Sunday, 14 November 2021 00:00

ፖለቲካውስ ቅጥ አለው? ለሦስት ማዕቀፍ እሺ ይላል?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

 የመንግስት ተቋማትን በሦስት ፈርጆች መተንተን ወይም በሦስት ማዕቀፎች ማጠቃለል የተለመደ ነው። የፖለቲካ “ሀሁ” ይሉታል። ሕግና ስርዓትን ማስፈን፣ መጠበቅና ማስከበር ነው - የመንግስት ስራ።
ለዚህም፤ ሕግ አስከባሪ ወይም ሕግ አስፈፃሚ ተቋማት አሉ - ፖሊስና መከላከያ ሃይል በቅድሚያ ይጠቀሳሉ። ሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በዚህ ማዕቀፍ የሚጠቃለሉ ናቸው - በአጠቃይ ሚኒስትር ወይም በፕሬዚዳንት የበላይ ሃላፊነት።
በእርግጥ፣ ሕግ አስፈጻሚው፤ ባሰኘው ጊዜ ሕግን የሚሽርና የሚያጸድቅ፣ ህግን የሚያፈርስና የሚጥስ ከሆነ፣ “ደሞዝ የሚከፍለው በደለኛ”፣ “ሕጋዊ ወንጀለኛ” ከመሆን ምን ይለየዋል?
ተቆጣጣሪ ያስፈልገዋል - ሕግ አውጪ የተሰኘው የመንግስት ፈርጅ፤ ሕግ አስፈጻሚውን የመቆጣጠር ሃላፊነት አለው። ትክክለኛ ሕጎችን በአግባቡ የማውጣት፣ የህግ አውጪ ተቋም ሃላፊነት ነው።
በሐሰት አትወንጅል፣ በሃሰት አትመስክር፣ በማለት የሸፍጥ ተግባራትን የሚከለክል ህግ ያውጃል። የሰው ምርትና ንብረትን አትድፈር፣ አትስረቅ፣ አትዝረፍ እየለ ኑሮን ከጥቃት የሚከላከሉ ህጎችን ያወጣል።
የሰው ሕይወትንና ክብርን አትዳፈር በማለትም፤ ማሰቃየትንና አካል ማጉደልን እንዲሁም ግድያን የሚከለክሉ ህጎችን ያውጃል።
በጥቅሉ፣ በሃሰት አትመስክር፣ አትስረቅ፣ አትግደል ብለን ልናሳጥራቸው አንችላለን- የትክክለኛ ህጎች ባህርያትን።
ህግ አውጪ ምክር ቤቶች፤ ህግ ከማውጣት አልፈው፤ ከማውጣት አልፈው፤  ከሳሽና ፈራጅ መሆን የለባቸውም።
 የዳኝነት ስልጣንና ሃላፊነት፣ የፍርድ ቤቶች ነው- ሕግ ተርጓሚ ተቋማት ይባላሉ በሦስተኛው ማዕቀፍ የሚጠቃለሉ።
ዋናዋናዎቹ  የመንግስት ተቋማት፣ ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስተፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ በሚሉ ማዕቀፎች የሚጠቃለሉ ናቸው- ፓርላማ፣ ካቢኔና ጠቅላይ ፍርድ ቤት። ተመራጭ፣ ፖሊስና ዳኛ እንደማለት ነው።
የሕግና ሥርዓት ሦስት ገፅታዎችን ወይም የመንግስት ተቋማት ዘርፎችን በሦስት ማዕቀፍ ማጠቃለል፣ በሦስት ፈርጆች መተንተን ቻልን። ነገር ግን ፣ “የፖለቲካ ሀሁ”  በዚሁተጀምሮ ተፈጸመ ማለት አይደለም።
የህጎች ትክክለኛነትና የስርዓቶች ተገቢነት፣ የመንግስት ትክክለኛ ሃላፊነትና ፋይዳ፣ አላማውንና ወሰኑን  ሁሉ አጥርተን የምናውቀው እንዴት ይሆን?
የሕይወት፣ የነፃነትና የንብረት
ባለቤትነ መብቶች
