Sunday, 07 November 2021 19:24

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ደጋግመን ስንናገር ሁላችንም ልንነቃ ይገባል!!
 
                               ጎበዝ! በል ተነስ! ጊዜ የለንም!!
                                       መሣይ መኮንን

               የህወሀት የፕሮፓጋንዳ ማሽኖችና በሽርክና የሚሰሩ የውጭ ሚዲያዎች የመጨረሻ ነው ያሉትን የሽብር ወሬ ለማሰራጨት እየተዘጋጁ ነው። ከወዲሁም አንዳንድ ሀሰተኛና ህዝብን ያሸብራል ያሉትን መረጃ መልቀቅ ጀምረዋል። እነሱ ዒላማ ያደረጉት ሀገርን የመጠበቅና ህልውናዋን የማስከበር ሃላፊነትና ግዴታ ያለበትን መላውን ህዝብ ነው። ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ሊኮበልሉ ነው፣ አከሌ የሚባል ሚኒስትር ሀገር ጥሎ ሊወጣ ነው፣ አዲስ አበባ ተከባለች፣ የሆኑ ጀነራሎች መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ እየተነጋገሩ ነው፣ የሚሉና መሰል ሀሰተኛ ወሬዎች በማናፈስ፣ በጦር ሜዳ መግፋት ያልቻሉትን ህዝብን በወሬ በማሸበር፣ ሰይጣናዊ ምኞታቸውን ለመፈጸም እየተረባረቡ ይገኛሉ።
ጎበዝ! መዘናጋት ፈጽሞ ሊኖር አይገባም!! አሁን የመጨረሻው ሰዓት ላይ እንገኛለን። አንድ ዓይናችን ጦርነቱ ላይ ሌላኛው ዓይን የፕሮፓጋንዳ እንቅስቃሴያቸው ላይ ልናደርግ ግድ ይለናል። እነሱ ለከፍተኛ ጥፋት ቆርጠው ሲነሱ እኛ ደግሞ የህልውና ዋስትናችን የሆነችውን ሀገራችንን ለማዳን የእነሱን እልህና ጽናት በሚያስከነዳ ሀገራዊ ወኔና ቁርጠኝነት በአንድነት መነሳት አለብን። ከሽብር ወሬያቸው ጋር በተያያዘ ሁለት ነገሮችን ማድረግ እንችላለን።
አንደኛው ሁላችንም የእነሱ የሽብር ወሬዎች የሚመጡባቸውን መንገዶች በሙሉ ጥርቅም አድርጎ መዝጋት ነው። የእነሱን ፌስቡክ፣ ሚዲያ፣ ማንኛውም ዓይነት የእነሱን ወሬ የሚያራግብ መድረክን አለመከታተል፤ ሁለተኛው ያን ማድረግ ካልቻልን በእነሱ በኩል የሚሰራጩትን መረጃዎች ውሸትና መርዛማ መሆናቸውን ከውስጣችን በማመን ለተዘረጋልን ወጥመድ እጅ አለመስጠት ነው። ይህን በማድረጋችን ብቻ ጦር ሜዳ ሳንሄድ ህውሓትን መደምሰስ እንችላለን፣ ከእነ ክፋቱ እድሜውን አሳጥረን እስከ ወዲያኛው እናሰናብተዋለን። እንበርታ፣ በወሬ አንረበሽ! በደምና አጥንት የተረከብናትን ውዲቷን ሀገራችንን በወሬ እንድትፈርስ መፍቀድ የታሪክ ተወቃሽ ያደርገናል።
