Sunday, 07 November 2021 18:36

የእርቅና የሰላም ጉባዔ እንዴት ይካሄድ?

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(3 votes)

 "--እንኳን መቶ ዓመት በሞላው በደል በዚህ ዓመትና ባለፉት ዓመታት  አይናችን እያየ፣ ጆሮአችን እየሰማ ለተፈጸሙ ጥፋቶች ይቅርታ የሚጠይቅ፣ ተሳስቻለሁ የሚል ወገን ለማየት ተቸግረናል፡፡ ለጥፋቱ ምክንያት የሚደረድር እንጂ የሚፀፀት ሰው ወይም ቡድን ገጥሞን አያውቅም፡፡ --"
                          በስም አራት፤ የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ትሕነግ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢህዲን)፣ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ  መኮንኖች ንቅናቄ (ኢዴመን) በተግባር አንድ ሆነው፣ ኢሕአዴግ በሚል መጠሪያ፣ በትሕነግ አድራጊ ፈጣሪነት እየተመሩ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ደርግን አስወግደው፣ የኢትዮጵያን የመንግስት ሥልጣን ተቆጣጠሩ፡፡
ትሕነግ  መራሹ     ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ለመያዝ እየተቃረበ በመጣበት ጊዜ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ የሽግግር መንግስት መመስረት እንዳለበት፣ በሽግግሩ ምስረታ መሳተፍ ያለባቸውን  ወገኖች በዝርዝር በመግለጽ የሚመለከታቸው ሁሉ በጉዳዩ ላይ እንዲረባረቡ ጥሪ አቀረቡ። የፕሮፌሰር መስፍን ሀሳብን እንደ ራሱ ሀሳብ አድርጎ የወሰደው ትሕነግ/ኢሕአዴግ፤ በሽግግር መንግስት ምስረታ ጉባኤ ታዋቂ ሽማግሌዎችና የኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች መሳተፍ እንደሚችሉ አስታወቀ፡፡ መግለጫውን አምነው ወደ አገር የተመለሱት እንደ ቢትወደድ ዘውዴ ገብረሕይወት አይነት ታዋቂ ሰዎች የሚቀበሏቸውና በጉባኤ እንዲሳተፉ የሚያደርጓቸው ሳያገኙ ቀሩ፡፡
የደርግን መንግስት በአገር ውስጥና በውጭ ሆነው ሲታገሉ የቆዩ እንደ ኦነግ፣ኢዲዮ፣አዲሀቅ፣ ኦ.ኤን.ኤል. ያሉ ድርጅቶች የተሳተፉበት የሽግግር መንግስት መስራች ጉባኤ፣ ሰኔ 20 ቀን 1983 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ተካሂዶ፣ የሽግግር መንግስት ተመሰረተ፡፡ በዚህ የሽግግር መንግስት ምስረታ ላይ እንደ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ያሉ የትሕነግን ሀሳብ የሚቃወሙ ኃይሎች እንዳይሳተፉ ተደረገ፡፡
የደርግ መንግስት ከወደቀ በኋላ ተመሰረተ የተባለው የሽግግር መንግስት፣ የኢትዮጵያን ችግር በዘላቂነት የሚፈታ ሆኖ ባለመገኘቱ፣ “ብሔራዊ እርቅ” ይደረግ የሚል ጥያቄ ተነሳ፡፡ ጥያቄው እንደ ማነፃፀሪያ የወሰደው በደቡብ አፍሪካ የተደረገውን የእርቅ መንገድ ስለነበር ብዙ የፖለቲካ ኃይሎችና ሕዝብ የሚደግፈው ጥያቄ ሆነ፡፡
