Saturday, 30 October 2021 00:00

በአካል እየተካሄደ ያለው የዶሮና የእንስሳት ሀብት አውደ ርዕይ ዛሬ ምሽት ይጠናቀቃል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አስረኛው የኢትዮ ፖልተሪ ኤክስፖ፣ 6ኛው የአፍሪካ እንስሳት ሀብት አውደርዕይና ጉባኤ ከትላንት በስቲያ ጥቅምት 18 ቀን 2013 ዓ.ም የተከፈተ ሲሆን ዛሬ ማምሻውን እንደሚጠናቀቅ ተገለፀ። በበይነ መረብ የሚካሄደው ደግሞ እስከ ህዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም ይቀጥላልተብሏል።
በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የንግድ ትርኢቶች አዘጋጅ የሆነው ፕራና ኢቨንትስና መቀመጫውን ሱዳን ያደረገው አጋሩ ኤክስፖ ቲም በጋራ ያዘጋጁትና ቀዳሚና ሁሉን አቀፍ የዶሮና የእንስሳት ሀብት ቴክኖሎጂ ግብአትና መፍትሄዎችን ያካተተው አውደ ርዕዩ በርካታ የአገር ውስጥና የውጪ ኩባንያዎች የተሳተፉበት ሲሆን ከአንድ ቀን የዶሮ ጫጩት አቅራቢዎች ጀምሮ በርካታ የግብርናና የእንስሳት ሀብት ውጤቶች የተጎበኙበት ነው። በእለቱ እስከ ዛሬ ያልተሞከሩና አዲስ የሆኑ የግብርናና የእንስሳት ሀብት ውጤቶች ይፋ የሆኑ ሲሆን ከነዚህ መካከል በሀሮሚያ ዩኒቨርስቲ በምርምር የተገኘው የግመል ወተትን  ወደ እርጎነት የመቀየር ስራ ሲሆን የግመል ወተት እርጎም ለእይታ ቀርቦ ነበር።
ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ኮፐንሀገን ዩኒቨርስቲ ጋር በጥምረት በአይነቱ ለየት ያለ በግመል ወተት እርጎ፣ አይብና ፓስቸራይዝድ የግመል ወተት መስራት መቻሉን የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የግብርናና ሳይንስ ኮሌጅ ተመራማሪና መምህር የሆኑት አቶ ገመቹ ጣፋ ተናግረዋል። ይህንን የምርምር ውጤትም ሀሙስ እለት ስካይ ላይት ሆቴል በተከፈተው በ6ኛው የአፍሪካ የዕንስሳት ሀብት ጉባኤ፣ በ10ኛው የዶሮ ኤክስፖና በ29ኛው የኢትዮጵያ እንስሳት አርቢዎች ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ ላይ አስተዋውቆ አድናቆትን አትርፏል። በዚህ አውደርዕይና ጉባኤ ላይ አጠቃላይ በዘርፉ ላይ የተሰማሩና ከኢትዮጵያ፣ ከጀመርመን፣ ሃንጋሪ፣ ኔዘርላንድስ፣ ስኮትላንድ እና ሱዳን የተውጣጡ ኩባንያዎች የተሳተፉ ሲሆን በአውደርዕዩ በርካታ የንግድ ትስስሮች፣ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ሽግግሮች፣ ውይቶችና የልምድ ልውውጦችም እየተካሄዱበት ነው ተብሏል።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ መከሰቱን ተከትሎ በአካል የሚካሄዱ አለም አቀፍ የንግድ ትርኢቶች ተቀዛቅዘው መቆየታቸውን የገለጹት የፕራና ኢቨንትስ ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ  ድርጅታቸው ከ4ኛው አግሮ ፉድ ፕላስት ፕሪንት ፓክ የግብርና ኤክስፖ  ጀምሮ በተከታታይ እያዘጋጃቸው ያሉት ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቶች ኢኮኖሚውንና አጠቃላይ የንግድ አንቅስቃሴውን ለማነቃቃት ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል።
ዛሬ ከሚጠናቀቀው 10ኛው ኢትዮ  የዶሮ ኤክስፖ፣ 6ኛው አፍሪካ የእንስሳት ሀብት ጉባኤና ከ29ኛው የኢትዮጵያ እንስሳት አርቢዎች ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ ጎን ለጎን በዚያው በስካይ ላይት ሆቴል በኔዘር ላንድስ ልማት ድርጅት አስተባባሪነት የወተት ሀብት ልማት ላይ ያሉ ተግዳሮቶችና ጥሩ አጋጣሚዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ የፓናል ውይይት የተከፈተ ሲሆን በዚህ ውይይት ላይ አለም አቀፍ የዘርፉ ምሁራን፣ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ፣ የተለያዩ የውጪና የሀገር ውስጥ ተመራማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ በወተት ሀብት ላይ ያሉ ተግዳሮቶችንና ጥሩ አጋጣሚዎችን የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል። በቀረቡት ጥናቶች ላይ ውይይትና የመፍትሄ ሃሳቦችን በመስጠትና ውሳኔ በማሳለፍ ጉባኤው ዛሬ አመሻሽ ላይ እንደሚጠናቀቅም ለማወቅ ተችሏል።

Read 1522 times