Sunday, 28 November 2021 00:00

ሰው ማለት፤… ሰው የሚሆን ነው፤ ሰው የጠፋ እለት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ተፈጥሮን አስተውለህ ትምህርትን መርምረህ የምትረዳ አዋቂና ጥበበኛ ከሆንክ፣ በመልካም ምግባርና በሙያ ብልሃት የምትተጋ ከሆንክ፣ ኑሮህ ይደላል፣ ሕይወትህ ይጣፍጣል፤ ያስደስታል። “የፈጣሪያችን ምሳሌም ትሆናለህ”። (የፈላስፋው የወልደሕይወት አባባል ነው - የሰውን ክቡርነት ለመግለፅ፣ መልካሙንም መንገድ ለማስተማር የፃፈው)። የሰው ተፈጥሮ፣ከሁሉም ፍጥረታት የላቀ፣ወደ ፈጣሪ እጅግ የቀረበ ነው ይባላል-ፈላስፋው
“ወደ አንተ የሚመጣውን ሰው ሁሉ አትመን። ያገኘውን ሰው ሁሉ የሚያምን፣ ሰነፍ ነው። ሁሉን መርምር። መልካሙንም አፅንተህ ያዝ” በማለት ይመክራል ወልደ ሕይወት። በስራህ ፍሬ፣ በጥበብህና በድካምህ እንጂ፣ በሌላ ሰው ሃብት አትመን። ነገ ጠላቶች ይሆኑሃልና፣ በወዳጆችህ አትተማመን” በማለትም ያስጠነቅቃል፡፡  በፍቅር በመተባበር ኑር። ወዳጅነትህም በልኩ ይሁን… እያለ የጥበብን ሚዛን ያስጨብጣል።
ስለ ሰው ብዙ ተነግሯል።
ሰው ብርቱ ነው! ሰው ክቡር ነው። ሰው ለሰው መድሃኒቱ ነው ተብሏል።
አምላክን የመሰለ፣ መላዕክት የሚያከብሩትና የሚሰግዱለት፣ ለእንስሳት ለእፅዋት ሁሉ ስም የሚያወጣ፣ ምድርን የሚገዛ፣ እጅግ ክቡር ፍጥረት ነው።
እውነትንና ሃሰትን አጥርቶ የሚያውቅ፣ ጥሩና መጥፎን ለይቶ የሚመዝን፣ በጎና ክፉን መርምሮ የሚዳኝ።
ምድርን እንደገነት የሚያለማ፣ ሰማየሰማያትን የሚያጠና፣ ወደ ከዋክብት የሚመነጠቅ ድንቅ ፍጥረት ነው! ሰው ማለት። አይደለም እንዴ?
ወይስ፣ ሰው ሚስኪን፣ ሰው ከንቱ? ደካማና ሃጥያተኛ? ጠማማና መሰሪ? አዎ፤ ይሄም ተብሏል። ስለ ሰው ብዙ ተወርቷል። “ሰውን ማመን፣ ቀብሮ ነው” እስከ ማለትም ተደርሷል - የአንዳንድ “ታማኝ” ሰዎች አባባል መሆኑ ነው። እንመናቸው እንዴት? ማለቴ ያለ ቀብር። “ሰውን ማመን መርምሮ ነው” ቢሉ ይሻል ነበር።
“ለሰው፣ ሞት አነሰው!” የሚል መራራና ክፉ አባባልም አለ። ለዚህ እንኳ፣ ብዙም ቦታ ላንሰጠው እንችላለን። “ለሰው ሞት አነሰው! - አለች ቀበሮ” ይባላል። ታዲያ፣ ለቀበሮ ጆሮ መስጠት አለብን? ይልቅ፣ ሌላ መንገድ እንሞክር። ቀበሮ እንዲያ የሚያማርር በደል ከደረሰባት፣ በግልፅ ትናገር፤ በደፈናው ሳይሆን ጥፋተኛውን ለይታ ትክሰስ። ስለ ሰውና ስለተግባሩ፣ እንደ ታዛቢ ለመናገርና ሃሳቧን ለማስረዳት ከፈለገችስ፣ ጆሮ መንፈግ አለብን?