በሜይንስትሪም ሆነ በማህበራዊ ሚዲያዎች የምንሳተፍ ኢትዮጵያውያን ከምንጊዜውም በላይ ተናበን መንቀሳቀስ ይገባናል። የመንግስት ሚዲያዎች አቀራረባቸውን በአስቸኳይ ማስተካከል አለባቸው። ስለ ህወሓት ጉድፍ በመናገር ብቻ ህወሓትን ማጥፋት አይቻልም። ጥቁር ቀለም ላይ ጥቁር ቀለም መቀባት ለውጥ አይኖረውም። ወኔ የሚቀሰቅሱ፣ ህዝብን ለጦርነት የሚያነሳሱ፣ በወሬ እንዳይሸበር የሚያደርጉ፣ ከህወሓት ሃይል ጋር እየተፋለሙ ያሉ ጀግኖቻችንን ተጋድሎ አጉልተው የሚያሳዩ ዝግጅቶች፣ ወቅታዊ መረጃዎች፣ ሙዚቃዎች በስፋት የአየር ጊዜ ተሰጥቶአቸው መተላለፍ ይገባቸዋል። የመንግስት ሚዲያዎች ከአንድ ቋት የሚፈስን መረጃ ብቻ በመጠቀም ህዝቡ በጠላት ፕሮፓጋንዳ እንዳይሸበር የተለየ የሚዲያ አቀራረብ ኖሯቸው መስራት ይገባቸዋል!
በማህበራዊ ሚዲያዎች ያለንም ከተቻለ አንድ ጊዜያዊ ግብረ ሃይል መስርተን፣ የህወሓትን የሽብር ወሬ እግር በእግር እየተከታተለ የሚያመክን እንዲሆን ማድረግ ይገባናል። በቁጥር ከእነሱ የትየለሌ ብንሆንም በአንድነትና ተናበን ስለማንቀሳቀስ ትንሽ ሆነው ሽብር መንዛቱ ላይ በልጠውናል። እናም በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ እንደ አዲስ ሊከፍቱት የተዘጋጁትን ህዝብን የማወናበድና የማሸበር ዘመቻ እንክትክቱ እንዲወጣ ማድረግ ትልቁ ሀገራዊ የቤት ስራችን መሆን ይገባዋል!!!
ጎበዝ! በል ተነስ! ጊዜ የለንም። እነሱ እንቅልፍ አጥተው ሀገር ለማፍረስ ሲሰሩ፣ እኛ እግራችንን ሰቅለን እየተኛን ሀገር ማዳን አንችልም። ዳይ ወደ ስራ! ደግሞም እናሸንፋለን። የእነሱ መወራጨት ጊዜያዊ ድል አስገኝቶላቸው ሊሆን ይችላል። የእኛ ድል ግን ዘላለማዊ ነው። ቴዲ አፍሮ እንዳለው፤ ዘር ያበቀለው መከራው ታጭዷል፣ የኢትዮጵያዊነት አሁን ነው ተራው!! ጊዜው የእኛ ነው። ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑርልን!! ማሸነፋችን_እርግጥ ነው!!

