Saturday, 27 November 2021 13:35

“መንግስት ለአገር ሰላምና ደህንነት ያሰጉኛል ያላቸውን የውጪ ዜጎች ከአገር ማስወጣቱን ይቀጥላል”

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

  - በሁለት ወራት ውስጥ 11 ዲፕሎማቶችና የተመድ ሃላፊዎች ከአገር ተባርረዋል
     -”የተባረሩት አራት ዲፕሎማቶቼ በቅርቡ ይመለሳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” -
                   
               ከሽብርተኛው የህውሃት ቡድን ጋር እየተደረገ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ ተገቢ ያልሆነ ጫናና ጣልቃገብነት እያካሄዱ ባሉና ከተፈቀደላቸው ስራ ውጪ ሲንቀሳቀሱ በተገኙ ዲፕሎማቶችና በተለያዩ  የውጪ ድርጅቶች ውስጥ በሚሰሩ የውጪ አገር ዜጎች ላይ የሚወሰደው ከአገር የማስወጣት እርምጃ እንደሚቀጥል መንግስት አስታወቀ። ሰሞኑን አራት የአየርላንድ ዲፕሎማቶች በአንድ ሳምንት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ ያዘዘው መንግስት፤ የሌሎች አገራት ዲፕሎማቶችም ሆኑ የአለም አቀፍ ድርጅቶች ሰራተኞች ስራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ አሳስቧል።ከስድስት ዲፕሎማቶቿ መካከል አራቱ ከአገር እንዲወጡ ትዕዛዝ የተላለፈባት የአየርላንድ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳይመን ኮቬኒ የኢትዮጵያ መንግስት በወሰደው እርምጃ እጅግ ማዘናቸውን ተናግረዋል። “እርምጃው የተወሰደው አየርላንድ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነትና ከሰብአዊ ቀውስ አንጻር በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤትና በዓለም አቀፍ መድረኮች በያዘችው አቋም ነው ያሉት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ውሳኔው ጊዜያዊ እንደሚሆንና ሰራተኞችን ወደ ስራቸው እንደሚመለሱ ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል። ውሳኔው ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉትን የአየርላንድ አምባሳደርንና አንድ ሌላ ዲፕሎማት የማይመለከት መሆኑንና በእነዚህ ሁለት ዲፕሎማቶች ስራቸውን እንደሚቀጥሉም የአየርላንድ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።ከ27 ዓመታት በፊት በአገራችን ኤምባሲዋን የከፈተችው አየርላንድ፤ በኢትዮጵያ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጊዜ ጀምሮ በጉዳዩ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እንዲሰበስብና በኢትዮጵያ መንግስት ላይ እርምጃ እንዲወስድ በተደጋጋሚ ግፊት ስታደርግ   የቆየች አገር ስትሆን፤ ይህንን አገሪቱ የምታራምደውን ጣልቃገብነትና ተገቢ ያልሆነ ጫና እንድታቆም የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ሲያሳስብ መቆየቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግስት የአገር  ሉአላዊነት በሚዳፈሩና በአገር  ውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ በሚገቡ አገራት ላይ የሚወስደውን እርምጃ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቋል።
በሁለት ወራት ውስጥ ከሚመለከታቸው ጉዳይ ውጪ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ሲንቀሳቀሱና ተገቢ ያልሆነ ተግባር ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው ከአገር እንዲወጡ የተደረጉት ዲፕሎማቶችና የአለም አቀፍ ድርጅቶች ኃላፊዎች ቁጥር 11 ደርሷል።

Read 11625 times