Sunday, 31 October 2021 18:25

ለተሰንበትና የኤንኤን የሩጫ ቡድን

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

በረጅም ርቀት ሶስቱ የዓለም ሪከርዶች በ5000 ሜትር 14፡06.62፤ በ10ሺ ሜትር ላይ  29:01.03፤ በግማሽ ማራቶን  62፡52
በኤንኤን የሩጫ ቡድን የተያዙ አትሌቶች ባለፉት 4 ዓመታት ከ12 በላይ ትልልቅ ማራቶኖችን አሸንፈዋል፣ ከ9 በላይ የዓለም ሪከርዶችን አስመዝግበዋል፤ ከ180 በላይ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮችን በዓለም ዙሪያ  ድል አድርገዋል፡፡


በዓለም አትሌቲክስ ላይ በ2021 እኤአ እንደ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ለተሰንበት ግደይ መነጋገርያ ለመሆን የበቃ የለም፡፡ የ23 ዓመቷ ለተሰንበት ከ2020 እኤአ ጀምሮ በ5ሺ እና በ10ሺ ሜትር የዓለም ሪከርዶችን ካስመዘገበች በኋላ ባለፈው ሰሞን ደግሞ በቫሌንሽያ በተካሄደ ግማሽ ማራቶን  62፡52 በሆነ ጊዜ ያስመዘገበችው አዲስ የዓለም ሪከርድ ርቀቱን ከ64 እና ከ63 ደቂቃዎች በመግባት በዓለም አትሌቲክስ የመጀመርያዋ ሴት አትሌት አድርጓታል፡፡ አስቀድሞ የነበረውን የዓለም ግማሽ ማራቶን ክብረወሰን በ70 ሰከንዶች ማሻሻሏም በውድድሩ ታሪክ ከ40 ዓመታት በኋላ የተመዘገበ ድንቅ ውጤትም ሆኗል፡፡
በርካታ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች በ2019 እአኤ ላይ ሆላንድ ውስጥ በተካሄደ የ15 ኪሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ላይ አትሌት ለተሰንበት 44፡20 በሆነ ጊዜ ስታሸንፍ በትራክ እና በጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች እንደሚሳካላት ገምተው ነበር፡፡ በ2020 እኤአ ላይ በ5000 ሜትር 14፡06.62 በሆነ ጊዜ የመጀመርያዋን የዓለም ሪከርድ ስታስመዘግብ በ2021 እኤአ ላይ ደግሞ በ10ሺ ሜትር ላይ  29:01.03 በሆነ ሰዓት በረጅም ርቀት ሁለተኛዋን የዓለም ሪከርድ ይዛለለች፡፡ የዓለም አትሌቲክስ የሪከርድ መዝገብ እንደሚያመለክተው  በግማሽ ማራቶን ለተሰንበት 62፡52 በሆነ ጊዜ በሩጫ ዘመኗ ያስመዘገበችው ሶስተኛዋ የዓለም ሪከርድ  በሁሉም ርቀቶች ከተመዘገቡት የሪከርድ ሰዓቶች ተነፃፅሮ ሲታይ የላቀ ታሪክ ሲሆን በ5000 ሜትር – 13:39.43፤  በ10,000 ሜትር – 28:38.00  እንዲሁም በማራቶን – 2:11:17   ምርጥ ሰዓቶችን እንደማስመዝገብ ይቆጠራል፡፡
ከለተሰንበት የግማሽ ማራቶን ሪከርድ በኋላ በታዋቂው የአትሌቲክስ ተንታኝ ድረገፅ ሌትስራን በተሰሩ ትንታኔዎች ደግሞ የተለያዩ ሃሳቦች ተንፀባርቀዋል፡፡ በአንደኛው  ትንታኔ ላይ እንደተገለፀው በ2021 እኤአ ላይ በማንኛውም አትሌት በልዩ ብቃት የዓለም ሪከርድ ሲመዘገብ  ሦስት ሃሳቦች መናፈሳቸው አይቀርም። የመጀመርያው የፈለገ ሪከርድ ቢሆንም ዶፒንግ  አለበት የሚለው ትችት ነው፡፡ በሌላ በኩል የአትሌቷን ምርጥ ብቃት በቴክኖሎጂ ከዳበሩ የመሮጫ ጫማዎች ጋር በማያያዝ ስኬቱን ትርጉም የለሽ ለማድረግም ይሞከራል፡፡ በመጨረሻም ግን በአድናቆት ‹‹ዋው  ይገርማል›› የሚሉም ይገኙበታል። በሌትስ ራን ድረገፅ ላይ በቀረበ ሌላ ትንታኔ አትሌት ለተሰንበት  የ5ሺ፤ የ10ሺ ሜትር እና በግማሽ ማራቶን ሶስት የዓለም ሪከርዶችን ጠቅልላ በመያዟ የኖርዌይ አትሌት ኢንግሪድ ክርስቲያንሰን በ1991 እኤአ ላይ ያስመዘገብችውን ታሪክ ለመጎናፀፍ አስችሏታል፡፡  ከታዋቂዋ እንግሊዛዊት የረጅም ርቀት ሯጭ ፓውላ ራድክሊፍ የሩጫ ዘመን ጋር የሚያመሳስሏት ሁኔታዎች መኖራቸውም ተወስቷል፡፡ ሁለቱም በአሥራዎቹ ዕድሜያቸው ላይ በዓለም የወጣቶች ሻምፒዮና ላይ አሸናፊ መሆናቸው፤ በዓለም አትሌቲክስ ላይ ለሪከርድ ሰዓቶች ዋንኞቹ ተጠቃሾች ቢሆኑም በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዎችን አለመሸነፋቸው ተጠቅሶ ነው።  ፓውላ ራድክሊፍ በዋናዎቹ ዓለም አቀፍ  ውድድሮች የወርቅ ሜዳልያ አሸንፋ የማታውቅ ሲሆን ለተሰንበትም በ2017 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዶሃ ላይ የብር እና በ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ የነሐስ ሜዳልያዎችን ነው ያገኘችው፡፡ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ትውልዷ በትግራይ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የምትወዳደረው በትራንስ ኢትዮጵያ ክለብ አባልነት ነው፡፡ የግል አሰልጣኟ ሀይሌ እያሱ ሲሆን በማናጀርነት ሆላንዳዊው ጆስ ሄርማንስ እንዲሁም በተወካይነት ጌታነህ ተሰማ አብረዋት እንደሚሰሩ እና የትጥቅ ስፖንሰሯም ናይኪ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
የአትሌት ለተሰንበት ግደይ ውጤት በዓለም አትሌቲክስ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እየፈጠረ የመጣውን የኤን ኤን የሩጫ ቡድንን NN Running Team   በከፍተኛ ደረጃ የሚያስተዋውቅ  ሆኗል፡፡ አትሌቷ በመጀመርያ የግማሽ ማራቶን ውድድሯ የዓለም ሪከርድ ልታስመዘግብ ስትበቃ ፕሮፌሽናል የሩጫ ቡድኑን በተቀላቀለችበት ማግስት ነው። በቫሌንሽያ ካደረገችው የግማሽ ማራቶን ውድድር በፊት የሩጫ ቡድኑን መቀላቀሏን አስመልክቶ በሰጠችው አስተያየት ከቡድኑ ጋር በመስራት የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደምትችል እምነት ማሳደሯን ገልፃ ነበር። «ስለኤን ኤን ቡድን በደንብ አውቃለሁ፡፡  በዓለም ላይ ከሁሉ የተሻለ ቡድንን በመቀላቀሌ ኩራት ይሰማኛል፡፡ በሥራዬ ቀጣዩን ርምጃ ማድረግ እንደምችልም ተስፋ አደርጋለሁ።›› በማለትም አስተያየት ሰጥታለች፡፡ የኤን ኤን  ቡድን ዲሬክተር የሆኑት ጆስ ሄርመንስም በበኩላቸው‹‹በዓለም ላይ ካሉት ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጮች መካከል አንዷን ቡድናችን ላይ በመጨመራችን ኩራት ይሰማኛል ። በቅርብ ዓመታት በዓለም አትሌቲክስ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገብን ቢሆንም በቡድናችን የሴቶችን ተሳትፎ   የማሳደግ ፍላጎት ሁልጊዜም ነበረን። ለተሰንበት ምርጥ ውጤቶችን በማስመዝገቧ  ብቻ ሳይሆን የአትሌቲክስ ስፖርትን በሚያሳድግ ባሕርይዋም ጭምር አባል አድርገናታል፡፡›› ብለዋል፡፡