ሀሳቡን ወይም አጀንዳውን ከደገፉ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ;(የቀድሞው መኢአድ) አማራጭ ኃይሎች ምክር ቤት፣ ደቡብ ህብረት፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የሚጠቀሱ ናቸው። "መድረክ" በተደጋጋሚ የሚያነሳው “ብሔራዊ መግባባት ይፈጠር” የሚለው ጥያቄም፣ ከዚሁ አንጻር የሚታይ መሆኑንም ማመላከት ተገቢ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ጥያቄው ባለፉት ዓመታት ውስጥ እየተነሳ እየወደቀ ቢቆይም፣ በመንግስት በኩል ተቀባይነት አግኝቶ በተግባር ሊታይ አልቻለም፡፡ የብሔራዊ እርቅ ወይም መግባባት ጥያቄ በተነሳ ቁጥር የመንግስት ሥልጣን የያዘው ኃይል የወንበር አጋሩኝ የማለት ያህል እየቆጠረው ሲሳለቅበት እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
በ2012 ዓ.ም መንግስት በአዋጅ የእርቅና የሰላም ኮሚሽን አቋቋመ፡፡ ለኮሚሽኑ ከተሰጡት ተግባሮች አንዱ፣ በዜጎች መካከል ላለመግባባት ምክንያት እየሆነ ያለ ችግርን በውይይት ፈትቶ መግባባትና መደማመጥ መፍጠር መሆኑ ይታወቃል፡፡ በቅርቡ መሳሪያ ከታጠቁ ኃይሎች በስተቀር ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የሚሳተፉበት የእርቅና የሰላም ጉባኤ እንደሚካሄድ መንግስት ገልጧል፡፡ ኦፌኮ በእርቀ ሰላም ውይይቱ ላይ ለመሳተፍ ይችል ዘንድ መሟላት አለባቸው ያላቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በዝርዝር አቅርቧል፡፡ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ያሉትን አልሰማሁም፡፡
ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም ለሰላምና እርቅ ኮሚሽን ሰብሳቢ ለብፁዕ አቡነ ብርሃነ እየሱስ አንድ ማስታወሻ አቅርቤ ነበር፡፡ በዚያ ማስታወሻ ላይ ለነገሬ ማስረጃ ያቀረብኩበት ታሪክ አለ፡፡ እሱን አቅርቤ የእርቀ ሰላም ጉባኤው ቢከተለው ይጠቅማል የምለውን ሃሳብ በመሰንዘር ነገሬን ልቋጭ፡፡
ሁላችንም አፄ ቴዎድሮስን እናውቃቸዋለን፡፡ አጼ ቴዎድሮስ እንደነገሱ ነገስታት እንደሚያደርጉት እሳቸውም ሁሉም “አባት ያለህ በአባትህ እደር፣ የሌለህ እኔን ደጅ ጥና;  በሚል አዋጅ አስነገሩ፡፡ ከትቤዝ  የተላኩ ሰዎች ወጥተው ወደ ንጉሱ መጡ፡፡
“እኛ የምንተዳደረው ሰርቀን በምናገኘው ሃብት ነውና እየሰረቅን  እንድንኖር ይፍቀዱልን” ብለው ንጉሱን ጠየቁ፡፡
“እናንተ ብቻ ናችሁ ወይስ ሌሎችም አሉ?” ሲሉ ንጉስ ጠየቁ፡፡ ብዙዎች መሆናቸውን መልዕክተኞቹ ስለገለጹ፣ "ሁሉንም ሰብስባችሁ አምጡልኝ" ብለው መልዕክተኞቹን ላኳቸው፡፡ ሰርቆና ዘርፎ የሚተዳደር ሁሉ ተሰብስቦ በመጣ ጊዜ፣ አጼ ቴዎድሮስ ሁሉንም አንድ እጃቸውንና እግራቸውን እየቆረጡ ቀጧቸው፡፡ ቴዎድሮስ ይህን የመሰለ ቅጣት ከሽፍታነት ዘመናቸው አንስተው ሲቀጡ የኖሩ ሰው ናቸው፡፡
ለደራሲ ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት ግን ይህ የቴዎድሮስ ክፉ ሥራ አልታያቸውም። ለእሳቸው የታያቸው ዘመነ መሳፍንት ያፈረሰው መቅደላ ላይ "እጄን አልሰጥም" ብሎ እራሱን የገደለው የቴዎድሮስ ባህሪ ነው፡፡ ዛሬ የምንወዳቸውን አፄ ቴዎድሮስን የፈጠሩልን ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት ናቸው፤ የቴዎድሮስን መጥፎ ሥራ ጠልተው መልካሙን በመውደዳቸው፡፡
