Saturday, 13 November 2021 12:53

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(20 votes)

  በኢትዮጵያ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተብለው ከሚፈረጁት ውስጥ FGM የሴት ልጅ ግርዛትና የልጅነት ጋብቻ ከፍተኛውን ጉዳት የሚያደርሱ ተብለው የሚታወቁ ናቸው፡፡ በእርግጥ የእነዚህን ድርጊ ቶች መሰረታዊ አመጣጥ ድርጊቱን ፈጻሚዎቹ ሲገልጹት በዘመኑ በነበረው አስተሳሰብ እና ከልማድ በጎ ነገር ተደርጎ ልጅ ሲወራረስ የኖረ ነው፡፡
የሴት ልጆች በመገረዛቸው ምክንያት እንደሚጎዱ እና ይህ ድርጊት የሰብአዊ መብትን መጣስ መሆኑን የሚያውቁት እና በራሳቸው ላይ ምን ያህል ችግር እንደደረሰባቸው የሚያውቁት እናቶች የአካባቢያቸውን ልማድ እና በዘር የወረሱትን ድርጊት ላለማጓደል በሚል ስም ብቻ በልጆቻቸው ላይ ይፈጽሙታል፡፡
ድርጊቱን የሚፈጽሙት ግለሰቦችም የሚሰሩት ስራ ምን ያህል ጎጂ እንደሆነ እየተነገራቸው ነገር ግን ያንን በመስራት የሚያገኙት የኢኮኖሚ ጥቅም እና በአካባቢያቸው ከሚኖሩ ሰዎች የሚያገኙትን ከበሬታ ላለማጣት ሲሉ ወንጀል ይሰራሉ፡፡
ልጆቻቸውን ካለእድሜአቸው የሚድሩትም ቢሆኑ በልጅነት ጋብቻ ምክንያት የሚከሰቱ የጤና (ፊስቱላ) እና የስነልቡና የመሳሰሉት ጉዳቶች ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ እየተረዱት ነገር ግን ካሉበት አካባቢ እና ከዘር ዘር ሲተላለፍ የመጣውን ልማድ ላለመሻር ሲሉ በሴት ልጆች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ወደ ጎን በመተው እና ችላ በማለት ይፈጽሙታል፡፡ ሴት ልጆች ልጅነታ ቸውን ሳይጨርሱ ትምህርታቸውን ሳይማሩ የቤተሰብ አስተዳዳሪ እንዲሆኑ ይፈረድባቸዋል፡፡
ከዚህም ውጭ አስገድዶ መድፈርና ጠለፋም ተጠቃሽ የሆኑ የሴት ልጆችን ካለእድሜአቸውና ካለፍላጎቸው ለከፋ ጉዳት የሚ ዳርጉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ናቸው፡፡  
በኢትዮጵያ ያለውን የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አፈጻጸም በሚመለከት ከአሁን ቀደም የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው በጋምቤላ ዝቅተኛ ተብሎ ከተመዘገበው 7% እስከ ከፍተኛው በአፋር 60% ድረስ ይፈጸማል፡፡ ከአፋር ቀጥሎ በአማራና 47% በሶማሌ 31% ያህል ተፈጻሚ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ ድርጊት በገጠር 24% በከተማ 15% መሆኑንም በጊዜው የነበረውን ይጠቁማል፡፡ በእርግጥ ይህ መረጃ አሁን ያለውን እውነታ አያሳይም፡፡
ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መሰረታዊ ምክንያታቸው የህብረተሰቡ አኑዋኑዋር ዝቅተኛ መሆን እና የግንዛቤ አለማደግ እንዲሁም ለሴቶችና ለሴት ልጆች ያለው ግምት ዝቅተኛ መሆን ነው፡፡ የስር አተ ጾታ ግንኙነት ሚዛኑን ያለመጠበቅ እና የውሳኔ ሰጪነት ድርሻዎች መዛባት ተደማምረው የሴት ልጆች ሰብአዊ መብት መጣስ እንዲሁም በህይወታቸው ምርጫቸው እንዳይከበር እና በኢ ኮኖሚና ማህበራዊ አኑዋኑዋራቸው ዝቅተኛ ደረጃን እንደያዙ እንዲቀጥሉ የሚያደርጉዋቸው ድር ጊቶች ናቸው፡፡  ስለዚህ በጥናቱ እንደተመዘገበው ከሆነ ሴት ልጆችን ለጎጂ ልማዳዊ ድር ጊቶች የሚያጋልጡ አበይት ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው ፡፡
ድህነት እና በኢኮኖሚው ዘርፍ የበታች መሆን፤
ትምህርት ያለመማርና ስልጠና ያለማግኘት፤
ወደትክክለኛው የጤና ተቋም በመሄድ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ያለማግኘት፤
ኃይማኖትና ባህላዊ ድርጊቶች የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
UNFPA July 2020 ባወጣው መረጃ በሴት ልጅ ግርዛት ላይ በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ከጥያቄዎቹም መካከል የተወሰኑትን ከነመልሶቻቸው ለንባብ ብለናል፡፡
FGM የሴት ልጅ ግርዛት የት ይፈጸማል?