ዋና መቀመጫውን በሆላንድ ያደረገው NN Running Team  በልዩ አደረጃጀቱ ፈርቀዳጅ ፕሮፌሽናል የሩጫ ቡድን ሆኖ ይጠቀሳል። ባለፉት 4 ዓመታትም በዓለም አትሌቲክስ ከፍተኛውን ውጤት በረጅም ርቀት፤ በጎዳና ላይ ሩጫ እና በማራቶን ውድድሮች ያስመዘገቡ አትሌቶች ተሰባስበውበታል፡፡  በአሁን ወቅት ፕሮፌሽናል የሩጫ ቡድኑ 15 የተለያዩ አገራትን የሚወክሉ ከ60 በላይ በዓለም አትሌቲክስ በረጅም ርቀት ሪከርዶችን ያስመዘገቡ ፤ የዓለም ሻምፒዮኖች እና ዝነኛ ኦሎምፒያኖች ይገኛሉ።  ከቡድኑ አባላት መካከል በወንዶች  ቀነኒሳ በቀለ፣ ብርሃኑ ለገሰ፣ ሙሌ ዋሲሁንና ሰለሞን ደቅሲሳ ...ከኢትዮጵያ፤  ኤሊውድ ኪፕቾጌ ጄፊሪ  ካምዎሮር፣ አቤል ኪሪዊ፣ ጄዮፍሪ ኪሪዊ፣ ላቦን ኮሪር ፣ጊድዮን ኪፕኬተርና ፊሊሞን ሮኖ ... ከኬንያ፤  ጆሽዋ ኬፕቴጂና  ስቴፈን ኪፕሮቲች ከኡጋንዳ፤ አብዲ ነገዬ ከሆላንድ፤ እንዲሁም ማርየስ አዮኔስኩ ከሮማኒያ ይጠቀሳሉ፡፡ በሴቶች በኩል ደግሞ  ከሳምንት በፊት ቡድኑን የተቀላቀለችው  ለተሰንበት ግደይ እና ታደለች በቀለ ከኢትዮጵያ እንዲሁም  ሳሊ ቺፕዬጎ እና ፍሎረንስ ኪፕላጋት ከኬንያ ይገኙበታል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶችን በማናጀርነት ከ35 በላይ ባገለገሉትና የታዋቂው ግሎባል ስፖርት ኮሚኒኬሽን ዲያሬክተር በሆኑት ጆስ ሄርማንስ ጠንሳሽነት NN Running Team  በ2017 እኤአ ላይ ተመስርቷል፡፡ ግሎባል ስፖርት ኮምኒኬሽን Global Sports Communication (GSC) ተቀማጭነቱን በሆላንድ ካደረገው የኢንሹራንስ ኩባንያ ኤንኤን ግሩፕ NN GROUP እና ከአሜሪካው ትጥቅ አምራች ኩባንያ ናይኪ NIKE በፈፀሙት የትብብር ስምነት ነው። ግሎባል ስፖርት ኮምኒኬሽን  በሆላንዷ ከተማ ኒጂማገን የሚገኝ፤ ከ34 የተለያዩ አገራት ከ200 በላይ አትሌቶችን በማኔጅመንቱ የሚያስተዳድር፤ 12 የአትሌቲክስ አሰልጣኞች፤ 12 የአካል ብቃት ፊዚዮቴራፒ ባለሙያዎች እና ከ28 በላይ ሰራተኞችን ያቀፈ ዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋም ነው፡፡ የአምስተርዳም፤ የሃምበርግና የሙምባይ ማራቶኖችን እንዲሁም የኒውደልሂ ግማሽ ማራቶንን እንደሚያዘጋጅም ይታወቃል፡፡  ኤንኤን ግሩፕ ደግሞ በ18 የዓለም አገራት የሚንቀሳቀስ  የመድህን ኩባንያ ሲሆን በዘርፉ ከ170 ዓመታት በላይ ልምድ ያካበተ በተለይ በአውሮፓ የሚካሄዱ ከ25 በላይ የጎዳና ላይ ሩጫዎችን ስፖንሰር የሚያደርግ ነው። ናይኪ  ዋና መቀመጫውን በፖርትላንድ አሜሪካ  ላይ ያደረገ ዓለምአቀፍ ኩባንያ ሲሆን በዓመት ከ37.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የሚያስመዘግብ የአትሌቲክስ ጫማ እና አልባሳት አቅራቢ እና ዋና የስፖርት መሳሪያዎች አምራች ነው። በዓለም ዙሪያ ከ76,700 ሰራተኞችን ቀጥሮ የሚያስተዳድረው ናይኪ በምርት ስሙ ብቻ ከ32 ቢሊዮን ዶላር በላይ በመተመኑ  በስፖርት ኢንዱስትሪው በጣም ዋጋ ያለው የንግድ ምልክት ሆኗል።
