይከፋናል? በረዶ ማቀዝቀዝ እንደሚችል ማወቅስ? እውቀት ተገኝቶ ነው!
ግን፣ “ምን ያደርጋል?” …”ምን ዋጋ አለው?”…
“ምን ያደርጋል?” ብለን ስንጠይቅ፣ ወደ ሦስተኛው ገፅታ የሚያሸጋግር ድልድይ እናገኛለን። በአንድ በኩል፣ ትርጉሙ፣ ያው “ምን ማድረግ ይችላል?” እንደማለት ይመስላል። በሌላ በኩል ግን፣ “ምን ይፈይዳል? ምን ይጠቅማል? ለምን አገልግሎት ይውላል?” ወደሚል ጥያቄ ያሻግረናል። “ምን ያደርግልኛል?” ይባል የለ! ይሄ ሦስተኛው የእውነታ ገፅታ ነው። የነገሮችን ምንነት፣ ለሕይወት ከሚኖራቸው ፋይዳ አንፃር እንድናውቅ ያግዘናል - ከሰው ሕይወትና ኑሮ ጋር በማስተሳሰር።
ሕይወት ሲኖር ነው፣ ፋይዳ የሚኖረው። “Life is the standard of value” ትላለች ፈላስፋዋ። ጠቃሚና ጎጂ፣ ጥሩና መጥፎ፣… የሚሉ ቃላት፣ አንዳች ትርጉም የሚኖራቸው፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሕይወት ጋር በሚኖራቸው ትስስር ነው። እንዴት?
መርፌ ለስፌት ወይም ለክትባት፣ እሳት ለጥብስ ወይም ለቡና፣ ነዳጅ ለምድጃ ወይም ለመኪና፣ በረዶም ለመጠጥ ማቀዝቀዣ ወይም ለትኩሳት ማብረጃ… ተፈላጊ ናቸው፤ ዋጋ አላቸው፤ ጥቅማቸውን አውቀንም ለአገልግሎት እንፈልጋቸዋለን። ታዲያ፣ መተማመኛችን ምን እንደሆነ አስታውሱ። መውጋት የሚችል ነገር ይወጋል የሚለው “የመርፊ ህግ” ነው - መተማመኛችን። ለልብስ ስፌትና ለክትባት ያገለግለናል።
ነገር ግን፣ “የመርፊ ህግ” ማስጠንቀቂያ ነው። ማቃጠል የሚችል ነገር ያቃጥላል። ሊሰበር የሚችል ነገር ይሰበራል። እዚው በዚያው፣  አሁኑኑና ወዲያውኑ ባይሰበርብንም፣ የማይቀር ነገር ነው። እና ምን ተሻለ?
ለህክምና መርፌ፣ መክደኛ የሚያበጁለት፣ መልኩን ለማሳመር አይደለም። መክደኛውን አልፎ፣ ሊወጋን አይችልም። መውጋት ካልቻለ፣ አይወጋም።
ለተሰባሪ ቁሳቁስ፣ የስፖንጅ ባሕሪ ያላቸው መጠቅለያና ማሸጊያ ዘዴ የተበጀላቸውም፣ በሌላ ምክንያት አይደለም። ለካ፣ የመርፊ ህግ፣ ልዩ ሚስጥር አይደለም ያስብላል። በእለት ተእለት ኑሮ ላይ እንጠቀምበታለና።
በአውሮፕላን ምህንድስና ደግሞ፣ “ተዛብቶ ተገልብጦ ሊገጠም የሚችል መለዋወጫ እቃ ካለ፣ የሆነ ጊዜ መለዋወጫውን አዛብቶ ገልብጦ የሚገጥም ሰው ይኖራል” ይላል ማስጠንቀቂያው። የሕጉ ወይም የአባባሉ አመጣጥም፣ ከዚህ ጋር የተዛመደ ነው። እና ምን ተሻለ?
በተቻለ መጠን፣ የአውሮፕላን መለዋወጫ እቃዎች፣ በትክክለኛ አቅጣጫ ካልሆነ በቀር፣ በቦታቸው እንዳይገቡ የሚከላከል ዲዛይን እንዲኖራቸው ይደረጋል። ከተዛባ፣ በቦታው አይገጥምም። ስለዚህ ሊዛባ አይችልም። የማስጠንቀቂያው አስፈላጊነት ግልፅ አይደለም?