እንደመረ ጃው እማኝነት በአለም ላይ በተለያዩ አገሮች የሚፈጸም ሲሆን በአፍሪካ ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ በ29 ሀገራት ይህ አስከፊ ድርጊት ይከናወናል፡፡ ቤኒን፤ ቡርኪናፋሶ፤ ካሜሩን፤ ሴንትራል አፍሪካን ሪፐብሊክ፤ ቻድ፤ ኮትዴቩዋር፤ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፤ ጂቡቲ፤ ኤርትራ፤ ኢትዮጵያ፤ ጋምቢያ፤ ጋና፤ ጊኒቢሳዎ፤ ኬንያ፤ ላይቤሪያ፤ ማሊ፤ ማውሪታንያ፤ ኒጀር፤ ናይጄሪያ፤ ሴኔጋል፤ ሴራሊዎን፤ ሶማሊያ፤ ሱዳን፤ ታንዛኒያ፤ ቶጎ፤ ኡጋንዳ እና ዛምቢያ ይፈጸማል፡፡
የሴት ልጅ ግርዛት FGM መቼ እና እንዴት፤ የት፤ ተጀመረ?
የሴት ልጅ ግርዛት የተጀመረው በዚህ ጊዜ እና እዚህ አገር ነው ለማለት ግልጽ የሆነ ማሳያ የለም፡፡ ነገር ግን የክርስትናና የእስልምና እምነት ከመከሰታቸው በፊት መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ፡፡ የሴት ልጅ ግርዛትን ለመጀመርም የግብጽ እናቶች ቅድሚያ ያላቸውና ከክር ስቶስ ልደት በፊት በ5ኛው ክፍለ ዘመንም ኢትዮጵያን ጨምሮ በአንዳንድ አገራት ይፈጸም እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ በጥንታዊ ሮማን እና አረቦች እንዲሁም በፒሊፒንስ፤ በላይኛው አማዞን አካባቢ፤በአውስትራሊያ፤እንዲሁም በአፍሪካ አንዳንድ ቦታዎች ድርጊቱ መለመዱን ማሳያዎች አሉ ይላል UNFPA፡፡ ከዚያም በተለያዩ የአለም ክፍሎች መፈጸም የጀመረ ሲሆን ብዙዎች ግን አስከፊነቱ ሲነገራቸው ድርጊቱን ለማስቆም የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ድርጊቱ እንዳይ ፈጸም የተቻላቸውን አድርገዋል፡፡    
ምን ያህል ሴቶችና ልጃገረዶች በዚህ ድርጊት ተጎድተዋል ?
በአለም ላይ እድሜአቸው ከ15-49 የሚደርሱ ሴቶች ከሚታወቁት የግርዛት አይነቶች ውስጥ አንዱ የተፈጸመባቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ በአለም ላይ ዛሬ በሕይወት የሚኖሩ በግምት እስከ 200/ሁለት መቶ ሚሊዮን የሚሆኑ ሴቶች ግርዛት እንደተፈጸመባቸው ይታመናል፡፡ የአለም ህዝብ ቁጥር የመጨመሩን ያህል የሚገረዙት ሴት ልጆችም ቁጥርም ይጨምራል ተብሎ ይታ መናል፡፡ ግርዛት የተፈጸመባቸው ሴቶችና ልጃገረዶች በአብዛኛው ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት እና በአረብ አገራት እንዲሁም በአንዳንድ የኤሽያ ሀገራት እና በምስራቅ አውሮፓ እን ዲሁም በላቲን አሜሪካ የሚገኙ ናቸው፡፡ በስደት ወደአውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ ፤አውስትራ ሊያ እና ኒውዝላንድ የሄዱ ቤተሰቦችም ሴት ልጆቻቸውን እንደሚያስገርዙ የ UNFPA መረጃ ይጠቁማል፡፡ ይህ ድርጊት በዚሁ ከቀጠለ እ.ኤ.አ ከ2015-2030 ባለው ጊዜ ወደ 68 ሚሊዮን የሚሆኑ ሴት ልጆች ድርጊቱ በሚፈጸምባቸው 25/ሀያ አምስት ሀገራት ይገረዛሉ ተብሎ ይገመ ታል፡፡ እ.ኤ.አ በ2019 ወደ 4.1 ሚሊዮን የሚሆኑ ሴት ልጆች በአለም ላይ ግርዛት የተፈጸመ ባቸው መሆኑ የሚገመት ሲሆን ከዚህ ቁጥር በመነሳት እ.ኤ.አ እስከ 2030 ድረስ በየአመቱ 4.6 ሚሊዮን ሴት ልጆች በየአመቱ ግርዛት ይፈጸምባቸዋል የሚል ግምት አለ ይላል UNFPA
FGM በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚያደርሰው የጤና ጉዳት ምንድነው?