______________________________________________

                        ኢትዮጵያ ከአጉዋ በላይ ናት!

      ሰሞኑን አሜሪካ ለኢትዮጵያ  ሁለት አማራጭ መስጠቱዋ የሚታወስ የአደባባይ ሀቅ ነው። የምርጫውም አንደምታ አጉዋን ወይም አድዋን ምረጡ ነው። አጉዋ በኢትዮጵያ  የሚመረቱ የማንኛውም አይነት ምርት ወደ አሜሪካ ያለምንም ቀረጥ እንዲገባ የሚደረግ የንግድ ሲስተም ሲሆን አሜሪካ ከዚህ የንግድ ሲስተም ሶስት የአፍሪካ ሀገራት ከአጉዋ ማርኬት እንዲወጡ አድርጋለች፤ ኢትዮጵያ  ማሊና ጊኒ ናቸው።
አሜሪካ ከዚህ የገበያ  ሲስተም እነዚህ ሶስት ሀገራት  እንዲወጡ የፈለገችበት ምክንያት  ምን ይሆን?
1ኛ. በሀገራቸው የፖለቲካ  ጉዳይ እኔ ጣልቃ  ካልገባሁ፣  የእናንተን የጥቅም መረብ እበጥሳለሁ ነው። ለጊዜው የሌሎችን ትተን ወደ እኛ እንመለስ፡፡
ወያኔ የተባለ የእርኩሰት ድርጅት  ወደ ኢትዮጵያ  ሲገባ አሜሪካና እንግሊዝ  በጀርባቸው አዝለው እንዳስገቡት ዛሬም በጀርባቸው አዝለው ከገባበት ጉድጓድ ለማውጣት ፍላጎት አላቸው። ለዚህም  ለኢትዮጵያ መንግስት ሀርድዌሩ ድርድር የሚመስል፣ ሶፍትዌሩ ዳግም የመከራ ቀንበር ወያኔ፣ በኢትዮጵያ ላይ ተጭኖ እንዲኖር፣ መርዝ የለበሰ የፖለቲካ ጥያቄ  አቅርበዋል።
በእውኑ እኛ ኢትዮጵያውያን ከአጉዋና ከህውሃት የቱን ልንመርጥ ይገባናል? እርግጥ ለትንሽ ጊዜ እንራባለን፤ እርግጥ ነው 1 ሚሊዮን ሰው ስራ ሊያጣ ይችላል፤ ነገር ግን  ለአንድ ሚሊዮን ሰው ስራ ማጣት ብለን 100 ሚሊዮን ሰው ላይ መከራ መጫን  የለብንም።
ስለዚህ ለእኛ ቀላሉ መንገድ ከአጉዋና ከህውሃት  አድዋ  ይሻለናል። አዎ የሚኒልክ ቆራጥነት የጣይቱ እምቢተኝነት፣ የራስ አሉላ ጀግንነት ለእኛ ኢትዮጵያውያን ይሻለናል። ስለዚህ ሰው ከሚመስል ፅልመት ጋር ልንደራደር አይገባም ። የመጀመሪያው ወያኔን ከገባበት ጉድጓድ አንድ ሆነን መቅበር፣ የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት ነው። ያኔ ሰላም ይመጣል፤ ያኔ እኛ ወደ አጉዋ አንሄድም፤ አጉዋ ወደ እኛ ይመጣል።
ወያኔ ወደ ስልጣን ከሚመለስ ሞቴን እመርጣለሁ፤ እኛ  ልጆቿ  በህይወት እያለን ወያኔ በአሜሪካና እንግሊዝ  ትከሻ ተፈናጦማ ወደ ስልጣን መምጣት የለበትም፡፡ ጎበዝ፤ አሜሪካ የወያኔ ነገር ባይሳካላትም፣ በግብፅና ሱዳን በኩል ምን እንዳሴረች ስለማናውቅ፣ ቅድሚያ ለአንድነታችንንና ለህልውናችን ስንል እንዝመት።  በጋራ ጠላታችንን ህውሃትን ወደ ሞት እንሸኘው።  ጉልበት ያለው በጉልበቱ ይዝመት፤ የጦር ስልት አዋቂው በጦሩ ይዝመት፤ ፀሐፊ በፅሑፉ ይዝመት፤ እናቶች ስንቅ በማቀበል ይዝመቱ፤ አባቶች በአርበኝነት መንፈስ ይዝመቱ፤ ገንዘብ ያለው በውጊያ ለሚዋደቁ ለሀገር ጀግኖች  በገንዘቡ ይዝመት፤ አበው ካህናት በፀሎት ይዝመቱ።  ይህን ካደረግን ታላቋ ኢትዮጵያ ከአጉዋ በላይ ትሆናለች።

___________________________________________________


                   ቴዎድሮስ ካሣሁን ገርማሞ፤ ተጽዕኖ ፈጣሪ ማለት! (“ቀና በል !” በጥቅምት 24 ዋዜማ)

                ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ባለፈው ማክሰኞ ዕለት “አርማሽ (ቀና በል)” የሚል ጋቢ ዘፈን ለቋል። ይገርማል በብዙ መልኩ። ሁሉም የማህበራዊ ሚዲያ ሰው እየተቀባበለውና አርማው እያደረገው ይገኛል። የሰራውን ዜማ እነ ሰርፀ ፍሬስበሀት ይናገሩበት። የግጥሙንም ጉዳይ ባለሙያዎቹ ይናገሩበት። እኔ ሁለቱም ቦታ የለሁም። ለእኔ አንድ “ቀና በል!” የሚለው ቃል ይበቃኛል። ቀና በል። ድምጻዊው ለሀይሌም ሆነ ለቀነኒሳ በድላቸው ወቅት ተወዳጅ ስራዎቹን አቅርቧል። አሁን ደግሞ ሀገሩ በጭንቅ በተያዘችበትና የሕዝቡ ስነልቦና በተወሰነም መልኩ ለጊዜውም ቢሆን ዝቅ ባለበት ሰዓት ደርሷል - “ቀና በል” ብሎ። ቀና ሊያደርግ። አንድ ታላቅ የጥበብ ሰው በሚጠበቅበት ጊዜና ቦታ። እንደ ዜጋ አመሰግነዋለሁ፤ አከብረዋለሁም።
ድምጻዊው የመጣበት ጊዜ ጥቅምት 24/13 መከላከያ ሰራዊታችን በሕወሓት ሀይሎች የተወጋበት ዕለት ዋዜማ ነው። ይህ ወቅት ደግሞ መከላከያ ሰራዊቱ የድል ብስራት ያሰማበት አይደለም። ደሴና ኮሞቦልቻ በአማጺው ቡድን የተያዙበትና በዚያ በደረሱ ዘግናኝ ድርጊቶች የሕዝብ ስነልቦና ዝቅ ያለበት ነው። ብዙዎች ድምጻቸውን በማያሰሙበት ብቻ ሳይሆን ማሰማት በማይፈልጉበት ወቅት ነው። የሀገራችን አንዳንዶቹ ድምጻውያን “ላሊበላ ተያዘ” ሲባል ለመከላከያው ድጋፍ ላለመዘመር ስልካቸውን አጥፍተው የጠፉ ናቸው። አንዳንዶችም ቀደም ሲል በሰሩት “ምነው በቀረብኝ” ማለት የጀመሩበት ጊዜ ነው። አንዳንዶቹ ድንገት ሕወሓት አዲስ አበባን ዳግም ቢቆጣጠር፣ አብረው ለመሰለፍ ቅያሪ ማሊያቸውን አጥበው ያሰጡበት ጊዜ ነው። እዚህ ላይ ነው ቴዲ አፍሮ “ቀና በል !” ብሎ የመጣው።
 በዚህ ወቅት “ቀና በል !” ትልቅ ቃል ነው። አርማ ነው። ጊዜ (Timing) ለአንድ የጥበብ ስራ ወሳኝ ነው። ዝም ብሎ መሮጥ ሳይሆን ለሪከርድ መሮጥ ከድምጻዊው ይጠበቃል። “ቀና በል!” በዚህ ወቅት ጀግናው ምሩጽ ይፍጠር ወይም እነ ሀይሌ ፀጥ ብለው ከኋላ ሮጠው በመጨረሻዋ ደውል ላይ ሪከርድ አሻሽለው አሸናፊ እንደሚሆኑት ማለት ነው። “ቀና በል!” ቃሉ ለዚህ ወቅት ተስተካክሎ የተተኮሰ ነው። መከላከያ ደሴና ኮሞቦልቻን አስለቅቆ ወደ መቀሌ ሲገሰግስ አይደለም “ቀና በል!” ትርጉም ያለው። ቴዲም ባይመጣ ራሱ ሕዝቡ ቀና ብሏል። ባለቀ ድግስ ላይ ቄጠማ ለመጎዝጎዝ ሳይሆን ከፖለቲከኞቹና የሀገር መሪዎች የጎደለውን ነው ቴዲ የሞላው።
በዚያ ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪነቱን ሁሌም በአግባቡ እንደተጠቀመበት ነው። አንዳንድ የፌስቡክ መንደር ሰዎች ሀሳባችን ሳይጥማችሁ ሲቀር ወይም ልታሸማቅቁን ስትፈልጉ “አንተ እኮ ተጽዕኖ ፈጣሪ ነህ“ ትሉናላችሁ። አንዳንዶችም 10 በመቶ እንኳን የሚሞላ የፌስቡክ ተጠቃሚ እንኳን በሌለበት ሀገር፣ በዚያ ላይ 1 በመቶው እንኳኑ ሳያውቃችሁ፣ በጥቂት አጯጯሂ ራሳችሁን እንደ ተጽዕኖ ፈጣሪ አድርጋችሁ ትቆጥራላችሁ። ይኸው ግን ተጽዕኖ ፈጣሪ ማለት። “ቀና በል!” ብሎ ቀና የሚያደርግ። አሁንም እንደገና ደግሜ አመሰግንሀለሁ - የካሣሁን ገርማሞ ልጅ!