ለማንኛውም፣ “የከበረ ፍጥረት”፣ “የወረደ ፍጥረት” የሚሉ አማራጮችን አይተናል። ለየት የሚሉ አባባሎችን እንፈልግ።
“ሰው ማለት፣ ሰው የሚሆን ነው፣ ሰው የጠፋ እለት። “ ብለዋል - ጥበበኛው የአገራችን ባለ ቅኔ።
ሰው፣ በሁለቱ አማራጮች፣ ወደ ከፍታው ወይም ወደ ዝቅታው፣ በተቃናው ወይም በጠመመው መንገድ መሄድ እንደሚችል፣ ባለ ቅኔው እየነገሩን ነው።
አዎ፤ ሰው መሆን ይቻላል። በአስቸጋሪ ጊዜ ላይም፣ ስብዕናን በፅናት መያዝ ይቻላል። ግን ደግሞ፣ ከ”ሰው”ነት በታች መውረድም አለ።
ክፋቱ ደግሞ፣ “ሰው” ሁሉ ወርዶ ተዋርዶ፣ “ሰው ጠፋ” የሚያስብል ከባድ ጊዜ እንዳለ ያስረዳል - የባለቅኔው አባባል።
ደግነቱ፣ በአስቸጋሪ ወቅትም፣ ክፋት በበዛበት ዘመንም ቢሆን፣ “ሰው”ነቱን የማያዋርድ፣ “ሰው የሚሆን” ጀግና እንደማይጠፋም ይገልፅልናል። መልካም ነው። በክፋ ዘመን ውስጥ፣የሰውን ክብር ጠብቆ በእውነት መቆምና በተቃና መንገድ መራመድ የሚችል ሰው፣በደህና ዘመን አይሸነፍም እናም፣በፈተና መሃል፣ “ሙሉ ሰው ነኝ” ለማለት የሚበቃ ሰው ማግኘት መታደል ነው፡፡ ሰብዕናውን በፅናት ይዞ የሚጓዝ ጀግና፣ ለሌሎችም አርአያ ይሆናል - መንፈስን የሚያነቃቃ፣ ብርታትን የሚሰጥ አርአያ።
ግን፣ “ሰው መሆን” ማለት እንዴት እንዴት ይሆን?
ሰው በጣም ድንቅ ፍጥረት የመሆኑ ያህል፣ በጣም “ውስብስብ” ባለ ብዙ ገፅ ፍጥረት ነው። ባለ ብዙ ጅረት፣ አንዳንዴም ባለ ብዙ ጅራት ፍጥረት ነው። አእምሮው፣ አካሉ፣ መንፈሱ፣…. ሃሳቡ፣ ተግባሩ፣ ስሜቱ….
ከብዛቱ የተነሳ፣ አንዱን ሲይዙት፣ ሌላው እያመለጠ፣ አንዱን ሲያሻግሩት፣ ሌላው የኋሊት እየቀረ፣ … ግራ ሊያጋባ ይችላል።
እንደዋዛ ትናንት የለመዱት አመል፣ ለዛሬ ፈተና ይሆናል። ለዛሬ ይጠቅማል ያዋጣል ብለው የጀመሩት ነገር፣ ወደ ነገ የማያዘልቅ፣ ከነገ ወዲያም መዘዝ የሚያመጣ ከባድ እዳ እየሆነ መሄጃ ያሳጣል።
ጥሩ ሃሳብ ያዘ ሲባል፣ ንግግሩ ሌላ ይሆናል። ጥሩ ተናገረ ሲሉት፣ ተግባሩ ተቃራኒ ነው። ሃሳቡና ተግባሩ ሲቃና፣ ስሜቱና መንፈሱ በድሮው ልማድ ተጠፍንጎ፣ እንደተጣመመ ይቀራል።
ይህ እርስ በርሱ የተጣረሰ የተቃወሰ ማንነት ግን፣ የሰው ልጅ አይቀሬ እጣ ፈንታ አይደለም። ጨለማውን ማብራት፣ የጠመመውን ማቃናት፣ የጠወለገውን ማለምለም ይቻላል። ሁሉንም አሳምሮ ማስማማት፣ ቀላል ባይሆንም ይቻላል።
እውቀቱ፣ ኑሮው፣ ነፍሱ (የግል ማንነቱ)፣ … አብረው ሲለመልሙ፣ በህብር ይደምቃሉ። የሰውን ክብር እና ሞገስን ይገልጣሉ። ይመሰክራሉ።
ሲጣረሱ ግን፣ … መከራ ነው።
ሰው፣እውቀት ሲያጣ፣ ህይወቱ፣ ጨለማ ውስጥ እንደመኖር ነው። በአንዳች ተዓምር ወይም በሌሎች ሰዎች ልግስና ኑሮው ቢሟላለት እንኳ፣ እድሜ ልክ እንደ ሕፃን ሆኖ መኖር ምን ትርጉም አለው?
