Saturday, 15 September 2012 12:58

የተሼ ደብዳቤ

Written by  ተሾመ ገ/ስላሴ
Rate this item
(3 votes)

አሁን የት ነው ያለሽው? የትስ ብዬ እፈልግሻለሁ፡፡ ከሰማይ ጠቀሶቹ የራስ ደጀንና የባሌ ተራሮች ወይስ ከሰንሰለታማዎቹ የአማሮ ኮረብቶች? የትስ ብዬ ልሻሽ? ዳሉል ወይስ ደንከል? እንጦጦ ወይስ ዝቋላ… እኮ የት? ዳሞት ወይስ ገንታ? የት? በሀመር ዳኞች በሙርሲ ሜዳዎች በብር ሸለቆዎች በኮንሶ ኩይሳዎች የት ብዬ የት? የነፍስ እስትንፋስሽ… ያ ውብ ድምፅ ናፈቀኝ፡፡

… ማሾው በርቷል፡፡ ብራናው የልቤን ውል ይተይባል፡

እርግጥ ነው በዚያ መንፈቀ ሌሊት እንቅልፍ ያሸለበሽ እንደሆነ ብዬ በማሰቤ የተኛሽበት የጠፈር አልጋችን ተደጋጋሚ ስቅታ ሲያሰማ አላስተዋልኩትም እንጂ ከጆሮዬስ ደርሶ ነበር፡፡ ጫን ያለው ትንፋሽሽ የቃተተ መሆኑ ትውስ ያለኝ አሁን አሁን ነው፡፡

ግና ብዕሬን አሳርፌ የማሾውን ብርሃን ቀንሼ የናፈቀ ገላሽን እንደናፈቅሁ ወደ መኝታ ብሄድ አጣሁሽ፡፡  የጋለ ገላዬ ከክፍቱ በር ትይዩ በዘለቀው ቀዝቃዛ ነፋስ በረደ፡ “ወይንዬ” እንዳልኩ ወደ ውጪ ተወረወርኩ፡፡ ግን አጣሁሽ፡፡ አንዳች የማደርገው መላ ቢርቀኝ ሰማይ ላይ ያለሽ ይመስል አንገቴን ወደ ሰማይ አቀናሁ፡፡ ከዋክብት በጥቅሻቸው የሚሳለቁብኝ መሠለኝና አንገቴን ደፋሁ፡፡ ምድርን ብማትር ፅልመት ከሸበበው የከዋክብት ስስ ውጋጋን በቀር አንዳች ውል የሚል ነገር አጣሁበት፡፡ እንግዲህ የት ብዬ የት ልሻሽ?

ሰማዩ ያህያ ሆድ ሲመስል ጉዞዬን በምስራቅ በኩል አቀናሁ፡፡ ነጋዴዎች ከነጭነቶቻቸው ተራራውን ተያይዘውታል፤ ተከተልኳቸው፡፡ አንድም አንቺን የሚመስል አጣሁ፡፡ ወይንም ድሮውንም እኮ የነብሱን ዝማሜ የሚያዳምጥ ዛራም ዘመናይ ደብተሯ መች ይመቻል? በሚሽቱስ መንገድ መች ተጉዞ ያውቃል?

“ከወደድኩህ ከነዛርህ እወድሃለሁ” አልሽኝ፡፡ ሞገደኛነቴና ዶሰኝነቴ ታሰበኝ፡፡

“ልቅርብሽ” አልኩሽ፡፡ እንደውም የእግዜሩ ልሁን ብዬ፡፡ የእግዜሩን ግብር የሚከውን ዛሬም ደስ ይለኛል፡፡ ትንሽ ነፍስ የለችውም” ብለሽ ሞገትሽኝ፡፡ ቃልሽ ሀያል ቢሆን ለሃያል ተረታሁ፡፡

“ይሁን!” አልኩሽ - ሆነ! ያለስስት ያለንፍገት ፍቅርሽን ሰጠሽኝ፡፡ ፍቅርሽ ፅናት ቢሆነኝ ሙቀትሽ ሙቀት ለግሶኝ ሀይል ቢሆነኝ ተንሰራፋሁበት፡፡

ግን እኮ ወይንዬ አንዳንዴ ለዛር ምጤ ጥሞና ብቸኝነቴን ብሻ ብቸኝነቴን ትነፍጊኝ ነበር እኮ! አይኖቼ ክንፍ አውጥተው እጆቼ መብረርን ሲያልሙ - ህሊናዬ የአድማሱን ሰማይ ሲናፍቅ “ሄድክ እኮ!” ትይኝና ከተመስጦዬ ታናጥቢኝ ነበር፡፡ ገና ውስጤ ቢረበሽም ላንዲት አፍታ እንኳን ክፉ ተናግሬሽ አላውቅም ነበር፡፡ አንዳንዴ ብዕሬን ከእጄ ቀምተሽ ብራናዬን ከሰንዱቅ ትወረውሪብኝ ነበር፡፡