___________________________________________

                      “ቁስለኛ ስንኞች”


በመከራው ህይወት ዳና … ከቆንጥሩ ተሻሽቼ፣
በተራራው ድርድር አናት … ቁጥቋጦውን ተቋጥቼ፣
ልጅነቴን ኖሬው ሳልውል … ለምሽግህ ተዛምጄ፣
ከ’ኔነቴ ተራርቄ …ባ’ንተ መሆን ተፈርጄ፣
ነብስያዬን ተሸልመህ … ወ’ቶ አደሩ ብሆንልህ፣
የሩቅ ህልሜን እንደቋጠርኩ … በማጀትህ ልሞትልህ፣
ለወንድምህ መመስገኛ … ለድካሜ ላብ መካሻ፣
ብድራቱ ቢጠር እንኳን … እንዲህ ነበር የእኔ ድርሻ?
ይሄ ነበር እንዴ ፍርዴ?
ከ’ርሻው መሀል መታረዴ፣
ጎኔን እንኳን ሳላሳርፍ … አትግደለኝ ብዬ ብልህ፣
እርቃኔን ነው ያረከስከው …ሰው መሆኔን ሰው ቢነግርህ፣
እህ!
እንዴት ጣትህ ታዘዘልህ?
ወትሮም ከሀዲ ከስሙ፣
የት ይራራል ለወንድሙ፣
ምስራቅ ፀሀይ … አድማስ አንባ፣
የምዕራብ ጌጥ … የድል ካባ፣
ለደቡቡ ድንበር ውሉ፣
የሰሜኑ ነበልባሉ፣
ዘራፍ በሉ ሞረሽ በሉ፣
የአድዋው ልጅ ባለ ቃሉ፣
ለምን ይሆን ሙት መባሉ፣
በርዝራዥ ሴራ ጥንስስ … ይገርመኛል መሰለሌ፣
ወይኔ እንድለው መፎከሩ … ሀገር አንሶ ከቀበሌ፣
ኡፍ ክርፋቱ!
የቀን ሀያ አራት ስሪቱ፣
የ’ኔናንተ ውለታማ … ከራስ በፊት ለሀገር፣
የምንገዝፍ ከመንደር፣
በክልል የማንታጠር፣
ለጠላት የማንበገር፣
ወታደር፣
ትለኝ ነበር፣
እልህ ነበር
በከፈልኩት ዋጋዬ ልክ … ውለታዬን ባታሰላው፣
ጥቃቴማ ለወገኔ …የሚፈጀው እሳቱ ነው፣
ለመድማትህ ደምቻለሁ፣
ለመቁሰልህ ቆስያለሁ፣
ለመሞትህ ሞቼም አለሁ፣
ታዲያ ለምን … እኮ እንደምን?
ታሪክ ይፍረድ ጭካኔህን፤
በሃዘኔ ድብብቆሽ … ደስታህን ስላሳደኩ፣
በጨለማው ድቅድቅ ግርዶሽ … መበልፀ’ክን ስለፈለኩ፣
በኩርማን ስንቅ ተሳንቄ … በጥሜ አንተን ስላረካሁ፣
መሆኔን ነው የተቀማሁ … ዘመንህን መቼ ነካሁ፣
በባለ’ድሜ ግፍ ተማጥኖ፣
ሀገር ይፍረስ ክልል ገኖ?
ይሄ ነበር ቃል ኪዳኑ?
ወታደር የመሆኑ!
በተዛምዶ ቢቧደኑ፣
መጥበብነት ነው መካኑ፤
ለካስ ዘይቤው ላንተ ነበር … የአሳ ግማቱ ካናቱ፣
እንደምንስ ተዘነጋህ … ጁንታ ስትሆን መከርፋቱ፣
ፍርድ ይካሰኝ … መጀን ለኔ፣
ተዘነጋህ ሰው መሆኔ?
ባንተ ልድማ ባንተ ልቁሰል፣
ባንተ ልንደድ ባንተ ልክሰል፣
ትታዘብህ ትግራይቱ፣
ለወጋþኝ በጥቅምቱ፤
አጀብ ጉዴ ጓዴ ስልህ … ባጉል ውሸት ተመሳስሎ፣
ዕድሜየን ነው የተሳከርኩ … ባ’ሰት ማላ ተበክሎ፣
ያንተን አቁስል ያንተን አድማ፣
ሙሾ ውረድ ተንከባለል … አለም ሁሉ እንዲሰማ፣
ትፈርሳለች ባልካት ሀገር … ፈርሰህ ቢያዩ ከገደሉ፣
ወይኔ ለካስ ቁጭት ኖሯል … ካንተ ሆነው ለታገሉ፣
እኛማ አለን!
ከፍ ብለን!
ሀገር ሆነን!
(ገዛኸኝ ታደሰ፤ ማስታወሻነቱ በግፍ ላጣኋቸው ኢትዮጵያዊ ወገኖቼ  ይሁን።)

