Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 September 2012 13:07

ድብርትና መዘዙ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

የጥርስ በሽታ፣ ጉንፋን፣ የሳንባ በሽታ የድብርት ተጠቂዎች ላይ በስፋት ይታያሉ

ድሮ ድሮ በስልጣኔ ያደጉና የበለፀጉ አገራት ችግር እንደሆነ ይታሰብ የነበረው Depression (ድብርት) ዛሬ ምን በልተን እናድር ይሆን የሚል ሃሳብ ሰቅዞ የያዛቸው ታዳጊ አገራትም አሳሳቢ ችግር ሆኗል፡፡ ችግሩ ከገጠር አካባቢዎች በባሰ መልኩ በከተማ ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች ላይ ጐልቶ ይታያል፡፡ በዚህ ዙሪያ የተደረጉ በርካታ ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም ስልጣኔና ቴክኖሎጂ የሰው ልጅ በድብርት ችግሮች ለመያዙ ዋነኛ ምክንያቶች እየሆኑ ነው፡፡ የሰው ልጅ ኑሮው ውስብስብ እየሆነ በሄደና በቴክኖሎጂ ባደገ ቁጥር ለውጥረትና ድብርት ችግሮች የመጋለጡ ሁኔታ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ከመጠኑ ያላለፈ ጭንቀት ሰውነትን ለማንቃት እንዲሁም ራስን ለነገሮች ዝግጁ አድርጐ ለማቆየት እንደሚረዳ የሚናገሩት በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች፤ ጭንቀቱ ከግለሰቡ ሁኔታዎችን የመቆጣጠር አቅም በላይ በሚሆንበት ወቅት ድብርትን በመፍጠር በሽታ ይሆናል ይላሉ፡፡ ድብርት በራሱ በሽታ የመፍጠር ባህርይ ባይኖረውም ለተለያዩ በሽታዎች መከሰት ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል፡፡ ድብርት በሰው ልጅ አዕምሮ ላይ በሚፈጠረው ጫናም ሥነልቦናዊ ቀውስ ይከሰታል፡፡

በ2009 በአሜሪካ የሥነ አእምሮ ተመራማሪዎች የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ በድብርት ምክንያት የሚገጥሙን የጤና ችግሮች እጅግ ውስብስብና በርካታ ናቸው፤ የሰው ልጅ ውጥረትን የመከላከል ብቃቱም ከሰው ሰው የሚለያይ ሲሆን በርካቶች ወደ ሐኪም ዘንድ ለመመላለሳቸው ዋንኛው ምክንያትም ድብርት የሚያሳድርባቸው ሥነ ልቦናዊ ችግር ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድና ቀጣይነት ያለው የአዕምሮ ድብርት በሰውነታችን ላይ አላስፈላጊ መሸማቀቅን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ለረጅም ጊዜያት በድብርት ባህርያት ውስጥ ተዘፍቀን የምንቆይ ከሆነ ሰውነታችን ከእለት ወደ እለት የተፈጥሮ የመከላከያ አቅሙን ያጣል፡፡ ድብርቱ የማይቀንስ ከሆነና ባለበት ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ችግሩ እስከሞት ሊያደርስ የሚችል አካላዊ ቀውስን ያስከትላል፡፡

በድብርት መንስኤነት የሚከሰተው በሽታ የሰውነታችንን የእለት ተእለት ተግባራት የሚያዛባ ሲሆን ሰውነታችን በአግባቡ ሥራውን እንዳያከናውን በማድረግ የከፋ የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ ችግሩ በተለያዩ ሰዎች ላይ የሚያስከትላቸው የጤና ችግሮች ተመሳሳይ ባለመሆናቸው ምክንያት የህክምና ባለሙያዎች በሽታውን ለማከምና ለማዳን በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ችግር ሲፈጥር ይስተዋላል፡፡ የድብርት የመጀመሪያ ምልክቶች የምግብ ፍላጐት ማጣት፣ የሆድ ህመምና እንቅልፍ ማጣት እንደሆነ የሚያመለክተው ጥናቱ፤ የገፅታ መለዋወጥ፣ የአተነፋፈስ ለውጥ መኖር፣ የድብርትና የመጫጫን ስሜት መፈጠር ለድብርት መከሰት ምልክቶች እንደሆኑ ይገልፃል፡፡ ይህም የድብርት መገለጫ ባህሪያት የሚንፀባረቁበት የድብርት ችግር መከሰቻ የመጀመሪያው ደረጃ ነው፡፡ ግለሰቡ የተፈጠረበትን መቋቋም ከቻለ የጭንቀቱ ደረጃ ወደ ቀጣዩና ውስብስቡ ደረጃ ሳይደርስ በአጭሩ ሊቀጭ ይችላል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግለሰቡ ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችለው አቅም ካጣና ከተዳከመ እንዲሁም የጭንቀቱ መጠን አየጨመረ የሚሄድ ከሆነ ግለሰቡ ሙሉ በሙሉ ወደ ድብርት ወስጥ ይገባል፡፡ ይህም ወደ ቀጣዩና እጅግ ውስብስብ በመሆኑ Myocardial infection (ሚዩካርድያል ኢንፌክሽን) ለሚባለውና ለሞት የማጋለጥ አቅሙ ከፍተኛ ለሆነው የልብ በሽታ ሊያጋልጥ ይችላል፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ የድብርት ችግርን ማዳን እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡

ጭንቀትን (ውጥረትን) የመከላከል ብቃት ከሰው ሰው የሚለያይ ቢሆንም ችግሩ ከግለሰቡ የመከላከል አቅም በላይ በሚሆንበት ጊዜ ለበሽታዎች መከሰት መንስኤ ለሆነው ድብርት ማጋለጡ አይቀሬ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ውጥረት (ጭንቀት) ሲከሰትባቸው ችግሩን በውስጣቸው መቆጣጠር ሳይችሉ ይቀሩና ስሜታቸውን በፊታቸው ላይ ያሳያሉ፡፡ የምግብ ፍላጐታቸው ይቀንሳል ወይንም ሙሉ በሙሉ ይጠፋል፡፡ የዚህ ችግር ሰለባዎች ለጨጓራ አልሰር፣ ለልብ ህመምና ለደም ግፊት በሽታዎች የመጋለጣቸው እድል ከፍተኛ ነው፡፡ በሌላ ወገን የተፈጠረባቸውን የድብርት ችግር በውስጣቸው ተቆጣጥሮ መያዝ የሚችሉና ሲታዩ የተረጋጉ ሰላማዊ ሰዎች የሚመስሉ ድብርታሞች አሉ፡፡ እነዚህኛዎቹ ውስጣቸው እጅግ የተረበሸ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር በውስጣቸው አፍነው ለመያዝ ስለሚፈልጉም ድብርታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰና እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ይህም ውስጣዊ ህመምን ያስከትልባቸዋል፡፡ ውስጣቸው የተረጋጋና ሰላማዊ ባለመሆኑ ምክንያትም ባህሪያቸው ነጭናጫና አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ድብርቱ እየተባባሰና እየጨመረ ሲሄድም ለከፍተኛ የደም ግፊት ለልብ ህመምና ለአእምሮ ችግር የመጋለጥ እድላቸው የበለጠ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ የጨጓራ አልሰር፣ የደም ግፊት፣ የልብ ህመምና የአእምሮ መታወክ በሽታዎች በድብርት መንስኤነት ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎች ሲሆኑ የሚፈጠሩትም ሰውነታችን ውጥረት ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ በሚያመነጨው ያልተመጣጠነ ውስጣዊ ኬሚካል ነው፡፡ ሌላው የድብርት ምክንያት የሚመጣው በሽታ የደም መርጋት ነው፡፡ ይህም ታማሚውን እስከሞት ሊደርስ ለሚችል አደጋ ያጋልጠዋል፡፡ ድብርት እድሜያቸው በገፋ ሰዎች ላይ የአጥንት መሳሳት ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ ብዙ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ በድብርት የሚጠቁ ሰዎች በካንሰር የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ የጥርስ በሽታ፣ ጉንፋን፣ የሳንባ በሽታ የድብርት ችግር ባለባቸው ሰዎች ላይ በስፋት ይታያሉ፡፡

የሰው ልጅ በተፈጥሮው ሙሉ በሙሉ ከጭንቀት መራቅ ባይችልም ጭንቀቱን መቀነስና መቆጣጠር እንዲሁም ለሌሎች በሽታዎች መንስኤ እንዳይሆን መከላከል ይችላል፡፡ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፤ ጭንቀትን ለመቀነስ የሚረዱ ሁለት የህክምና መንገዶች አሉ፤ ከእነዚህ መንገዶች የመጀመሪያው Rises medicine የተባለውና በችግሩ ለተያዙ ሰዎች በመድሃኒት መልክ የሚሰጥ ህክምና ነው፡፡ ይህም ጭንቀት ባስከተለባቸው ድብርት መንስኤነት የተፈጠሩ እንደ ደም ግፊት፣ የልብ ህመምና የጨጓራ አልሰር የመሳሰሉ በሽታዎችን ለማከም የሚረዱ ሲሆን የችግሩ ሰለባ የሆነው ሰው ከድብርቱ በተጨማሪነት ከሚያሰቃዩት ህመሞች እፎይታን እንዲያገኝ ያደርጉታል፡፡ ሌላው Preventive እየተባለ የሚጠራውና የአኗኗር ዘይቤን ሙሉ በሙሉ በመለወጥ የችግሩ ሰለባ ለሆኑ ሰዎች የሚሰጥ (የሚደረግ) ሕክምና ነው፡፡

ይህም ለድብርቱ መነሻ የሆነውን ምክንያት ለይቶ በማወቅና ግለሰቡ ጭንቀቱን ሊቋቋም ያልቻለበትን ምክንያት በመለየት የመቋቋም አቅሙን ለማሳደግ የሚደረግ ህክምና ነው፡፡ ይህ አይነቱ ህክምና ከመድሃኒት ይልቅ የአካል እንቅስቃሴ፣ ዮጋ ስፖርት፣ መዝናናትና አእምሮን ፈታ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ይከናወናል፡፡

እንግዲህ ድብርት የሰውነታችንን የእለት ተእለት ተግባራት በማዛባት ለበርካታና እጅግ አደገኛ ለሆኑ በሽታዎች መንስኤ ከሆነ፣ ለችግሩ መነሻ ምክንያቶችን ለይቶ በማወቅ ጭንቀትን ማስወገድና ራሳችንን ከድብርት በመከላከል ከበሽታ መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ እንዲሉ አበው፡፡

 

 

Read 9520 times Last modified on Saturday, 15 September 2012 15:37