Monday, 29 November 2021 00:00

ሰላም ይስፈን - በሴቶችና በህጻናት ላይ የሚደርስ ጥቃት ይቁም!!!

Written by  -በዓለማየሁ ማሞ-
Rate this item
(0 votes)

ልጃገረዶችና ታዳጊ ሴት ህጻናት የአስገድዶ መደፈር ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል፡፡ ብዙዎችን ደግሞ ያለ ወላጅና ያለ አሳዳጊ አስቀርቷል፡፡
               ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት በሁሉም የዓለማችን ክፍል የሚፈጸም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው። ይህ ጥቃት በተለይም በሴቶችና ታዳጊ ሴቶች ላይ ጎልቶ የሚታይ ችግር ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሦስት ሴቶች መካከል አንዷ ማለትም 35 በመቶ የሚሆኑት በሕይወት ዘመናቸው አካላዊ ጥቃት ወይም ወሲባዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸውና በአጠቃላይ በዓለማችን ካሉት ሴቶች 50 በመቶ የሚሆኑት አንድ ወይም ሌላ አይነት ጾታዊ ጥቃት እንደሚያጋጥማቸው መረጃዎች  ይጠቁማሉ።
እንደ 2016 የሥነ-ህዝብና ጤና ዳሰሳ መሰረት፤ በሀገራችን 26 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች አካላዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል። በሴቶችና ታዳጊ ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የተለያየ መልክ ቢኖራቸውም፣ መገለጫቸው በዋነኛነት አካላዊ፣ ወሲባዊ፣ ስነ-ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቃት ነው። በተጨማሪም የስርዓተ-ጾታ እኩልነት አለመከበር፣ አድሎዓዊ እና የተዛቡ አመለካከቶች፣ ልማዶችና ባህሎች ናቸው።
እነዚህ ጥቃቶች ከሚያመጡት አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት በተጨማሪ የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ይገድባሉ። ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ዳፋው በልጆች፣ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በሀገር ደረጃም የሚያስከትለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ከፍተኛ ነው፡፡
ከኖቬምበር 25 እስከ ዲሴምበር 10 ባሉት ተከታታይ 16 ቀናት እንዲከበር መነሻ የሆነው በካናዳ ሞንትሪ ኢንጂነሪንግ ት/ቤት ውስጥ “አክራሪ የሴት እንቅስቃሴ መሪዎች” በሚል በአንድ ወንድ የተገደሉትን 14 ሴቶችና ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚሞቱ ሴቶችን ለማስታወስ ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ ቀኑ ህዳር 16 /ኖቬምበር 25/ እንዲከበር የተደረገው በ196ዐ በአምባገነኑ የዶክሚኒካን ሪፐብሊክ መሪ ራፋኤል ትሩጂሎ የተገደሉትን የሚራባል እህትማማቾችን /Mirbal sisters/ ለመዘከር እንደሆነ አንዳንድ  ፅሁፎች ያትታሉ፡፡ እነሆ በአሉ በአለም አቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ ቀናቱ በተለያዩ መሪ ቃሎች ሲከበር ቆይቷል፡፡
ዘንድሮም ዓለም አቀፍ የፀረ-ጾታዊ ጥቃት ቀናት ከህዳር 16 - 30 ቀን 2014 ዓ.ም “ሰላም ይስፈን - በሴቶችና በህጻናት ላይ የሚደርስ ጥቃት ይቁም !!” በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ30ኛ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡
ሃገራችን ወደ ምትፈልገው እድገት እንድትደርስና ከድህነት በመውጣት ዜጎች የሚኮሩበት ሃገር እንድትሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ችላ በማለት እድገትን መጠበቅ የማይታሰብ ስለሆነ፣ የሚደርስባቸውን ጾታዊ ጥቃት በመከላከልና በማስቆም ልማታዊ አስተዋፅኦቸውን ማበርከት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ ሊፈጥርላቸው ይገባል፡
እንደሚታወቀው በሰሜኑ አካባቢ እየተካሄደ ባለው የህልውና ዘመቻ አሸባሪው ህውሓት ታዳጊ ህጻናትን በአውደ ውጊያ እንዲሳተፉ በማስገደድ ለከፋ ስቃይና እንግልት አልፎ ተርፎም ለህልፈተ - ህይወት እንዲዳረጉ በማድረግ፣ ቀጣይ ትውልድ ለማሳጣት ሃላፊነት በጎደለው መልኩ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡
በተለይም በሀይል ወረራ በፈጸመባቸው አማራና አፋር ክልል፣ ህጻናትን ጨምሮ በንጹሃን ዜጎች ላይ አረመኔያዊና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት መፈጸሙ ይታወሳል፡፡ አሸባሪው ሀይል በማህጸን ካለ ጽንስ ጀምሮ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ጨቅላና ታዳጊ ህጻናት ያለርህራሄ ሲጨፈጭፍ፣ ለበርካቶች አካል መጉደልም ምክንያት ሆኗል፡፡
ልጃገረዶችና ታዳጊ ሴት ህጻናት የአስገድዶ መደፈር ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል፡፡ ብዙዎችን ደግሞ ያለ ወላጅና ያለ አሳዳጊ አስቀርቷል፡፡
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል በተለይ በአገራችን እየተካሄደ ባለው የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ምክንያት ለተፈናቀሉ ሴቶችና ህጻናት እንዲሁም የአንድ መስኮት እና የማገገሚያ አገልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት ድጋፍ ለማድረግ እንዲያስችል ከህዳር 16 - 25 ቀን 2014 ዓ.ም ባሉት ቀናት  “የእህቴ ጠባቂ ነኝ” ወይም `I Care for MY Sister` በሚል መሪ ቃል ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከግል ባለሃብቶች፣ ከሲቪል ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ደረቅ ምግቦች፣ ወተት፣ ዘይት፣ የማብሰያ ቁሳቁሶች፣ የንጽህና መጠበቂያዎች፣ የተለያዩ ልብሶች፣ ብርድ ልብሶች፣ አንሶላዎች፣ ፍራሾችና ሌሎች ግብዓቶችን በማሰባሰብ ለየተቋማቱ ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
በዋናነትም  ይህን የአሸባሪ ቡድን ጥፋት በአስቸኳይ ለማስቆም አካባቢያችንን በመጠበቅ፣ ወደ ግንባር በመዝመትና መከላከያ ሰራዊታችንን በመደገፍ ልንረባረብ ይገባል፡፡
 እንዲሁም ለጾታዊ ጥቃትና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችና ህጻናትን ህይወት በመታደግና የተከፈተብንን የውስጥና የውጭ ወረራና ህገወጥ ድርጊት በማስቆም ጉልህ አስተዋጽዖ እንድናበረክት ኢትዮጵያ የሁላችንንም አስተዋጽዖ የጠየቀችበት ወቅት መሆኑን በመገንዘብ ፈጣን ምላሽ በመስጠት የዜግነት ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡
ከንቅናቄው ጋር ተያይዞ ጾታዊ ጥቃትን በተመለከተ የወንዶችን ተሳትፎ የሚመለከተው የነጭ ሪቫን ንቅናቄም አብሮ እየተካሄደ ነው። ይህንን ነጭ ሪቫን ማድረግ በሴቶች ላይ ጥቃት አልፈጽምም፣ የሚፈጽሙትን አወግዛለሁ፣ ሲፈጸምም ዝምታን አልመርጥም የሚል አንድምታ ያለው ነው፡፡
ጾታዊ ጥቃትን በመከላከልና ምላሽ በመስጠት ዙሪያ የበለጠ ውጤታማ የሆኑ ስልቶች ላይ ልምድና ተሞክሮ ለመለዋወጥ ጾታዊ ጥቃትን በመከላከልና ምላሽ በመስጠት ዙሪያ መንግስታዊ የሆኑና ያልሆኑ ተቋማት ያላቸውን ትብብርና ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡
ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከል የመንግስት ፆታዊ ጥቃትን ያለመታገስ አቋም ቅንጅታዊ አሰራርን  ከማጠናከር ባሻገር ከህብረተሰቡ በዋናነት የሚጠበቀው ተግባር ጾታዊ ጥቃትን መጸየፍ፣ ጥቃት የሚያደርሱ አካላትን ማጋለጥና ለፍትህ ማቅረብ እንዲሁም  የጥቃቱን መንስኤዎች አስቀድሞ በመለየት፣ በተቋሙ ስትራቴጂክ እቅድ ላይ በተቀመጡ የማስፈጸሚያ ስልቶች በመመራት በእውቀት፣ በቅንጅትና በባለቤትነት ስሜት ልንሰራ ይገባል፡፡
በተለይም የመኖር ህልውናቸው አደጋ ላይ የወደቁ ሴቶችን፣ አረጋውያንን፣ አካል ጉዳተኞችንና  ህጻናትን እንዲሁም  በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን በበጎ ፈቃድ መደገፍና መንከባከብ የአእምሮ እርካታና የህሊና እረፍት የሚሰጥ ሰናይ ምግባር መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል::
በዚህ መሰረት ህብረተሰቡ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሙያና ሲቪክ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ባለሃብቶችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ከመንግስት ጎን በመሰለፍ በቅንጅት እንዲሰሩና ሁሉም የድርሻቸውን እንዲወጡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪውን ያቀርባል፡፡

Read 9001 times