Saturday, 23 October 2021 14:02

ሚርዳድ ስለ ፍቅር እንዲህ ይላል...

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  ፍቅር የእግዚአብሔር ሕግ ነው፡፡ የምትኖሩት ፍቅርን ትማሩ ዘንድ ነው። የምታፈቅሩትም መኖርን ትችሉ ዘንድ! ለሰው ልጅም ከዚህ ውጪ ሌላ ትምህርት አያሻውም፡፡
ማፍቀር ማለትስ ምንድነው፣ አፍቃሪ ተፈቃሪውን ለዘለዓለሙ ወደ ራሱ ስቦ ሁለቱ አንድ እንዲሆኑ እንጂ?
ደግሞስ … ማንን ወይም ምንን ይሆን ማፍቀር የሚገባ? እውን ከሕይወት ዛፍ ቅጠሎች አንዷን መርጦ ልብ ያጋተውን መላውን ፍቅር ማዝነብ ይገባ ይሆን?
ግና፣ ቅጠሉን ያፈራው ቅርንጫፍ፣ ቅርንጫፉን የያዘው ግንድ፣ ግንዱን ያቀፈው ቅርፊትስ…? ቅርፊት፣ ግንዱን፣ ቅጠላ ቅጠል፣ ቅርንጫፎቹን የመገቡት ስሮችስ? ስሮቹንስ ያቀፈው አፈር? አፈሩንስ ያለማው ፀሐይ? ውቅያኖስ … አየሩስ?
ዛፍ ላይ ያለች ትንሽ ቅጠል፣ ለፍቅራችሁ ከተገባች፤ መላ ዛፉን ምን ያህል እጥፍ ትወዱት!? ከአጠቃላዩ ነጥሎ አንዱን ክፋይ የሚወድ ፍቅር፣ ራሱን ለሐዘን አጭቷል ቀድሞ ነገር!
እናንተ ግን፣ “ከአንድ ዛፍ ቅርንጫፍ እንኳ፣ እልፍ አእላፍ ቅጠሎች አሉ…
አንዳንዱ ጤነኛ፣ አንዳንዱ ታማሚ፤ ገሚሱ ቆንጆ ሌላው አስቀያሚ፡፡
ከፊሉ ግዙፍ ከፊሉ ድውይ፣ አማርጦ መውደድ አይገባም ወይ?”
ስትሉ ሰማሁ…
እኔ ግን እንዲህ እላችኋለሁ፣
ከታማሚው መጠውለግ ነው የጤነኛው ትኩስነት የሚመነጭ፡፡ እናም እንዲህ እላችኋለሁ፣ አስቀያሚነት የውበት መኳያዋ፣ ቀለም እና ብሩሿ ነው፡፡ ኧረ ለመሆኑ፣ ድውዩ ቁመቱን ለለግላጋው ባይሰጥ ለግላጋው መለሎ የሚሆን ይመስላችኋል?
እናንተ የሕይወት ዛፍ ናችሁ፡፡ ራሳችሁን ላለመከፋፈል ተጠንቀቁ፡፡ ፍሬን በፍሬ ላይ፣ ቅጠልን በቅጠል ላይ፣ ቅርንጫፍን በቅርንጫፍ ላይ አታስነሱ፤ ግንዱንም በሥሮች ላይ፣ ዛፉንም ከእናት አፈሩ አታጣሉ፣ አታናክሱ፡፡ ይህ ደግሞ … በእርግጥም … አንዱን ከሌላው አስበልጣችሁ ወይም ከተቀረው ሁሉ ለይታችሁ ስትወዱ የምታደርጉት ነው፡፡
አዎን … እናንተ ሁላችሁም … የሕይወት ዛፍ ናችሁ፡፡ ሥራችሁም የትም ነው። ቅርንጫፍና ቅጠሎቻችሁም በሁሉም ሥፍራ፣ ፍሬዎቻችሁም በሁሉም አፍ ውስጥ! በዚያ ዛፍ ላይ ያሉት የትኞቹም ፍሬዎች፣ የትኞቹም ቅርንጫፍ እና ቅጠሎች፣ የትኞቹም ሥሮች፤ የእናንተው ፍሬ፣ የእናንተው ቅጠልና ቅርንጫፍ፣ የእናንተው ሥሮች ናቸው፡፡