ዛሬ መጥፎውን የሚጠላ የሚንቅና የሚረሳ፣ በጎውን የሚወድና የሚያደንቅ ሰው የለንም፡፡ ከመቶ ዓመት በፊት በነበረ ታሪክ ቁርሾ ሰው እየተገደለ፣ ደም እንደ ውሃ በሀገራችን ምድር እየፈሰሰ ነው፡፡ በነበረው ቁስል ላይ አዳዲስ ቁስል እየተጨመረ ነው። እንኳን መቶ ዓመት በሞላው በደል በዚህ ዓመትና ባለፉት ዓመታት  አይናችን እያየ፣ ጆሮአችን እየሰማ ለተፈጸሙ ጥፋቶች ይቅርታ የሚጠይቅ፣ ተሳስቻለሁ የሚል ወገን ለማየት ተቸግረናል፡፡ ለጥፋቱ ምክንያት የሚደረድር እንጂ የሚፀፀት ሰው ወይም ቡድን ገጥሞን አያውቅም፡፡
በዚህ አይነቱ ሁኔታ ሽምግልና ተቀምጦ እርቅ ማውረድ ለእኔ ቀላል ሆኖ አይታየኝም። እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የሚፈጠሩ ክፉ ሁኔታዎች እንደይፈጠሩ መንገዱን ለመዝጋትና የቆሰለውን ለማከም ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ሌላ አዲስ ቁስል እንዳይፈጠር ማድረግ የግድ ነው፡፡ እንደ እኔ የእርቀ ሰላም ጉባኤው መጀመር ያለበት አዲስ ቁስል እንዳይፈጠር ማድረግ በመቻል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሊሆን የሚችለው እስካሁን ሲያጫርሰን የቆየውን ታሪክ በማገላበጥ ሳይሆን፣ የዛሬዋን ኢትዮጵያን እንዴት ጠብቀን እናሳድጋት ብለን መምከር ስንጀምር ነው፡፡ ወደ ኋላ ማሰብ አቁመን ወደፊት አርቀን ለማየት ስንነሳ ነው፡፡ እኛ እርስ በእርስ በተላለቅናባቸው ዓመታት እንደ ሲንጋፖር፣ኢንዶኔዥያና ቬትናም ያሉ አገሮች ከየት ተነስተው የት እንደደረሱ ስንመረምር መንፈሳዊ ቅናት ሲያድርብን ነው፡፡
በየራሳቸው የደረሰባቸውን በደል እያሰቡ የእርቅ ነገር ሲነሳ “እንዴት ሆኖ” የሚሉ ብዙ ወገኖች እንደሚኖሩ አምናለሁ፡፡ የሆነውን ሁሉ ከአዕምሮአችን ጠርገን ልናወጣው እንደማንችልም ይገባኛል፡፡ የሆነውን ሁሉ ወደ አለመኖር ማምጣት አይቻልም፡፡ አንድ ጊዜ ውሃው ፈሷል ብሎ ማመንና መቀበል ግድ ይሆናል፡፡ ክፉን ትቶ በጎውን መያዝ፣ አሁን በዚህ ልማድና ተግባር የደረሰው ጉዳት ይበቃናል ማለት ያስፈልጋል፡፡ ያለ ምርጫ የሚመረጥ ውሳኔ መሆንም አለበት፡፡ ለመካሰስና ለመበቃቀል የምናውለውን ጊዜ፣ ጉልበት ገንዘብና እውቀት ለአገር ልማት ብናውለው ቁስላችን ይደርቃል፤ የጠገገው ፊታችን ይለመልማል የሚል እምነት ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡
 ስለዚህም የእርቅና ሰላም ጉባኤው መጀመር አለበት ብዬ የማምነው፣ የትናንቱን በደል በማንሳትና በእርሱ ላይ በመነጋገር ማን ይካስ? ስንት ይካስ? በሚል ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ብዙ ጊዜ ተፅፎ፣ ብዙ ጊዜ ተነግሮ የታየ መስማማትም ሆነ መቀራረብ የለም፡፡ እዚህ አጀንዳ ውስጥ መግባት ለእኔ የተገኘውን ጥሩ አጋጣሚ ማባከን ነው የሚሆነው። ትኩረቱ የዛሬዋን ኢትዮጵያ መጠበቅ፣ የነገዋን ኢትዮጵያ በእቅድ መምራትና ማሳደግ ላይ መሆን ይኖርበታል፡፡
አነሳሱም ልክ እንደ ሕዝብ ቆጠራ መሆን አለበት፡፡ ቆጠራው ህዳር 10 ቀን 2014 ዓ.ም የሚካሄድ ቢሆን፤ ሕዳር 9 የሞተ ሰው አለ ከተባለ አይመዘገብም፡፡ ሕዳር 9 ቀን የተወለደ ልጅ ግን ይመዘገባል፡፡ አንድ መነሻ ቀን ተይዞ ወደፊት ማሰብ ይቻላል፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን!


Read 1584 times