_____________________________________

                       ምን እናድርግ?
                          Ha Hu+


     ከአጎዋ ጋር ትስስር ካላቸው ፋብሪካዎችና ምርቶች ጋር በተገናኘ፣ ከ85 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን  ተቀጥረው ይሰራሉ ተብሏል። ከነዚህም ውስጥ 95% ገደማ የሚሆኑት ሰራተኞች እናቶችና ወጣት ሴቶች ናቸው። ከ800 ብር እስከ 3000 ብር በሚደርስ ደሞዝ ተቀጥረው ይሰራሉ።
ለፋብሪካው ምርት ከሚያቀርቡት ጀምሮ እስከ መጨረሻው የንግድ ሰንሰለት የሚሳተፉትን ከቆጠርን ደግሞ ቁጥሩ በብዙ ያሻቅባል። እነዚህ ግለሰቦች በስራቸው የሚያስተዳድሯቸው ወይ የሚደጉሟቸው ብዙ የቤተሰብ አባላት እንዳሏቸውም ልብ አድርጉ።
ፋብሪካዎቹ ምርታቸው ካልተሸጠ ወይም የገበያ ትስስር ካጡ ፋብሪካቸውን ነቅለው፣ ሰራተኛ በትነው፣ ምናልባትም ካሳ ተቀብለው ሊወጡ ይችላሉ። ከዚህ መለስ ሲልም ባሉበት ሰራተኛ ሊቀንሱ ይችላሉ። እነዚህን እናቶቻችንን ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ‘አንተ’ ያለተጨማሪ ድካም በቀላሉ የምታደርጋቸው ነገሮች እንዳሉ ተገንዘብና:-
1ኛ) የሃገር ምርቶቻችንን መጠቀም አበረታታ። በእናቶቻችንና እህቶቻችን የሚመረቱ የሃገር ውስጥ ጫማዎችን፣ ልብሶችን መጠቀም ጀምር። ለእናቶችህ ስትል Nike, Puma, Adidas, Gucci, LV, Dior, CK,... ተውና በሃገር ውስጥ የሚመረቱ እነ አርቨንዲ፣ ፒኮክ፣ ካባኒ፣ አንበሳ ምናምን ፈልገህ ሞክር፤ ላንተ የሚሆን አይጠፋም! እንዲህ ስታደርግ ከእናቶቻችን ባለፈ ሃገርህ ቀና ትላለች። የምትኮራበት የሃገርህ ብራንድ እንዲፈጠር የራስህን አሻራ ታኖራለህ። የውጭ ምርት መጠቀምን የዘመናዊነት መለኪያ አድርገው ከሚያስቡ ‘ምስኪኖች’ ጎራ ራስህን ነጥል!
2ኛ) የጥቁር ገበያ ቀለበት ውስጥ ራስህን አታስገባ። ዶላር፣ ፓውንድ፣ ዩሮ፣ ሪያል ወዘተ... ያለህን ባንክ ሄደህ ቀይር። በጥቁር ገበያው መንዝረህ የምታተርፈው አገር ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት አንፃር ምንም ነው!