ዛፉ፣ ጣፋጭና ባለማራኪ መዓዛ ፍሬ ቢቸር፣ ሁሌ ጠንካራና ፍፁም አረንጓዴ ሆኖ ቢታይ … ሥሮቹን ወደ መገባችሁበት የሕይወት ወለላ እዩ…
ፍቅር የሕይወት ወለላ ነው፡፡ ጥላቻ ደግሞ የሞት መግል፡፡ ፍቅር ግን ልክ እንደ ደም፣ ሳይታጎልና ሳይገደብ በሕይወት ሥሮች ውስጥ ሊፈስስ ይገባዋል፡፡ የደም ፍሰት ሲገደብ በሽታ እና ወረርሽኝ ይሆናል፡፡ ጥላቻስ ምንድነው? ለጠይውም ለተጠይውም፣ ለመጋቢውም ለተመጋቢውም ገዳይ መርዝ የሆነ የታፍነ፣ የተገደበ ፍቅር እንጂ…
በሕይወት ዛፋችሁ ላይ ያለች ቢጫ ቅጠል፣ ሌላም ሳትሆን ፍቅር-ያስጣሏት ቅጠል ነች፡፡ ቢጫዋን ቅጠል አትውቀሷት። ደርቆ የተንጨፈረረው ቅርንጫፍም ሌላም ሳይሆን ፍቅር የተራበ ቅርንጫፍ ነው። የደረቀውን ቅርንጫፍ አትውቀሱት፡፡ የበሰበሰው ፍሬም ቢሆን ሌላም ሳይሆን ጥላቻ የመረዘው ፍሬ ነው፡፡ የበሰበሰውን ፍሬ አትኮንኑት፡፡
ይልቁንም የሕይወትን ወለላ፣ ለጥቂቶች ብቻ ችሮ ለብዙዎች የሚነፍገውን፣ በዚህም ራሱን ጭምር የነፈገውን፣ ዕውርና ንፉግ ልባችሁን ውቀሱ፡፡ የፍቅር መጸነሻው፣ የመውደድ አብራኩ ራሥን ማፍቀር ነው፡፡
የራስ ፍቅር ቢኖር እንጂ ፍቅር የሚባል ጨርሶ የለም፤ የሚቻልም አይደለም። ከሁሉን አቃፊው እኔነት በቀር የቱም እኔነት እውን አይደለም፡፡ ስለዚህም፣ እግዚአብሔር መላ ፍቅር ነው፤ ምክንያቱም ራሱን ይወዳልና፡፡
ፍቅር ካሳመመህ … መውደድ ስቃይ ከሆነብህ … እውነት እልሃለሁ … እስካሁን ድረስ እውነተኛው ማንነትህ፣ የፍቅር ወርቃማ ቁልፍ ገና እጅህ አልገባም ማለት ነው፡፡ አላፊ ጠፊ እኔነትን ስላፈቀርክ፣ ፍቅርህም እንዲሁ አላፊ ጠፊ ነው፡፡
 የወንድ ሴትን ማፍቀር ፍቅር አይደለም። ይልቁንም የሩቅ ተምሳሌቱ ነው፡፡ ወላጅ ለልጁ ያለው ፍቅርም፣ ሌላም ሳይሆን የፍቅር ቤተ መቅደስ ደጀ ሰላሙ ነው፡፡ የትኛውም ወንድ የሁሏም ሴት አፍቃሪ፣ የትኛዋም ሴት የሁሉም ወንድ አፍቃሪ እስክትሆን ድረስ፤ የትኛውም ልጅ የሁሉም ወላጅ ልጅ፣ የትኛውም ወላጅ የሁሉም ልጅ ወላጅ እስኪሆን ድረስ … ወንዶችና ሴቶች … ሥጋና አጥንት ከሥጋና አጥንት ጋር ስለመተቃቀፍ ይለፍፉ እንጂ … ፈፅሞ በተቀደሰው የፍቅር ሥም ሰይመው አያርክሱት፡፡ ይህ የፍቅርን ሥም ማጠልሸት ነውና፡፡ አንድ እንኳ ጠላት ካለህ ምንም ጓደኛ እንደሌለህ እወቀው። ጠላትነት ያሸመቀ ልብ ለወዳጅ ማደሪያ ይሆናል እንዴ ?