የዛሬ ድክመት፣ ዛሬ ወይም ነገ ባይሆን እንኳ፣ እዚያው በዚያው ባይሆን እንኳ፣ ዞሮ ዞሮ፣ ውሎ አድሮ፣ መዘዙን እየጎተተ ከተፍ ይላል። በጊዜያዊ ምስልና በእለታዊ ውሎ ብቻ አትታለሉ ይላል - ማስጠንቀቂያው። የዚህ አባባል ሌላኛው ገፅታ ግን፣ ማበረታቻ ነው።  
“ጊዜው ሲደርስ፣ ውሎ አድሮ፣ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል”… ይላሉ የጥንት አዋቂዎች።
ጥንታዊው በዘመነኛ ትንታኔ፣ “Treshold” ከተሰኘው ቃል ጋር ያዛመዳል። የዛሬ ተግባርና ጅምር፣ ወዲያውኑ፣ ለውጤት ላይበቃ ይችላል። በሂደት፣ ሄዶ ሄዶ፣ ቀስ በቀስ፣ የሆነ ደረጃ ላይ ካልደረሰ፣ “እድገቱ፣ እግሩና ለውጡ” አይታይም።
ቢሆንም ግን፣ በርቱ፣ ተስፋ አትቁረጡ የሚል ነው ቁምነገሩ። ዋናው ነገር ምንድን ነው? “ማስቆጠር ነው፤ ጥረትህ ይመዘገብልሃል፤ ለጊዜው ውጤት ባይወጣውም፤ የስራህን ያህል ማግኘትህ አይቀርም”። “ልፋት ቆጣሪ” ቴክኖሎጂ የለም።
ነገር ግን፣ አስተውል።
አንደኛ ነገር፣ ጥረትህ በውጤታማ መንገድ መሆን አለበት። አለበለዝያ፣ ልፋትን ማስቆጠር፣ ለብቻው ውጤትን አይወልድም።
ሁለተኛ ነገር፣ ስራህን በእንጥልጥል ማቋረጥ የለብህም። በግማሽ የቀረ ስራ፣ ከንቱ ድካም ነው። “calling”፣ “Installing” ሲል ቆይቶ፣ 100% ካልደረሰ፣ ሙከራው ሙሉ ለሙሉ ካልተሳካ፣ ዋጋ የለውም። 99% ደርሶ ቢከሽፍ፣ ጥሪው ሳይሳካ ቢቋረጥ፣ ውጤቱ፣ እንደ ዜሮ ነው።
ያልተፈለፈለ እንቁላል፣ ትንሽ ቀን ሲቀረው ቢስተጓጎል፣ “ትንሽ የቀረው ጫጩት” አይሆንልንም። 75% ጫጩት ብሎ ነገር የለም።
ታዲያ፣ ከዚህ የተለየ የተፈጥሮ መልክ እንዳለ አትርሱ።
“የሺ እርምጃ ጉዞ፣ በአንድ እርምጃ ይጀመራል” የሚለውንም አባባል አስታውሱ።
“arithmetic progression” የሚሉት ነው። አንድ ስንራመድ፣ ወደ መድረሻችን በአንድ እርምጃ እንቃረባለን። የመኪና ጉዞ፣ እስከ ጥግ ባያደርስ፣ ወደ መሃል ባያስገባ እንኳ፣ ያስጠጋል። 50% ወይም 75% ስኬት ልንለው እንችላለን። ዜሮ አይደለም። እንደ ጥረታችን ልክ፣ እንደ ፍጥነታችን መጠን ነው- ውጤታችን።
በሰዓት 100 ኪሎሜትር የሚጓዝ መኪና፣ በእያንዳንዱ ሰዓት፣ 100፣ ከዚያም 200፣ 300፣ 400 እያለ፣ ውጤቱን እየደመረ ይወስደናል። ወደ ግባችን ያስጠጋናል።
ለስደት ከሆነ ደግሞ፣ ከአገራችን ጋር ያራርቀናል።
ለክፉም ለደጉም፣ ለውጡና መዘዙ፣ ደረጃ በደረጃ፣ ስንዝር በስንዝር ነው። ከዚህ ጋር የሚመሳሰል፣ ሌላ የለውጥ አይነት አለ። ስለሚመሳሰል፣ ያሳስታል፣ ያዘናጋል። ነገር ግን እጅግ የተለየ የለውጥ አይነት ነው - የሚያስደንቅ ወይም የሚያስደነግጥ የለውጥ አይነት።
“ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት” የሚለውን ትዕዛዝ መጥቀስ ይቻላል።
“geometric progression” የሚሉት ይህን ነው። ጥቂት ሰዎች እየተዋለዱ ምድርን መሙላት የሚችሉ አይመስልም። አንድ፣ ሁለት ሶስት እያለ እንደመቁጠር ይሆንብናል። ግን፣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እጥፍ ድርብ እየተባዛ፤ ይትረፈረፋል።
ለሲሳይ ያድርገው። ለክፉ ከሆነ ግን፣ እንደማዕበል ነው። አጀማመሩ በትንሽ ነው። በዝግታ ስለሆነ፤ ያዘናጋል። አነሳሱ እንደ ዋዛ ነው። ግን ይባዛል፤ ይዛመታል። እየተዳመረ ሳይሆን እየተባዛ። ልዩነቱ፤ የትየሌለ ነው። ለማመን የሚከብድ ነው ለውጡ።
1000 በዓመት በአምስት በመቶ ቢጨምር 1050 ይናል። በሃያ አምስት ዓመት ዞር ብላችሁ ስታዮት ነው የምትደነቁት ወይም የምትደነግጡት።
አንደኛው በ5 በመቶ እያደገ፤ ወደ 4,000 ይጠጋል። ሌላኛው በሃያ በመቶ እየጨመረ፣ 64,000 ይደርሳል። ልዩነቱ ትንሽ ነው? የሁለት አገሮች ኢኮኖሚ እንዲህ እንዴት እንደሚራራቅ አስቡት። የዋጋ ንረት ወይም የብድር ጉዞ፣ ለበጎ ሲሆን ድንቅ ነው፤ ለችግር እንዳይሆን መጠንቀቅ ከተቻለ።



Read 12435 times