Saturday, 27 November 2021 13:40

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ከግንባር የድል ብስራት አስተላለፉ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(6 votes)

  ‹‹የምንፈልገው እኛ ሞተን የምትቆም ኢትዮጵያን ማየት ነው….››
                     
           ከህውሃት የሽብር ቡድን ጋር የሚካሄደውን የህልውና ጦርነት ለመምራት ባለፈው ህዳር 13 ቀን 2014 ዓ.ም ወደ ግንባር ያመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ ትናንት ጦርነቱ ከሚካሄድበት ግንባር የድል ብስራት አስተላልፈዋል።
የጠላት ሃይል እስካለፈው ሀሙስ ድረስ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮት የቆየውን ስፍራ ማስለቀቃቸውንና ካሳጊታን መያዛቸውን  የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ጭፍራና ቡርቃን እንይዛለን ብለዋል።
“የእኔ ስራ በግንባር ሆኖ ጦርነቱን መምራት ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በውጪ ያሉ ወገኖች ባላቸው አቅም ሁሉ እየጮሁ መሆኑንና የኢትዮጵያ ነጻነት እስከሚረጋገጥ ድረስ   ወደ ኃላ እንደማይሉም ገልጸዋል።
“የምንፈልገው እኛ ሞተን የምትቆም ኢትዮጵያን ማየት ነው፤ የምንፈልገውም ኢትዮጵያዊ መሆን ወይንም ኢትዮጵያ መሆንን ነው” ብለዋል።
 በጣም ትልልቅ ድሎች እየተገኙ መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ውጤቱ በጣም ጥሩ ነው በርቱ” ብለዋል።
የሰራዊቱ ሞራል እጅግ ደስ የሚል መሆኑንና ጦርነቱ በከፍተኛ ድል መቀጠሉን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ጠላት ከእኛ ጋር ሊስተካከል የሚችል ቁመና  የለውም እናሸንፋለን ብለዋል።ህዝባችን ከጎናችን ነው፤ ነፃ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን እናሻግራለን” ሲሉም ከግንባር ባስተላለፉት የድል ብስራት ገልጸዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡


Read 12111 times