ግርዛት በሴቶች እና በሴት ልጆች ስነተዋልዶ እና ስነ ጾታ ላይ ትኩረት የሚሻ የጤና ችግር እንደሚያስከትል ጥርጥር የለውም፡፡ የሴት ልጅ ግርዛት አስከፊ ጉዳት እንደ አተገባበሩ ማለትም እንደግርዛቱ አይነት እንዲሁም ግርዛቱን እንደሚፈጽሙት ሰዎች እውቀትና ተግባር ፤ግርዛቱ እንደሚፈጸምበት ቦታ ጽዳት፤ግርዛቱን እንደሚፈጽሙበት መሳሪያ ደህንነት ጥንቃቄ ከመሳሰ ሉት ነገሮች ጋር ተያይዞ በተለያዩ መንገዶች ሊገለጽ የሚችል ነው፡፡  ከዚህም በተጨማሪ የሚገረዙት ሴት ልጆች ወይንም ሴቶች የሚኖራቸው በሽታን የመቋቋም እና አስቀድሞውኑም ያላቸው የጤና ሁኔታ በግርዛት ወቅት ከሚፈጸምባቸው ትልተላ ጋር ሲገናኝ ሊቋቋሙት መቻል አለመቻላቸውም ሌላው አሳሳቢው ነገር ነው፡፡
ሴት ልጆች ልክ ሲገረዙ ተከትሎ ከሚመጣው ጤና ቀውስ ውስጥ የህመም ስቃይ፤ መንቀጥ ቀጥ፤ ከፍተኛ የደም መፍሰስ፤ ኢንፌክሽን (መመረዝ) ሽንት የመሽናት ችግር፤ የመሽናት ስጋት ወይንም ሽንትን አፍኖ መቆየት፤ ቁስለት…ወዘተ የመሳሰሉት ብዙ ጉዳቶች የሚደርሱ ሲሆን ከሁሉም ግን የደም መፍሰሱና ኢንፌክሽኑ ህጻናቱን ለሞት ሊያደርሳቸው ይችላል፡፡
ሴት ልጆች ካደጉ በሁዋላ በረዥም ጊዜ በግርዛቱ ምክንያት የሚደርስባቸው ሌሎች ችግሮችም አሉ፡፡ እንደ ግርዛቱ አይነት የሚደርሰው ችግር የተለያየ ሲሆን ልጅ በሚወልዱ ጊዜ ከሚፈጠ ሩት ልማዳዊ ድርጊቶች ባሻገር ቀደም ሲል በተደረገው ግርዛት ምክንያት በሚፈጠረው ጠባሳ ምክንያት ሰውነት አለመለጠጥ ወይንም እንደልብ አለመከፈት፤በወሲብ ግንኙነት ጊዜ ስቃይ ማጋጠም፤ለወሲባዊ ግንኙነት ዝግጁ አለመሆን ወይንም እርካታን ማጣት፤የስነ ልቡና ችግር የመሳሰሉት ሊያጋጥማ ቸው ይችላል፡፡
ማንኛዋም ሴት ልጅ ከሚደርስባት ጉዳት በማንኛውም ሁኔታ ሁልጊዜ መጠበቅ አለባት፡፡ የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የሚደረጉ ጥረቶች በአለምአቀፍም ይሁን በብሔራዊ ደረጃ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡ ለዚህም መላው ህብረተሰብ ፤ሴቶች፤የሀይማኖት መሪዎች እና የህብረተ ሰብ መሪዎች፤መገናኛ ብዙሀን፤መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት…ወዘተ ግዴታ ቸው ሊወጡ ይገባል፡፡


Read 13869 times