እውቀት ሲያዳብር፣ በተግባር ቁምነገር የማይሰራበትና ለኑሮው ፋይዳ የማያመጣለት ከሆነ፣…. ዋሻ ውስጥ በረሃብ እንደመሰቃየት ይሆናል።
ለአእምሮው፣ ለአካሉ፣ ለግል ማንነቱ ልምላሜ፣ የግል ሃላፊነትን የማይወስድ ከሆነ፣…. ከሮቦት በምን ይለያል? ሰብዕናው እየደነዘዘ ወደ “ኮማ” እየሰጠመ፣ “ኑሮ ሁሉ ቢሟላለት” እንኳ፣ የሕይወት ጣዕሙ ምኑ ላይ ነው?
“ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ፣ ነፍሱን ግን ቢያጎድል፣ ምን ይጠቅመዋል?” የሚለውን አባባል አስታውሱ።
እውነትም፣ “ሰው መሆን”፣ የአንድ ርዕሰ ጉዳይ ወይም የአንድ ወቅት ጉዳይ አይደለም። የሁሉም ገፅታዎች ሕብር ነው።
የትናንት ጉዞው ውጤታማነት ብቻ ሳይሆን፣ የዛሬ እርምጃው ስኬትም፣ የነገ መንገዱ መቃናትም ጭምር ነው- የሰው ሕይወት ማለት።
የሰው ማንነት፣ ማለት አላማው ብቻ ሳይሆን ጥረቱም ነው። የስራ ውጤቱ ብቻ ሳይሆን፣ የሙያ ብቃቱም ነው። የእውቀቱና የስነምግባር መርሁ ብቻ ሳይሆን፣ የሰብዕና ንፅህናውና ፅናቱም ነው።
ሁሉንም አዋህዶ፣ አስማምቶ፣ አጥርቶና አጉልቶ መግለፅ ያስቸግራል። ነገር ግን፣ አይቻልም ማለት አይደለም። ሰው መሆን ማለት እንዴት እና በየት በኩል እንደሆነ፣ ምንስ እንደሚመስል የሚያሳዩ የኪነ ጥበብና የፍልስፍና ሰዎች አልጠፉም - ብዙ ባይሆኑም። “መሸ ደሞ አምባ ልውጣ” የሚለውን የባለቅኔ ፀጋዬ ገብረመድህን ግጥም፣ካሁን በፊት ጠቅሻለሁ፡፡ ለዛሬ “If” የሚባለውን ግጥም እናጣጥማለን፡፡
ከሳምንት ደግሞ፣ ከወደል ሕይወት ፍልስፍና ትምህርት የምናገኛቸው ቁምነገሮች እንቃኝ ይሆናል፡፡ የሰውን ነገር ለማየት ጉራንጉሩንና ብሩህ አደባባዩን፤ ዋሻውንና ባለ ግርማ ሞገስ ሕንፃውን ለማየት፤ የፈላስፋውን የጥበብ ሚዛን እንይዛለን፡፡


Read 3707 times