በልቦቻችሁ የጥላቻ ዘር እስካለ ድረስ የፍቅርን ሐሴት አታውቋትም፡፡ የሕይወት ወለላን ለሁሉም መግባችሁ ለአንዲት ቅንጣት ነፍሳት ብትነፍጉ፣ ያቺ የተነፈገችዋ ሕይወታችሁን ታመርረዋለች፡፡ የቱንም ነገር ሆነ ማንንም ስትወዱ፣ እንደ እውነቱ ከሆነ የምትወዱት ራሳችሁን ነው፡፡ ስትጠሉም እንዲሁ ነው … የቱንም ነገር ሆነ ማንንም ስትጠሉ እንደ እውነቱ የምትጠሉት ራሳችሁን ነው፡፡ የምትወዱትና የምትጠሉት ልክ እንደ አንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ላይነጣጠሉ ተጣምረዋልና፡፡ ለራሳችሁ ታማኝ ብትሆኑ ኖሮ፣ የምትወዱትንና የሚወድዳችሁን ከመውደዳችሁ በፊት የምትጠሉትንና የሚጠላችሁን ትወድዱ ነበር፡፡
ፍቅር መልካም ምግባር አይደለም፡፡ ፍቅር መሰረታዊ ፍላጎት ነው፡፡ ከዳቦና ከውኃ፣ ከዓየርና ከብርሃን የበለጠ ፍቅር ያሻችኋል፡፡ ማንም በማፍቀሩ አይኩራራ፣ ይልቁንም ነጻ ሆናችሁ እንዲሁ በዘፈቀደ አየሩን ወደ ውስጥ እንደምትስቡትና እንደምታስወጡት ሁሉ ፍቅርንም እንዲሁ በነጻነት ልብም ሳትሉ ተንፍሱት፡፡ ፍቅር፣ ማንም እንዲያወድሰው አይሻም፡፡ ይልቁንም ለፍቅር የተገባ ልብ ሲያገኝ ያን ልብ ያወድስ ይቀድሰዋል እንጂ። ከፍቅርህ ወሮታ አትጠብቅ፡፡ ፍቅር በራሱ ለፍቅር በቂ ሽልማቱ ነው፤ ልክ ጥላቻ ለጥላቻ በቂ ቅጣቱ እንደሆነው ሁሉ፡፡ ከፍቅር ጋር ሒሳብ አትተሳሰቡ፡፡ ፍቅር ሒሳብ የሚያወራርደው ከራሱ ጋር ብቻ ነውና፣ ተጠያቂነቱም ለማንም ሳይሆን ለራሱ ብቻ!
ፍቅር አያበድርም፣ አያውስምም። ፍቅር አይገዛም፣ አይሸጥምም፡፡ ሲሰጥ ግን ሁለመናውን ይሰጣል፡፡ ሲወስድም ሁለመናውን ይወስዳል፡፡ መቀበሉ በራሱ መስጠት ነው፡፡ መስጠቱም በራሱ መቀበል! እናም፣ ለዛሬም፣ ለነገም ለከነገወዲያም እንዲሁ ነው፡፡
ራሱን ሳይሰስት ለባሕሩ የሚለግስ የትኛውም ወንዝ፣ ዘወትር በባህሩ ደግሞ እንደሚሞላ ሁሉ እናንተም እንዲሁ ፍቅር መልሶ ይሞላችሁ ዘንድ ራሳችሁን አንጠፍጥፋችሁ ለፍቅር ስጡ፡፡
አዎን … የባሕሩን ሥጦታ ከባሕሩ የሚነፍግ ኩሬ መጨረሻው መበስበስም አይደል !? በፍቅር … ትንሽ ወይም ትልቅ የሚሉት ነገር የለም፡፡ ፍቅርን መለካት፣ መመተር … ለፍቅር ደረጃ ማውጣት ስትሞክር፣ ፍቅር መራር ትዝታዎቹን አስታቅፎህ እብስ ይላል...
በፍቅር ዘንድ … ትናንት ወይም ዛሬ፣ ዛሬ ወይም ነገ… እዚህ ወይም እዚያ ብሎ ነገር የለም፡፡ ሁሉም ወቅቶች የፍቅር ወቅቶች ናቸው፡፡ የትኛውም ቦታ ቢሆን ለፍቅር ማረፊያነት የተገባ! ፍቅርን … ወሰንም ሆነ ዳር ድንበር፣ ካቴናም ሆነ የተዘጋ በር አይገድበውም፡፡ የትኛውም መሰናክል ጉዞውን ያሰናከለው ፍቅርም በተቀደሰው የፍቅር ሥም ለመጠራት ባልተገባው፡፡
ዘወትር፣ ፍቅር ዕውር ነው ብላችሁ ስታወሩ እሰማለሁ፡፡ አዎን፣ አፍቃሪ በተፈቃሪው ላይ አንዳችም እንከን አያይም ማለታችሁ ነው፡፡ እኔ ግን እላችኋለሁ … ይሄ ዓይነት አለማየት የማየት ከፍታ ጫፍ ነው፡፡
በምንም ነገር ላይ እንከን አታዩ ዘንድ ምነው ሁሌ በታወራችሁ፡፡----
(ከ“መጽሐፈ ሚርዳድ” በሚካኤል ኔይሚ - ትርጉም - ግሩም ተበጀ)

Read 2615 times