3ኛ) ህገ-ወጥ ነጋዴን ስታይ ተጋፈጥ፣ አጋልጥ፣ ጠቁም። ከህጋዊ ነጋዴ ግዛ፤ ያለደረሰኝ አትግዛ! ታዝበህ ከመሄድ አንድ እርምጃ አለፍ ብለህ ተጋፈጥና የሚመጣውን ለመታገል ቁርጠኝነት ይኑርህ።
4ኛ) አላስፈላጊ ወጭዎችን ተቆጣጠር፤ ላንተ ብቻ ሳይሆን እንደ ሃገር ዋጋ እያስከፈሉን ያሉት አላግባብ የሚባክኑ የቅንጦት ወጭዎች ናቸው። አንተ እንደ ቀልድ ለቅንጦት ለአንዴ ከምታባክነው ባነሰ ወጭ የወር ቀለባቸውን መሸመት የሚችሉ በርካቶች በየጎረቤትህ ይኖራሉ። አይንህን ግለጥ...
5ኛ) ራስህን በስራ ወጥር፤ አትስነፍ! ባለህበት ቦታ፣ በየትኛውም መስክ ብትሰማራ ጊዜ ሳትሸራርፍ፣ ጉልበት ሳትሰስት፣ ሰው አየኝ አላየኝ ሳትል ከልብህ ስራ! የአገራችን ጥቅል ጂዲፒ የእኔ፣ የአንተ፣ የአንቺ  ድምር አለበት። ቢያንስ እንደ ግለሰብ የነፍስ ወከፍ ገቢያችን የሚወሰነው በኛ ጥረት ልክ እንደሆነ አስብ።
6ኛ) ነጋዴ ከሆንክ በደረሰኝ ሽጥ። በዓመቱ ከሰው የሰበሰብከውን፣ ያስከፈልከውን የገቢ ደረሰኝ ሳትሰርቅ ሳታጭበረብር ለመንግስት አስረክብ።
በአንተ ክንድ ሃገር እንደሚገነባ፣ በቅንነት ግብር በመክፈልህ በርካቶች በልተው እንደሚያድሩ አስተውል።
... በዚህ መልክ እናቶቻችን፣ እህቶቻችን ከሚሰሩበት ፋብሪካ እንዳይቀነሱ፣ ነጋዴዎች ምርት ማምረታቸውን እንዳያቆሙ ልናግዛቸው እንችላለን።


_____________________________________________________

                     ኢትዮጵያዊነት!
                      አበረ አያሌው


             ሰ...ፊ  ነው ኢትዮጵያዊነት - ፍቅር ነው የስፋት ልኩ፤
ከፍቅር ባነሰ መዳፍ - ለመቁረስ ጫፉን አትንኩ።
አለው ስምና ግብር - ትንሣዔን አምላክ ያደለው፤
አፈር አራግፎ ይነሳል - ተቀብሯል፥ ሞተ ስትለው።
የማንም ንፋስ ቢወጣ - ከየሥርቻው ጀግኖ፥
(ባቧራ ቢከለል እንጂ...)
ኢትዮጵያዊነት ሰማይ ነው - አይጠፋም እንደጉም በኖ።


Read 1790 times