Saturday, 27 November 2021 14:26

‹‹እሳት መጣብህ››ቢሉት፤ ‹‹ምንም አይደል ሣር ለብሻለሁ›› አለ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

 ሓቂ አተወካ እንተበልዎስ፣ ደሓን ሳዕኒ ተኸዲነ ኣለኹ በለ (የትግረኛ ተረት)

          አንዳንድ ተረትና ምሳሌ አንዴ ተነግሮ አልደመጥ ይላል። ስለዚህ ደግመን እንድንተርተው እንገደዳለን። የሚቀጥለው ተረትም የዚህ ዓይነት ነው።
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ እግረ-ጠማማ ገበሬ፣ ዘር ሊዘራ ወደ እርሻው ሄዶ ዘርቶ ሲመለስ፣ አለቃ ገብረሃናን መንገድ ላይ ያገኛቸዋል። ከዚያም፤ “አለቃ እንደምን ውለዋል?” ይላቸዋል።
አለቃም፤
“ደህና እግዚሃር ይመስገን፣ ደህና ውለሃል?”
“ደህና ነኝ አለቃ። ከወዴት እየመጡ ነው?”
አለቃ፤
 “እንዲህ ወደ ደጋው ሰዎች ተጣልተው ላስታርቅ ሄጄ መመለሴ ነው”
እግረ ጠማማው ገበሬ ነገረኛ ብጤ ነው። አለቃ አፍ ላይ ተልባ ፍሬ አይቶ   ኖሮ፤
“አለቃ፤ ዛሬ ተልባ ስንት ስንት ዋለ?” ይላቸዋል።
አለቃም ወደ ገበሬው እግር አየት አድርገው፤ “በጠማማው/ጣሳ ሰባት ሰባት   ነው!” ብለው ቀልደውበት አለፉ።
ገበሬው መንገዱን ሲቀጥል፣ አንዲት ጦጣ ከዛፍ እዛፍ እየተንጠላጠለች ስትዘል ይደርሳል። ገበሬው ዘርቶ የመጣው አተር ነው። ጦጢት ይሄንን ካወቀች ከእርሻው ገብታ ቦጥቡጣ ቦጥቡጣ  እንደምትጨርሰው ያውቃል።
 ጦጢትም ቸኩላ፤ “ገበሬ ሆይ! ዛሬ ምን ዘርተህ መጣህ?” አለችው።
ገበሬም፤ በብልጠት ሊመልስላት ብሎ፤
“ተልባ! ተልባ ነው የዘራሁት” አላት።
ጦጢትም ተልባ-እርሻ ገብታ ልቦጥቡጥ ብትል እንደሚያሟልጫትና     እንደማትችል አውቆ፤ “ተልባ ነው የዘራሁት” እንዳላት ገባትና፤
“ደህና፤ ለማንኛውም ወርደን እናየዋለን!” አለችው ይባላል።
***

“እባብ ለእባብ ይተያያል ካብ ለካብ” እንደሚባለው መሆኑ ነው።
ይቺ አንድ እናት አገራችን የችግር ፈረቃ ሲያጠቃት ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል። ርሃቡን ተወጣን ስንል፣ በሽታና ወረርሺኝ ያጣድፈናል። ወረርሽኙ ጋብ አለልን ስንል፣ ጦርነት ይከሰትብናል። ጦርነቱን በስንት ደም፣ በስንት መስዋዕትነት፣ በስንት የሞራልና የሀብት ድቀት ተወጣነው ስንል ዐይኑን ያፈጠጠ ሙስና ከራስጌ እስከ ግርጌ እንደ አራሙቻ ይወርረናል። ከሙስናው ለመገላገል መመሪያ ሲወጣ መመሪያው ራሱ ሙስና የተጠናወተው ሆኖ ይገኛል። ዕቅዶች ይነደፋሉ፤ አይተገበሩም። ህግጋት ይደነገጋሉ፤ አይከበሩም። የህዝብ መብት ይናቃል። ህግጋት ይደነገጋሉ፤ አይከበሩም። የህዝብ መብት ይናቃል። ፍትሕ ቦታ ካጣ ሰንብቷል። ሙስ በሥልጣን የፊት ለፊት በርም ይምጣ፣ በፖለቲካው የጓሮ-በር፣ ዞሮ ዞሮ የአገርንና የህዝብን ገንዘብና ንብረት ለግል ጥቅም ማዋል ነው። ስለዚህም ህዝብ የፖለቲካ ባለስልጣንም ሆነ የመንግሥት መዋቅር ሹሙን መጠየቁን፣ በዙሪያው የተገኘውንም “በቢላህ ገብር፣ በሰማህ መስክር” ማለቱ አይቀሬ ነው።
 ህዝብ የበደሉትን ይቅር ማለት ያውቃል። ይችልበታል። ከተሳሳተም ከስህተቱ ይማራል። ያም ሆኖ  #በጊዜ ንሥሐ ግቡ!” ማለትንም ጠንቅቆ ልቆበታል።
በኢትዮጵያ በየዘመኑ እንደታዘብነው በአንድ ወገን የፖለቲካ ድርጅት አባል፣ በሌላ ወገን የመንግስት መዋቅር ባለቤት ሲኮን፤ በሁለት  ልብ የመተዳደርን ያህል ከባድ ነው። የብቻ አካሄድም ጣጣው ብዙ ነው። የራስ ደሴት፣ የራስ አምባ፣ የራስ ሀብትና ቅርስ አበጅቶ፣ መንግሥትና ህዝብ ለእኔ-ምኔ ማለትም ከባድ ቅዠት ነው። በዚህም ሆነ በዚያ ንክኪው አይቀርምና! የአገራችንን ፖለቲካ የፈለገ ፖለቲከኛ ቢተነትነው፣ ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረ ውስብስብ ይዘትና ቅርጽ-አልባ መልክ ያለው መሆኑ ጸሐይ የሞቀው እውነት ነው። እስከዛሬ እንዳየነውም ፖለቲካና ኢኮኖሚው አልመጋገብ ካለ አያሌ ጊዜ ሆኖታል። እየተባባሰ የሚመጣውንም መፍትሔ ፈልጉለት ቢባል “ከድጡ ወደ ማጡ” እያሽቆለቆለ አልያዝ አልጨበጥ ብሏል።
ሁነኛ ዲሞክራሲያዊ እልባት ያበጃሉ የተባሉት ምሁራን፣ የፖለቲካ አመራሮችና ተራማጅ አካላት፤
“እሳት መጣብህ” ቢሉት “ምንም አይደል ሣር ለብሻለሁ” አለ እንደተባለው ሆነውብናልና፣ ፈጣሪ መላውን እንዲሰጠን እንማፀን።

Read 12528 times