Print this page
Saturday, 04 December 2021 13:04

ከ3 መቶ በላይ የሲቪል ማህበራት ለአፍሪካ ህብረት ደብዳቤ ፃፉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 ህጋዊ መንግስትን በሃይል ለማስወገድ የሚደረግ እንቅስቃሴን እንዲያወግዝ ጠይቀዋል
               መሰረታቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ ከ3 መቶ በላይ የሲቪክ ማህበራት፣ ህጋውያን የኢትዮጵያ መንግስት በምዕራባውያን ጫናና በጦር ሃይል ለመጣል የሚደረግን እንቅስቃሴ የአፍሪካ ህብረት በይፋ እንዲያወግዝና በጉዳዩ ላይ አቋም እንዲወስድ ጠየቁ።
የሲቪክ ማህበራቱ በጋራ ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በጻፉት ባለ 3 ገፅ ደብዳቤ፤ በኢትዮጵያ በህጋዊ መንገድ በሰፊ የህዝብ ድጋፍ የተመረጠን መንግስት በሃይል ለማስወገድ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህን ጥረት የአፍሪካ ህብረት በአፋጣኝና በአንድ ድምፅ ሊያወግዘው ይገባል ብለዋል።
“ህውሃትና አጋሮቹ ህጋዊውንና ቅቡልነት ያለውን የኢትዮጵያ መንግስት ህገወጥ በሆነ መንገድ በሃይል ለማፍረስ የሚያደርጉትን ጥረት አጥብቀን እናወግዛለን” ብለዋል- ማህበራቱ በደብዳቤያቸው። በአፍሪካ ህብረት መተዳደሪያ ደንብም ሆነ በኢትዮጵያ ህገመንግስት ከህግ ውጪ የሚደረግ የመንግስት ለውጥ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ያመለከተው ደብዳቤው፤ አሁን የሚደረገው እንቅስቃሴ ይን የህብረቱ መተዳደሪያ ደንብን የጣሰና የአፍሪካውያን ቃልኪዳን የሚያፈርስ ነው ብሏል።
ህብረቱ፤ በምዕራባውያን ጣልቃገብነት የሚካሄዱ ህገ-ወጥ መንግስት ግልበጣ ሙከራዎችን እስከዛሬ ዝምታውን በመስበር አጥብቆ እንዲቃወምና እንዲያወግዝ በደብዳቤው ጠይቀዋል።
በሃይልና በህገ-ወጥ መንገድ የመንግስት ግልበጣ የማድረግ የሚደረግ ጥረት የአፍሪካን የወደፊት ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ነው ያለው ደብዳቤው፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ህጋዊ ቅቡልነት ያለውን መንግስት ለመጣል የሚደረገው ጥረትም አጠቃላይ የአፍሪካ ሃገራትን ክብርና ህልውና የተዳፈረ መሆኑን የሲቪክ ማህበራቱ አመልክተዋል።

Read 11458 times