 የፖለቲካ ሁሉ መንጭና ማጠንጠኛ፣ “የሰው ተፈጥሮ” ነው ይላሉ - የብሩህ ዘመን ፈላስፎች። “Natural law” የሚለውን አባባል የሚጠቀሙት፤ ትክክለኛ ሕጎች ከተፈጥሮ እውነታ የሚመነጩ መሆን እንዳለባቸው ለመግለጽ ነው።
የሰው ሕልውና ከሌሎች እንስሳት ሁሉ የተለየ አስደናቂና ሃያል ተፈጥሯዊ ባህርይ አለው። የማወቅ፣ የመምረጥ፣ የመስራት ልዩ አቅም አለው ሰው። የሕልውና ዋስትናዎቹም እነዚህ አቅሞቹ ናቸው። ሃላፊነት ወስዶ አቅሞቹን የመጠቀምና ሕይወቱን የማለምለም ድርሻ የእያንዳንዱ ሰው ፈንታ ነው።
መማር  ማስተማር ይቻላል፤ ነገር ግን አንድ ሰው ሌላውን ተክቶ ሊያውቅለት አይችልም-  አእምሮ የግል ነው።
መመካከር ይቻላል፤ አማራጮችን ማመልከት፣ ወዲህና ወዲያ  ማበረታታትና ማስጠንቀቅ፣ መገፋፋትና መወትወት ጭምር ሊኖር ይችላል። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ የሚኖሩት፣ አንድ ሰው ሌላው ተክቶ ሊመርጥለት ስለማይችል ነው።
አካላዊ አቅሞችም የግል ናቸው- መተጋገዝ፣ በሽርክና መስራት ይቻላል። ነገር ግን ፣ አንድ ሰው ለሌላው፣ እጅና እግር ሊሆንለት አይችልም።
እውነታን የማወቅ፣ አላማውን የመምረጥ፣ እንዲሁም ምርት ለማግኘት ለማምረጥ የመስራት ሃላፊነት፤ የግል ሃላፊነት ነው። ሃላፊነትን መጨበጥ ደግሞ፣ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ የሕይወት ዋስትና ነው።
ሕይወቱን የሚወድና የሚያከብር ሰው፤ የግል ሃላፊነትን መውሰድና መወጣት ይገባዋል - ይሄ የስነ-ምግባር መርህ ነው። ከሰው ተፈጥሮ የሚመነጭ የስነ-ምግባር መርህ ብለን ልንሰይመው እንችላለን- ትክክለኛ የህይወት መንገድ። ይህንን በጉልበት የሚያግድ ሃይል መኖር የለበትም። ለምን? ሕይወትን ማክበር ማለት፣ የህይወት የንግድ ከማክበር የተነጠለ ትርጉም ሊኖረው አይችልም።
በሌላ አነጋገር፣ የማወቅ፣ የመምረጥና የመስራት ነፃነትን ከማክበር ውጭ፤ ሕይወትን ማክበር ብሎ ነገር አይኖርም።
ታዲያ፤ የእውቀቱ፣ የምርጫውና የስራው፤ ትርጉም፤ ከፋይዳው ጋር የተያያዘ ነው። በውጤቱ ኑሮን ማሻሻልና ሕይወትን ማለምለም የሚቻል መሆኑ ነው ፋይዳው።
የምርቱ ጌታ፣ የንብረቱ ባለቤት መሆኑ፣ የህልውናው ጉዳይ ነው።
ማምረትና ንብረት ማፍራት የግል ሃላፊነት የመሆኑ ያህል፤ ምርቱንና ንብረቱን በጉልበት የሚነጥቅ፣ የሚያጎድል፣ የሚያወድም ሌላ ሃይል መኖር የለበትም።
በአጭሩ፣ የንብረት ባለቤትነት መከበር አለበት- ህይወት መከበር ስላለበት።
በሦስት ማዕቀፍ ሲጠቃለል፤ እያንዳንዱ ሰው፣ በተፈጥሮው፣ “የሕይወት፣ የነጻነትና የንብረት ባቤትነት መብቶች” አሉት የሚል የፖለቲካ መርህ ላይ እንደርሳለን።
 ቶማስ ጀፈርሰን፣ The right to life, liberty and the pursuit of happiness ብለው ገልጸውታል። ፍሬድሪክ ባስትያት ደግሞ Life, Liberty and property ብለውታል።

Read 2649 times