የኤንኤን ሩጫ ቡድን ዋና መቀመጫ በሆላንድ ቢሆንም በተለያዩ  አገራት  የማሰልጠኛ ካምፖችን በማቋቋምና አሰልጣኞችና ማናጀሮችን በሃላፊነት አስቀምጦ በመስራት በዓለም አትሌቲክስ የጎላ አስተዋፅኦ ማድረጉን ቀጥሏል፡፡ በኬንያ ካፕታጋት፤ በሆላንድ ኤነስቼዴ፤ በኡጋንዳ  ካፖሆሮዋ እና በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ከተሞች ላይ በመሰረታቸው ካምፖች የስልጠና ፕሮጀክቶቹን እያካሄደም ነው፡፡ በስፖርት ተቋሙ በአፍሪካ በተለይ በኢትዮጵያ እና በኬንያ ከሚሰሩ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የአትሌት ተወካዮች፤ ማናጀሮችና አሰልጣኞች መካከል በኢትዮጵያ ጌታነህ ተሰማ እና በኬንያ ፓትሪክ ሳንግ የሚጠቀሱ ናቸው። ፕሮፌሽናል የሩጫ ቡድኑ የአትሌቶችን የዝግጅት ሁኔታ፤ ከሩጫ ውጭ ያለ ህይወት፤ የውድድር ተሳትፎ፤ ውጤቶች እና ሌሎች ተያያዥ መረጃዎችን እያደራጀ የሚሰራ ሲሆን በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች በየዓመቱ ከ40 ሚሊዮን በላይ ተከታታዮችን አግኝቷል፡፡ በዓለም ዙርያ ከ25 በላይ የጎዳና ሩጫዎችን ስፖንሰርነት የሚያደርግ ሲሆን ፤ ልዩና ፈታኝ የረጅም ርቀት ሩጫዎችን በማዘጋጀትም ይታወቃል፡፡  ኬንያዊው ኤሊውድ ኪፕቾጌን በዋናነት ባሳተፉት ሁለት ፕሮጀክቶች ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት በናይኪ በተቀረፀው Breaking2 እና በ The INEOS 1:59 Challenge ላይ አጋር ከመሆኑም በላይ በቅርቡ በቫሌንሽያ NN Valencia World Record Day የተባሉት ውድድሮች ይገኙበታል፡፡
የኤንኤን ሩጫ ቡድን በግሎባል ስፖርት ኮምኒኬሽን ስር ለተያዙ እና ፕሮፌሽናል ቡድኑን በመወከል ለሚወዳደሩ አትሌቶች ውጤታማነት አጠቃላይ ደህንነት ይሰራል። በቡድኑ በሳይንሳዊ መንገድ የሚታገዙ ስልጠናዎች እና የስነ ምግብ ስርዓቶች  በስፋት ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡ይህም  የስፖርቱን አሠራር ለማሻሻል ከሁሉ የተሻለ አማራጭ እንደሆነም እየታየ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት አትሌቶች የተሻሻለ ስልጠና፣ የህክምና ክትትልና ተጨማሪ  ድጋፎችን እንዲያገኙ አስችሏል፡፡ በስልጠና ካምፖች እና በውድድር ወቅት ለአትሌቶች ቋሚ የፊዚዮቴራፒ ሕክምና ማቅረብ ረገድ ተችሏል። በአጠቃላይ ከላይ በተዘረዘሩት ለአትሌቶች የተደረጉት ተጨማሪ ድጋፎች ከፍተኛ ውጤቶችን አስገኝተዋል፡፡ ኤን ኤን የሩጫ ቡድን መንቀሳቀስ ከጀመረ ገና 4 ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም  በስሩ የያዛቸው አትሌቶች ከ12 በላይ የትልልቅ ማራቶኖችን አሸንፈዋል፣ ከ9 በላይ የዓለም ሪከርዶችን አስመዝግበዋል፤ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ከ180 በላይ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮችን ድል አድርገዋል፡፡

Read 11708 times