ወይንዬ ቢሆንም ልቤ ሁሌም ክፍት ቦታ አልነበረውም - በጣም አፈቅርሽ ነበርና ነው! አንቺ እኮ ማለት ለራቁት ማህበረሰብ ድልድይ፣ በብቸኝነቴ ውስጥ የብቸኝነት መንፈሴን የምትገፊ… ሰው በመሆኔ ውስጥ የሚመለዝገኝን የሰው ጠኔ የሚያስታግስ ቅዱስ ህብስት ሆነሽ ትታይኝ ነበር፡፡ ግና በመንፈቀ ሌሊት ለወና ጐጆ ዳረግሺኝ፡፡

አሁን የት ነው ያለሽው? ታቦር ግርጌ ወይስ ጫሞ? አማያ ወይስ ነጭ ሳር? ከአባያ ሃይቅ መሀል ደሴት ከጋንጁሌዎች መንደር በደንገል ታንኳ ተሻግሬ ፈልጌሻለሁ፡፡ ከዴሎ ተራራ ጫፍ የክረምቱ ውርጭ አላስፈራኝም፡፡ የት ይሆን የማገኝሽ?

ያን ምሽት ባስታወስኩ ቁጥር አንጃች ነገር ያንጨረጭረኛል፡፡ የሃሳብ ምጥ ህሊናዬን ሰቅዞ ሲይዝብኝ እንጂ እምባ ያቀረሩ አይኖችሽ ከግንባሬ አርፈው ወለሉ ላይ ቆመሽ በሀዘን ስታቃኚ የፍቅር ጥሪ እድሞ እንደሆነ ገብቶኛል፡፡ ምንኛ ደስ ባለኝ ወይንዬ ምጥን ዞማ ፀጉርሽ የቀጭን ወገብሽን ህዳግ ተከትሎ ሲወርድ… የኮራ ዳሌሽ ሲሞናደል በስሱ ነጠላ አሻግሬ ማየቱንስ አይቼ ነበር፡፡

የፈረጠሙ ተንቧካ ጭኖችሽ ኦ! አምላኬ እኒያ እንደ ሰለሞን ድንኳኖች የተሠሩት ጡቶችሽ… ከአንፃሬ ተደግነው የለጋ መአዛሽ ጠረን ቤቱን አጥኖት… ምነው መንፈሴ ያኔ ታወረ? እንደ ለጋ ቀንበጥ ይንቀጠቀጡ የነበሩት ከናፍሮችሽ አንዳች ሊሉ ዳድቷቸው ሲቃ የተሞላ አንደበታቸውን ምነው መረዳት ተሳነኝ?

ዛሬ ያ ሁሉ የለም፤ የገፅሽ ፀዳልሽ ሽውታ በፊቴ ውል ባለ ቁጥር ፀፀት ይመለዝገኛል፡፡ አዎ እኩል አማጥን -   አንቺ የፍቅር ምጥ እኔ ደግሞ “የዛር” ምጥ!  ከምጤ ተገላግሌ ብሻሽ ከነምጥሽ አጣሁሽ፡፡ አንቺም ሳትረጂኝ እኔም ሳልረዳሽ፡፡

ወይንዬ - ከዚያ በፊት የነበሩት ቀናት “ከዛርህ አዋይ ጋር ልትሴስን ሃይል እንዳታገኝ ይረዳኛል፡፡” ብለሽ ሁለት ቀን በጠኔ ቀጣሽኝ፡፡ ታዲያ ተቀየምኩሽ? እንዴት? እንዴት አድርጌ ወይንዬ? ወትሮስ ይኸው አይደለ “ሁለት የወደደ ሚዛኑ የዋለለ እለት ወይ አንዱን ከከፋም ሁለቱንም ያጣል፡፡ አሁን እንግዲህ ያለ አንቺ እንደምን ይገፋል? የነፍስ ጥሪ ምላሽ የፈጣሪ ሚና ግብር ያለ አጋር እንደምን? አሁን የት ነው የማገኝሽ? በእኩለ ሌቱ ይስፋችሁ ብለሽ ጥለሺኝ የነጐድሽው የነፍስ ጥሪ፣ የተልኮ አውሊያ፣ የኑሮ ቅኔ ትርጉም እንደምን ልትረጂው ከበደሽ?

የኔ ሆድ ብራናውን ክፍት እንደነበር ትቼ፤ ብዕሬን ቀለም እንዳነጠበች የቤታችን ደጅ ሳይዘጋ እንደነበር ትቼ ለፍለጋ ወጣሁ፡፡

የት ነው የበረርሽው የኔ  ወፍ? ከየትኛው ዛፍ ላይ ነው ያረፍሽው የኔ እርግብ? እንግዲህ ከአዋዬ ጋር ላስታርቃችሁ፡፡ ልቤ በቂ ነውና አብቃቅታችሁ ንገሱበት፡፡

ያም ቢሆን አሁን የት ነው ያለሽው? ከዚራ ነው ጀጐል? ጦሳ ነው ገራዶ? አክሱም ነው አድዋ? የት ነው የዋልሺው? የትስ ነው ያደርሽው?

(ሐምሌ 29,1992 አዲስ አድማስ)

 

 

Read 3086 times Last modified on Saturday, 15 September 2012 13:05